ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተለያዩ አገራት የሚገኙ ወጣቶችና ታዳጊዎች የዲያስፖራ አባላት ወደአገራቸው መጥተውም ሆነ ባሉበት ሆነው ለአገራቸው ልማትና እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቀረቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትላንት በጽህፈት ቤታቸው አማካይነት ባስተላለፉት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳሉት ይህንን መልዕክት ለማስተላለፍ የፈለኩት ይህ አገር ቤታችሁ ስለሆነና እናንተም የዚህ አገር አካል ስለሆናችሁ ነው ብለዋል።
“በውጭ አገራትባደረኳቸው የሁለትዮሽ ግንኙነቶች ሁሉ ለአገራችሁ ምን ያህል ተስፋ እንዳላችሁ ተገንዝቤያለሁ፤ ኢትዮጵያውያንም በምን አይነት ሁኔታ እንዲኖሩ እንደምትመኙ ተረድቻለሁ፤ የመደመርን እሳቤም ተረድታችሁ አንድነታችሁን ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላችሁ እገነዘባለሁ፤ ስለአገራችሁ ዜጎች ያላችሁ ስሜትና እነሱንም ለመርዳት ያላችሁ ተነሳሽነት ስለአገራችሁ ያላችሁን ስሜት የሚያሳይ ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ዛሬ አገራችን የተስፋ መጓደል ይታይባታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ እናንተ ከሩቅ ሆናችሁ የምትፋለሙለት ተስፋ፤ በቅርብም ሆነ በሩቅ ያሉት ወላጆቻችሁና እናንተ የምትፀልዩለት ሠላምና አንድነት፤ የማይቻል በሚመስልበት ወቅት እንኳን የምትተማመኑበት ሠላም ዛሬ የናንተን ድጋፍ ይሻልም ብለዋል። በዚህም መሰረት ፍላጎቶቹ በርካታ እና ባላችሁ አቅም ለመሳተፍ ሰፊ እድል ቢኖራችሁም ለእናንተ የእረፍት ጊዜ በሆነው መጪው ክረምት ከዚህ በሚከተሉት አምስት ጉዳዮች ላይ እንድትሳተፉ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል።
በዚህም መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በአገራችሁ ተስፋ አትቁረጡ፤ አቅማችሁንና ሃይላችሁን እንዲሁም የተስፋ ቡቃያችሁን ሁሉ በሁላችንም የተባበረ ጥረት በአጭር ጊዜ ወደ ተጨባጭ ውጤት እንደሚለወጥ ተስፋ አድርጋችሁ ተንቀሳቀሱ፤ መለወጥ እንደምንችል እመኑ፤ በአገራችሁ ጉዳይ በመሳተፍ ታሪክ ሥሩ፤ ጊዜያዊ እንቅፋቶች የኛ መገለጫ እንዳልሆኑ እመኑ” ብለዋል። ከዚህም ባሻገር እውቀትን ወደአገራቸው ለማሸጋገር የተመቸ መሣርያ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም መሰረት “ የተለያዩ ነገሮች የሚሠሩበትን ትላልቅ መንገዶች አስተዋውቁ፤ መጽሐፍትን ኮምፒውተሮችን፣ የህክምና መሣርያዎችን እና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን ባላችሁበት ቦታ ሰብስቡ፤ ይህንንም በማድረግ እዚህ የሚገኙና የሚፈልጓችሁን የወንድሞቻችሁንና የእህቶቻችሁን ህይወት መቀየር እንደምትችሉ እመኑ፤ የዲጂታል ላይብረሪዎችን በማበልፀግ ከዚህ ኢትዮጵያ የሚገኙ ተማሪዎችን በግብአት አግዙ፣ መጥታችሁም ክህሎትን ለማሳደግ ጥረት አድርጉ፣ አንዳንድ የትምህርት አይነቶችንም አስተምሩ” ብለዋል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገራችን ለሚገነባው ትልቅ ላይብረሪ በማንኛውም ቋንቋ የተፃፉ መጽሐፍትና ሌሎች የህትመት ውጤቶችን ለማሰባሰብ በቅድሚያ ተደራጁ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህ ላይብረሪ የኢትዮጵያን ቀጣይ መሪዎች፣ ዶክተሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ መምህራን፣ እንዲሁም በተለያዩ የሙያ መስኮች በሁለተኛ ደረጃ፣ በመጀመርያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪም ወይም በፒኤች ዲ ደረጃ ለሚማሩ ተማሪዎች እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
ባላችሁ የእረፍት ወቅትም ወደአገራችሁ መጥታችሁ በተለያዩ የበጎ አገልግሎት ሥራ ላይ ተሰማሩ በሚል ጥሪ ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች እንዲሰማሩም ጠይቀዋል። በተለይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራዎች ላይ ያላቸውን እውቀትና ችሎታም ለአገራቸው ጥቅም እንዲያውሉትም ጠይቀዋል። ለምሣሌ በየቀኑ ኢትዮጵያን እናፅዳ ዘመቻ እና የአራት ቢሊየን የችግኝ ተከላ ፕሮጀክትም ወጣቶቹ ሊሳተፉባቸው ከሚችሉባቸው የበጎ አድራጎት ተግባራት ውስጥ እንደሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
“በተለያዩ አካባቢዎች የወጣቶች የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ሃሳባችሁን አካፍሉ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በአገሪቱ ወቅታዊ ተግዳሮቶች እና እነዚህንም ለመቋቋም ባሉ ዕድሎች ላይ ወጣቶች ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ ጥሪ አቅርበዋል። የጥናት ወረቀቶችን እንዲያቀርቡና ርዕስ በርዕሳቸውም እንዲወያዩ፣ ሃሳብ አፍላቂና መፍትሄ አመላካች እንዲሆኑም በመግለጫቸው አመላክተዋል። ወጣቶቹና ታዳጊዎችም ለአገራቸው በሚያደርጓቸው ድጋፎች ሁሉ መንግሥትም ከጎናቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
በጋዜጣው ሪፖርተር