በእያንዳንዱ የዕውቀት ዘርፍ የሚደረግ ጥናትና ምርምር የሰዎችን ሕይወት ማሻሻል ላይ ትኩረት ያደረገ መሆን እንዳለበት ብዙዎች ይስማማሉ፡፡ አንድ ሰው በትክክል “ምሁር” ለመባል ብቁ የሚሆነው ዕውቀቱን ከራሱ አልፎ በሌሎች ሕይወት ላይ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚጠቀምበት ከሆነ ነው፡፡ ምሁርነትም ከዚህ አንፃር ታይቶና ተመዝኖ የሚሰጥ ክብር እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ።
አብዛኞች እንደዋዛ ጥለዋት በሚለይዋት ዓለም በተቃራኒው ጥቂቶች ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች የሚተርፍ አስተዋጽኦ አበርክተው ማለፉ ይሳካላቸዋል። በሚያልፍ ዕድሜ የማያልፍ ሥራ ሠርተው ስማቸው ሲወሳ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል መስራች ዶክተር በላይ አበጋዝ ናቸው። ዕውቀት ብስለት ከጥበብ ጋር የሰመረላቸው እና ለኢትዮጵያ ሕፃናት እና ወላጆች ተስፋ የሆኑ ሰው ናቸው።
የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል መስራች የሆኑ ዶክተር በላይ፤ በደቡብ ወሎ ኩታበር 1937 ተወልደው፣ ደሴ በሚገኘው ወይዘሮ ስህን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በየዓመቱ ከልብ ሕመም ጋር ለሚወለዱ ከ50 እስከ 60 ሺህ ለሚሆኑ ሕፃናት ተስፋ መሆን የቻሉ ሰው ናቸው። ዶክተር በላይ አበጋዝ ከምንም ነገር በፊት ሀገርና ወገንን ያስቀድማሉ፡፡ መነሻቸውን ቅንነትና አገልጋይነት ነው፡፡
በተግባር የተፈተነ የሀገር ፍቅር ያላቸው እኚህ ጉምቱ ኢትዮጵያዊ በአንድ ቃለ ምልልሳቸው ዶክተር ኢትዮጵያዊ መሆን ምን የተለየ ስሜት አለው? የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ሱዳናዊ፣ ኬንያዊ፣ አሜሪካዊ ከመሆን በምን ይለያል? በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ተናግረው ነበር፡፡ እኔ ምን አውቄ ሱዳናዊ ወይም የጠቀስካቸው ሀገሮች ዜጋ ሆኜ አላውቅ። “ሀ” ሲባል ኢትዮጵያዊ ነኝ። ኢትዮጵያዊ ሆኜ መሞትም ነው የምፈልገው። በሕይወቴ የማልክዳቸው ሶስት ለራሴ የገባኋቸው ቃል ኪዳኖች አሉ። ከነሱ አንዷ ሀገሬ ናት ሲሉ ይናገራሉ።
ዶክተር በላይ በተጨማሪ ሲናገሩ፤ ስለ ሀገር ከተነሳ ሌላ አንድ ነጥብ ላንሳልህ ብለው በመቀጠል አንድ ገጠመኛቸውን በዚህ መልኩ አጋርተዋል፡፡ ትልቁ ልጄ ገና ትንሽ ልጅ ሆኖ (በወቅቱ አሜሪካ ነበርን) “ሀገራችን እንሂድ?” አለኝ “ለምን?” አልኩት። “ ይሄ ሀገር (አሜሪካ) ልክ አይደለም። ልክ ቢሆን ኖሮ እኔን ስለ አሜሪካ ታሪክ ሲያስተምሩኝ ክፍል ውስጥ ላሉት ደግሞ የኢትዮጵያን ታሪክ ማስተማር ነበረባቸው” አለኝ። በወቅቱ የሱ አዕምሮ ይሄን አሰበ። ሁለት ሳምንት ሳይሞላው ደግሞ ትንሹ ልጄ እናቱን “ወደ ሀገራችን እንሂድ አላት” “ለምን?” ስትለው “ብትሞቺብንስ?” አላት። “ እኔ ብሞት በሥርዓት የሚያሳድግ አባት አላችሁ” ብላ መለሰችለት። አስበው በጣም ትንሽ ልጅ ነው።
ዶክተር በላይ በመቀጠል “አባቴስ ቢሞት አላት?” “ለምን ይህን ታስባለህ? አለችው። “ሁለታቹሁም ብትሞቱ ወላጅ አልባ ነው የምንሆነው። ወላጅ አልባ ከሆንን ደግሞ የሀገራችን ሕዝብ እንዲያሳድገን ነው የምንፈልገው።” አላት። አንተ በዚህ ልጅ ወይም በኔ ቦታ ብትሆን ምን ነበር የምትመልሰው? ሰባት ዓመት ያልሞላው ልጄ ገና በአንድ ዓመቱ ለቋት በሄደው ሀገሩና በማያውቃቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ እምነቱን እንዲህ ጥሏል። ልክ በሃይማኖት ሳንከራከር እንደምናምነው ኢትዮጵያዊነትንም ሳልከራከር ነው የምቀበለው። ምንም ቢሆን ይህንን ተስፋዬን ማጣትም አልፈልግም። ገንዘቤ ሊወሰድ ይችላል። ጤንነቴ ሊጓደል ይችላል። ተስፋዬን መነጠቅ ግን በፍፁም አልሻም። በማለት መልሰዋል።
ዶክተር በላይ አበጋዝ ሀገራቸውን ያገለገሉት በሕክምና ሙያ ብቻ አይደለም፡፡ የሕይወት መስዋዕትነት በሚያስከፍለው የውትድርና ሙያ ላይም ተሰማርተው የቆዩ ሰው ናቸው። በሐረር ወታደራዊ ትምህርት ቤትም የወታደራዊ ሳይንስ ተምረዋል፡፡ በዚህ ሙያቸውም የሌተናል ኮሌኔልነት ማዕረግ ተቀብለዋል፡፡ ጀግና፤ በጎ አድራጊ፣ ጎበዝ ወታደር ሆነውም በንጉሠ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አራት ጊዜ ተሸልመዋል።
ዩኒቨርሲቲ ገብተው አጠቃላይ ሕክምናን ካጠኑ በኋላ የልብ ሕክምናን በተለይም የሕፃናትን ልብ ሕክምና በማጥናት አሁን ላይ መሠረት እንዲጣል ለተደረገው የዘርፉ ሕክምና አበርክቷቸው የጎላ እንዲሆን አድርጎታል፤ የሕፃናት ልብ ስፔሻሊስቱ ዶ/ር በላይ አበጋዝ።
ዶክተር በላይ፣ ከራስ ወዳድነት የፀዳ አመለካከት እንዳለቸው የተለያዩ ግለሰቦች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ ከእነዚህ መካከል፤ ምስ ጅዝ ልዘክ የተባሉ ፀሐፊ a man with heart for all children’s በተባለ ጽሑፋቸው ዶክተር በላይ አበጋዝ ራስ ወዳድ ያልሆነ ቁሳቁስን ለማጋበስ ፍላጎት የሌለውና ሀገሩን፣ ሕዝቡን የጎረቤት ሀገራትን የልብ ሕመም ሕፃናትንና ወላጆቻቸውን በነፃ የሚያገለግል ሐኪም ነው በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ዶክተር በላይ አበጋዝን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በስፋት ያስተዋወቀቸው የልብ ሕሙማን ሕፃናት መርጃ ድርጅት ነው። የልብ ሕመም ያለባቸው ሕፃናት ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ለመታከም የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው የሚያጋጥማቸውን ጉዳት ለመቀነስ ዶክተር በላይ በመላው ዓለም ዞረው ድጋፍ በማሰባሰብ የመሠረቱት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ተስፋ ለሆኑ ሕፃናት የደረሰ ድርጅት ነው። ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን፣ የውጭ ሀገር ዜጎችን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የነፃ ሕክምና አገልግሎት ሰጭ ሐኪሞችንና መሳል ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ለትውልድ የሚተርፍ ስኬታማ ሥራን ሰርተውበታል።
መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብና ባለሀብቶችን በማስተባበር ያቋቋሙት የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል ለበርካታ ሕፃናትና የልብ ሕክምና ፈላጊዎች ሕክምናው በስፋት እንዲሰጥና ተደራሽ እንዲሆን የእሳቸው ጥረትና መና ከፍተኛ ነው። በ30 ዓመታት ቆይታውም ከ10ሺህ በላይ ሕፃናት የልብ የሕክምና ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችለዋል። ለአንድ ሕፃን ሕክምና ያስፈልግ የነበረውን የ30ሺህ ዶላር ወጪ፣ የጊዜ ብክነት፣ የወላጆችን እንግልትና ስቃይ ያስቀረ ነው።
ዶክተር በላይ ከሕፃናት የልብ ሕክምና ማዕከሉ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም የሚያስተምር፣ ጥናት የሚያደርግ የልብ ሕክምና ኮሌጅ እንዲመሰረት ከማድረጋቸው ባሻገር በሚያስፈልጉት እገዛዎች የተለያዩ ግለሰቦች፣ ሀገራትንና ተቋማትን በማናገር የሕክምና ኮሌጁ በሁለት እግሩ ቆሞ ለኢትዮጵያ ሕፃናት ተገቢውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከፍተኛ ሚና ተወጥተዋል።
ዶክተር በላይ አበጋዝ በትህትናቸው ይታወቃሉ፡፡ ብዙዎች ጥቂት ሰርተው ብዙ በሚናገሩበት ዘመን አያሌ ለሀገርና ሕዝብ የሚጠቅም ነገር ሰርተው “ገና ምንም አልሰራሁም” የሚሉ ናቸው፡፡ ይህ ስብዕና ብዙዎች ጋር የሌለ ለጥቂቶች የሚሰጥ መልካም ፀባይ ወይም ባህርይ ነው። ዘርፉን ለማጥናት የወሰኑበትን ምክንያት ሲናገሩ “በየዓመቱ ከ50ሺህ በላይ ሕፃናት ከልብ በሽታ ጋር ይወለዳሉ፤ በተጨማሪ ከ50 ሺህ – 60ሺህ ደግሞ ከተወለዱ በኋላ የልብ በሽተኛ ይሆናሉ። ሕክምናውን ስለማያገኙ ደግሞ ይሞታሉ” ይላሉ።
ዶ/ር በላይ አበጋዝ ከ1973 ዓ.ም ጀምረው ላለፉት 41 ዓመታት በሕጻናት ሕክምና እና በሕጻናት ካርዲዮሎጂስትነት በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር በሙያቸው አገልግለዋል። ከሕክምናው በተጨማሪም የሕጻናት ሕክምና ሳይንስን (ፔዲያትሪክስን) አስተምረዋል፣ ስለ ሙያውም ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን አሳትመዋል። በተጨማሪም በተለያዩ አካዳሚዎች ውስጥ ተሣትፎ በማድረግ ይታወቃሉ።
ከነዚህም ውስጥ ከ1981 ዓ.ም ጀምረው የአሜሪካ ፔዲያትሪክስ አካዳሚ በአባልነት፣ በInternational Society of Hypertension in Blacks በአባልነት፣ በThe Pan African Society of Cardiology በአባልነት፣ The National Drug Advisory Board of Ethiopia አባል ሲሆኑ፣ በEthiopian Medical Journal በአባልነት፣ በረዳት ዋና ፀሐፊነትና በሊቀ መንበርነት አገልግለዋል፡፡ የHealing the Children USA, Save a Child’s Heart ISREAL and Chain of Hope UK ተባባሪ ናቸው። የአዲስ አበባ ላየንስ ክለብ አባል እና ዋና አራማጅም ናቸው።
ዶክተር በላይ አበጋዝ ለበርካታ ዓመታት ደከመኝ ሠለቸኝ ሳይሉ በወቅቱ የሚያጋጥማቸው መስናክሎችና ችግሮች ሳይበግራቸው ለሀገራቸው በሕክምናው ዘርፍ የማይረሳ ዐሻራ አሳርፈዋል። በዚህም ምክንያት በሀገር ውስጥ እንዲሁም ከሀገር ውጭ በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ በ2008 ዓ/ም በልብ ሕክምና ዘርፍ ባደረጉት በጎ አስተዋጽኦ ከወሎ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ ተቀብለዋል።
በ2006 ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ነበሩ፤ የልብ ሕሙማን ሕክምና መርጃ ማህበር ምስረታ 30ኛ ዓመት ሲከበርም ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶክተር) እጅ የሕይወት ዘመን አገልግሎት ሜዳልያ ዕውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በአሁኑ ወቅት የብሩክ የሕክምና አገልግሎቶች ድርጅት በሙሉ ጊዜያቸው በግላቸው እየሰሩ ይገኛሉ። እሳቸው የመሠረቱት የኢትዮጵያ የልብ ሕክምና ማዕከል በርካታ ሕጻናትን ጨምሮ በኢትዮጵያ የልብ ሕክምና በስፋት እንዲሰጥ የሳቸው ዐሻራ ዘመን ተሻጋሪ ነው።
ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ሕፃናት ወደ ውጭ ሀገራት ሄደው በቋንቋ ከማይመስሏቸው በመልክ ከማይመስሏቸው ውሃ ብለው ቢጠይቁ ውሃ ምን እንደሆነ በማያውቁ ነርሶችና ሐኪሞች መታከሙ እራሱን የቻለ በደል በልጆች ላይም የሚያሳድረው የአእምሮ ጠባሳ ቀላል እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶክተር በላይ በራስ ወገን የልጆቹም ወላጆች ባሉበት መታከም መቻሉ ፋይዳው ትልቅ በመሆኑ እንደ ቀላል የሚታይ ስላለመሆኑ ይናገራሉ።
ከዛሬ 14 ዓመት በፊት የተቋቋመው የሕፃናት የልብ ሕክምና ማዕከል በኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ከባድ ሊባሉ የሚችሉ የልብ ቀዶ ጥገና በሀገር ውስጥ መስጠት መቻሉ የሚናገሩት ዶክተር በላይ ነገር ግን በአላቂ ዕቃዎች ዕጥረት የተነሳ ሆስፒታሉ የተሟላ አገልግሎት መስጠት አለመቻሉ የሚያስቆጫቸው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ ይናገራሉ።
ዶክተር በላይ በተለይ በአላቂ ዕቃዎች ዕጥረት ምክንያት ቀዶ ሕክምና ማድረግ እያለባቸው ሕክምና ማግኘት ያልቻሉ ሮጠው ያልጠገቡ ሕፃናት ሕይወት እንዳይጠፋ መንግሥት ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ በማንሳት ከዚህም ባሻገር ማዕከሉ ጠንክሮና በሁለት እግሩ ቆሞ ለብዙዎች መድረስ እንዲችል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎኑ መቆም እንዳለበት ይናገራሉ።
ቀደም ባሉት ዓመታት የልብ ሕመም የሰለጠኑ ወይም የሀብታም ሀገራት የጤና ችግር ብቻ ተደርጎ ይታሰብ ነበር። ይሁን እንጂ ችግሩ በማደግ ላይ ያሉ ወይም የደሃ ሀገራትም ዋነኛ አሳሳቢ ፈተና መሆኑ አልቀረም። ከዚህ ቀደም በበለፀጉ ሀገራት ሕዝቦች ዘንድ በስፋት ይታይ የነበረው የልብ ሕመም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ ሀገራት ሕዝቦች ላይም የተጋረጠ ፈተና መሆነ በጉልህ እየታየ ይገኛል።
የልብ ቀዶ ጥገና በኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች መሰጠት በጀመረ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ እስከ መቶ የሚደርሱ የልብ ታማሚዎች በሀገር ውስጥ ያለ ምንም ወጪ ይታከማሉ። ይሁን እንጂ አሁንም በኢትዮጵያ የልብ ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ቁጥራቸው ቀላል የማይሆኑ ሕፃናት ወረፋ በመጠባበቅ ሕክምናቸውን በጊዜ ለማግኘት እንደሚቸገሩ የኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ይገልፃል። በየዓመቱ እስከ 500 የሚደርሱ ሕጻናት የልብ ቀዶ ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ እና ቀዶ ሕክምና የሚፈልጉ ሕጻናት ቁጥር በየቀኑ እንደሚጨምር ማዕከሉ ያስረዳል።
በማዕከሉ አላቂ እቃዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖራቸው የተነሳ ወረፋ የሚጠብቁ ሕጻናት ሕክምና እያገኙ አለመሆናቸውን እና መድኃኒትም ቢሆን በሚፈለገው መጠን አለመገኘቱ በሥራው ላይ እንቅፋት እንደሆነበት በተደጋጋሚ የሚገልጸው ተቋሙ፤ አላቂ እቃዎች እና መድኃኒቶች በበቂ መጠን ቢያሟሉ ኖሮ ግን በዓመት ከ 1 ሺህ 500 ያላነሰ ቀዶ ጥገና ማድረግ ይቻል እንደነበር ያስረዳል።
እኛም በእኚህ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ምሁር የተመሠረተውን ይህንን የነገ ሀገር ተረካቢ ሕፃናት ተስፋ የሆነውን ተቋም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው ሁሉ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል እያልን ለማዕከሉ መስራች ዶክተር በላይ አበጋዝ ረጅም ዕድሜ ከጤና ጋር ፈጣሪ እንዲሰጣቸው እንመኛለን።
ክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2016