የስሜት ትኩሳት

በሆስፒታሉ የድንገተኛ ክፍል ውስጥ አንድ አባት ሰመመን ውስጥ ወድቀዋል። አጠገባቸው ነጭ የሙያ ልብስ የለበሰች ጠይም ሴት በትካዜ ትታያለች። ከሽማግሌው ወደ እሷ የሚፈስ የሃሳብ ውቅያኖስ በመካከላቸው ተንጣሏል። ፊቷ ላይ በትላንቷ ውስጥ የረቀቀ እውነት ይታወሳታል..በዛሬዋ ውስጥ የወገገ አሁን..በነገዋ ውስጥም ከሁሉ የተባረከች አንድ ነፍስ ትመጣባታለች። ይሄን መባረክ የሰጣት እሱ ነው…ድንገተኛ ክፍል ውስጥ የተኛው ሽማግሌ።

ጠዋት ከእንቅልፏ ስትነሳ ማለዳዋን የምትጀምረው የእሱን ድምጽ በመስማት ነበር። የኔ ቆንጆ ነቃሽ? ጣፋጭ ቁርስ ሰርቼልሻለው፣ ፊትሽን ታጥበሽ ጠብቂኝ› ብሏት ከአልጋው ላይ ወርዶ ወደ ማዕድ ቤት ሲሄድ አልጋ ላይ ሆና ታየዋለች። ዛሬም ድረስ ያልበላችውን ጣፋጭ ቁርስ እያጎረሰ ያበላታል። በጣም የሚገርመው ደግሞ እሷን ከማጉረስ በቀር አንዴም አለመጉረሱ ነበር። ስሟት..አቅፏት.. እንደሚወዳት ሚሊየን ጊዜ ነግሯት ወደ ትምህርት ቤት ይሸኛታል። ሆስፒታሉ ጀርባ የተማሪዎቹ ሰርቪስ ከዓይኑ እስኪሰወር ድረስ ቆሞ ያያታል..። ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ ያለው ጊዜ ለነዚህ ርሀብተኛ ነፍሶች የዝንተ ዓለም ያክል ሩቅ ነበሩ። በእሷ ትንሽዬ ነፍስ ውስጥ የአባቷ ገናና ነፍስ የእግዜርን ያክል ጉልበት ነበራት። በልጅነቷ እግዜርን አታውቀውም..እግዜር የእሷ አባት ነበር የሚመስላት። በእሱ ገናና ነፍስ ውስጥ የእሷ ትንሽዬ ነፍስ ሰፊ የፍቅር ግዛት ነበራት። ይገርመዋል አባትነት..ይገርመዋል ወንድነት..ይገርመዋል ተፈጥሮ። በትንሽ ነፍስ ትልቅ ነፍሱ አቅም ማጣቷ ይገርመዋል። በትላንት በዛሬና በነገው ውስጥ ያለ ያልተመለሰ አምላካዊ ሚስጢር ይለዋል..የፍቅርን ኃይል።

ማታ ሲሆን በቆመበት ቦታ ሆኖ ይቀበላታል። ገና ስታየው በልጅነቷ ውስጥ ይሄ ነው የማትለው ስሜት ይለኮሳል። የጓደኞቿን ስንብት ችላ ብላ፣ የነባሮክና፣ የነአምራን ቻው ቻው ሳይሰማት ወደ አባቷ ትከንፋለች። ከብርሃን ፈጥና፣ ከንፋሳት በና፣ ዓይኖቿን ከአባቷ አካልና ነፍስ ላይ ሳታዛንፍ እጆቿን እንዳንጨፈረረች እቅፉ ውስጥ ትወድቃለች። ያኔ አባቷ እግዜር ይመስላታል። ያኔ ለዘላለም በማይጥሉ ጽኑ ክንዶች የታቀፈች ይመስላታል። ያኔ እንዳባቷ ኃይል የተቀባ ሌላ ነገር ታጣለች። ያኔ አባቷን የዓለም ሁሉ ጌታ ታደርገዋለች። ይሄ ጊዜ አይደለም ቆማ አልፋም የሚታወሳት ይመስላታል። አባቷ በእሷ ሕይወት ውስጥ ሁሉም ቦታ አለ..ያ ጊዜ ግን ከሁሉም የተለየ ነው። ለዘለዓለም የተለያት የሚመስላትን አባቷን እሷን ሲጠብቅ ቆሞ የምታገኘው እዛ ቦታ ነው…ከሆስፒታሉ ጀርባ። ያ ጊዜ በሕይወቷ ውስጥ ዳግም እንዲመጣ የምትሻው የሴትነቷ አልፋ ነው።

እቅፉ ውስጥ እያለች ደጋግሞ ይስማታል። ዓይኗን፣ ጉንጯን፣ ግንባሯን። እቅፉ ውስጥ እያለች ከነቦርሳዋ ተሸክሟት ወደ ቤት ይሄዳሉ። በሆስፒታሉ አጠገብ ሲያልፉ ነጫጭ የለበሱ ሐኪሞችን ማየት ግድ ነበርና እሷም እንዲህ ማለት ግድ ነበረባት..‹አባ እኔ ሳድግ ዶክተር ነው የምሆነው..›

‹ለምን..?

‹አንተን እንዳክምህ…አንተን በሽታ እንዳያምህ› አለችው፡

ሳማት..ነፍሷን በነፍሱ ሳማት። ጉንጩዋ ለአፉ ቅርብ ነበርና ደጋግሞ ሳማት። በዚያ ሰዓት ሊያደርገው የሚችለው የመጨረሻ ውድ ስጦታው እሷን መሳም ነበርና ሳማት። ነፍሱ ውስጥ በቀለች..። እሱ ይሄን ሁሉ ሲሆን እሷ በአባቷ እቅፍ ውስጥ አንገቷን ሰብራ ከሆስፒታሉ ግቢ ወዲያ ወዲህ የሚሉትን ነጭ ለባሽ ዶክተሮች በቅናት እያየች ነበር።

ማታ ሲሆን ሌላ ታሪክ አላቸው…የእሱም የእሷም ነፍስ የሚሹት ልጅነታዊና አባታዊ ታሪክ። ተረት ያነብላታል፣ እየተጫወቱና እያስጠናት ትንሽ ይቆያሉ። ከዛ ሁሉም ነገር በእሷ እንቅልፍ ይጠናቀቃል። ወደመኝታዋ እስክትሄድ ድረስ እሱ ክንድ ላይ ነው እንቅልፍ የሚጥላት። ካለአባቷ ጉያ አንቀላፍታ አታውቅም። ካለአባቷ ክንድ ዓለም ላይ ምቹ ነገር ያለ አይመስላትም። ክንዱ ላይ ተኝታ ጠዋት ክንዱ ላይ ትነቃለች። ፍቅሯ በእንቅልፍ ይሸነፋል። ጠዋት ራሷን ማታ እንደሆነችው ክንዱ ላይ ታገኘዋለች። ከዛም ‹የኔ ቆንጆ ነቃሽ? ጣፋጭ ቁርስ ሰርቼልሻለሁ፣ ፊትሽን ታጥበሽ ጠብቂኝ› ከወፎቹ ዜማ ቀድማ የምትሰማው የአባቷ ድምጽ ይከተላል። በዚያ ማለዳ ከአባቷ ጎን ራሷን እንደማግኘት የሚያስደስታት ምንም አልነበረም። በዚያ ማለዳ ከወፎቹ ድምጽ ልቆ የአባቷን የእንዴት አደርሽ ድምጽ እንደመስማት የሚባርካት ምንም አልነበረም። በዚያ ማለዳ ከአባት የእምነት ጽላት ስር የእሷን የተስፋ ጽላት እንደ ማግኘት ምንም አልነበራትም። አባቷ የሴትነቷ ቀለም ነው። ዓለምን በልኳና በመጠኗ የሰራላት። ከወዙና ከወዟ እያጠቀሰ ያበጃት። ዓለምን የሞሏት የመልካም ወንዶች ነፍስ በመልካም ሴቶች ነፍስ የሰለጠኑ እንደሆኑ ታውቃለች። የአባቷ አሰልጣኝ ማን ትሆን? ሚስቱን ማወቅ ጓጓች..ሚስቱ እናቷ እንደሆነች ስታውቅ ደግሞ በይበልጥ ጓጓች..ክብር የዋጀው ጉጉት። ወደፊት..ወደፊት ብቻ አይደለም ለዘላለም እንደ አባቷ ዓይነት ባል እንዲኖራት ተመኘች። እንደ አባቷ ዓይነት ወንድም፣ እንደ አባቷ ዓይነት ልጅ፣ እንደ አባቷ ዓይነት ጓደኛ እንዲኖራት ተመኘች። ሴቶች ሁሉ፣ ልጆች ሁሉ፣ ሰዎች ሁሉ እንደ አባቷ ዓይነት ወንድ ቢያገኙ ስትል..

መስፍን አባቷ እንደሆነ ያወቀችው ቆይታ ነው..እናቷም አባቷም እንደሆነ ነበር የምታውቀው። እናትነት ምን እንደሆነ ያወቀችው ትምህርት ከጀመረች በኋላ ነበር። ትምህርት ቤት ጓደኞቿ እናታቸውንና አባታቸውን ይዘው ሲሄዱ እሷ ግን ከአባቷ ጋር ብቻ ነበር የምትታየው። እኚህ ቀናት..እኚህ አጋጣሚዎች ተደጋገሙና መስፍን አባቷ ብቻ እንደሆነ ነገሯት። አንድም ቀን ግን እማዬስ ብላው አታውቅም። ከፍቅሩ ጢሻ ውስጥ ያጎደለባት አንዲት አለላ ሰበዝ አልነበረችም። ለምን እማዬስ ትበለው? እናት ቢኖራት መስፍን እያደረገላት ካለው ነገር በላይ ምን ታደርግላት ነበር? መልሷ ዛሬም ነገም እስከ ዘላለም ድረስ ምንም የሚል ነው። ልክ እንዳባቷ ነፍስ አንዳንድ ነፍሶች ጥንድ ናቸው። ለዘላለም እንዳይታክቱ ሆነው የተበጁ። ልክ እንዳባቷ ነፍስ አንዳንድ ወንዶች ወንድና ሴት ናቸው። ሳይጎድሉ የሚኖሩ። ልክ እንደ አባቷ ነፍስ የአንዳንድ አባቶች ነፍስ ሰማያዊ ናት..በጸጋ የተሞላች።

አደገች..! በልጅነቷ አባቷ ትከሻ ላይ ሆና ሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ እንዳየቻቸው ሐኪሞች ዶክተር ሆነች። አባቷ ደግሞ አጠገቧ ሰመመን ውጦት አንቀላፍቷል…

አባቷን ስታስብ..ስታስብ..ወደእሱ ስትሄድ አይደክማትም…ትበረታለች። በመኖሯ ውስጥ ሌላ መኖር አለ። አምላክ በዚህ ሁሉ ውስጥ አንድ እውነት አለ፤

የፈጣሪ ማስተዋል ይገርማታል። የተፈጥሮ..ውስጥ ያለው

ከሁሉም በኋላ አንድ መራራ እውነት ላይ ደረሰች..መስፍን አባቷ እንዳይደለ አወቀች…ከመንገድ ላይ አግኝቶ ሊያሳድጋት እንደወሰዳት ነገራት። እሱና ነፍሱ በሕይወቷ ሁሉ ያስደንቋታል።

የልጅነት ጠረኗ አይረሳውም..የአንገቷ ስር ሽታ..የቀሚሷ አቧራ፣ የመዳፏ ስር እድፍ። እንዳባቷ ዓይነት መልካም ነፍስ ያላቸውን ስታገለግል ግን ትኖራለች። አጠገቧ ድንገተኛ ክፍል ውስጥ ሰመመን የዋጣቸው አዛውንት ዓይናቸውን ገለጡ…

በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You