አዳማ፡- ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት በአዳማ ገልማ አባገዳ ጊቢ ውስጥ የመጀመሪያውን ችግኝ በመትከል በክረምት ወቅት ለማከናወን የታቀደውን የ4 ቢሊየን ዛፍ ተከላ መርሐ ግብር በይፋ አስጀምረዋል። መርሐ ግብሩ በይፋ በተጀመረበት የተከላ ፕሮግራም ላይ የክልል ፕሬዚዳንቶችና ምክትል ፕሬዚዳንቶች፣ ከወረዳ እስከ ክልል ያሉ የግብርና ቢሮ ሃላፊዎች፣ እንዲሁም የወረዳና የዞን አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን፤ በወቅቱም አምስት ሺ ችግኞች ተተክለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብሩን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ደን ሽፋን ቀደም ሲል ከነበረበት 30 በመቶ አሁን ላይ ከአራት በመቶ ወደማይበልጥበት ደረጃ ደርሷል። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያ የመሬት ስፋት አኳያ ሲታይ እጅግ ዝቅተኛና አስደንጋጭ ነው። ይህም የነበረው ደን የመጨፍጨፍ ውጤት እንደመሆኑ ይሄንን ደን መልሶ የማልማት ተግባር ለነገ የሚባል አይሆንም። እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለፃ፤ አራት ቢሊዬን ችግኝ ለመትከል አንድ ሰው አርባ ችግኞችን መትከል ይጠበቅበታል።
ይሄንንም እንደ ቀድሞው ርቆ በመሄድ ሳይሆን በመኖሪያና ሥራ አካባቢዎች በማድረግ በቅርበት ተንከባክቦ እንዲፀድቅ ማድረግን ይጠይቃል። ሥራውም የአየር ንብረትን ለመጠበቅ፣ አካባቢን ጽዱና ለጤና ተስማሚ ለማድረግ፣ ብሎም ተፈጥሮን ለማስማማት የሚያግዝ ነው። በዚህ ሂደት በጽሕፈት ቤታቸው ጊቢ ውስጥ አንድ ሺህ ችግኞችን እንደሚተክሉ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ ሥራው ሁሉን አቀፍ ሊሆን እንደሚገባውም አሳስበዋል። ለዚህም በስብሰባዎች መክፈቻና መዝጊያ፣ በትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጭምር ይሄው ተግባርተጠናክሮ ሊተገበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ ካለው አቅምና የዝግጅት ጊዜ አኳያ አራት ቢሊዬን መደረጉን በማንሳትም፤ በቀጣይ ከዚህ በላይ በመሥራት የደን ሽፋኑን ለማሳደግ እንደሚሠራ ተናግረዋል። በውይይቱም ባለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በመቀነሱ በዚህ መርሐ ግብር 40 ዛፍ በነፍስ ወከፍ መልሶ ለመትከል መታቀዱን ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። በዚህ መሰረትም ዛሬ በይፋ በተጀመረው ብሔራዊ የአረንጓዴ ልማት ፕሮግራም መርሔ ግብር በቀጣዩ ክረምረት ወቅት በመላ ሀገሪቱ 4 ቢሊየን የሚሆኑ ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዟል።
የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ የደን ልማት ንቅናቄና የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እንደሚከናወን ማስታወቁ ይታወሳል። ኮሚሽኑ በብሔራዊ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የሚመራና የተለያዩ ዘርፎችን የሚመሩ የሚኒስትሮች ኮሚቴ አባላትን በመያዝ ዓላማውን ለማሳካት እንደሚሠራም ተነግሯል። የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄው ዓላማም በችግኞች ፅድቀት ተግዳሮቶች ምክንያት የከሰሙና የቀጨጩ ችግኞችን በተሻሻለ ሁኔታ ለመተካት መሆኑ ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ወንድወሰን ሽመልስ