ለኢትዮጵያ የሚበጃት መከባበር ነው

እነዘውዴ መታፈሪያ እንደልማዳቸው የመንግሥትን ጥፋት እያነሱ ከመውቀስ ወጣ ብለዋል:: የዛሬ የመወያያ ርዕሳቸው የኖረ የመከባበር እሴት እንዳይጠፋ መጠንቀቅ እና ከበፊቱ በተሻለ መልኩ ማዳበር የሚል ነው:: ቀድሞም ቢሆን ለሀገር ስኬት ማኅበረሰብ ላይ መሠራት አለበት፤ በማኅበረሰብ አስተሳሰብ ላይ ዕድገት ካልመጣ ለውጥ ማስመዝገብ አይቻልም የሚለውን የገብረየስ ገብረማሪያምን ሃሳብ የሚደግፍ ነበር:: ተሰማ መንግሥቴም በማኅበረሰብ ላይ በመሥራት ያለፈውን የመተሳሰብ እና የመተጋገዝ መንፈስ በማጠናከር ሁሉንም በሚያስማማ እና በሚያከባብር መልኩ ወደ አንድ መንፈስ መሳብ ተገቢ ነው የሚለውን አስተያየት በፅኑ ይደግፋል::

ገብረየስ ‹‹እኔ ቀድሞም ቢሆን ኢትዮጵያን አላሳድግ ያሏት በየጊዜው ከተፈራረቁት መንግሥታት ባልተናነሰ መልኩ ማኅበረሰቡ ነው የሚል እምነት አለኝ::›› ብሎ ሲናገር፤ ዘውዴ በበኩሉ ‹‹በእርግጥም የየዘመኑ መንግሥታት የቻሉትን ሲሞክሩ ነበር:: ዋናው ችግር ግን ማኅበረሰቡ እግር ጎታች የሚሆንበት አጋጣሚ በጣም ብዙ በመሆኑ ሀገራችን ተቀብራለች የሚለው ጉዳይ እኔንም ያስማማኛል:: ነገር ግን ማኅበረሰብ ላይ ለሚታዩ ዘመን አመጣሽ ችግሮች በተዘዋዋሪም ሆነ በቀጥታ ዘላቂ ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ አዝማሚያዎችን በጊዜ መቆጣጠር የመንግሥት ኃላፊነት ነው:: በዚህ በኩል በተለይ የመከባበር እሴት እንዲያድግ በማመቻቸት በኩል በየጊዜው የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም ክፍተት ነበረባቸው:: ይህን ተከትሎ አሁን አንዱ ሌላውን አክብሮ የሚራመድበት ሁኔታ ተመናምኗል›› ሲል በእርሱ በኩል ያለውን እምነት ገለፀ::

ዘወትር ሁለቱንም የሚቃወመው ዘውዴ ዛሬ ከሁለቱም ሃሳብ ጋር በሚያስማማ መልኩ ሃሳቡን ቀጠለ፤ ‹‹በእርግጥም በተለይ አሁን አሁን ሠለጠንን በማለት ሽማግሌን እና የሃይማኖት አባትን ለመስማት እና ለማክበር ፈቃደኛ ያለመሆን ዝንባሌ እየተስተዋለ ነው:: ይህ ማኅበረሰቡ መልካም እሴቱን በገዛ እጁ ገዝግዞ እየጣለ መሆኑን ያረጋግጣል:: ጎንበስ ብሎ ሰላምታ እና ክብር የሚሰጣቸው የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች በአንዳንድ አውቀናል ባይ የዕውቀት ድሃዎች በድፍረት ሲንቋሸሹ እና ሲሰደቡ ማየት እውነትም ማኅበረሰቡ ወዴት እያመራ ነው የሚል ጥያቄን ያስነሳል::›› ሲል በዘመኑ መከባበር መቅረቱን ለማስረዳት ሞከረ::

ገብረየስ ከዘውዴ ቀጠል አድርጎ ‹‹ማኅበረሰቡ ራሱ የማን ውጤት እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም:: የግለሰብ ስብስብ ማኅበረሰብን ይፈጥራል:: ግለሰብ የተለያየ እሴትን የሚሸረሽር ሃሳብ ሲሰጥ፤ ከማኅበረሰብ የተነጠለ ለማስመሰል ቢሞክርም ያነሳው ሃሳብ ገዢ አግኝቶ ወደ ማኅበረሰቡ ሊዘልቅ ይችላል:: ስለዚህ ግለሰብ ተነጥሎ መታየት አይችልም:: መንግሥት የማኅበረሰብ ውጤት ነው:: ማኅበረሰብ ደግሞ የግለሰቦች ስብስብ ነው:: እዚህ ጋር መረዳት ያለብን ችግሩን ወዲህ እና ወዲያ እያልን ከምንጎትተው ማንኛውንም ግለሰብ ማክበር እና መከባበር ከራሱ የሚጀምር መሆኑን ቢያምን ጥሩ ነው ›› ሲል ሀሳቡን አጠናከረ::

ገብረየስ ደግሞ፤ ‹‹አንዱ ሌላውን ታናሽ ታላቁን እያከበረ፤ ታላቅ ታናሹን እየመከረ ሁሉም በመተሳሰብ ሕይወቱን ማሻሻል ሲኖርበት፤ ምክር አልሰማ አስተያየት አልቀበል ሲል አንዱ ሌላውን እየጠለፈ ሲገድል እና ሲገዳደል ሀገር ከማደግ ይልቅ እንደካሮት ቁልቁል ትቀበራለች:: ጭራሽ የበላይ የታላቅንም ሆነ የበታች የታናሽን ምክር ከመስማት ይልቅ ሙገሳ እና መሞካሸትን ብቻ መፈለግ፤ የሚገስፅ እየሠራህ ያለው ትክክል አይደለም አስተካክል የሚል ሽማግሌ ሲገኝ ከማክበር እና የተሰጠውን አስተያየት ተቀብሎ ከማስተካከል ይልቅ ለማንቋሸሽ መሞከር ፍፁም ተገቢነት የጎደለው ነው::›› ሲል እርሱም የሚያምንበትን ተናገረ::

ተሰማ እፊቱ የተቀመጠውን ቢራ እየተጎነጨ፤ ‹‹በፊትም ቢሆን የነበረው ችግር ራስን እንደጀግና ማሞካሸት እና ሌሎችን ከማክበር ይልቅ እንዳላዋቂ እየቆጠሩ ማጥላላት ሀገር ሲጎዳ ቆይቷል:: በዚህ ሒደት የበሰበሰ መኖሩን መካድ አይቻልም:: ነገር ግን መበስበስን ለማመን ዝግጁነት ካለ መታደስ ይቻላል:: ሥነምግባር ያለው ራሱን በራሱ የሚያርም ከሰፊው ሕዝብ ጋር በመከባበር አብሮ ለመጣመር የተዘጋጀ ካለ በሩ ክፍት ነው:: ነገር ግን ከማኅበረሰብ ጋር ለመጣመር ከስህተት ነፃ ለመሆን በማያቋርጥ መልኩ ራስን ለማረም ዝግጁነት ያስፈልጋል:: ከዚህ በተቃራኒው ሌሎችን ለማሳነስ መሞከር ፍፁም ተገቢነት የሌለው እና የታናሽንም ሆነ የታላቅን ሞራል የሚነካ ኅብረተሰቡን ወደ ኋላ የሚጎትት ነው:: አሁን ለደረስንበት ደረጃ ያደረሰን የመረጥነው መንገድ ተቃራኒ በመሆኑ ነው::›› ሲል ያለውን እምነት ገለፀ::

ገብረየስ በበኩሉ፤ ‹‹ዋናው ጉዳይ ግን አሁንም ቢሆን ከሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት አባቶች በዕውቀት የዳበረ ሒስ መቀበል ይገባል:: ይህ ከመንግሥትም ሆነ ከየትኛውም ዜጋ የሚጠበቅ ሲሆን፤ በሽማግሌዎች በኩልም ያፈነገጠን ማረቅ፤ የሚታዩ እንቅስቃሴዎች በስሜታዊነት በደም ፍላት ሳይሆን በማስተዋል በብልሃት እንዲካሔዱ መስመር ለማበጀት መሥራት አለባቸው:: ትውልዱ አንበገርም በማለት መበታተንን በአንድነት መንፈስ በማልፈስፈስ አንድነታችንን እናጠናክር ብለው በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ማኅበረሰቡ እንዲታነፅ ተደጋጋሚ ትግል ያስፈልጋል:: ነገር ግን ይህንን ደግሞ በተለይ መንግሥት በፅኑ መደገፍ አለበት›› ሲል ተናገረ::

ተሰማ፤ ‹‹እኔ በበኩሌ በደም ፍላት የሚንቀሳቀሱትን አልደግፍም:: አሮጌ ነገር ሊቆሽሽ እና ሊበላሽ ሊበሰብስ ይችላል:: ነገር ግን ሲበሰብስ መታደስ አለበት:: በመከባበር እንዲታደስ ማገዝ ይገባል:: ከዛ ውጪ ይሉኝታ የሌለው ሰው ለራሱ አዘውትሮ ሽር ጉድ ይላል እንደሚባለው ለራስ ብቻ ክብር እየሠጡ ራስን ተራራ ማሳከል አያዋጣም:: የሀገርን እና የሕዝብን ችግር፤ እንዲሁም ደስታን እንደራስ ከማየት ይልቅ እየተስተዋለ እንዳለው የግል ትርፍ እና ዝርፊያ ላይ ማተኮር ድፍረት ከመሆን አልፎ ማንንም የማያኗኑር በመሆኑ ከወዲሁ መጠንቀቅ ይገባል::

ልጆችን፣ ወጣቶችን፣ ሽማግሌዎችን እና የሃይማኖት አባቶችን አለማክበር ዘመን አመጣሽ ቅጥ ያጣ ቅንጦት ሲሆን፤ ይህ ቅንጦት እና አመል ማጣት ለሀገሩ ተቆርቋሪ ሕዝብ ለሀገር ዕድገት ኃይል ይሆናል የሚለው ሃሳብ በተቃራኒው እንዲተገበር ያደርጋል:: ምንም እንኳ ቅራኔዎች ቢኖሩም ቅራኔዎቹን ለመፍታት መናናቅ፣ መጠላላት እና ጦርነት ውስጥ መግባት ሳይሆን ተከባብሮ በመነጋገር መፍታት ዘመናዊነት ነው:: ቅራኔን ተከባብሮ ከመነጋገር ውጪ ራስን በማዋደድ ሌላውን በማዋረድ ላይ ከተመሠረተ የመጠላላት ደረጃውን ከፍ ከማድረግ ውጪ የሚሰጠው ምንም ዓይነት ጠቀሜታ የለም::›› ሲል የሚያስበውን ተናገረ::

ገብረየስ በተሰማ ንግግር ላይ ሀሳብ ለመጨመር ፈልጎ፤ ‹‹በእርግጥም ቅራኔን የመፍቻው ምርጥ መንገድ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ሰላማዊ የመወያያ መድረክ ነው:: አሁን አሁን እንኳን በውስጥ ከውጪ ኃይልም ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት የሚያዋጣ አይደለም:: እንደውም የውጪ ጠላትን የማሸነፊያው ጥበብ እርስ በእርስ ተነጋግሮ ችግርን መፍታት እንጂ አስታራቂ ሽማግሌ የሚለውን አልሰማም ብሎ የውጪ ጠላት የመሣሪያ ሽያጭ ገበያን ማሟሟቅ ሞኝነት ነው:: ጦርነት ለመክፈት እየተሯሯጡ በተንሻፈፈ መልኩ መቀጠል ቀድሞም ቢሆን እንደማያዋጣ አምናለሁ::

በጦርነት ከመቀጠል በመከባበር ተሳስቦ በመነጋገር ፖለቲካውን አንድ ደረጃ ማሳደግ የተሻለ ነው:: ለዚህ ግን ማኅበረሰቡ ፈቃደኛ መሆን አለበት:: ማኅበረሰቡ በሽማግሌ ለመመከር፣ ለመነጋገር ችግሩን በፈቃደኝነት ለመፍታት ሲሞክር ማመቻቸት ደግሞ የመንግሥት ድርሻ ነው:: ሁለቱም ማኅበረሰቡም ሆነ መንግሥት በተቃራኒው መንገድ ከተራመዱ ያሰቡበት መድረስ አይችሉም:: በአንድ አጋጣሚ የተገነባው ሁሉ መፍረሱ አይቀርም:: የማኅበረሰብ እሴት እየተሸረሸረ ከፈራረሰ፤ የፈራረሰን ሕዝብ መምራት ስለሚያዳግት አደጋው እስከመበተን የሚያድግ ይሆናል:: ለዚህ ሁሉ መፍትሔው መከባበር ነው::

ቀድሞም ቢሆን በሰላማዊ መንገድ ተከባብሮ በአንድነት መኖር ይበልጣል በማለቴ ከፖለቲካው ዓለም ተባርሬያለሁ:: በመባረሬ አልከፋም:: ነገር ግን ከፖለቲካው ከወጣሁ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ አስቆጥሬ ያየሁት ተመሳሳይ አለመከባበርን መሆኑ ያሳዝነኛል:: በቀዳማይ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በተሻለ መልኩ መከባበር ነበር:: ነገር ግን መከባበሩ ፍፁምነት የጎደለው ስለመሆኑ አይዘነጋም:: ያ ከቀን ወደ ቀን እየጎደለ የቀጠለው መከባበር ንጉሥን እንደፈጣሪ ከማየት ይልቅ ወደ ማዋረድ አሽቆለቆለ:: ከላይም ሕዝብን አለማክበር፤ ለሕዝብ ሥልጣን ላለመስጠት ማንገራገር ሙሉ ለሙሉ ሥልጣን አሳጣ:: የማኅበረሰቡም የላዩን አካል አለማክበር መልካም ውጤት አላስከተለም::

በደርግ ዘመንም የሃይማኖት አባቶችን እና አዛውንቶችን እንዳላዋቂ ማየት ምክራቸውንም አለማዳመጥ ሀገሪቷን ለከፍተኛ ጦርነት ዳረጋት:: አለመከባበር እና አለመደማመጥ ባመጡት ጣጣ ሕዝብ አለቀ፤ ሀገር ወደመ:: መሣሪያ ቢቆለልም ሥልጣንን ማጣት የግድ ሆነ:: ቀረብ አድርጎ ማነጋገር ሲቻል ጠያቂን ባለማክበር በተፈጠረ ስህተት ሕዝብ አለቀ:: አገር ወደመ:: በዘመነ ኢሕአዴግም ሆነ አሁን በለውጡ ዘመን በተመሳሳይ መልኩ ከታች ወደ ላይም ሆነ ከላይ ወደ ታች ተገቢው መከባበር ባለመኖሩ ተደጋጋሚ ጦርነቶች ተከሰቱ:: የብዙዎች ሕይወት ጠፋ:: ሕዝብም ሀገርም ተጎዳ::

ለሁሉም መፍትሔው መከባበርን መሠረት አድርጎ መነጋገር እና መደማመጥ ነው:: ቀድሞ በመከባበር ላይ ያልተመሠረተ መነጋገር ባለመግባባት መቋረጡ አይቀርም:: ስለዚህ አሁን ላይ ለኢትዮጵያውያን ዋነኛው መፍትሔ ግጭት፣ ማፈናቀል፣ ቂምን መውጣት እና ጦርነት ሳይሆን መሠረታዊው መፍትሔ በመከባበር ላይ የተመሠረተ መመካከር እና መወያየት ነው:: አንዱ ሌላውን አክብሮ፤ አንዱ ራሱን በሌላው ቦታ ላይ አስቀምጦ በአንክሮ ካዳመጠ እና ሁሉም ከተደማመጠ የኢትዮጵያ ችግር የሚቃለልበት ቀን ሩቅ አይሆንም:: ችግሩ ከመቃለል አልፎ ሙሉ ለሙሉ የሚቀረፍበት ሁኔታም ሊፈጠር ይችላል:: ስለዚህ በእኔ እምነት ኢትዮጵያን የሚያድናት መከባበር ነው::›› ሲል ተሰማ ንግግሩን ቋጨ::

ተሰማ፤ ‹‹አንጀቴን አራስከው በእርግጥም ዋነኛው መፍትሔ እርስ በእርስ ተከባብሮ ተመካክሮ ችግርን ማቃለል ነው:: ማንም የማንም የበላይ መሆን አይችልም:: ማንም ማንንም ተጭኖ እንዲከበር ማድረግ አይችልም:: ታናሽ ታላቅን፤ ታላቅም ታናሽን ካከበረ ችግሩ ይፈታል:: ይህ የእኔም እምነት ነው:: እኛ እርስ በእርሳችን ስንከባበር ዓለም ያከብረናል:: ያለበለዚያ እናንተ ‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይሸከመውም› እንዳላችሁት በዓለም የተናቅን እንሆናለን:: ሽማግሌን ከማክበር እና ታላላቆች የሚሉትን ከመስማት በተጨማሪ እርስ በእርስ ካልተከባበርን በፖለቲካውም ሆነ በኢኮኖሚ መውደቃችን አይቀርም:: ውድቀታችን ለጠላቶቻችን ደስታን የሚፈጥርላቸው ከመሆኑም በተጨማሪ፤ ከወደቅንበት እንዳንነሳ እንዳይኮረኩሙን ተጠንቅቀን ተከባብረን ብናድግ ይሻለናል::›› አለ::

ዘውዴም፤ ‹‹እኔም እንደማምነው ግጭት እና ጦርነት ለማንም አይበጅም:: የረጋ ደም ጥቁር ሆኖ ጨለማን የሚያሳይ መቅሰፍት ነው:: ቆመንም ተኝተንም ስለ ጥቁር ደም ማሰባችን እስከ አሁን ያመጣብንን አይተናል:: በኖረው እሴታችን ሽማግሌዎችን በማክበር እና እርስ በእርስ በመከባበር ላይ አድርገን፤ የቀን የሌሊት ሕልማችን በረጋ ደም ምትክ ብሩህ ተስፋ የሚያሳየውን የረጋ ወተት ስናይ ኢትዮጵያ ከሕመሟ ትፈወሳለች:: እኛ ኢትዮጵያን ስናከብራት፤ ዓለምም ኢትዮጵያን ያከብራታል::›› ብሎ እንደለመደው ወደ ቤቱ ለመሔድ ከመቀመጫው ተነሳ::

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You