አዳማ፡- የነገዋን ኢትዮጵያ መገንባት መጠበቅና ማበልጸግ የአንድ ቡድን ወይም አካል ተደርጎ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ተግባር መሆኑን ተገንዝቦ መሥራት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ። የኢትዮጵያን እድገት ከማረጋገጥ አኳያም ግብርናው አይተኬ ሚና ያለው እንደመሆኑም ቀዳሚና መሰረታዊ ጉዳይ ተደርጎ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡
“ለግብርናው ትራንስፎርሜሽን የአመራሩ ሚና” በሚል ሀሳብ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው አገርአቀፍ የምክክር መድረክ ማጠቃለያ ላይ ትናንት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ መጻኢዋን ኢትዮጵያ መጠበቅ፣ መገንባትና መንከባከብ የቡድኖች ወይም የተወሰኑ አካላት ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ሃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከማረጋገጥ አኳያ ደግሞ ግብርናው ተኪ የሌለው እንደመሆኑም፤ መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ እንደ አንድ ዘርፍ ሳይሆን ቀዳሚና መሰረታዊ ጉዳይ አድርጎ እንደሚሠራም ገልፀዋል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ገለፃ፤ በአንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ በኢትዮጵያ የታየው ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ለውጥ አበረታች ነው፡፡
ምክንያቱም ከአንድ ዓመት በፊት የማይታሰቡ የነበሩ ፖለቲካዊ ጉዳዮች በዚህአንድ ዓመት ውስጥ ሲሆኑ ታይተዋል። በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በተሠሩ ሥራዎችም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን መጨረስ፣ ብድር መመለስና የሠራተኛ ደመወዝ እንኳን መክፈል የማትችልበት ደረጃ ላይ የነበረችበትን ታሪክ መቀየር ተችሏል።
ይሁን እንጂ ለውጡ አዲስና ከተለመደው የጠርጎ ማሸነፍና መሸነፍ አካሄድ የተለየ መሆኑ፤ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አደገ የሚባለው ደመወዝ ሲጨመር ነው ተብሎ መታሰቡ፤ በለውጡ ዙሪያ ያሉ አስተሳሰቦች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀ ረም። በህብረተሰቡ ዘንድ እያዳበረ የመጣው ከመስጠት ይልቅ ለመቀበል እጅን የመዘርጋት ሂደትም ሌላው ጉዳይ ነው።
ለምሣሌ፣ ዳያስፖራው ውጭ ሆኖ ብዙ ይጠይቃል፤ በሚጠይቀው ልክ ግን አገሩ ለምታቀርብለት ጥሪ ምላሽ እንደማይሰጥ በዳያስፖራ ትረስት ፈንድ ድጋፍ ታይቷል፤ ባለሀብቱም ቢሆን በሸገር ፕሮጀክት ላይ ባለው ተሳትፎ ተመዝኗል። ሆኖም አገርን የማልማት፣ መገንባትና የመንከባከብ ሥራው የሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን መገንዘብ ይገባል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት፤ ግብርናው በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቁና በቀጣይ ሃያ እና ሰላሳ ዓመታትም መንግሥት ቀዳሚ አድርጎ የሚሠራበት ነው። በዚህ ረገድ ደግሞ ትልቅ ተስፋ የሚጣለው ታማኝ በሆነው አርሷደር ላይ ነው። የዚህ አርሷደር ትጋት ግን በግብዓት፣ በቴክኖሎጂ፣ በምርምርና ሌሎችም ግብርናውን በሚያዘምኑና ምርታምነቱንም በሚያሳድጉ ነገሮች መታገዝ ይኖርበታል።
ይህ እውን እንዲሆን ደግሞ የአመራሩ ሚና ጉልህ ድርሻ ያለው ሲሆን፤ መንግሥትም ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት የዘርፉን ችግሮች ከመለየት ጀምሮ የሥራ አቅጣጫ በማስቀመጥና ኮሚቴ በማቋቋም እየሠራ ይገኛል። የግብርናውን ዘርፍ አይተኬ ሚና ማሳደግ የሚቻለው ቀድሞ መሠራት ያለበት ሲሠራ ብቻ እንደመሆኑም፤ መንግሥት የግብርናውን ዘርፍ ሪፎርም ከማድረግና የፋይናንስ በጀቱን በመጨመር ዘርፉ በምርምር እንዲታገዝ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም እንደ ማዳበሪያ ያሉ የግብርና ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለማምረት፣ የገበያ ሥርዓትና ትስስሩን ለማዘመንና ለማጠናከር፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የግብርና ሴክተሮችን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ ናቸው።
ከእነዚህ መካከል የአነስተኛ መስኖ ልማት አንዱ ሲሆን፤ በተለይ ቆላማ በሆኑት እንደ ሶማሌና አፋር ክልሎችን በመሳሰሉ አካባቢዎች ሰፋፊ የመስኖ ሥራዎችን በማከናወን ከውጭ የሚገባን የግብርና ምርት ማስቀረት ይቻላል። ለዚህ ሲባልም 20 በሊዬን ብር ተጨማሪ በጀት የተያዘ ሲሆን፤ ሥራው ተጠናክሮ ውጤት ሲያመጣ በዚህ ዓመት ብቻ ግማሽ ብሊዬን ዶላር ያክል ለስንዴ መግዣ የወጣውን አይነት ፋይናንስ ግብርናውን ለማዘመን ተግባር ለማዋል ያስችላል።
የከተማ ግብርናን ማጠናከርም ሌላው ሥራ ሲሆን፤ ለዚህ እንደ ማሳያ ይሆን ዘንድም በቤተ መንግሥት ጊቢ ውስጥ ከሙዚዬምና ፓርክ ጎን ለጎን የእርሻ ቦታ ተዘጋጅቷል። የአካባቢ ሚዛንን መጠበቅና የግብርናውን ውጤታማነት ማገዝ የሚያስችለው የደን ልማት ሥራውም አብሮ ሊሠራ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 19/2011
ወንድወሰን ሽመልስ