አማራጭ የባህር በር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የዲፕሎማሲ አቅምን ማጎልበት

ለቀይ ባህር የቀረበው የአፍሪካ ቀንድ ከሌሎች የአፍሪካ ቀጠናዎች ልዩ ገፅታ አለው:: አካባቢው የበለፅገ ታሪክን እና ባህልን ያዘለ የአፍሪካ አካል ነው:: የመንግሥት ምስረታ ታሪክም በአፍሪካ ቀንድ ረጅም ታሪክ አለው:: ከቀኝ ግዛት መስፋፋት በፊት ስር የሰደደ የመንግሥት ምስረታ ታሪክ ያለው ሕዝብ የሚኖርበት አካባቢ ነው:: ቀኝ ገዢዎች ወደ ቀጠናው ሲመጡ በነበረው ሀገር በቀል ሃይማኖትና ታሪክ ላይ ሌላ ታሪክ ይዘው መጥተዋል::

በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቀኝ ግዛት በአፍሪካ ቀንድ በተጠናከረ መንገድ መስፋፋት የጀመረው ስዊዝካናል መከፈቱን ተከትሎ ነው:: የዓባይን ወንዝ ከምንጩ ጀምሮ እስከ ማረፊያው ግብጽ ድረስ ያለውን ለመቆጣጠር ከሚደረግ ፉክክር ጋር የተያያዘ ነው:: የቀይ ባህርን አስፈላጊነት ስትራቴጂክ ሚናን ተከትሎ ቀኝ ገዢዎች አካባቢውን ለመቆጣጠር የነበረው ፉክክር ጋር በተያያዘ የቀጠናችንን ታሪክ ልዩ ያደርገዋል::

በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜም በአሜሪካኖችና በሶቪየቶች/በምዕራባዊያንና በሶቪየት/ መካከል የነበረው ፉክክርና ፍልሚያ በአፍሪካ ቀንድ ላይ በተጠናከረ መንገድ ይንፀባርቅ ነበር:: ይህ ታሪክ በጠለቀ መልኩ ኢትዮጵያንም ይመለከታታል::

ቀይ ባህርና ጂኦ ፖለቲካውን በተመለከተ ጥናት እና ጽሑፍ በማቅረብ የሚታወቀው ሰለሞን ባርናባስ እንደሚገልፀው፤ የቀይ ባሕር አካባቢ ከፍተኛ የዓለም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግበት፣ በርካታ መርከቦች በስዊዝ ካናልና በባብኤል ማንዴብ ሸርጦች የሚተላለፉበት፣ ከዚህ የተነሳም ሀገራት ትኩረት ሰጥተውት ፀጥታው የተረጋጋ እንዲሆን የሚጓጉለት አካባቢ ነው።

ከዚህም ባለፈ በርካታ የአካባቢው ሀገራት በባሕር መተላለፊያው ላይ ጉልህ ተጽእኖ ለማድረግ የሚፈልጉ፣ አንዳንዶች የአካባቢው ሁነኛ አዛዥ መሆን የሚፈልጉበት ዓለም አቀፍ መተላለፊያ መስመር ነው::

አሜሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ጃፓን ወዘተ… በርቀት ከሚገኙ ሀገራት መካከል በቀይ ባሕር ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርገው ከሚንቀሳቀሱ ሀገራት ጥቂቶቹ ናቸው:: በቅርብ ከሚገኙት ደግሞ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ግብጽ፣ የዓረብ ኢምሬት፣ ኳታር፣ እስራኤል፣ ቱርክ፣ ወዘተ… ተጠቃሽ ናቸው።

እንደ ሰለሞን ገለፃ፤ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ለቀይ ባህር በጣም ቀረቤታ ያላቸውና ምናልባትም በአካባቢው ሊከሰት የሚችል ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ሊጎዳቸው ወይም ሊነካቸው የሚችል ነው:: ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሶማሊያ ወይም ሶማሊላንድ የቀይ ባህር አጎራባች ሀገራትና ሌሎቹ አባላትም ቢሆኑ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴያቸው ከቀይ ባህር ጋር የተቆራኘ ነው::

ለምሳሌ የኢትዮጵያ 90 በመቶ የወጪና የገቢ ንግድ እንቅስቃሴ የሚተላለፈው በቀይ ባህር በኩል ነው:: እነደቡብ ሱዳን፣ ኬንያና ኡጋንዳም ቢሆኑ የንግድ እንቅስቃሴያቸው በቀይ ባህር ላይ የሚተላለፍ ነው:: ስለሆነም በቀይ ባህር የሚደረግ ማንኛውንም ፖለቲካዊ፣ ወታደራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወዘተ… እንቅስቃሴዎች አፍሪካ ቀንድ አባል ሀገራትን ጥቅም የሚነካ መሆኑ ግልጽ ነው::

አለፍም ሲል ከቻይና፣ ከጃፓን፣ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ መጥተው ጅቡቲ ላይ ወታደራዊ መሠረት መጣላቸው ስጋት ቢኖራቸው ነው:: ኢትዮጵያም ተመሳሳይ ስጋት ገብቷታል:: የባህር በር የምትጠቀምበትን አካሄድ እየቀየሰች ትገኛለች:: አሁን ያለው በቀይ ባህርና በኤደን ባህረሰላጤ አካባቢ ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴና የፖለቲካ ውዝግብ ሊያሳስባትም ይገባል::

ስለኢትዮጵያ ስናወራ መጀመር ያለብን ከሕዝብ ቁጥራችን ነው:: ከ120 ሚሊዮን በላይ ነን:: ያለወደብ ካሉ ሀገራት መካከል በሕዝብ ብዛት አንደኛ ነን:: ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ ያሳየቸው የኢኮኖሚ እድገት ከአፍሪካ ተወዳዳሪ የለውም:: እቅዷም ከማደግ ጋር የተያያዘ ነው:: ኢትዮጵያ በምታስበው የማደግ ጉዞዋን ከቀጠለች ከንግድ ጋር የተሳሰረ ነው::

አስተማማኝ የሆነ የባህር በር ያስፈልጋታል:: እስካሁን የምትጠቀምበት አስተማማኝ ወደብ ጅቡቲን ነው:: አሁን ላይ ኢትዮጵያ ከዓመታዊ በጀቷ እስከ 25 በመቶ የሚሆነውን የምታወጣው ለወደብ ኪራይ በመሆኑ ይህ ደግሞ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና ያሳድርባታል::

የባህር በር የአንድ ሀገር የህልውና ጉዳይ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ያለወደብ ኖራለች:: ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ተጠቃሚ እንድትሆን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ጥሩ መግባባት እንዲፈጠር እየተጋች ትገኛለች:: ጎረቤት ሀገራት የሚፈልጓቸውን ነገሮች በስፋት ለማቅረብ ቃል ገብታለች::

በሰጥቶ መቀበል መርህ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በጋራ ለመጠቀም የሚያስችሉ ሌሎች አማራጮችን ጎረቤት ሀገራት እንዲመለከቱ እየጠቆመች ትገኛለች:: ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በፖለቲካ ሳቢያ የወደብም ሆነ የባህር በር ተጠቃሚነቷን ማረጋገጥ ሳትችል ቆይታለች:: በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባህር በር ተጠቃሚነትን አሁን ላይ ለመጠቀም ጥያቄ ማንሳቷ ተገቢም ሕጋዊም ነው:: የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው ዓለም አቀፍ ሕግ ኢትዮጵያ የተጠቃሚነት ጥያቄዋን መፍታት ያስችላታል::

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እ.ኤ.አ 1982 ድንጋጌ አውጥቷል:: በዓለም ላይ የባህር በር የሌላቸው 44ቱ ሀገራት እድል እንዲያገኙ ድንጋጌው በግልጽ ያስቀምጣል:: በዚሁ መሠረት ባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በርን የመጠቀም ነፃነት ሰጥቷቸዋል:: የባህር ሀብትን የመጠቀም፣ በባህር የማለፍ መብት አላቸው:: ድንጋጌው የባህር በር ያላቸው ሀገራት የሽግግር ሀገራት ይላቸዋል:: ስለዚህ ቀይ ባህር የዓለም ሀብት ነው ማለት ነው::

ለቀይ ባህር የቀረቡ ሀገራት ደግሞ ከሌሎች ሀገራት የበለጠ ሀብታቸው፣ መውጫቸው፣ መግቢያቸው፣ ማረፊያቸው ነው:: ኢትዮጵያም ከቀይ ባህር 12 ማይል ብቻ የምትርቅ በመሆኗ የመሸጋገርም የመጠቀምም መብት አላት:: ሽግግሩ እንዴት ይፈፀም የሚለውን ሀገራት መነጋገር ያስፈልጋቸዋል::

በተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌ ኢትዮጵያ የቀይ ባህርንም ሆነ የህንድ ውቂያኖስን መጠቀም ሙሉ መብት ሰጥቷታል:: በዚህ ደግሞ ሁሉም ሀገራት ይግባቡበታል:: ኢትዮጵያም የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም የቀይ ባህር የጋራ ተጠቃሚነት መብቷን ታረጋግጣለች:: ለዚህም ሰጥቶ መቀበል መርህን እንደምትከተል በተደጋጋሚ ወትውታላች:: የምትከተለው መንገድ ሰላማዊ የሆነውን እንደሆነ ግልጽ አድርጋለች::

ኢትዮጵያ ብዙ ሀብት ስላላት በጎረቤቶቿ ሆነ በዓለም ሀገራት የምትፈለግ ሀገር ነች:: በጎረቤቶቿ ሁሉ የምትፈለግ ሀገር እሷ የምትፈልገውን ለማክበር ዝግጁ መሆን አለባቸው:: ለምሳሌ የኢትዮጵያ ወንዞች በሙሉ የሚፈሱት ወደ ውጭ ነው:: አንድም ወንዝ ወደ ኢትዮጵያ የሚፈስ ወንዝ የለም:: ጎረቤቶቻችን በሙሉ ወንዞቻችንን ለመጠጣት ይጠብቃሉ:: በተመሳሳይ ጎረቤቶቻችን በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ የምጠብቀውን ሊሰጧት ዝግጁነት ያስፈልጋቸዋል::

ለቀይ ባህር ቅርብ የሆነው የምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ሰላም፣ እድገት፣ ፀጥታ በስትራቴጂክ መንገዱ ትልቅ ሸክም ያለባት ኢትዮጵያ ነች:: ኢትዮጵያ አካባቢውን ለማረጋጋት ከሌሎች ሀገራት የተሻለ ልምድም ባህልም አላት:: ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ታሪክ እና ሥርዓተ መንግሥት ግንባታ በኢትዮጵያ ስር የሰደደ ስለሆነ መረጋጋትን የመፍጠር ባህል ብርቱ ነው:: ስለዚህ ከየትኞቹም ሀገራት የበለጠ የስትራቴጂ ኃላፊነት ያለባት ሀገር ነች:: የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአካባቢው መረጋጋት ዋስትና ነው:: ኢትዮጵያ ጉንፋን ከያዛት ሁሉም ያስነጥሰዋል:: ኢትዮጵያ ካደገች ሁሉም ያድጋል:: ሁሉም የማደግ ሁኔታ ይፈጠርለታል::

ለአብነት ጅቡቲን ብንመለከት እንኳ ባለፉት 12 ዓመታት ያስመዘገበችው እድገት የሚያስገርም ነው:: ለምን ቢባል ከኢትዮጵያ እድገት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ነው:: ከኬንያ፣ ከሱዳንና ከሌሎች ጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ግንኙነት እየተጠናከረ እየሄደ ነው:: በኢኮኖሚም፣ በፀጥታ፣ በሁሉም ዘርፎች ጥሩ ውጤት እያሳየ ነው:: ኢትዮጵያ በፀጥታ ማስከበርም ሆነ በኢኮኖሚ እድገት ለአካባቢው ያላት አስተዋፅኦ ወደር የለውም::

ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ቦታ ላይ የምትገኝ በመሆኗ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከሚተማመኑባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ነች:: ከብዙ ነገር አንፃር ኢትዮጵያ በጥሞናና ከምር ሆነው የሚመለከቷት ሀገር ነች:: ከዚህ ቀደም በኢኮኖሚ ረገድ ከምር ሆነው የሚመለከቷት ሀገራት አልነበሩም:: አሁን ይሄ ተቀይሯል:: ከፀጥታና አካባቢውን ከማረጋጋት አንፃርም የኢትዮጵያ ቁልፍ ሚናዋን እየተጫወተች ትገኛለች::

በርግጥ ኢትዮጵያ ሁልጊዜ ፀጥታዋንና ህልውናዋን የምታስከብረው በራሷ በመመካት ነው:: ከዛም አልፎ ብሎ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ጀምሮ የራሷን ውስጣዊ አቅም፣ የራሷን ህልውና ለማስጠበቅ ከበይነ መንግሥታት ወይም መልቲላተራል በሆነ ሥርዓት ትደጉመዋለች::

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት እንዲቋቋም መስራች አባል ሀገር ነች:: የተባበሩት መንግሥታት ሲቋቋም ኢትዮጵያ እንዲቋቋም አባል የሆነችው የጋራ ፀጥታን ማዕከል አድርጋ ነው:: አፍሪካ አንድነትም ሆነ አፍሪካ ህብረት እንዲቋቋም ኢትዮጵያ መስራች ሀገር ነች:: በመሪነትም ደረጃ ያደረገችው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም:: ይሄ ሁሉ በይነ መንግሥታት ወይም መልቲላተራል ተቋማት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደህንነቷ ደጓሚ ናቸው:: የብሔራዊ ደህንነቷ አጋዥ ናቸው:: ኢትዮጵያም በአፍሪካ ውስጥ ያየለ ሚናዋን እንድትጫወት አጋዥ ናቸው::

ኢትዮጵያ እያነሳችው ያለውን የባህር በር መጠቀም ጉዳይ ከላይ የጠቀስናቸው ተቋማት እንዲያግዟትና በፅሞና እንዲመለከቱት ከጎኗም እንዲቆሙ ማድረግ አለባት:: በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያ የባህር በርን መጠቀም ጉዳይ እንደሚያሳስባት ማስገንዘብ መቻል አለባት:: የአፍሪካ ህብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ለሌላ ተመሳሳይ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጉዳዩን እንዲመለከቱት ማድረግ ያስፈልጋል:: ኃያላን ሀገራት እነአሜሪካ፣ እነቻይና፣ የፅጥታው ምክር ቤት ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ግንዛቤ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል:: ለዓረብ ሊግ ጨምሮ ለሁሉም መናገር መጀመር አለባት::

ከኬንያ በስተቀር ሁሉም ጎረቤቶቻችን የዓረብ ሊግ አባል ሀገራት ሆነዋል:: በአንድ ማህበር ተደራጅተዋል:: ስለዚህ ይህንን መብታችንን ለማስከበር ከዓረብ ሊግ አባል ሀገራት ጋር የምናደርገው ግንኙነት ወሳኝ ይሆናል:: ስለሕዳሴ ግድብ ስናወራ ስለባህር በር ማግኘታችንም በሰጥቶ መቀበል በሙሉ ልባቸው ሊደግፉልን ይገባል:: ለምሳሌ ግብጽ በዓባይ ውሃ ታሪካዊ መብት እንዳላት ስታነሳ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት እንዳለባት ቀድማ መደገፍ እንደሚገባት ማሳመን ያስፈልጋል:: ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትም ቀድመው ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷን መደገፍ አለባቸው:: እንዴት ትጠቀም እንዴት ታግኝ በመነጋገር የሚፈታ ይሆናል::

በተለይ የአፍሪካ ህብረት በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት እንዲሰጠውና የአፍሪካ ቀንድን ሁኔታ በሚያይበት ጊዜ ልዩ ትኩረት ሰጥቶት እንዲመለከተው ማድረግ ያስፈልጋል:: ህብረቱ የጋራ ተጠቃሚነትን ታሳቢ አድርጎ ኢትዮጵያ ውሃ ታካፍል እንዳለ ሁሉ የባህር በር ኢትዮጵያ ልታገኝ ይገባል ብሎ መቀመጥ አለበት::

በአጠቃላይ በይነ መንግሥታት /መልቲላተራል ተቋማት/ አንዱ ተግባራቸው ሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ላይ መሥራት ስለሆነ ለዚህም ስኬት ኢትዮጵያ ተመራጭ ሀገር ነች:: ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የፀጥታ አስከባሪ በማቅረብ /ወታደሮችን በማቅረብ/ ያላት ሚና ተጠቃሽ ነው:: ይህ የሆነው ሀገሪቱ ስለተከበረችና የኢትዮጵያ አስፈላጊነትን ስለተገነዘቡ የተደረገ ነው:: ኢትዮጵያ ያላት ሀብት ብዙ በመሆኑ መደራደሪያም ይሆናል::

በርካታ የመደራደሪያ መሳሪያ አላት:: ኢትዮጵያ ልክ እንደሕዳሴው ግድብ ሁሉ የባህር በር የመጠቀም መብቷን ለማረጋገጥ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለበይነ መንግሥታት በግልጽ ማሳየት ይጠበቅባታል:: ኢትዮጵያ ዓለም ላይ ያላትን የዲፕሎማሲ ተሳትፎ መሠረት አድርጋ የባህር በር ተጠቃሚነት አቋሟ እንዲደገፍና ፍትሀዊ ጥያቄ መሆኑን ማስረዳትና ማሳመን የሚጠበቅ ተግባር ነው::

ታሪኩ ዘለቀ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You