ኢትዮጵያ ነፃነትን ለዓለም በማስተማር ደማቅ ታሪክ አላት:: ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አሸናፊ የሆኑት የዓለም ልዕለ ኃያል የተባሉ አራቱ ሀገራት (አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ እና ሶቪየት ሕብረት) የጣሊያን ቅኝ ግዛት የነበሩት ሀገራት እንዴት ይሁኑ? በሚለው ጉዳይ ላይ ከ10 ዓመታት በላይ ተከራክረዋል:: በእነዚህ ክርክሮችና ውይይቶች ውስጥ ቅኝ ያልተገዛችው ኢትዮጵያ ከኃያላኑ ሀገራት ጋር በአንድ አዳራሽ ተቀምጣ መክራለች:: ሙሉ ታሪኩን ‹‹የኤርትራ ጉዳይ›› ከሚለው የአምባሳደር ዘውዴ ረታ መጽሐፍ ላይ ማግኘት ይቻላል::
ኢትዮጵያ ለዚህ ክብር የበቃችበት ምክንያት ቅኝ ያልተገዛች ሀገር መሆኗ ነው:: ቅኝ የተገዙ ሀገራትን ልክ እንደ ሕጻን ልጅ ሞግዚት እናድርግላቸው ወይስ ራሳቸውን ችለው መኖር ይችሉ ይሆን? እየተባለ ሲመከር ኢትዮጵያ ግን የይገባኛል ጥያቄ ይዛ (ኤርትራንና ሱማሌን) አብራ መካሪ ነበረች:: በጀግኖች ልጆቿ ሉዓላዊነቷን ባታስከብር ኖሮ በዚያ ውይይት ላይ መካሪ ሳይሆን ‹‹ማንን ሞግዚት እናድርግላት?›› እየተባለ የሚመከርባት ትሆን ነበር::
በዛሬው ሳምንቱን በታሪክ ዓምዳችን 82 ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻውን ውጊያ አድርጎ የተሸነፈበትን እና የኢትዮጵያ ሙሉ ነፃነትና ሉዓላዊነት መከበሩ የተረጋገጠበትን የታሪክ ክስተቶች እናስታውሳለን:: ከዚያ በፊት እንደተለመደው ሌሎች ክስተቶችን በአጭር በአጭሩ እናስታውሳለን::
ከ171 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1845 ዓ.ም ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ‹‹ዳግማዊ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ከመንገሣቸው በፊት ከግዛት ባላባቶች ጋር ካደረጓቸው ታላላቅ ጦርነቶች መካከል አንዱ የነበረውን የጉር አምባ ጦርነት ከደጃዝማች ጎሹ ዘውዴ ጋር አደረጉ:: ይህ ጦርነት ለአጼ ቴዎድሮስ ወደ ንጉሠ ነገሥትነት መምጣት እና ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ወሳኙ ጦርነት ነበር:: በዚህ ጦርነት ላይ የደጃች ጎሹ ጦር ለማሸነፍ ተቃርቦ ነበርና አንድ አዝማሪ ለደጃች ጎሹ አድሮ እንዲህ አለ::
ያንዣብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሳ
ወርደህ ጥመድበት ከሽንብራው ማሳ
ወዲያውኑ የደጃች ካሳ (አጼ ቴዎድሮስ) ጦር አሸነፈ:: ያ አድርባይ አዝማሪ አቋሙን ቀይሮ እንዲህ አለ::
አወይ የአምላክ ቁጣ
አወይ የእግዜር ቁጣ
አፍ ወዳጁን ያማል የሚሰራው ሲያጣ
ዱላ ይገባዋል የአዝማሪ ቀልማጣ
ከ49 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1967 ዓ.ም ብርጋዴር ጄኔራል ተፈሪ ባንቲ የደርግ ሊቀመንበር ሆነው ተመረጡ::
ከ163 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 21 ቀን 1853 ዓ.ም የታሪክ ጸሐፊ፣ ተርጓሚ፣ ደራሲ፣ የቅኔ ሊቅ፣ የሃይማኖት መምህር የነበሩት እና በኢትዮጵያ የሥነ ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎላ ብሎ የሚጠቀሱት አለቃ ታየ ገብረማርያም ተወለዱ::
ከ113 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 22 ቀን 1903 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ መድኃኒት ቤት (ፋርማሲ) ተቋቋመ::
ከ29 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 22 ቀን 1987 ዓ.ም ደራሲ፣ የሥነ ጽሑፍ መምህር፣ ገጣሚ እና የተውኔት ጠቢብ የነበረው ዳኛቸው ወርቁ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ:: ደራሲ ዳኛቸው ወርቁን ‹‹የሥነ ጽሑፍ አብዮተኛው›› በሚል ርዕስ ባለፈው ዓመት ሳምንቱን በታሪክ በዝርዝር መሥራታችን ይታወሳል::
ለዛሬው በዝርዝር ወደምናየው ሳምንቱን በታሪክ እንሂድ::
ወራሪው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ኢትዮጵያ ውስጥ የመጨረሻውን ውጊያ አድርጎ የተሸነፈውና ኢትዮጵያ ሙሉ ነፃነትና ሉዓላዊነቷን ያረጋገጠችው ከ82 ዓመታት በፊት በዚህ ሳምንት ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ነበር:: ይህ
ወቅት ጣሊያን በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀርመን ጋር ተባብራ ባደረገችው ውጊያም የተሸነፈችበት ነበር::
ወደ ኢትዮጵያ ታሪክ እንመጣ፤ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቢውለበለብና የፋሺስት ጦር መሸነፉ ይፋ ቢሆንም፤ ጦሩ ከአንዳንድ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ጨርሶ አልወጣም ነበር:: በዚሁ ሳምንት ኅዳር 18 ቀን 1934 ዓ.ም የፋሺስት ጦር የመጨረሻ ይዞታው የነበረችውን ጎንደርን ለማስለቀቅ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ከእንግሊዝ ጦር ጋር በጋራ በመሆን ውጊያ ከፈቱ:: በዕለቱ የአካባቢው የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር መሪ የነበረው ጀኔራል ናዚ የኢትዮጵያውያን አርበኞችና የእንግሊዝ ወታደሮች የጋራ ጥቃት ጥንካሬው ተስፋ ስላስቆረጠው ከአደባባይ ኢየሱስ ወደ መድኃኔዓለም ሄዶ ነጭ ጨርቅ አውለበለበ:: ምርኮ የመረከብ ሥራ ተጀምሮ ነበር፤ አርበኛውም ሁሉ ጉራያ ማስጫ ከግንቡ ስር አደረ::
በምስራቅ በኩል የተሰለፈው የኢትዮጵያ ጦር ግን ወደ ጎንደር ለመግባት ሲሞክር ተቀብሮ የነበረው የፋሺስት ጦር ቦምብ ፈንድቶ ጉዳት አደረሰበት፤ ርምጃውንም አዘገየበት:: በማግስቱ ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ራስ ብሩ ወልደብርኤል ከእንግሊዛዊው ሜጀር ጄኔራል ፎክስ ጋር ወደ ጎንደር ገቡ:: ‹‹ባለህበት እርጋ›› ተባለና ሁሉም ተረረጋ:: ጄኔራል ናዚ ያለድርድር እጁን ሰጠ:: የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በፋሲለደስ ግንብ ላይ ተውለበለበ።
በማግሥቱ ኅዳር 20 ቀን 1934 ዓ.ም ልዑል አልጋወራሽ አስፋወሰን ኃይለሥላሴ ጎንደር ገቡ:: የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ የነበረው ቆይታም በዚሁ ተደመደመ:: በጎንደሩ ውጊያ የጣሊያን ሽንፈት የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በአፍሪካ ምድር ያካሄደው የመጨረሻው ውጊያና የተከናነበው የመጨረሻው ሽንፈት ሆኖም ተመዘገበ::
አራት ኪሎ የሚገኘው የአርበኞች ድል መታሰቢያ አጼ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ተመልሰው አዲስ አበባ የገቡበት ቀን ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ነው ተብሎ በታሪክ መዝገብ ላይ ቢሰፍርም፤ ኢትዮጵያ ከፋሺስቶች ሙሉ በሙሉ የተላቀቀችበት ቀን ኅዳር 19 ቀን 1934 ዓ.ም ነው፤ በዚሁ ዕለት ጄኔራል ናሲ የተባለው የፋሺስት ጦር መሪ ከነሠራዊቱ እጁን ሰጥቶ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በፋሲለደስ ግንብ ላይ ተውለበለበ። በነገራችን ላይ በደርግ ዘመነ መንግሥት ጊዜ የአርበኞች ቀን የሚከበረው ሚያዚያ 27 ቀን አልነበረም:: ደርግ የንጉሠ ነገሥቱን ታሪክ መቀየር እንደሚፈልግ ግልጽ ቢሆንም ሚያዝያ 27ም ቢሆን ግን ታሪካዊ ቀን ነው::
በወቅቱ ይታተም የነበረ ‹‹ባንዲራችን›› የተሰኘ ጋዜጣ በ1ኛ ዓመት ቁጥር 39 የካቲት 18 ቀን 1934 ዓ.ም ዕትሙ፤ ከፋሽስት ጣሊያን ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ስለተደረገው የጎንደሩ ጦርነት የሚከተለውን መረጃ አትሟል::
ብዙ ሽንፈት የተከናነበው ሞሶሎኒ የጠቅላይ ጦር አዛዥነቱን ሥልጣን ለጀኔራል ናዚ ሰጠው። ናዚ የቀረውን አርባ ሺህ የሚሆነውን የጣሊያን ጦር አሰባስቦ የመጨረሻውን ፍልሚያ ለማድረግ ጎንደር ላይ መሽጎ መጪውን ጊዜ በጭንቀት ይጠባበቃል።
በደጃዝማች ኃብተሥላሴ በላይነህ የሚመራው አምስት ዓመት ሙሉ ጠላትን መግቢያ መውጫ ያሳጣው የሸዋ አርበኛ አምባላጌ ላይ ዱክ ዳውስታን ማርኮ በየቦታው የመሸገውን የጠላት ጦር እየደመሰሰ በተለይም ጠላት መቼም አይደፈሩም ብሎ የመሸገባቸውን ወልክፊት፣ ፍርቃ በር እና ቁልቋል በር የተባሉትን የጠላት ምሽጎች ሰባብሮ ጎንደር ደርሶ ለመጨረሻ ጊዜ ፋሽቱን የጣሊያን ጦር ለመቅበር ዝግጅቱን ጨርሷል። በጀኔራል ፎክስ የሚታዘዘው የእንግሊዝ ጦርም በአየር፣ በመካናይዝድ እና በእግረኛ ጦር ተዘጋጅቶ የመጨረሻውን ትዕዛዝ ይጠባበቃል:: በመጨረሻም የጎንደር ከተማ በየአቅጣጫው ተከበበች::
የጎንደር ከተማ ከተከበበች በኋላ ህዳር 18 ቀን 1934 ዓ.ም ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጦርነቱ ተጀመረ:: የእንግሊዝ እና የጠላት መድፎች ሰማይና ምድሩን ያናውጡት ጀመር:: የእንግሊዝ የጦር አውሮፕላኖችም ከዳባት በመነሳት የናዚን የጦር ሰፈር በቦንብ ይቀጠቅጡት ጀመር።
በደጃዝማች ኃብተሥላሴ የሚመራው በደቡብ ጎንደር ሰፍሮ የነበረው አርበኛ ሌሊቱን ተጉዞ አድሮ ወደ ምሽጉ ተጠግቶ ስለነበር በፈንጂ ላይ እየተረማመደ የጣሊያኑን የጄኔራል ማርቲንን ሠራዊት ሰብሮ ቀድሞ ጎንደር ገብቶ የጠላትን ጦር ያርበደብደው ጀመር:: በጄኔራል ፎክስ የሚታዘዘው የእንግሊዝ ሜካናይዝድ ጦር የአዘዞን ግንባር ጥሶ ገባ:: በምስራቅ በኩል የነበሩት አርበኞችና የእንግሊዝ ወገን የሆኑት የኬንያ ወታደሮች ደፈጫ የነበረውን የጠላት ጦር በጥንካሬ ወግተው አስለቅቀው ወደ ጎንደር ለመግባት ሲሞክሩ በተጠመደ ፈንጂ ከባድ ጉዳት ደረሰባቸው።
የእንግሊዝ ጦርም ከሰዓት በኋላ ወደ ስምንት ሰዓት ተኩል ሲሆን ወደ ፋሲል ግንብ ተጠጋ:: በዚህ ጊዜም ጀኔራል ናዚ በተጠባባቂነት ያስቀመጠውን የመጨረሻውን ጦር ቢልክም ውጤት ሳያመጣለት ቀረ። ከትንሽ ጊዜም በኋላ ጄኔራል ናዚ ከተደበቀበት ‹‹ካዲ ኢጣሊያ›› ከሚባለው ቤት አስተርጓሚ ሆነው ሲያገልግሉት ከነበሩት ከፊታውራሪ አስፍሓ ወልሚካኤል ጋር በመሆን እጁን ሰጠ።
ከዚህ በኋላ ሠራዊቱ እንዲረጋጋ የተማረኩና የተበተኑት የጠላት ወታደሮችም እንዲሰበሰቡ በተማረኩ የጠላት ወታድሮች ላይም አርበኞች ምንም ጉዳት እንዳያደርሱ የማረኳቸውን እንዲያስረክቡ የሚል ትዕዛዝ በመተላለፉ አርበኞች የማረኳቸውን የጠላት ወታደሮች እያመጡ ያስረክቡ ጀመር።
በዚህ ጦርነት አራት ሺህ የጣሊያን ወታደሮች ሲገደሉ፣ ስምንት ሺህ አራት መቶ የቆሰሉ ሲሆን ሃያ ሰባት ሺህ ተማርከዋል:: ጄኔራል ናዚም የጦር ወንጀለኛ ሆኖ በእስር ወደ ኬንያ ተላከ።
በዚህ ጦርነት ከጠላት የተማረከውን ከባድና ቀላል የጦር መሣሪያ መድፍ፣ ታንክ፣ እና ከባድ የጦር ተሽከርካሪ አንድም ሳያስቀሩ እንግሊዞች በሱዳንና በኤርትራ በኩል አግዘው ወስደዋቸዋል።
ከድሉ በኋላ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የሚከተለውን የደስታ መግለጫ መልእክት ጎንደር ለሚገኙት አርበኞች አስተላለፉ::
‹‹በዚህ በታላቅ ደስታ ምልክት በሚታይበት ቀን በሰንደቅ ዓላማችን ዙሪያ ተሰብስባችሁ በአየር ሲውለበለብ የምትመለከቱት አርበኞች ዓይኖቻችሁ ከኢትዮጵያ አየር ተለይቶ በማያውቀው ቀለም የተጌጠውን የነፃነት ምልክት ለማየት ሲወረወሩ ልባችሁ የሚሰማውን የደስታ ወለልታ መላ በጌምድር እንደሚሰማው ለኛም ይሰማናል። በዚህች ሰዓት በተወደደ ልጃችን አማካኝነት ስንነገራችሁ በመካከላችሁ እንዳለን ቁጠሩት።
በአለፉት ዓመቶች የደረሰውን ፈተና ድል አድራጊ ለመሆንና በጎንደር ከተማ በዛሬው ቀን ይህን ለማየት ስትችሉ መሪር መንገድ አልፋችሁ ወደዚህ ቦታ ለመድረስ የበቃችሁ አርበኞቻችን በጦር ሜዳ የተመሰገኑ ጀግኖቻችንን እሬሳና አፅም ተራምዳችሁ ነው። ይህም ዛሬ የምታዩት ሰንደቅ ዓላማ በነዚያ ደምና በናንተ ገበሬነት በለሰለሰ መሬት ላይ በቅሎና ለምልሞ ያደገ የነፃነት ሕይወት ዛፍ ነው። የአለፉት መታሰቢያና የኛና በሕይወት የተረፋችሁት ድካም አልጠፋምና እኛን ደስ እንዳለን እናንተም ደስ ይበላችሁ:: ይህ በወገኖቻችን ደም የበቀለው የሰንደቅ ዓላማ ዛፍ የዘለዓለም የሕይወት ዛፍ እንዲሆን ያለፉት በመሥዋዕትነት የደከሙትን ያህል በሕይወት የቀረነው ወደፊትም የሚመጣው ትውልድ በአስፈለገ ጊዜ በመሰዋት የሚሰጥበት የቃል ኪዳን ምልክት ነው››
ከዚህ በኋላ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋወሰን ጎንደር መጥተው ስለነበር እርሳቸውን ተቀብለው ከእርሳቸው ጋር ሀገር ሲያረጋጉ ከቆዩ በኋላ ደጃዝማች ኃብተሥላሴ ከነሠራዊታቸው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው የካቲት 16 ቀን 1934 ዓ.ም በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከፍተኛ የጦር ሰልፍና ሥነ ሥርዓት አቀባበል ተደርጎላቸዋል:: በጊዜው በቦታው ተገኝቶ የነበረው ‹‹ባንዲራችን›› የተባለው ጋዜጣ ሥነ ሥርዓቱን በምልከታ ሐተታ ዘግቦታል::
በአጠቃላይ፤ ኢትዮጵያ በዓድዋ ጦርነት ያሳየችውን የጀግንነት ድል በድጋሚ አስመስክራለች:: ከ40 ዓመታት ዝግጅት በኋላ ቂሙን ለመወጣት የመጣው የጣሊያን ወራሪ በድጋሚ ሽንፈት ተከናንቦ ተመልሷል:: ኢትዮጵያም ሉዓላዊነቷን በማስከበሯ በዓለም አቀፍ መድረኮችና ማህበራት ላይ ከአድራጊ ፈጣሪዎች ጋር ተሳታፊ ለመሆን በቅታለች:: ክብር ለጀግኖች አርበኞቻችን!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 23/2016