የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ተኪ ምርቶች መጠቀም ተገቢና ሊደገፍ የሚያሻው ጉዳይ ነው። ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ግብዓት መሆን ከሚችሉ ጥሬ ዕቃዎች መካከልም ባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይ አንዱ ነው። ይህ ባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይ ለኮንስትራክሽን ዘርፍ ከፍተኛ እገዛ እንዳለውና በሀገሪቱ በስፋት እንደሚገኝ መረጃዎች ያሳያሉ። በተለይም በሰሜን፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ ክልል እና በሌሎች አካባቢዎችም ይገኛል።
አገልግሎቱም ከአስፓልት ሥር ንጣፍ በመሆን አስፓልቱን ከመሰንጠቅ ይታደገዋል። በተጨማሪም በርካታ የፋይበር ምርቶችን ለማመረት፣ ለጂኦቴክስታይል እና ለተለያዩ የኮንስትራክሽን አገልግሎት በግብዓትነት ያገለግላል። ይሁን እንጂ የትኛው ባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይ ለየትኛው አገልግሎት ይውላል የሚለውን ናሙና ወስዶ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል።
ለኮንስትራክሽን ግብዓት የሚውለውን ባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይ በጥናት ለይቶ በመጠቀም ከውጭ የሚገቡ የግንባታ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ መተካት ያስችላል። በዚህም ለዘርፉ ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል። ከዚህ ባለፈም ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪን ማግኘት እንደሚቻልና የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩትም ከሰሞኑ ባዘጋጀው መድረክ ይህንኑ አመላክቷል። ትኩረቱን የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን አሟጦ መጠቀም ላይ ባደረገው ጉባኤ የተገኙት አቶ ነብዩ ነጋሽ በኢትዮጵያ የባዛልት ወይም የጥቁር ድንጋይ ኮንቲኒየስ ፋይበር እና ውህድ አካላት ቴክኖሎጂ ተወካይ ናቸው። የባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይን ለኮንስትራክሽን ግብዓት ለማዋል እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አስመልክተው ገለፃ አድርገዋል።
አቶ ነብዩ እንደሚሉት፤ የባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በበለጸጉት ሀገራት በተለይም በምዕራባውያን ባለፉት 40 ዓመታት በስፋት በግንባታ ግብዓትነት የዋለ ሲሆን ከሚበላ እና ከሚጠጣ ውጭ ለበርካታ አገልግሎቶች መዋል የሚችል እንደሆነ ያስረዳሉ። እሳቸው እንዳሉት የባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይ ቴክኖሎጂን ለግንባታ ግብዓትነት በስፋት መጠቀም እና በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲደረግ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ተከታታይ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይቷል።
አሁን ሀገሪቷ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ባለችበት ጊዜ ያሏትን የግንባታ ግብዓቶች ወደ ተሻለ ደረጃ ማሳደግ እና እሴት ጨምሮ መጠቀም ተገቢ ነው። ከዚህም ባለፈ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ የምንዛሪ እጥረቱን መደገፍ ይገባል። ጥራታቸውን የጠበቁ የግንባታ ግብዓቶችን ከማምረት ረገድ የቻይናን ምሳሌ መውሰድ ተገቢ እንደሆነ ጠቁመው፤ ቻይናውያን በሀገራዊ እቅድ (National Program) አካትተው የያዙት መሆኑን አንስተዋል።
ከፋይበርነት ጀምሮ የተለያዩ ዓይነት የማኑፋክቸሪንግ ሲስተሞችን በመጠቀም ጨርቃጨርቅን ጨምሮ በርካታ ነገሮችን ለማምረት የሚያስችል አዲስ ምዕራፍ እንደሆነም ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ማስተካከል ከተቻለ ማህበራዊ ችግሮችንም በዚያው ልክ ለማስተካከል የራሱ ጉልህ ድርሻ አለው ብለዋል። ለምሳሌ ቤት መግዛት ባለመቻላቸው ወጣቶች ትዳር ሊመሰርቱ አልቻሉም የሚሉት አቶ ነብዩ፤ ምርቱ የቤት ግንባታን ጨምሮ ለአልባሳትና ለሌሎች ምርቶችም የሚያገለግል ነው በማለት፤ ለሀገሪቷ ከፍተኛ የኤክስፖርት እድል ሊፈጥር የሚያችልና ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ የሚችል ትልቅ አብዮት ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ነብዩ ማብራሪያ፤ ከዚህ ቀደም የጥቁር ድንጋይ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ካዛኪሲታን፣ ዩክሬን፣ ኡዝቤክስታን ሀገራት ጥቅም ላይ የዋለ ነው። እንዲሁም እንደ BMW፣ ቮልስዋገን ያሉ መኪና አምራች ካምፓኒዎችም ለኤሌክትሪክ መኪና ምርት ቀላልና ጠንካራ በመሆኑና የባትሪያቸውን እድሜ ለመጨመር የሚገለገሉበት መሆኑንም አመላክተዋል። የኮንስትራክሽን ዘርፉ በርካታ ወጪዎች ያሉበት እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የውጭ ምንዛሪዎችን ከሀገር ውስጥ የሚያስወጣ ነው። በመሆኑም ይሄንን ችግር ለመቅረፍ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን አሟጦ መጠቀም እና በሀገር ውስጥ ምርቶች መተካት ይገባል። በሀገር ውስጥ መተካት
ሲባልም ጥራቱ ቀንሶ ወይም ለሕንፃ ግንባታ እድሜው አጥሮ ሳይሆን በተሻለ ሁኔታ ማምረት እና የውጭ ምንዛሪ ወጪውን ማስቀረትና በምትኩም ጥራታቸውን የጠበቁ የግንባታ ግብዓቶችን ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ማምጣት ያስችላል።
ባዞልት ወይም ጥቁር ድንጋይ አንደኛ በዘልማድ “ፌሮ” የሚባለውን ጨምሮ ኮንስትራክሽን ላይ ሊገቡ የሚችሉ ብረት፣ እንጨት እና ፕላስቲክ ውስጥ ገብቶ ሊመረት ይችላል። ሁለተኛነትም “ቾፕ ፋይበር” የሚባለውን ከሲሚንቶ እና አሸዋ ጋር በመቀላቀል ጥንካሬ እንዲኖረው ተደርጎ የሚመረት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ነብዩ፤
በሶስተኛነት ደግሞ “ጂኦ ቴክስታይል ሜሽ” የሚባለውን መረብ የሚመስለውን ዓይነት በማምረት በተለይ ቁልቁለታማ በሆኑ አካባቢዎች ላይ አስፓልት በሚሰራበት ጊዜ ከስር በማንጠፍ አስፓልቱ እንዳይሸሽ፣ እንዳይቆራረጥ እንዲሁም መሬቱ እንዳይሸረሸር እንደ ማጠንከሪያ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸው፤
በአስፓልት ብቻም ሳይሆን ማንኛውንም መሰንጠቅ ሊከሰትባቸው የሚችሉ ግንባታዎችን ከአደጋ ለመከላከል መረቡ ከስር ተደርጎ ከላይ ሲሚንቶ ወይም ልስን በማድረግ ለማጠናከርና እድሜውን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል። በተጨማሪም ማዳበሪያ ሊመረትበት እንደሚችል ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም መጠቀም ከጀመረ ገና 40 ዓመት ያስቆጠረና አዲስ ቴክኖሎጂ በመሆኑ መንግሥት የግል ባለሀብቱን በማሳተፍ በፕሮግራሙ አስገብቶ ቢጠቀምበት ሀገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ትሆናለች ነው ያሉት። እሳቸው እንዳሉት፤ ባዛልት ወይም ጥቁር ድንጋይ ከምግብና ከመጠጥ ውጭ ባሉ በማንኛውም ነገር ውስጥ ሊገባ የሚችል በመሆኑ በተለያየ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ማስቀረት ይቻላል። በተመሳሳይ ቴክኖሎጂው በአውሮፓ እና በቻይና ሳይቀር ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው መሆኑም ምርቱን ወደ ውጭ በመላከ የሀገሪቷን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ቴክኖሎጂው ነገሮችን በተሻለ ሁኔታ የሚተካ ነው ያሉት አቶ ነብዩ፤ ድንጋዩ በባህሪው የሚዝግ ባለመሆኑ ብረትን በተሻለ ሁኔታ እንዲሁም እንጨትንና ፕላስቲክን በተሻለ ሁኔታ የሚተካ እንደሆነ ገልጸዋል። ሀገሪቷ ለተለያዩ ምርቶች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታወጣ ሲሆን፤ ከምታወጣው ወጪ ቢያንስ 15 ቢሊየን ዶላር ያለ ወጪን የሚቀንስ እንደሆነ አመላክተው፤ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተደረገው ጥናትም 10 ቢሊየን ዶላር ያህል ወደ ውጭ ኤክስፖርት ማድረግ የሚያስችል እንደሆነ ተናግረዋል።
ባዞልት ወይም ጥቁር ድንጋይ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኝ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ነብዩ፤ በተለይም በረሃማ በሆኑ እና ለእርሻ አመቺ ባልሆኑ ቦታዎች የሚገኝ ሲሆን፤ በግብርናው ቋንቋ እነዚህን ቦታዎች ምርታማ ማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል።
ከዚህ አንፃርም በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር ገቢ እንዲኖራቸው ማድረግ የሚቻል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ወጣቶች ባዞልት ጥቁር ድንጋዩን ፋይበር ከተመረተ በኋለ እየገዙ ሞልድ በማድረግ ወይም ቅርጽ በማስያዝ የቤት እቃ እንዲሁም የተለያዩ ነገሮችን እየሰሩ በከተማም ሆነ በገጠር ላለው ወጣት ከፍተኛ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል እንደሆነ አመላክተዋል።
ቴክኖሎጂው ላይ ምንም ጥያቄ አለመኖሩን ያነሱት አቶ ነብዩ፤ ሰዋዊ በሆኑ ምክንያቶች ሲጓተት ቢቆይም አሁን ግን ናሙናዎችን ወደ ማምረት ደረጃ ተደርሶ በዝግጅት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። ቴክኖሎጂው በዓለም ላይ በተለይም በምስራቅ አውሮፓ 40 ዓመት ያልቆየ እና የደረጀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ የተወሰዱ የጥቁር ድንጋይ ናሙናዎችም በጣም ጥሩ ጥራት ያላቸው ፋይበሮች እንደወጣቸው ገልጸዋል።
የአዋጭነት ጥናቱን በተመለከተ በጥቅሉ በተሰራው ጥናት መሠረት በአሁን ወቅት አንድ ኪሎ ብረት 150 ብር አካባቢ የሚሸጥ መሆኑን አመላክተው ይህን ከ28 እስከ 30 ብር ማውረድ እንደሚቻል ገልጸዋል። እስካሁንም ወደ ተግባር ለመግባት ያልተቻለበት ሁኔታ በሀገራችን ለአዲስ ነገር ይሰጥ የነበረው ትኩረት አናሳ መሆን፣ የመንግሥታት መቀያየር እና ከፍተኛ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገው መሆኑን እንዲሁም ለዘርፉ ተገቢ የሆኑ ባለድርሻ አካላት ሥራዎቻቸውን በንፁህ ልብ ማከናወን ባለመቻላቸው ተግባራዊነቱን እንዳጓተተው አንስተዋል።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የዚህ ዓይነት መድረኮችን አዘጋጅቶ ተገቢው የመንግሥት አካላትን በመጋበዝ መሰል መድረኮችን ማመቻቸቱን አንድ ርምጃ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል። አሁንም በቀጣይ መንግሥት እጁን አስገብቶ እንደ ፕሮግራም ይዞ ሊሰራበት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ጉዳዩ የእያንዳንዱን ኪስ የሚነካ ጉዳይ በመሆኑም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር ፈለቀ አሰፋ በበኩላቸው፤ ብዙ የግንባታ ፍላጎቶች በሀገሪቱ ስለመኖሩ አንስተው በዚያው ልክ ከፍተኛ የኮንስትራክሽን ግብዓት ችግሮች በየቦታው እንደሚስተዋሉ ተናግረዋል።
በመሆኑም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌሎች ሀገራት የተሰሩ የኮንስትራክሽን ግብዓት ቴክኖሎጂ ተሞክሮዎች ወደ ሀገራችን እንዲገቡ እና ሀገር ውስጥ መመረት እንዲችሉ ኢንስቲትዩቱ መደላድሎችን እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የሀገሪቱ የኮንስትራክሸን ግብዓቶች በብዛት እየተጓተቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለአብነት ብረት የመሳሰሉት የውጭ ምንዛሪ ላይ መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ እንደሆነ ገልጸዋል። በተመሳሳይ የሲሚንቶም ዋጋው እየተወደደ የሄደበት ሁኔታ መኖሩን አንስተው፤ አሁን ላይ ፍላጎታችን እየሰፋ የሚገኝ በመሆኑ እነዚህን በማስታረቅ ሂደት በስፋት እየተሰራ ነው ብለዋል።
“ችግሩን ለመፍታትም ቢያንስ ሀገሪቷ ውስጥ ያሉ ግብዓቶችን መልሶ መጠቀምና በተፈጥሮ ፕሮሰስ ማድረግ የሚቻለውን ደግሞ ፕሮሰስ በማድረግ ወደ ግንባታ ግብዓትነት በመቀየር የሥራ እድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን መቀነስ፣ የግንባታ ወጪን መቀነስ የሚል አሰራርን ማጸደቅ፣ አካባቢንም ተስማሚ ማድረግ እና የአካባቢንም ብክለት በመቀነስ ተስማሚ የኮንስትራክሸን ዘርፉን መገንባት ላይ ታሳቢ ተደረጎ እየተሰራ ነው” ብለዋል።
አንዳንዶቹ የኮንስትራክሸን ግንባታ ግብዓቶች በቀጥታ ከተፈጥሮ ሀብት ጋር የሚያያዙ ናቸው ያሉት ኢንጂነር ፈለቀ፤ “የፋይበር ግላስ ሪኢንፎርስመንት እንዲሁም የባሳልቲክ ፋይበር ሪኢንፎርስመንት በየቦታው ሀብት ያለበት በመሆኑ ተግባራዊ ሽራዎችን ማፋጠን እና በሚገባ ከተሰራ አምርቶ ወደ ውጭ መላክ የሚቻልባቸው እድሎች ሰፊ ናቸው፤ በቀጥታም የግንባታ ወጪዎችን በመቀነስ፣ የግንባታ ጥራትን ማስጠበቅና በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የሚል ዓላማ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ጥረት ሲደረግ የነበረው የባዛልት ቴክኖሎጂ እስካሁን ተግባራዊ አለመደረጉ በመንግሥት በኩል የነበረው እገዛ እና ምላሸ ፈጣን አለመሆኑን አንስተው ለምን ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ላይ እንደገለጹት የጉዳዩ ባለቤት ማነው ከሚለው አንፃር ለይቶ ካለማወቅ የመጣ እንደሆነ ገልጸዋል። አያይዘውም ከማይመለከተው ባለድርሻ ጋር የመሄድ እና ተገቢውን ምላሽ ያለማግኘት ችግሮችም በስፋት ተስተውለዋል ነው ያሉት።
ለግንባታ ግብዓት የሚውሉ ቴክኖሎጂዎችን ይዘው ወደ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ለሚመጡ ቴክኖሎጂው አሳማኝ መሆኑን ለማሳየት ባለሙያዎች በቂ ግምገማ ያደርጋሉ። በዚህም ኢንስቲትዩቱ ስታንዳርድ ማውጣት የሚችልበት እና በግብዓትነት እንዲጸድቁ መደገፍ የሚችል መሆኑንም ጠቁመዋል።
የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ በበኩላቸው ኮንስትራክሽን ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጠርበት እና ለሀገር ግንባታ ያለው ፋይዳ የላቀ ቢሆንም 60 በመቶ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ከውጭ የሚገቡ መሆኑ ዘርፉን እየፈተነ ይገኛል ብለዋል። ይህን ችግር ለማቃለልም በዘርፉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና በሀገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ለመተካት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
በኃይሉ አበራ
አዲስ ዘም ህዳር 22/2016