“የባህር በር የነጻነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው”  – አቶ ፈረደ ፍትሐነገሥት -የቀድሞ ባህር ኃይል

በ1952 ዓ.ም ነው የተወለዱት :: ያደጉት ደግሞ ወለጋ አካባቢ ነው:: የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን እዛው ወለጋ ነቀምት ከተማ መስከረም 2 በሚባል ትምህርት ቤት ተከታትለዋል:: የዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችን የቀድሞ ባህር ኃይል ባልደረባ አቶ ፈረደ ፍትሐነገሥት::

አቶ ፈረደ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በቀጥታ አዲስ አበባ አጎታቸው ጋር በመምጣት በመድሃኒአለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ቀጠሉ::

“………እኔ ለሀገሬ ላቅ ያለ ፍቅር ያለኝ ወታደር ነኝ ፤ እዚህ ተወለድኩ እዛ ማለትም አልፈልግም:: ግን ኢትዮጵያዊ መሆኔን አውቃለሁ፤ ከዛ በተረፈ እድገቴ ወለጋ ነቀምት ከተማ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርቴንም እዛው ነው የተማርኩት:: የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በአዲስ አበባ ነው” ይላሉ::

የስምንተኛ ክፍል ትምህርታቸውን በነቀምት እንዳጠናቀቁ ለተሻለ ትምህርት አዲስ አበባ የገቡት አቶ ፈረደ የልጅነት ህልማቸው የሙያ ትምህርት ነበርና እሱን ለመማር ጭምር መምጣታቸውን ይናገራሉ:: ነገር ግን የፈለጉት የትምህርት ዓይነት የመመዝገቢያ ወቅቱ ስላለፈ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርት ጀመሩ::

ከዘጠኛ እስከ 11 ክፍልም ትምህርታቸውን በጥሩ ሁኔታ እየተከታተሉ ባሉበት ወቅት ግን ሕይወታቸውን የሚቀይር የተለየ ምዕራፍ የሚያስይዝ ክስተት ገጠማቸው ፣ አቶ ፈረደም ምንም እንኳን ከዛ ቀደም ስለ ጉዳዩ አስበውበት የሚያውቁ ባይሆንም እድሉ አጠገባቸው ሲመጣ ማሳለፍን በፍጹም አልፈቀዱም ፤ በእድሉ ተጠቅመው የሚሆነመውን ለማየት ጓጉ እንጂ::

” ……..አዲስ አበባ የመጣሁት ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ለመማር ነበር፤ ነገር ግን የምዝገባው ወቅት ስላለፈ ዝም ብዬ የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቴን ጀመርኩ፤ እሱን እየተከታተልኩ አስራአንደኛ ክፍል ስደርስ ሃሳቤን የሚያስቀይር አጋጣሚ ተፈጠረ ” ይላሉ::

አቶ ፈረደ በመድሃኒያለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማሩ ሳሉ እጅግ በጣም የሚያማምሩ አለባበሳቸው የተስተካከለ ቁመናቸው ልብ የሚያሸፍት ከሁሉም በላይ ደግሞ ቆፍጠን ብለው ሲናገሩ ልብ የሚያርዱ ከፍ ያለ ኢትዮጵያዊነት ስሜት በላያቸው የሚነበብ ሰዎች በአንዱ ቀን በትምህርተ ቤታቸው ጊቢ ውስጥ ተከሰቱ:: ሁኔታው ሁሉንም የትምህርት ቤቱን ተማሪዎች ያስደመመ በጣምም ያስደሰተ ቢሆንም አቶ ፈረደና ጥቂት ጓደኞቻቸው ግን ከመደመምም ከመደሰትም ከመደነቅም አልፈው እንደነሱ መሆንን ተመኙ:: እነዚህ ሰዎች የቀድሞ የኢትዮጵያ ባህር ኃይሎች ነበሩ::

ባህር ኃይሎቹ በእዛ ትምህርት ቤት የመገኘታቸው ዋናው ቁምነገር ደግሞ ተተኪ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችን በተለይም ባህር ኃይል የመሆን ፍላጎት ያላቸውን ለመመልመል ነበር:: እናም በየክፍሉ እየገቡ ኀገር ምን ማለት እንደሆነ፤ የሀገር ፍቅር የሚጀምረው በማገልገል መሆኑን፤ ባህር ኃይል ምን እንደሚሠራ በአስገምጋሚው ድምጻቸው፣ በዛ ቁመናቸውና ሽክ ባለው አለባበሳቸው ታግዘው ሲናገሩ ሁሉም ተማሪ ተደመመ:: እነሱም ማስተላለፍ ያለባቸውን መልዕከት አስተላልፈው ፍላጎቱ ያላችሁም አስቡበትና ተመዝገቡ የሚለውን መልዕከት ትተው ከትምህርት ቤታቸው ወጡ:: አቶ ፈረደም ይህንን ካዩና ከሰሙ በኋላ ለማንም ምንም ሳይተነፍሱ ባህር ኃይልን ለመቀላቀል ወሰኑ::

“…….. በመጀመሪያ ደረጃ ስለ ባህር ኃይልም ሆኖ ውትድርና እውቀት ኖሮኝ የተዘጋጀሁበት ወቅት አልነበረም፤ ባህር ኃይሎቹ በትምህርት ቤታችን መጥተው የሚናገሩት ነገር በጣም ልዩ ነው:: አነጋገራቸው ሳትወጂ በግድሽ ወደ ሙያው እንድትሳቢ የሚያደርግ ነው:: ከዛ ሁሉ በላይ ደግሞ አሁን ትምህርታችንን ብናቋርጥም እዛው ሆነን መማር እንደምንችል ዓለም አቀፍ

 መርከበኛ እንደምንሆን ነገሩን፤ ይህ የሚሆነው ደግሞ የመግቢያ ፈተናውን ለሚያልፍ ብሎም የህክምና ምርመራ ተደርጎለት ሙሉ ጤነኛ መሆኑ ለተረጋገጠ ብቻ እንደሚሆንም ገለጹ፤ በዚህ ጊዜ ባህር ኃይልን የመቀላቀል ፍላጎቴ በጣም ጨመረ፤ እኔና አራት ጓደኞቼ በቃ እድላችንን እንሞክር ብለን ተመዘገብን ” ይላሉ::

ወቅቱም ኢህአፓ የተመታበት በመሆኑም ለሁሉም ወጣት ጊዜው በጣም አስፈሪ ነበርና እነ አቶ ፈረደም ተምረን ከፍተኛ ትምህርት ተቋምን እንቀላቀላለን የሚለውም ሃሳብ አዋጭ ስላልነበር ይህንን እድል እንደ ጥሩ አጋጣሚ ከመውሰዳቸውም በላይ ጊዜውን ለማምለጫም ጥሩ አማራጭ ስለመሆኑ ተረድተው ምዝገባውን አከናወኑ፤ ከምዝገባው በኋላ እንግሊዘኛ፣ ሂሳብና ፊዚክስ ትምህርቶች ተፈትነው አለፉ:: በመቀጠልም ሁለት ቀን የፈጀ የጤና ምርመራን በማድረግ ውጤታቸው ጥሩ በመሆኑ የመጀመሪያ መቀበያ ወደሆነው ዊንጌት ገቡ::

አቶ ፈረደ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸው ሲማሩ ጀምሮ ጋዜጣ ሸጠው ራሳቸውን በማስተዳደር ብሎም በራሳቸው ላይ የሚሆኑ አብዛኞቹን ነገሮች ጥቅምና ጉዳቱን እየለዩ ውሳኔ እየሰጡ የኖሩ በመሆኑ ባህር ኃይልን ለመቀላቀል ሲያስቡም የማንንም ውሳኔ አልጠበቁም፤ በራሳቸው ከወሰኑና ማለፍ የሚገባቸውን ሁሉ ካለፉ በኋላ ግን በታናሽ ወንድማቸው አማካይነት አጎታቸው አወቁ :: እንደ አጋጣሚ ኮረኔል ማዕረግ ድረስ የደረሱ ሌላ አጎት ነበሯቸውና አብረው ካምፓቸው በመምጣት ስለውሳኔያቸው ትክክለኝነት ስለሃሳባቸው ጠየቋቸው፤ አቶ ፈረደም ውሳኔያቸው ትክክለኛ መሆኑን የሰሙትም

 ነገር ስሜት የሚሰጥ መሆኑን በዚህም ባህር ኃይልን መቀላቀላቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው ሲነግሯቸውም ውሳኔያቸውን እንዳከበሩላቸው ይናገራሉ::

ጉዞ ወደ አሰብ

ከወለጋ አዲስ አበባ በልጅነታቸው ከመምጣት ባለፈ ረጅም ርቀትን ተጉዘው የማያውቁት አቶ ፈረደ አሁን ወደማያውቁት ምናልባትም ስማቸውን ሰምተዋቸው ስለማወቃቸው እርግጠኛ ወዳልሆኑባቸው የሀገራችን ክፍሎች ከመሰሎቻቸው ጋር በመሆን በመኪና ጉዞ ጀመሩ፤

“……..ሚሌ ገዋኔ የሚባሉ ቦታዎችን አናውቃቸውም በጣም ሞቃታማ ናቸው:: እኛ ደግሞ ከቀዝቃዛ አካባቢ የወጣን ነን:: ለማደር የወረድንበት ቦታ ላይ ሁላችንም በጣም ነው የደነገጥነው ሙቀቱ ከልክ ያለፈ ወላፈን ያለው ነበር እየወሰዱን ያሉት ሰዎችም በቀጣይ የሚያጋጥሙን አካባቢዎች ሙቀታቸው ከዚህም የባሰ ስለመሆኑ እየነገሩንም ነበር በዚህ ጊዜ በጣም ፈራን ደነገጥን” ይላሉ::

አቶ ፈረደ ከሁሉ በላይ ያስደነገጣቸው ከአውቶቡሱ ሲወርዱ ያለቅጥ አልቧቸው ስለነበር የለበሱትን ካኔቴራ አውልቀው ላቡን ሲጨምቁት የተጣጠፈ ላሜራ ሆነ በሁኔታው በጣም ተደናግጠው ምንድነው ነገሩ ሲሉም ጨዋማ ስለሆነ ነው የአየር ንብረቱ እጠበው ተብለው ስለማጠባቸውና ያስታውሳሉ:: ለመጀመሪያ ጊዜ ሙቀት እንደዚህ እንደሚያደርግ ያዩበት አጋጣሚም በመሆኑ አይረሱትም::

አቶ ፈረደና ጓደኞቻቸው የሚያዩት ነገር በተለይም የአየር ሁኔታው ፍጹም ከባድና የማይችሉት እየመሰላቸው ቢሆንም እንኳን ወጣትነት ጉልበት፣ ጉጉትና አልሸነፍ ባይነት ነውና በፍጹም ወደኋላ ማፈግፈግን አልፈለጉም ደርሰን የሆነው ይሁን በሚል ብቻ ወደፊት መጓዝን መረጡ::

ይህንን ሁሉ አልፈው አሰብ ደረሱ በዛም ሁለት ቀናትን አደሩ:: ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በተዘጋጀላቸው መርከብ ተጭነው ምጽዋ ገቡ::

ለመጀመሪያ ጊዜ መርከብ ላይ መውጣት

መርከበን በፊልም አልያም በስዕል ካልሆነ በቀር የማያውቁት አቶ ፈረደና ጓደኞቻቸው ለመጀመሪያ ጊዜ መርከብ ላይ ወጡ:: ስሜቱ እጅግ ከባድ ስለመሆኑ ይናገራሉ::

“………መርከብ ላይ ስንወጣ መንገዱን ውጣ ውረዱን ሙቀቱን ስቃዩን ብቻ በአጠቃላይ ሁሉንም ነገር እንዳልነበር ረሳነው፤ መርከቡ ላይ የገባነውም እንደ ተሳፋሪ ነበርን ፤ የሕይወት ሌላው ምዕራፍ በመሆኑ ስሜቱ ልዩ ነው:: ግልጽ ባለው ባህር ላይ መሬት ሳይታይ ዶልፊኖች የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች በሚሯሯጡበት ውሃ ላይ መንሳፈፍር ደስ ይላል:: ብቻ በጠቅላላው ተዓምር የሚመስል ስሜት ነው ያለው” በማለት ፊታቸው ላይ በሚነበበው ደስታ አጅበው ይናገራሉ::

ባህር ኃይል መሆን የሚያበረታታ ክፍያ የለውም የተለየ ጥቅምም አይገኝበትም ፤ ነገር ግን ሀገር የማገልገል ስሜቱን መፍጠር የሚያስችል ሥልጠና ይሰጣል ከዛ በኋላ ምግብ መጠለያ ህክምና አሳሳቢ አይደሉም ልብስም የደንብ ልብስ ስላለ ኑሮ ቀላል ነው::

አቶ ፈረደ መጀመሪያ ሲቀጠሩ የወር ደመወዛቸው 66 ብር ከ 20 ሳንቲም ነበር፤ ግን ደግሞ ወጪ ስለሌለባቸው 50 ብሩን ለቤተሰብ ይልካሉ በ15 ብሩ ይዝናናሉ በቃ የባህር ኃይል ኑሮ ይህ ነው::

በዚህ መልኩ የተቀላቀሉት ባህር ኃይል ሥልጠናቸውን ይጀምሩ ዘንድ ምጽዋን የማየት እድል ለሁለት ቀን ተሰጣቸው ፤ መርከቦችን ጎበኙ አሁን እዚህ ያለው ቆይታቸው ተጠናቀቀና በጭነት መኪና ጉዞ ወደ አስመራ ሆነ::

አስመራ

ወደ አስመራ ከተማ ጉዞ የተጀመረው በጭነት መኪና ነው:: 128 ኪሎ ሜትር ዳገታማና ጠመዝማዛ መንገዶችን ከተጓዙ በኋላም አስመራ ከተማ ደረሱ::

“……..አስመራ ከተማ ስንገባ ባህር ኃይሉ የሚቀበለን ቦታ ስላላዘጋጀ ወደ 5 ሜትር የግንብ አጥር ባለው የአስመራ ፖለቲካ ክፍል ውስጥ ገባን :: ልክ እስር ቤት ነው የሚመስለው በጣም ያስፈራል:: ይህ አንዱ ወታደራዊ ሳይኮሎጂ ሲሆን እኛን በፈተና ውስጥ የማሳለፍ ወታደራዊ ሥርዓቶችንና ታዛዥነት ማስተማሪያም እንደሆነም በኋላ አውቀናል :: የሚገርምሽ ብዙ ሰዎች ለሶስትና አራት ቀን በከፍተኛ ሁኔታ የታመሙ ነበሩ” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ::

እዚህ ካምፕ ውስጥ ለአንድ ሳምንት ከቆዩ በኋላ የሥልጠናው አካል የሆነ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ተነስቶ አስመራ ከተማን በሩጫ ዞሮ ለ 12 ሩብ ጉዳይ ወደካምፕ መግባት በ15 ደቂቃ ታጥቦ 12 ሰዓት ለቁርስ መገኘት እስከ 1 ሰዓት ቁርስ በልቶ አጠናቅቆ ወደ ሥልጠና ቦታ መሄድ ተጀመረ ይላሉ::

እነ አቶ ፈረደ በዚህ መልኩ የጀመሩት መሠረታዊ የወታደርነት ሥልጠና እንዳለ ሆኖ ስለመርከብ እንዲያውቁ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና፣ ስለመርከብ ማወቅ፣ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎችን ባህርይና አጠቃቀም፣ መርከቦች ላይ ስለሚገጠሙ መድፎች ሚሳኤሎችና ሌሎችንም ማወቅ የሚሉ ትምህርቶችን መከታተል ጀመሩ::

አቶ ፈረደ መጀመሪያ መውሰድ ያለባቸውን ሥልጠና ካጠናቀቁ በኋላ የአንድ ዓመት ሥልጠናቸውን ደግሞ ጀመሩ እያሉ ቀጣዩን የተማሩትን ትምህርት መርከብ ላይ ወጥተውም የመሥራት ትምህርታቸውን በአግባቡ አጠናቀቁ :: ትምህርቱ ቀጣይነት ያለውም ነበርና ቀጣይ ሥልጠናቸውንም ወሰዱ በዚህም ራሳቸውን በማዕረግ በእውቀት በአገልግሎት እያሳደጉ መጡ::

“……በዚህ ሁሉ የትምህርት ሂደት ውስጥ የእኛ ዘላለማዊ ትምህርት የሀገር ፍቅር ነበር:: የሀገር ፍቅር ስሜቱ የሚቀረጸው ባህር ኃይል ውስጥ ነው ብል አላጋነንኩም:: ውስጣችን የሚያኖሩት ሀገር የሚለው ቃል በደሎችሽን ሁሉ ተሸክመሽ ሀገርሽን እንድታስቀድሚ የሚያስገድድ ነው፤ እኛ መንግሥት በተለያዩ ነገሮች በድሎን ሊሆን ይችላል፤ በወቅቱ በነበረው መንግሥት ላይ የነበረን ተቃውሞ አለ ፤ ነገር ግን በሀገራችን ድርድር አናውቅም ፤ እኛ ውስጥ ሀገሬ የሚለው ነገር ከፍ ያለ ነው ” በማለት እንባ እያነቃቸው ይናገራሉ::

ኢትዮጵያ የባህር በር በነበራት ወቅት

በወቅቱ የውሃ ድንበር ነበረን ያንን ድንበር ካለፍን ዓለም አቀፍ መስመር ውስጥ ነው የምንገባው:: የራሳችን አካባቢ በእኛው መርከቦች ነበር የሚጠበቀው:: በወቅቱ ከራስ ካሳ እስከ ራስ ዱሜራ የሚል ክልል (ግዛት) ነበረን፤ ያንን ሁሉ በተለያየ ሰዓትና ጊዜ የእኛው መርከቦች እየተዘዋወሩ ይጠብቃሉ:: አንዳንድ ጊዜ እዛው ድንበሩ ላይ ለወርና ከዛ በላይ ቆመን ልንጠብቅ እንችላለን በማለት የወቅቱን ገናናነታችንን ይናገራሉ::

ባህር በራችንን ማሳጣት በስትራቴጂ የመጣ ነገሮችን እያጠበቡ መጥተው ባህር በር አልባ ሆንን እንድንቀር የተደረገበት ሂደት የሃያላን ሀገራት ፍላጎት እንዲሁም በቅኝ ሳንገዛ እንደውም ለሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች የነጻነት ተምሳሌት በመሆን እምቢ ማለትን የፈጠርን ከመሆናችን ጋር የተያያዘ ቂም ውጤትም ነው ለእኔ ይላሉ::

ባህር ኃይሉ ግን መፍረሱ ሀገራችን ላይ ቀላል የማይባል ጉዳትን ነው ያደረሰው የሚሉት አቶ ፈረደ የጣለው ዐሻራም አሁን ድረስ እያደማን ያለ በኢኮኖሚ በፖለቲካ ሃያልነታችንን የተነጠቅንበት ሆኖ አልፏል::

 ዛሬ ላይ ዳግም ባህር በር እንዲኖረን እየተደረገ ያለው ጥረት ተቋሙንም ዳግም ለማደራጀት የተጀመረው ሥራ በእውነት መልካም የሀገራችንንም ገናናነት ሊመልስ የሚችል በመሆኑ እኛም በማህበራችን አማካይነት የምንችለውን ነገር ሁሉ እያገዝን ነው::

“………የባህር በር ሲኖር እኮ ወጪና ገቢ ንግዱ ላይ የሚኖረው መሳለጥ ቀላል አይደለም:: ከሁሉም በላይ ደግሞ የሀገር ምስጢር ከፍ ባለ ሁኔታ ይጠበቃል፤ ዛሬ ላይ ምስጢራችን በጅቡቲ በኩል ሲመጣ ምስጥርነቱ ያጣል:: ይህ ደግሞ በጣም ትልቅ ውድቀት ነው:: ባህር በር የኃይል ሚዛናችንን የምናሳይበት ሉዓላዊነታችንን የምናጸናበት ከመሆኑም በላይ ዙሪያችንን በመጠበቅ የሚወጡ የሚገቡ መርከቦችን የመቆጣጠር እድላችንንም የሚያሰፋ ይሆናል” ይላሉ::

በሌላ በኩል ወደብ በነበረን ወቅት ድፍድፍ ነዳጅን የምናጣራበት ፋብሪካም ነበረን:: ይህ ሁኔታ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም የሚሉት አቶ ፈረደ ድፍድፍ ነዳጅ ስናጣራ አስፋልት መስሪያ ሬንጅንም እናገኝ ነበር:: እነዚህን ሁሉ ነገሮች ሲታሰቡ ዛሬ የት እንደርስ እንደነበር መገመት አይከብድም::

በሌላ በኩል የራሳችን ወደብ ኖረን ማለት ነጻነታችንም በዛው ልክ ተጠበቀ ማለት ነው፤ ከዛ ሁሉ በላይ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ትልቅ የንግድ ከተማንም ለመፍጠር ያስችላል ብቻ ጠቀሜታው ብዙ ነው::

አሁናዊ በሁኔታ

አቶ ፈረደ ባህር ኃይል ከተበተነ በኋላ እንደ ብዙዎቹ አባላት በእሳቸውም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ላይ ቀላል የማይባል ሥነ ልቦናዊና ኢ ኮ ኖ ሚ ያ ዊ ውድቀት ቢደርስም ይህንን ግፍ ቁጭ ብለው የሚያመነዥጉ አልሆኑም:: ይልቁንም ወታደር ቤት የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ወደሥራ መመንዘርና ከእሳቸው አልፈው ለብዙዎች እንጀራ ለመሆን ቻሉ::

አቶ ፈረደ ባህር ኃይል ሆነው ስፖርትንም አብረው ከመሥራትም በላይ ለውድድርም የሚቀርቡ ነበሩ፤ ከዛም በኋላም ቢሆን ከስፖርቱ አልተራቁም:: በተለይም እጅ ኳስ ለእሳቸው ሁለም ነገር ነው ፤ ባህር ኃይልንም ወክለው ተጫውተዋል:: በኋላም በተለያዩ ቦታዎች ላይ የመጫወት እድልን አግኝተዋል::

እድሜያቸው እጅ ኳሰን ለመጫወት የማያስችልበት ሁኔታ ላይ ሲደርሱ ደግሞ የሀገር ውስጥ ዳኛ በመሆን የጀመሩት ወደ አፍሪካ ከዛው ዓለም አቀፍ ዳኛ (ኢንተርናሽናል አልቢትር) ሆነው እንዲሠሩ በር ከፍቶላቸዋል::

አሁን ደግሞ የስፖርት አሠልጣኝ (ኢንስትራክተር) ሆነው በመሥራትም ላይ ስለመሆናቸው ይናገራሉ:: በዚህም በርካታ ሀገራትን የማየት እድልንም ፈጥሮላቸዋል:: ይህ በየሀገሩ መዞራቸው ግን ከግል ጥቅማቸው አልፈው ሀገራቸውን እንዲያስቡ በተለይም በስፖርቱ ዘርፍ የቀሩት ዓለማት የት ደርሰዋል? በምን ዓይነት መሣሪያዎች እየተጠቀሙ ነው ውጤታማ የሆኑት? የሚለውን በጉልህ እንዲመለከቱ እድልን ፈጠረላቸው::

በመሆኑም እኛ ሀገር የሌለ ሌላው ጋር ያለ የሚሉትን ሁሉ ባገኙት አጋጣሚዎች በመሰብሰብ ቴክኖሎጂን በመቃረም አሁን ላይ የስፖርት እቃዎች ማለትም የእጅ ኳስ ቦርዶች፣ ጎሎች ፣ሜዳዎች ፣ የጠረጴዛ ቴኒስ መጫዎቻዎችና ሌሎችንም በማምረት ላይ ናቸው::

 ስፖርትና ኢትዮጵያውያን

“…….በስፖርቱ ላይ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዱ ነገራችን ላይ ግንዛቤን የመፍጠር ከፍ ያለ ችግር አለብን፤ ስለ ግብርና ብናወራ ምናልባት ጤፍ ብቻ ነው ሃሳባችን ላይ የሚመጣው ፤ ይህ ደግሞ ጤፍ ላይ ብቻ በማተኮር አማራጭ ወደማጣት እንሄዳለን ፤ ስፖርቱም ላይ ቢሆን የሚየታየው ይኸው ነው:: በመሆኑም ሕዝብ ልብ ውስጥ መስረጽ ያለበት ነገር ሁሉም ስፖርት ጠቃሚ መሆኑን በዓለም አደባባይ ልንጠራበት እንደምንችል ነው”ይላሉ::

የተፈጥሯችን ሁኔታ አካባቢያዊ አየር ንብረታችን ሌላም ሌላም ተደማምሮ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን ችለናል:: ይህ ሁኔታና እድል ግን ሌሎቹም ስፖርቶች ላይ ሊደገም ይገባል የሚሉት አቶ ፈረደ ለዚህም ግንዛቤያችን ለይ መሥራት የሚጠይቀን ዘርፍ ነው::

በሌላም በኩል ስፖርት የሀገርን ስም ከማስጠራት ገንዘብ ከማስገኘት ባለፈ ከመድሃኒት ነጻ አድርጎ ጤናንም የሚሰጥ ነው:: በመሆኑም ስፖርት የሁልጊዜ ምርጫችን ቢሆን በማለትም ጥሪያቸውን ያቀርባሉ::

የምንሳተፍባቸው ስፖርቶች ውስንነት

አዎ እንደ ሀገር በጣም ውስን በሆኑ የስፖርት አይነቶች ላይ ነው እየተሳተፍን ያለነው የዚህ ትልቁ ምክንያት የቁርጠኝነት ማጣት ነው የሚሉት አቶ ፈረደ የሀገርን ስም የሚያስጠራ ባንዲራዋን ከፍ አድርጎ የሚያውለበልብ ስፖርተኛ አወጣለሁ የሚል አሠልጣኝ በጣም ያስፈልገናል:: ሁለተኛው ከቤት ጀምሮ ለስፖርት የሚሰጠው አመለካከት ሊሻሻል ይገባል ምክንያቱም እኛ ሁሌም የምናስበው ልጆቻችን በትምህርት ብቻ እንዲዘልቁ ነው ፤ ትምህርቱን ከስፖርቱ ጎን ለጎን አድርገው መጓዝ የሚችሉበት ሰፊ እድል አለና እሱንም ማመላከት ያስፈልጋል::

በመሆኑም እንደ ሀገር ቁርጠኝነቱ ካለ በብዙ ስፖርቶች ገነን የምንወጣ ነን:: ለምሳሌ ከአሁን በፊት ባለን ልምድ በቦክስ ስፖርት በኦሎምፒክ ደረጃ የተሳተፉ ብዙ ስፖርተኞች ነበሩን፤ ገነን የመውጣት እድላችንም ሰፊ ነበር ፤ ብስክሌተኞች ማውጣት ይቻላል፤ ካለን የውሃ ሀብት ተነስተን በዓለም አደባባይ ሀገራቸውን የሚያስጠሩ ዋናተኞችን ማውጣቱም ከባድ አይሆንም፤ ይህ ሁሉ እንዲሆን ግን ዘመናዊ የስፖርት ግብዓቶችን ማሟላት ሥልጣኔዎችን መኮረጅ ከዛ ሁሉ በላይ ግን ቁርጠኝነት ያስፈልገፈናል:: አሁንም ቢሆን ይህንን ሃላፊነት መሸከም የሚችል ለስፖርቱ ማደግ ከልቡ የሚጥር አመራር ከተገኘ ዛሬም የረፈደ ነገር የለም ይላሉ አቶ ፈረደ::

በስፖርቱ ዘርፍ ቢሆን

በውትድርና ብትሄጂ ስፖርተኛ ያልሆነ ወታደር ረጅም ጉዞ አይጓዝም:: ሌላው ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎች አእምሯቸው ተነቃቅቶ እውቀት ይይዙ ዘንድ አካላዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ ነው:: ግን የሚገርምሽ ነገር እስከ አሁን ባለው ሁኔታ ስፖርት አንዲት 40 ደቂቃ ተሰጥታው ብቻ የሚሠራ ሆኖ ነው የቆየው እሱም አሁን ላይ የመቀዛቀዝ ሁኔታ ላይ ደርሷል:: ግን ደግሞ ሊጠናከር የሚገባውና ብዙ ዓለም አቀፍ ስፖርተኞችን የምናፈራበት ነው፤ እኔም በዚህ መልኩ የስፖርት ትምህርት ተጠናክሮ ቢቀጥል ልጆች እርስ በእርሳቸው በስፖርታዊ ውድድሮች እየተፎካከሩ ከፍ ያለ ሥራ ቢሠራ ብዬ እመኛለሁ::

የቤተሰብ ሁኔታ

አቶ ፈረደ ትዳርን በወቅቱ በሚባል ደረጃ ነው የመሠረቱት የዛሬ 40 ዓመትም ከወይዘሮ ጽድቀ መክብብ ጋር ትዳር መሥርተውም አምስት ልጆችን አፍርተዋል:: አሁን ላይ በሁለቱ ልጆቻቸው አማካይነት አያት የመሆንንም እድል አግኝተዋል::

መልዕክት

ማንም ሰው ከሀገሩ በላይ የለውም ቆም ብሎ ሲታሰብም ደስታም ሆነ ኀዘን በሀገር ነው የሚደምቀው፤ ሀገርን ማስቀደም ደግሞ ይጠበቅብናል ፤ በመሆኑም በጋራ በሚያቆሙን በሚያራምዱን በሚያሳድጉን ነገሮች ላይ ትኩረት ማድረግ ካልቻልን ሁል ጊዜ የምዕራባውያኑ ጥገኛ ተመጽዋች ዜጎቻችንም ተሰዳጅ ሆነው ነው የሚቀሩት ስለዚህ ሀገራችንን የተሻለ ለማድረግ እንጣር በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ህዳር 23/2016

Recommended For You