በአገራችን ባሳለፍነው ሳምንት በአብዛናው አገሪቱ ክፍሎች የነበረው ዝናብ ከመደበኛው የዝናብ መጠን ከፍ ያለ እንደነበር ተጠቆመ። ዝናቡ በቀጣዮቹ አስር ቀናትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የብሔራዊ ሜትሮሎጂ አገልግሎት አስታውቋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ለአዲስ ዘመን በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው በአገራችን ባለፉት አስር ቀናት ለዝናብ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥሩ የአየር ሁኔታ ክስተቶች በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ተጠናክረው ታይተዋል።
በዚህ መሰረት በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ዝናብ ተመዝግቧል። በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ የተመዘገበው ከባድ ዝናብ እንደነበርም ታውቋል። ከባድ ዝናብ ከተመዘገበባቸው አካባዎችም ውስጥ በደሎመና 149 ነጥብ 5፣ በአቦምሳ 107 ነጥብ 1፣ በደብረሲና 92 ነጥብ 6 እንዲሁም በሊሙ ገነት 82 ነጥብ 4 መሆኑን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ባለፉት አስር ቀናት የዘነበው የዝናብ መጠን ከሀገሪቱ የቦታ ሽፋን አንፃር ሲታይ የአፋር ዞን አንድና ሦስት፣ ምስራቅ ጎጃም፣ አገውአዊ፣ ደቡብ ወሎ፣ መካከለኛውና ምስራቅ ትግራይ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ በአሶሳ፣ ቶጎና ካማሺ ዞኖች፣ ጋምቤላ፣ በአብዛኛው ኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር፣ ብረሰቦችና ህዝቦች ክልል፣ በሶማሌ ክልል ደገሃቡር፣ ፊቅና አፍዴር ዞኖች፣ አዲስ አበባ እንዲሁም ድሬደዋና ሐረሪ ከ2 እስከ 9 ቀናት ያህል ከ25 እስከ 317 ሚሊሜትር የሚደርስ ዝናብ ተመዝግቧል።
በነዚህ ቀናት የነበረው ዝናብ ከመደበኛው ጋር ሲነፃፀር በአብዛኛው በትግራይ፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ በአፋርና ሶማሌ ክልሎች፣ በጉጂ፣ በጅማ፣ በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ፣ በአርሲ እና ባሌ፣ በከፋ፣ በሸካ፣ በጉራጌ፣ በስልጤ፣ በሐድያ፣ በወላይታ፣ በጋሞጎፋ፣ በሲዳማ፣ በጌዲኦ፣ በሸዋና ምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ እንደነበር ተጠቅሷል።
ባሳለፍነው ሳምንት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች በተለይ በልግ አብቃይ አካባቢዎች ላይ የነበረው እርጥበታማ የአየር ሁኔታ ለበልግ ሰብሎች ፍሬ ማፍራትና ለቀጣይ እድገታቸው ጠቃሚ መሆኑንና ለመኸር ተጠቃሚ አካባቢዎች ለማሳ ዝግጅትና ለዘር ሥራ እንቅስቃሴ፣ ለቋሚ ሰብሎች የውሃ ፍላጎት መሟላትና ለአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎችም ምቹ ሁኔታን የፈጠረ እንደሆነ ትንበያው አመልክቷል።
ባሳላፍነው ሳምንት በነበረው ከፍተኛ ዝናብም በሆሳእናና በማሻ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቆመው ኤጀንሲው መጪውም ክረምት በመሆኑ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አመልክቷል። የትንበያ መረጃዎቹ እንደጠቆሙት በቀጣይ የሚኖረው ዝናብ ሰፊ ቦታዎችን አካቶ የሚቀጥል ሲሆን ይህም ሁኔታ በተለያየ የእድገት ደረጃ ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች ጠቀሜታ ይኖረዋል። በተለይ ለቋሚ ተክሎች የውሃ ፍላጎት መሟላትና ለአርብቶ አደሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች የግጦሽ ሳር መሟላት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ትንበያው አመልክቷል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር