አዲስ አበባ:- የወቅቱ የዓለማችን ሥጋት በሆኑት የደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ለውጥ ተግባራት ላይ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ርዕስ በርዕስ በመናበብና በቅንጅት እየሠሩ አለመሆኑን የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
በአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻው በተለይ ለአዲስ ዘመን እደገለፁት በእነዚህ አንገብጋቢና ፈጣን የሆነ የጋራ መፍትሔን በሚሹ ተግባራት ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት እየሠሩ ቢሆንም በቅንጅት የመሥራት ክፍተት አለባቸው።
በዚህ ዘርፍ በርካታ ባለ ድርሻ አካላት መኖራቸውንና የመሥሪያ ቤታቸው ተግባር እና ኃላፊነት እነዚህን መቆጣጠርና ማስተባበር መሆኑን የገለፁት አቶ ተስፋዬ እነዚህ ባለ ድርሻ አካላት ካስቀመጡት ግብ አንፃር ምን ያህሉን እንዳከናወኑ፣ ምን ያህል እንደቀራቸው እየተገመገሙ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም ይህም የፌዴራልና የሃይማኖት ተቋማትን፣ መንግሥታዊ ያልሆኑና በጎ አድራጎት እና የረድኤት ድርጅቶችንና ሌሎች በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩትን ሁሉ እንደሚያካትት አስረድተዋል። ሁሉም ለአንድ ዓላማና ለአንድ አገር እንደሚሠሩ ይታወቃል ያሉት ዳይሬክተሩ የተናጠል እቅድና እንቅስቃሴን ትተው በጋራ፣ በመናበብ እና በቅንጅት መሥራት የሚጠበቅባቸው መሆኑንም አስረድተዋል።
በአገር ደረጃ ያለው የህግ ማእቀፍ አንድ ሆኖ እያለ እሱን ለማሳካት በቅንጅት መሥራትና ውጤት ማምጣት እየተቻለ አንዱ ያንዱን እየደገመ፣ አንዱ ያንዱን እያፈረሰ መሥራቱ አገርንም ሆነ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ አያደርግም የሚሉት አቶ ተስፋዬ እቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ እስከ እቅዱ ተፈፃሚነት ድረስ እየተናበቡ መሥራት ጠቃሚ መሆኑንም አሳስበዋል። እንደ ዳይሬክተሩ አገላለጽ በተለይ ክልሎች ከክልሎች፣ በክልሎች ያሉና በዚሁ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ተናበውና ተነጋግረው መሥራት ካልቻሉ እንደ ሀገር ውጤት ማምጣትና ግብን ማሳካት ይቸግራል።
እንደሚታወቀው የደን፣ አካባቢ ጥበቃና የአየር ለውጥ ጉዳይ የአንድ አካባቢ ወይም ክልል ጉዳይ አይደለም። ሥራው በባህርይው በአንድና ሁለት ተቋማት የሚሳካ ሳይሆን ተቀናጅቶ መሥራትን፣ የጋራ ጥረትን እና እንቅስቃሴን የሚጠይቅ በመሆኑ ተቀናጅቶ መሥራትን ግድ ይላል ያሉት ዳይሬክተሩ ይህ ተቀናጅቶ የመሥራቱ ሁኔታ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ግርማ መንግሥቴ