ውጤታማ አመራር ለውጤታማ ጤና ሥርዓት

ለጤናው ዘርፍ መሻሻል የባለሙያዎች አቅም ከፍተኛ መሆን፣ ጤና ተቋማት አስፈላጊ የህክምና ግብዓቶችን በበቂ ሁኔታ ማሟላት፣ የጤና አገልግሎቱን ለመስጠት በጤና ተቋማት ውስጥ አመቺ ሁኔታዎች መኖር፣ መንገድ፣ ስልክና መብራትን የመሰሉ የመሠረተ ልማቶች በበቂ ሁኔታ መሟላትና ሌሎችም ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ። እነዚህ ብቻ ግን የጤናውን ዘርፍ ሊያሻሽሉ አይችሉም። የጤናው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን የሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ተሳትፎም ወሳኝ ነው።

ከሁሉ በላይ ደግሞ ውጤታማና ብቃት ያላቸው አመራሮች ሲኖሩ ነው የጤናው ዘርፍ በሁለንተናዊ መልኩ ሊሻሻልና ዜጎችም ከዚህ ዘርፍ ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉት። ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ነው እንግዲህ የጤና ሚኒስቴር የጤናው ዘርፍ ውጤታማ አመራር ፕሮግራም/high impact leadership program/ ከሰሞኑ ያስጀመረውና ለሚለከታቸው የጤናው ሴክተር አካላት ፕሮግራሙን ያስተዋወቀው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አየለ ተሾመ እንደሚናገሩት፣ በሁለቱም የጤና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች እንደሀገር በጤናው ዘርፍ ውጤቶች ላይ የተሳኩ በርካታ መልካም ነገሮች አሉ። በተለይ በእናቶችና ህፃናት ጤና፣ በተላላፊ በሽታዎች ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል። የጤናውን ሥርዓት ምሰሶ ያደረጉ በርካታ ሥራዎች በመግሥትና በግል አጋርነት ተሠርተዋል።

በነዚህ የትግበራ ሂደቶች ደግሞ በርካታ ስኬቶች እንዳሉ ሁሉ ብዙ ተግዳሮቶችም አሉ። በተለይ ደግሞ አብዛኛው ኢንቨስትመንቶችና የተገኙ ውጤቶች አብረው ጎን ለጎን እንዲሄዱ ከማድረግ አንፃር ብዙ ክፍተቶች ታይተዋል። በተለይ በጤናውና በአመራር ሥርዓቱ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች እነዚህን ኢንቨስትመንቶችን ከውጤት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከማጥበብ አንፃር ያላቸው ድርሻ በጣም ከፍተኛ ነው።

ባለፉት ዓመታትም የጤና ሥርዓት አመራሩን የተሻለና ውጤታማ ለማድረግ የተሠሩ በርካታ ሥራዎች አሉ። በነዚህ ሂደቶች ደግሞ ትምህርት የተወሰደባቸውና ሊሻሻሉ የሚገቡ ነገሮች በርካታ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል።

ስለዚህ በሁለተኛው የጤናው ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ በጤና ሚኒስቴር ትኩረት ከተደረገባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ውጤታማ አመራርነትን ማረጋገጥ ነው። በርካታ ኢንቨስትመንቶች ካሉና ኢንቨስትመንቶቹ ውጤት እንዲያመጡ ከተፈለገ ተፅእኖ ፈጣሪ አሠራሮችና ቁርጠኝነትን ማምጣት ያስፈልጋል። ነገን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ሥራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል። በዚህ ረገድ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው ደግሞ አመራሩ ነው።

ስለዚህ አመራሩ ላይ ከነበሩ ጥንካሬዎች በመነሳትና ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት የአመራር ፕሮግራሙን ለመቅረፅ ባለፈው አንድ ዓመት መዋቅሩን ተከትሎ ሥራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። ባሉ መልካም ነገሮች ላይ በመጨመር በተለይ ደግሞ በመሠረተ ልማቱ ላይም ይሁን በሰው ሀብት ልማት ላይ ያለውን በጎ ጅምር ወደኋላ ሄዶ ማጥናት ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል የህብረተሰቡን በሕይወት የመቆየት ምጣኔ ማሳደግ ያስፈልጋል። የአኗኗር ዘይቤን ተከትሎ በተለይ በከተሞች አካባቢ ካንሰር፣ ስኳርና ደም ግፊትን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና ሌሎች ከኢንዱትሪ ጋር ተያይዞ እየመጣ ያለው ድንገተኛ አደጋ ጫና ቀላል የሚባል አይደለም። ከጊዜ ወደ ጊዜ ደግሞ የጤናው ሴክተር ዋጋ እየጨመረ መጥቷል። ይህ ዋጋ ላላደጉ ሀገሮች አንድምታው ብዙ ነው።

ከዚህ ባለፈ የማህበረሰብ ባለቤትነትና ጠያቂነት ፍላጎት በእጅጉ ጨምሯል። ይህ ደግሞ እንዲያድግ የሚፈለግ ነው። ስለዚህ እነዚህና ሌሎችንም ታሳቢ ያደረገ ምላሽ የሚሰጥ የዓመራር ሥርዓት እንደሀገር ያስፈልጋል። ለዛም ነው ከዚህ ቀደም የነበሩ መልካም ነገሮችን ታሳቢ ባደረገ፤ ግን ደግሞ የነበሩ ክፍተቶችን በመሙላት ውጤታማ አመራርነትን መሠረት ያደረገ የአመራር ልማት ፕሮግራም ያስፈልጋል በሚል ሥራዎች ሲሠሩ የቆዩት።

በተለይ ባለፉት ዓመታት የጤናው ዘርፍ አመራር ፕሮግራሞች በጣም የተበጫጨቁ ነበሩ። ስለዚህ እንደሀገር የአመራር ሥርዓቱን ማቀናጀት ያስፈልግ ስለነበር እነዚህን በተለያዩ ሁኔታዎች ሲተገበሩ የነበሩትን የአመራርነት ፕሮግራሞችን የማቀናጀት ሥራ አንዱ መሠረታዊ ነገር ነበር። ሁለተኛ ደግሞ የአመራር የማስፈፀም አቅም ከአመራርነት ክህሎት ባሻገር የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ክህሎቶችን ባካተተ መልኩ መዳሰስ ስለነበረበት በተለይ ደግሞ መረጃን መሠረት ያደረገ ውሳኔ ከመስጠት አንፃር አሁንም ከፍተኛ ክፍተት ይታያል።

ጊዜው የኢኖቬሽን እንደመሆኑ ኢኖቬሽንና ማኔጅመንትን ታሳቢ ያደረገ በተለይ ደግሞ የጤና ሥርዓቱን ቅኝትን የተከተለ አመራሮችን ማፍራት ያስፈልጋል። የሴቶችን የአመራርነት ተሳትፎ ለማሳደግ ሲባል ይህን ፕሮግራም ለመቅረፅ ታሳቢ ተደርጎ ወደ ሥራ ተገብቷል።

ሚኒስትር ዴኤታው እንደሚናገሩት የጤናው ዘርፍ ኢንቨስትመንት የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን ውጤታማ አመራሮችን ማፍራት ላይ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ባለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ ችሏል። በዘርፉ እየተደረገ ካለው ኢንቨስትመንት አንፃር ግን የበለጠ ውጤት ማስመዝገብ ይቻል ነበር። ለዚህም ውጤታማ አመራሮች ልማት ላይ ትኩረት ተደርጎ መሥራት ይኖርበታል። ይህም የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ሆኖ ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት ውጤታማነትን ለማሳደግ ያግዛል።

በጤናው ዘርፍ የሚደረግ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ ውጤት እንዲያስገኝ ለማድረግ ከሚደረጉት ጥረቶች አንዱ የውጤታማ አመራር ፕሮግራም ልማት ሲሆን ፕሮግራሙ በቀጣይ ተግባራዊ ይሆናል። በኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰቱ የሚገኙ እንደ ወረርሽኝ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በውጤታማነት ለመከላከል የአመራር ፕሮግራሙ ከፍተኛ ድርሻ ይኖረዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ማብራሪያ፣ ፕሮግራሙ ሶስት ምሰሶዎችን እና ስድስት ንዑስ ፕሮግራሞችን በውስጡ አካቷል። ሶስቱ ምሰሶዎች ውጤታማ የአመራር ብቃትን መገንባት (improve high impact leadership competencies)፣ ሴቶችን ለጤና አመራርነት ማብቃት፣ የአመራር ተጠያቂነትን ማስፈን/ማዳበር (Cultivate managerial accountability) ሲሆኑ ስድስቱ ንዑስ የአመራር ልማት ፕሮግራሞች ደግሞ የከፍተኛ አመራር ፣ የመካከለኛ አመራር፣ የታችኛው አመራር ፣ ሴቶችን ለጤና አመራርነት ማብቃት ፣ የክሊኒካል አመራርነት ማሻሻል እና ተተኪ የጤና አመራሮችን ማፍራት (High Impact Leadership Incubation-HI-LIP) ናቸው።

በጤና ሚኒስቴር የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አባስ ሃሰን በበኩላቸው እንደሚሉት ሀገራዊ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችና የፌዴራል ተቋማት መዋቅራዊ ክለሳና አደረጃጀትን ተከትሎ የጤና ሚኒስቴርም የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ጥራት መሪ ሥራ አስፈፃሚ በአዲስ መልክ አቋቁሟል። በስሩም የጤና አመራር የሚያስተባብር ዴስክ በአዲስ መልክ አደራጅቶ ሥራ ጀምሯል። በዚህም ቀደም ሲል የነበሩ ተለምዷዊ ሁኔታዎች ማዘመንና አዳዲስ ተግዳሮቶችን በአዳዲስ አመራርና ክህሎትን በመጠቀም መፍታት እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ተወስዷል።

ተለዋጭና እርግጠኛ ባልሆነ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የጤናና ሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ እድሎችን በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል ብሎም ከፍተኛና ምርታማ አመራር የሚገነባና ሀገራዊና ተቋማዊ ውጤቶችንና ግቦችን በማሳካት ረገድ ዐሻራን ማሳረፍ የሚያስችል የውጤታማ አመራር ፕሮግራምና የማስፈፀሚያ ፕሮግራም ፓኬጆችና ስልቶች ሲቀረፁ ቆይተዋል። ፕሮግራሙ የማስፈፀሚያ ፓኬጆችና ስልቶች ቀረፃው አውን እንዲሆን የጤና ሚኒስቴር የማኔጅመንት አባላትና የተለያዩ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች እንዲሁም የመስኩ ከፍተኛ ባለሙያዎች ብሎም አጋር ድርጅቶች ያላሰለሰ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ከነዚህ ፕሮግራሞች ውስጥ አንዱ የጤናው ዘርፍ ውጤታማ አመራር ፕሮግራም/high impact leadership program/ ነው። ይህ ፕሮግራም የተቀረፀው ከዚህ ቀደም የነበሩ መልካም ተሞክሮዎችን እና ተግዳሮቶችን ታሳቢ በማድረግ ሲሆን የጤና ሥርዓት ኢኖቬሽንና ማሻሻያ መሪ ሥራ አስፈጻሚ በጤና ሚኒስቴር መቋቋሙ የአመራር ፕሮግራሙ ስኬታማነትን ለማረጋገጥ ያስችላል። ፕሮግራሙ በአዲስ መልኩ የተቀረፀበት ዓላማ እንደሀገር በጤናው ዘርፍ ያለውን ሀብትና አቅም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተቀመጡ ግቦች ጋር በማጣጣም ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የጤናው ዘርፍ ግቦችን ለማሳካት ነው።

ፕሮግራሙ ተግባራዊ ሲሆን በየደረጃው ያሉ አመራሮች ማለትም ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ ያሉትን አመራሮችንና በሁሉም ደረጃ ያሉ ተቋማትን ያካትታል። ስለዚህ ፕሮግራሙ ከዚህ በፊት ከነበሩት ፕሮግራሞች በተለየ መልኩ ለአመራሮች ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል። አውቅና የሚያገኙበትንም አሠራር ይዞ የመጣ ነው። ፕሮግራሙ ወደታች ሲወርድ የራሱ የሆኑ የአቅም ግንባታና የማስፈፀሚያ ፓኬጆችም አብረው ተቀርፀውለታል።

በዚሁ መሠረት በየደረጃው ያሉትን አመራሮች አቅም በመገንባት የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው አመራሮች ሥልጠና ሲያጠናቅቁ ያጠናቀቁበት ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል። በሥለልጠናው ጥሩ ውጤት ያመጡ አመራሮች ደግሞ ራሱን የቻለ ሰርተፍኬት እንዲያገኙ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው። ከዚህ በኋላም እያንዳንዱ የጤናው ዘርፍ አመራር በሥልጠና ብቻ ሳይሆን የሚለካው በውጤትና ተፅእኖ በማምጣትም ጭምር ይሆናል። በዚህም የተሻለ አፈፃፀም የሚያመጡ አመራሮች እውቅና የሚያገኙበት አሠራርም ተዘርግቷል።

መሪ ሥራ አስፈፃሚው እንደሚያብራሩት፣ በጤናው ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ አመራሮች ካሉ የኢኖቬሽን ባህልም አብሮ ይዳብራል። ኢኖቬሽንን /ግኝት/ ተጠቅመው በተለየ እይታ፣ በተለየ አመራር የተለየ ውጤት ማምጣት ለሚፈልጉ አመራሮችና በጤናው ሴክተር የተቀመጡ ግቦችን ለማፋጠን የተለየ የአሠራር ሥርዓት ያስፈልግ ነበር። በዚህ መሠረት የብሄራዊ ጤና ኢኖቬሽን መመሪያ ተዘጋጅቷል። አመራሩ ይህን መመሪያ በመጠቀም በቀጣይ ውጤት እንዲያመጣ ይጠበቃል። አንደኛው የሚፈለገው ውጤት የጤና አገልግሎት ጥራትን ማሻሻልና ለተገልጋዮች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው።

እንደሀገር የአመራር ፕሮግራሙ ውጤታማ እንዲሆን በሀገር አቀፍና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጡ መለኪያዎች መሠረት ተወዳዳሪ የሆኑ ተቋማትን ማፍራት ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ ወደ 537 የሚሆኑ በተለያዩ ደረጃዎች ላይ ያሉ የጤና ተቋማት በተቀመጡ ደረጃዎች መሠረትና እየተዘጋጀ ባለው ትግበራ ማንዋል መሠረት የመለየትና እውቅና የመስጠት ሥራ ይከናወናል።

በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያ የሜዲካል ቱሪዝም መዳረሻ የመሆን ትልቅ አቅም ያላት እንደመሆኑ ይህን እንደመልካም አጋጣሚ በመውሰድና በጤናው ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት የጤና ተቋማት በቅድሚያ በሀገር አቀፍ ደረጃዎች፤ በቀጣይ ደግሞ በዓለም አቀፍ ደረጃዎች አውቅና የመስጠት ሥራ ይሠራል። ለዚህ ደግሞ ከመንግሥትም ሆነ ከግሉ ዘርፍ በኩል ያለው ተነሳሽነት ከፍተኛ ነው።

አስናቀ ፀጋዬ

አዲስ ዘመን  ግንቦት 3 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You