ግለኝነትን ያነገሱ ማህበራዊ ሚዲያዎች

በጊዜ ሂደት የሰዎች የአኗኗር ሁኔታ በሁለንተናዊ መልኩ እየተቀየረ መጥቷል። ይህ ክስተት ዓለም አቀፋዊ ነው። ለሰዎች የኑሮ ሁኔታ በሁለንተናዊ መልኩ መቀየር በርካታ ምክንያቶች አስተዋጽኦ አድርገዋል። ለአብነትም የፖለቲካዊና ማህበራዊ ሕይወት በየጊዜው መለዋወጥ፣ የኢኮኖሚ እድገት፣ የፈጠራ ውጤቶች ማደግና መሻሻል፣ ቴክኖሎጂ፣ ሳይንስና ምርምር ሌሎችም ይጠቀሳሉ።

በተለይ ደግሞ በየዘመኑ የመጡ ሕይወትን የሚያቀሉ ልዩ ልዩ የፈጠራ ውጤቶችና ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ለሰዎች አኗኗር መለወጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። ሚዲያውም በራሱ በጊዜ ሂደት መልኩን እየቀያየረ መምጣቱና አዳዲስና በህብረተሰቡ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተፅእኖ የሚያሳደሩ መረጃዎችን በገፍ መልቀቁ በሰዎች አኗኗር ላይ የማይናቅ ተፅእኖ አሳድሯል።

አሁን አሁን ደግሞ የማህበራዊ ሚዲያዎች በስፋት መምጣት ዓለምን አቀራርቧል። በዚህም ዓለም ወደ ትንሽ መንደር ተቀይራለች። ይህም ማለት በግሎባላይዜሽን /ሉዓላዊነት/ የዓለም ሕዝብ ማህበራዊ ሚዲያዎች በሚያቀርቧቸው መረጃዎች ተቀራርቧል። አኗኗሩም በሁለንተናዊ መልኩ ተቀይሯል።

ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ከየትኛውም የምድር ጫፍ ሆኖ መረጃ ማግኘትና መላክ ቀላል ሆኗል። መረጃ ደግሞ በብዙ መልኩ ጠቀሜታው የጎላ በመሆኑና በሰዎች ሕይወት ላይ ቀላል የማይባል ተፅእኖ ስላለው ከጦር መሳሪያ እኩል ትልቅ ኃይል ሆኗል። በማህበራዊ ሚዲያ መረጃዎች አማካኝነት ፖለቲካን፣ ማህበራዊ ሕይወትንና ኢኮኖሚን እንደየራስ ፍላጎትና ጥቅም መቃኘት ተችሏል። በዚህም ማህበራዊ ሚዲያዎች በሰዎች አኗኗርና ሕይወት ላይ በጎ ተፅዕኖ አሳድረዋል፤ እያሳደሩም ይገኛሉ።

ማህበራዊ ሚዲያዎች በሰዎች ሁለንተናዊ ሕይወት ላይ እያሳደሩ ያሉትን በጎ ተፅዕኖ ያህል አሉታዊ ተፅዕኖዎቻቸውም የዛኑ ያህል እያደገ መጥቷል። በማህበራዊ ሚዲያዎች በሚቀርቡ መረጃዎች አማካኝነት ሰዎች ሕይወታቸውን የመቀየራቸውን ያህል በነዚሁ ሚዲያዎች በሚወጡ የተዛቡ መረጃዎች ወደ ግጭትና አለመግባባት እየገቡ ነው። የራስን ማንነትና ባህል ለቆ የሌላውን መያዝ፣ በጎ አመለካከትን ባልሆነ መቀየርና…. ወዘተ ሌሎችም ይኸው ማህበራዊ ሚዲያው በሰዎች ላይ የፈጠረው በጎ ያልሆነ ተፅዕኖ ነው።

ከዚህ በተጨማሪም ማህበራዊ ሚዲያዎች ለማህበረሰቡ መረጃ ከመስጠት ባሻገር የመዝናኛ አማራጮችንም ፈጥረዋል። በዚህም በርካቶች ውስን ከነበረው የመዝናኛ አማራጭ ወጥተው እንደ እድሜያቸው፣ እንደፆታቸው፣ እንደእምነታቸው፣ እንደየራሳቸው ፍላጎትና ምርጫ እንዲዝናኑ እድል ተፈጥሮላቸዋል። የዛኑ ያህል ደግሞ ሰዎች ይህን መሠረት ባላደረገ መልኩ በማህበራዊ ሚዲያ የሚቀርቡ መዝናኛዎችን ያለምርጫና ያለገደብ መጠቀማቸው ያልሆነ ሁኔታዎች ውስጥ ከቷቸዋል።

ማህበራዊ ሚዲያዎች በአብዛኛው እያንዳንዱ ሰው በራሱ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ላፕቶፕ አልያም ደግሞ ኮምፒዩተር አማካኝነት የሚጠቀማቸው በመሆኑ ከሌሎች ሰዎች ጋር መነጋገርና ማውራትና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የመወያየት እድሎችን ገድቧል። እንደ ፌስቡክ፣ ዩቲዩብና ቲክቶክ የመሰሉ የማህበራዊ ሚዲያ ውጤቶች መመልከት አንዳንዴ ሱስ እስከማስያዝ ድረስ ስለሚደርሱ በአንድ ቤት ውስጥ ያለ ቤተሰብን እንኳን የመነጋገርና ሃሳብ የመለዋወጥ እድል ያሳጣል። አሁን አሁን እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።

ልጆች በአብዛኛው በቪዲዮ ጌሞችና ዩቲዩብ ላይ ተተክለው ነው የሚውሉት፤ ተተክለው ነው የሚያመሹት። ከእናት አባታቸው ጋር ስለትምህርታቸውና ስለቀን ውሏቸው አያወሩም፤ አይነጋገሩም። የሚነጋገሩት ከታብሌት ወይም ከስልክ ጋር ነው። ለብቻቸው እንጂ ከሰው ጋር መሆን አይፈልጉም። እንደ ልጅ አይጫወቱም።

እናትም ብትሆን ስልኳን ይዛ ፌስቡክ፣ ቲክቶክ ወይ ደግሞ ዩቲዩብ ነው የምታየው። ብዙ ጊዜዋን የምታሳልፈው ይህንኑ ማህበራዊ ሚዲያ በማየት ነው። በዚህ መሃል ልጆችን መከታተል፣ ምን ተምረው እንደመጡ መጠየቅ፣ ስለውሏቸው ማውራት የሚባል ነገር የለም። በእናትና ልጅ መካከል የሚደረግ ንግግርና የሃሳብ ልውውጥ ብዙ አይኖርም።

አባትም ቢሆን በላፕቶፕ ላይ ተተክሎ ቤት እንኳን ሳይቀር ሥራውን ነው የሚሰራው። ሥራው ሲሰለቸው ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያዎችን መመልከቱ አይቀርም። ቲክቶክ፣ ፌስቡክና ዩቲዩብ ይመለከታል። ይህን ከማድረግ ፈንታ ለልጆቹ ጊዜ አይሰጥም። ለራሱ ብቻ ነው ጊዜ የሚሰጠው። ልጆቹ ምን ተምረው እንደመጡ እንኳን አይጠይቅም። በቃ! ግለኛ ነው።

ይህ እንግዲህ የማህበራዊ ሚዲያዎች በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ምን ያህል ግለኝነትን እየፈጠሩ እንደመጡና ቤተሰብ እርስ በርስ እንዳይነጋገርና ሃሳብ እንዳይለዋወጥ ተፅእኖ እያሳደሩ ስለመምጣታቸው ይጠቁማል። ከቤተሰብ ባለፈ በጎረቤት፣ በሰፈር፣ በአካባቢ፣ በማህበረሰብና በሀገር ላይም ከማህበራዊነት ይልቅ ግላዊነት እንዲነግስ አሉታዊ ተፅእኖ እያሳደሩ ይገኛሉ።

በዛሬ ዘመን ልክ እንደበፊቱ ቡና አፍልቶ፤ ጎረቤት ተጠራርቶ መነጋገር፣ መጫወት፣ ሃሳብ መለዋወጥ የሚባል ነገር እየጠፋ መጥቷል። ቡናው ቢፈላ እንኳን ቡናውን ለመጠጣት ከመጣው ሰው ውስጥ ግማሽ ያህሉ ስልኩን የሚጎሮጉር እንጂ የሚጫወትና ሃሳብ የሚያካፍል አይደለም። ሁሉም በየቤቱ የራሱን ሕይወት ነው የሚኖረው።

አሁን አሁንማ በሠርግም በለቅሶም፣ በልደትም በተስካርም ሰው ታዘበኝ አልታዘበኝ ሳይሉ ስልካቸው ላይ አፍጠው ፕሮግራሙ እንዴት እንኳን እንደተካሄደ በቅጡ ሳይረዱ ወደቤታቸው የሚሄዱ ብዙዎች ናቸው። በየመንገዱ ስልካቸውን እየነካኩ ዞር ብለው የማያዩና ለአፍታ እንኳን ቀና የማይሉ ከፖል አልያም ከሰው ጋር የሚጋጩ፤ ወይም ከመጋጨት ለጥቂት የተረፉም በርካታ ናቸው።

እንግዲህ ማህበራዊ ሚዲዎች ይህን ያህል ቀልብ እስከ ማስረሳት የሚያደርስ ተፅእኖ በሰዎች ላይ እያደረሱ ነው። ሰዎች የግልኝነት ባህሪን እንዲላበሱም የማይናቅ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ነው። ያ የምንኮራበትን ማህበራዊ ሕይወታችንንም እያናጉ ነው። እና? እናማ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን በወጉ ይሁን!!

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 26/2016

Recommended For You