አዲስ ዘመን ትናንት እንደምን ሰነበተ እያልን ከትውስታ ማህደሩ ቀንጨብ በማድረግ በአዲስ ዘመን ድሮ እናስታውሳቸው ዘንድ ወደናል፡፡ 1965ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን የቦይንግ አውሮፕላን የመጥለፍ ሙከራ ስላደረጉት ወንበዴዎች ከፖሊስ የተሰጠ መግለጫ፣ ባላገሮችን የማታለያ ዘዴው አሁንም ቀጥሏል፡፡ ከወዲህ ደግሞ ማስጠንቀቂያ ለአማርኛ አንባቢያን…ከጳውሎስ ኞኞ ደበዳቤዎችም የተወሰኑትን እናካፍላችኋለን፡፡
አውሮፕላን ለመጥለፍ ስለሞከሩት ወንጀለኞች ከፖሊስ መግለጫ ተሰጠ
ባለፈው ዓርብ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ለመጥለፍ ሙከራ አድርገው የነበሩትን ወንጀለኞች ዓላማ ለማወቅ የፖሊስ ሠራዊት ሰሞኑን ስለፈጸመው ምርመራ ውጤት ትናንት ከዚህ የሚከተለውን መግለጫ ሰጥቷል።
ኅዳር 29 ቀን 1965ዓ.ም የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ መስመር ቁጥር 720 ቦይንግ ጄት አውሮፕላን 94 መንገደኞችና 9 የአውሮፕላኑን ሠራተኞች አሳፍሮ ከጧቱ 1 ሰዓት ተኩል በአሥመራ በኩል ወደ አቴንስ ሮም፤ፓሪስ ለመሔድ ከአዲስ አበባ ተነሥቶ 13 ደቂቃ ያህል እንደበረረ በወቅቱ ማንነታቸው ያልታወቀ ወንበዴዎች ለማስገደድ በመሞከራቸው ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ25 ደቂቃ ተመልሶ አዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ጣቢያ አርፏል።
ሁኔታው እንደተሰማ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የመንግሥት የፖሊስ ሠራዊት የደረሠው የምርመራ ቡድን በሥፍራ ላይ ተገኝቶ ባደረገው ምርመራ አምስት ወንዶችና ሁለት ሴቶች የጦር መሳሪያና ቦንብ ይዘው ለማስገደድ በመሞከር በአውሮፕላኑ ውስጥ ባስነሱት ተኩስ በተደረገው መከላከል ከአንዷ ሴት በቀር የተቀሩት በሙሉ ተገድለዋል።
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 9 ቀን 1965ዓ.ም)
ባላገሮችን ያታለሉ ተፈረደባቸው
“ከሀብታሞች ዘንድ ወስደን ገንዘብ እናሰጣለን” በማለት ከገጠር የሚመጡትን ገበሬዎች ከመንገድ እየጠበቁ አታለው ገንዘብ የወሰዱት ሁለት አታላዮች የ15ዓመት እሥራት ተፈረደባቸው፡፡
ከአሩሲ ጠቅላይ ግዛት ከአርባ ጉጉ አውራጃ የመጡት አቶ ኢንካ አብዲን “ሀብታሞች ለድሃ ገንዘብ ይሰጣሉ” በማለት 30 ብርና አንድ ጋቢ አጭበርብሮ የወሰደው ታደሰ ቢነግዴ የ10 ዓመት እሥራት ትናንት ተፈረደበት፡፡ ከሸዋ ጠቅላይ ግዛት ከሜታ ሮቢ የመጡት አቶ ጐንፋ ሙለታን “ትልልቅ አዛውንት ገንዘባቸውን በነፃ ለሕዝብ ስለሚያድሉ በኪስዎ ያለውን ገንዘብ ከእኔ ዘንድ አስቀምጠው ብዙ ገንዘብ ተቀብለው ሲመጡ ይወስዳሉ” በማለት 100 ብር የወሰደባቸው አሰፋ መንገሻ በ5 ዓመት እሥራት እንዲቀጣ የአዲስ አበባ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትናንት በየነበት ፡፡
ሁለቱም አታላዮች ወይም እንደፖሊሶቹ አጠራር “እነ ቁጭበሉ” በአዲስ አበባ ከተማ አንዳንድ ባላገሮች በማታለል “ለአርበኞች ፤ለአገለገሉ ፤ለሸመገሉና ምንም ለሌላቸው ሰዎች ገንዘብ በነፃ ይሰጣል፡፡ የያዛችሁትን ሁሉ ከኛ ዘንድ አስቀምጣችሁ ስትመለሱ ትወስዳላችሁ” በማለት ይዘው እየጠፉ የሚያታልሉ መሆናቸው ተመስክሮባቸዋል፡፡
ወንጀለኞቹ ደኅና ልብስ እየለበሱ ታማኞችና ሽማግሌዎች በመምሰል ባላገሮችን “ገንዘብ በነፃ ለመቀበል በምትሄዱበት ጊዜ ተፈትሻችሁ ገንዘብ ከኪሳችሁ የተገኘ እንደሆነ ትወረሳላችሁ፤ደኅና ልብስ የለበሳችሁ እንደሆነ ትገፈፋላችሁ በማለት” የሚያታልሉ መሆናቸው በምስክር ተረጋግጦባቸዋል፡፡
(አዲስ ዘመን ሰኔ 15 ቀን 1964ዓ.ም )
ለአማርኛ አንባቢያን ማስጠንቀቂያ
አቶ ጥላሁን በየነ የተባሉ ሰው በቅርቡ በተጻፈች “ልሳን” በተባለች መጽሐፋቸው ውስጥ”የቀ.ኃ.ሥ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የሆኑት ዶክተር ጌታቸው ኃይሌና ዶክተር አብርሃም ደሞዝ መጽሐፌን ከመታተሙ በፊት ባማረና ልዩ ልዩ ጽሑፎችን በማቅረብ እርዳታ ሰጥተውኛል” ብለው መሠረተ ቢስ የሆነ መግለጫ ከመጽሐፉ መግቢያ ላይ አስፍረው ትንሽ የሆነች መጽሐፋቸውን አንዷን በአሥር ብር ሒሳብ ጉዳዩን ለማያውቅ ሕዝብ በመቸብቸብ ላይ ናቸው።
….
እንዲያውም በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኘው ስሕተት ከመጠን በላይ የበዛ ስለሆነ ያንን ሁሉ ስሕተት ከማረም አዲስ መጽሐፍ ለመጻፍ የሚቀለን መሆኑን ገልጠን ጊዜያችንን ለማባከን እንደማንፈቅድ አስረድተናቸዋል።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 17 ቀን 1966ዓ.ም)
ጥያቄ አለኝ
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*ጅማ ሆኜ ሶዶ ያለችውን የምወዳትን ልጅ በሕልሜ የማየው እግዚአብሄር ነው የሚያሰየኝ ወይንስ ሰይጣን?
እሥራኤል መና (ከሚዛን ተፈሪ)
-ነገሩ ከአሳብህም ሊሆን ይችላል። ግን ሰይጣን አሳየህ ከማለት እግዚአብሄር አሳየህ ማለት ይሻላል?
*ጥላሁን ገሠሠ በደንብ ስለሚያጫውት ለምን ይሰድቡታል? አንተስ ለምን አዝማሪ ትለዋለህ?
መ.ጥ (ከአዲስ ከተማ)
– ታዲያ ምን ልበለው?
(አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 1965ዓ.ም)
*የሴቶች ማኅፀን ወደ ወንዶች ተለወጠ የሚሉትን ነገር ሰማሁ። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
-የተለወጠው ማኅፀን ሳይሆን ወንዱን ሴት አደረጉት። ይህም ተችሎ ተሥነ ሥዕሉ አይተናል። የሰው ልጅ ተራቅቆ ከእንዲህ ያለው ደረጃ በደረሰበት ጊዜ እናንተ ከእዚህ ምቀኛ አስቸገረኝ እያላችሁ ልቤን ውልቅ ታደርጉታላችሁ። ድሀ ድሀን ቢመቀኘው ምን ሊጎዳው? ይልቅስ ለሥራው እንበርታ።
(አዲስ ዘመን የካቲት 3 ቀን 1965ዓ.ም)
*ሦስቱ ሀሐኀ በአንድ ቢጠቃለሉ አይሻልም ወይ?
ሁሴን ያሲን
– ምን ሦስት ብቻ ናቸው? ሰባት ናቸው ሀሃሐሓኀኃኻ እነዚህ ሁሉ አንድ ቢሆኑ እንዴት ጥሩ ነበር። ይህ ነገር እንዲሻሻል በጋዜጣ ላይ ንትርክ የተጀመረው ከዛሬ 50 ዓመት በፊት ጀምሮ ነበር። 1917ዓ.ም ይታተሙ በነበሩ ጋዜጦች ላይ ሁሉ ይቀነሱ በዝተዋል የሚል ክርክር የበዛ ነበር። ግን እስካሁን አልተሻሻሉም። በተለይ በአሁኑ ዘመን ጽሕፈት በመኪና በሚካሄድበት ዘመን ብዙ አስቸግረውናልና ሊሻሻሉ የሚገባ ይመስለኛል።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 17 ቀን 1965ዓ.ም)
*ጫት እንደ ጎመን ተሠርቶ ይበላል አሉ፡፡ እውነት ነው?
ዮናስ ዘሺፍ(ልደታ)
-ጥሬውን እየቀረደዱት ምን መሥራት ያሻል? ወይንስ ሆዳቸውን እንዳያማቸው፡፡
ሙሉጌታ ብርሃኑ
(አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 1965ዓ.ም)