‹‹እንደ ሀገር አብረን ለመዝለቅ ሀገራዊ ምክክሩ ከፍተኛ ፋይዳ አለው›› – ወይዘሮ አዜብ አልፍሬድ ሻፊ

እዚሁ አዲስ አበባ ተወልደው ያደጉት የዛሬዋ የዘመን እንግዳችን ወይዘሮ አዜብ አልፍሬድ ሻፊ ይባላሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በሊሴ ገብረማርያም የተማሩ ሲሆን፤ በመቀጠል የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ናዝሬት የልጃገረዶች ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የ11ኛ እና የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በምድረ አሜሪካ ውድሮ ዊልሰን ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተምረዋል።

በአሜሪካ ምርጥ የተሰኘ ሰውን እነኩዋሜ ኑኩሩማ የተማሩበትን የጥቁሮች መማሪያ ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲን መርጠው፤ በፖለቲካል ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተምረዋል። ቀጥለው ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቴክኖሎጂ ማኔጅመንት በዛው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ ተከታትለው አጠናቀዋል። ለ38 ዓመታት በአሜሪካን የኖሩ ሲሆን፤ አሜሪካን እንደገቡ በልጅነት ዕድሜያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ ማምጣት አለበት የሚል ድርጅት ተቀብሏቸው እርሳቸውም ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር ሲታገሉ ቆይተዋል።

የፖለቲካው ፍላጎት ስለነበራቸው ቀዳማይ ኃይለ ስላሴ ይውረዱ ብለው ባንዲራ ይዘው ከፊት ተሰልፈው ተቃዋሚ ሆነው በወቅቱ መንግሥት እንዲቀየር ጠይቀዋል። በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ ወጥተው ለ38 አመታት ቢኖሩም ኢትዮጵያን ከልባቸው ማውጣት አልቻሉም። ስለዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወነውን እያንዳንዱን ነገር በአንክሮ ይከታተላሉ፤የተቻላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ይጥራሉ። በአሁኑ ወቀትም በኢትዮጵያ ውስጥ ሀገራዊ ምክክር መጀመሩ አስደስቷቸውም የበኩላቸውን ጥረት ለማድረግ ተነስተዋል። በተለይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ ምክክሩ በንቃት እንዲሳተፉ በኩላቸውን ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። እኒህ እንግዳችንም ወይዘሮ አዜብ አልፍሬድ ሻፊ ጋር የሚባሉ ሲሆን በሀገራዊ ምክክሩ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አዘጋጅተንላችኋል መልካም ንባብ።

 አዲስ ዘመን፡- ወደ አሜሪካን እንዴት ሔዱ ከሚለው እና በአሜሪካ ስለነበረው ሕይወትዎ ከማውራት እንጀምር?

ወ/ሮ አዜብ፡- ኢትዮጵያ እያለሁ ወደ 11ኛ ክፍል ትምህርቴን ከመቀጠሌ በፊት ታናሽ ወንድሜ ሳምሶን አልፍሬድ በመኪና አደጋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። በዛው በቤታችን አቅራቢያ ሃያ ሁለት አካባቢ የወንድሜ ሕይወት ማለፉ እና በሁለታችን መካከል የነበረው ግንኙነት፣ ልጅነቴ ሁሉም ነገር ተደራርቦ ሃዘኔን አከበደው። መሞቱን መቋቋም አቅቶኝ ነበር።

ቤተሰቦቼ የመንፈስ ጤንነቴ ጉዳይ አሳሰባቸው። ከሀገር ወጥቼ ሃዘኑ እንዲቀልኝ በማሰብ ወደ አሜሪካን ላኩኝ። በዛ አጋጣሚ ኢትዮጵያን ለቅቄ አሜሪካን ስገባ ፓን አፍሪካኒዝም የጀመረበት ጊዜ ነበር። እኔም የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ ገባሁ። ነገር ግን ትምህርቴን አላቋረጥኩም ነበር። የመጀመሪያ ዲግሪዬን እንደያዝኩ ከዛ በላይ ትምህርቴን ለመቀጠል ብፈልግም መሥራት እና ከትምህርት ማረፍ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ሥራ ስይዝ ትዳር መስርቼ ልጅ ወለድኩ። ስራዬን እየሠራሁ ልጄን አሳድጌ ዩኒቨርሲቲ ለማስገባት ደረስኩኝ።

ልጄ ስታድግ በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ ሥራ ጀመርኩኝ። እዛ ዩኒቨርሲቲ የገባሁበት ምክንያት ለልጄ እና ለራሴ ነፃ የትምህርት ዕድል ለማግኘት ነበር። ያኔ እርሷን ሳስተምር እኔም በቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ሁለተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ። ልክ የሁለተኛ ዴግሪዬን ስይዝ ዕቅዴ ከአምስት ዓመት በኋላ ወደ ሀገሬ እገባለሁ የሚል ነበር። አምስት ዓመት ያልኩበት ምክንያት አሜሪካን ሀገር ሁሉ ነገር የሚገኘው በብድር ነው። መኪና በብድር ነው። ቤት በብድር ነው። በዛች አምስት ዓመት ሁሉንም ዕዳ ጨርሼ ሀገሬ ለመግባት አሰብኩ።

ጓደኞቼ ውሸት መስሏቸው ነበር። እኔ ግን ሀገሬ ስለመግባት የወሰንኩት ተንበርክኬ እየፀለይኩ ነበር። ለፈጣሪዬ ‹‹ ሀገሬ ብትወስደኝ ውሃ ተቋርጧል፤ መብራት የለም፤ የቆሻሻ ሽታ አለ›› ብዬ አላማርርም እል ነበር። ፈጣሪ ፈቅዶልኝ በዕቅዴ መሠረት ልጄን ዩኒቨርሲቲ ካስገባሁ በኋላ አክሰስ ካፒታል ተቋቁሞ ስለነበር እዛ ተቀጥሬ ኢትዮጵያ ገባሁ። ለ38 ዓመት አሜሪካን ኖሬ ወደ ኢትዮጵያ ተመለስኩ። አሁን አስራ አምስት ዓመት ሆነኝ።

አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ፖለቲካል ሳይንስ ከተማሩ በኋላ ደግሞ ለምን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንትን መረጡ?

ወ/ሮ አዜብ፡- የትምህርት ዘርፌን የቀየርኩበት ምክንያት አንደኛ ፖለቲካን በጣም ጠልቻለሁ። ሌላው ማኔጅመንት ቴክኖሎጂ ጥሩ ፊልድ ነው። ምክንያቱም ዘመኑ የቴክኖሎጂ ነው።

አዲስ ዘመን፡- አሜሪካን ሀገር በነበሩበት ጊዜ ኢትዮጵያን በተመለከተ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳትፎዎ ምን ያህል ነበር? በተጨማሪ

ወ/ሮ አዜብ፡– ከኢትዮጵያ ከመውጣቴ በፊት የናዝሬት የልጃገረዶች ትምህርት ቤት እና የሴንጆሴፍ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ለዕረፍት ትምህርት ሲዘጋ ገጠሩን ለማየት በሐራምቤ ኢትዮጵያ ፕሮግራም አማካኝነት ከከተማ ወጣን። ወሎ፣ ትግራይ፣ አስመራ ፣ ጎንደር እና ጎጃምን አየን። ለመጀመሪያ ጊዜ ሌላውን ኢትዮጵያን የገጠሩን ሕዝብ አኗኗር አወቅን። ያ በእኔ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል። በሰዓቱ የነበረው ነገር አልገባኝም። ረሃቡ እየጀመረ ነበር።

በተለይ ደሴ የነበረው ጭንቅላቴን ጎድቶት ነበር። ልክ አሜሪካ ስደርስ የተማሪ ንቅናቄ ማህበርተኞች ተቀበሉኝ። ለእንደዛ ዓይነት ነገር ዝግጁ ነበርኩኝ። ማህበሩ ኢዙና (ኢትዮጵያን ዩኒየን ኢን ኖርዝ አሜሪካ) ይባላል። እዛ ውስጥ ገባሁ። በዛ ጊዜ ‹‹ሀገር መለወጥ አለባት፤ መንግሥት መለወጥ አለበት›› አልኩ። ቀዳማይ ኃይለስላሴ ከስልጣን ይውረዱ እያልኩ ባንዲራ ይዤ ሰልፍ ወጣሁ።

በጊዜው የኮሚኒስት መጽሐፍን እያነበብን ውይይት እናደርግ ነበር። በስሜት የተነዳን ወጣቶች ነበርን። ስሜታዊነታችን ሀገር ከመውደድ የመነጨ ነበር። የሔድነው ከደህና ቤተሰብ ወጥተን ነው። ነገር ግን የሌላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ሕይወት ያሳስበን ነበር። ያ የሐራምቤ ኢትዮጵያ ጉብኝት በጣም ልቤን የነካው ስለነበር የፖለቲካ ፍላጎቴ ከፍተኛ ሆነ።

ነገር ግን ብዙ ጓደኞቼ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። መጀመሪያ ንቅናቄ ውስጥ ስንሳተፍ ትምህርት አቁመን ወደ ኢትዮጵያ ሔደን ለመታገል መዘጋጀት አለብን የሚል ሃሳብ መስተጋባት ጀመረ። እኔ ብልጥ ሆኜ ‹‹እኔ አባቴ ከምንም በላይ ትምህርትሽን አስቀድሚ ብሎኛል። ›› አልኩና ትምህርቴን ቀጠልኩኝ። ጓደኞቼ ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ መጡ።

ጓደኞቼ ኢትዮጵያ ሲመጡ መንግሥት ተለውጧል። ቀዳማይ ኃይለስላሴ ወርደው ደርግ ሀገሪቷን ተቆጣጥሮ ነበር። በእኔ እድሜ የነበሩ ምርጥ ሀገር የሚለውጥ ጭንቅላት ያላቸው ብዙ መሥራት የሚችሉ ወጣቶች በሙሉ አለቁ። የመጣው ለውጥም ከቀዳማይ ኃይለስላሴ የተለየ አልነበረም። የጓደኞቼ መሞት፤ ለውጡ እንደታሰበው አለመሆኑ፤ በፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ አልነበረብኝም ብዬ እጅግ እንድቆጭ አደረገኝ። ሙሉ ለሙሉ ፖለቲካውን ጠላሁት። ነገር ግን ያም ቢሆን ማንበቤን እና መጠየቄን አላቆምኩም።

ለወጣቶች እኛ የሠራነውን ስህተት አትድገሙት የሚል መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ። በጦርነት ከእልቂት ውጪ የሚመጣ ለውጥ የለም። ይህንን የምለው የጓደኞቼን መጨረሻ ስላየሁ ነው። ጓደኞቼ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ምን ዓይነት ሕዝብ የሚያገለግሉ የሕክምና ባለሙያዎች እና ኢንጂነሮች መሆን ይችሉ ነበር? እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። በጣም ሀገር ወዳዶች ስለነበሩ ሀገራቸውን ምን ያህል ይጠቅሟት እንደነበር ለመገመት ይከብዳል። ተምረው ሲጨርሱ ሀገራቸው እንደሚመጡ እርግጠኛ ነኝ። ፈረንጅ ሀገር ቁጭ ብለው ዘላለማቸውን ፖለቲካ እያወሩ አይኖሩም ነበር።

በዛ ጊዜ ዘመኑ የሶሻሊዝም ጊዜ ነበር። ሃዋርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የነበሩት መምህሮቼ በጣም ባለምጡቅ አዕምሮ ነበሩ። በተለይ ፖለቲካል ሳይንስ ያስተምሩ የነበሩ፤ ከሶስተኛው ዓለም እና ከሌሎችም ጥቁሮች በብዛት ካሉበት ትንንሽ ደሴቶች የመጡ ነበሩ። የፖለቲካል ሳይንስ መምህራኖቼ በወቅቱ ሶሻሊዝምን የሚደግፉ ዓይነት ነበሩ። በፖለቲካው ላይ መሳተፌ ትምህርቴ ላይም ረድቶኛል። የጥናት ወረቀት ለመስራት በፖለቲካ ውስጥ የነበረኝ ተሳትፎ በእጅጉ አግዞኝ ነበር።

አዲስ ዘመን፡- በእርግጥ መጀመሪያ ወደ ፖለቲካው የሳብዎ የሐራምቤ ኢትዮጵያ ጉብኝት ብቻ ነው? ወይስ አባት እና እናትዎ በፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው?

ወ/ሮ አዜብ፡- አባቴ ተራማጅ አስተሳሰብ ያለው ሰው ነበር። በቀዳማይ ኃይለስላሴ ጊዜ የፀጥታ ዳይሬክተር ነበር። ድሬዳዋ ሀገረ ገዢም ነበር። በጣም ጥሩ ሥራዎችን ሠርቷል። የሀገር ፍቅር ስሜት ነበረው። ለእኛም የሚያስተላልፈው ያንኑ የሀገር ፍቅር ስሜቱን ነበር። ደጋግሞ የሚናገረው ‹‹ከእኔ ዕርስት እና ሀብት አትጠብቁ፤ ለውጥ ይመጣል፤ ያለን መሬት ይወረሳል፤ ስለዚህ በማይወረሰው ጭንቅላታችሁ ላይ ሥሩ። ›› ይለን ነበር።

እናቴም ሀገር ወዳድ ናት። ቀዳማይ ኃይለ ስላሴን በጣም ትወድ ነበር። እርሳቸውን የሚቃወም ሰው እኔ እረግመዋለሁ ትል ነበር። አሜሪካን መጥታ ልጄን ስታሳድግልኝ እኔም ተቀየርኩኝ። አባት እና እናቴ ይመክሩኝ ነበር። ሀገር እንድወድ ሀገርን እንድጠቅም ሀገርን እንዳገለግል ይመክሩኝ ነበር።

አዲስ ዘመን፡- እርሶ እንደአንድ የፖለቲካ ተሳትፎ እንደነበረው እና የፖለቲካ ባለሙያ እንደሆነ ሰው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛው ችግር ምንድን ነው?

ወ/ሮ አዜብ፡– ይህንን ለመመለስ ይከብደኛል። ነገር ግን አንድ ኢትዮጵያዊ ከአስተዳደጉ አንፃር ምኞቱ የተለያየ ነው። እኔ ወጣት በነበርኩበት ጊዜ አብዮታዊ ለውጥ ተመኝቻለሁ። አሁን ግን የምፈልገው ሰላማዊ ለውጥ ነው። ምክያቱም የኃይል አማራጩን አየነው፤ ወደታች ወረድን እንጂ ወደ ላይ አልወጣንም።

 ስለዚህ ከአሁን በኋላ ሀገርን የሚጎዳ ነገር ሳይሆን ሀገርን የሚጠቅም ነገር ላይ መሥራት አለብኝ ብዬ ተነስቻለሁ። በእርግጥ በፊትም ሁኔታውን ስላልተረዳሁ ጃንሆይ ይውረዱ ብዬ ተሳትፎ ሳደርግ ነበር።

አሁን ላይ የእናት እና የአባቴ መሬት ላይ የሕፃናት ማቆያ ገንብቼ ሕፃናቶች ላይ እየሠራሁ ነው። ከአንድ ዓመት ጀምሮ እስከ አራት ዓመት ዕድሜያቸው እኔ ጋር ሲቆዩ፤ ብሔራዊ መዝሙር ይዘምራሉ፤ ባንዲራ ይሰቅላሉ። ያቺ ትንሿ ጥረቴ ታድጋለች ብዬ አስባለሁ። እኔ በልጅነቴ የተሠራብኝ የሀገር ፍቅር አድጎብኛል። ስለዚህ መፍትሔው የሀገር ፍቅር ላይ መሥራት ነው ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ደረጃ የደረሰችው በትውልዱ የልጅነት ሕይወት ላይ በተገቢው መልኩ ባለመሠራቱ ነው ማለት ይቻላል?

ወ/ሮ አዜብ፡- አዎ! የሕፃናት ትምህርት ቤት ላይ ትኩረት ያደረግኩት ለዚህ ነው። ልጆች ስለሀገራቸው በጥሩ መንገድ ቢማሩ ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ትልቅ ሰው ላይ ተፅዕኖ መፍጠር ጥሩ አይመስለኝም። ራሱ ሲያድግ በልጅነቱ የተሠራበት ነገር ተመልሶ ይመጣል። ለምሳሌ እኔ ስለሀገር ፍቅር የተማርኩት አሜሪካን ውስጥ ገብቼ አይደለም። በልጅነቴ እናት እና አባቴ ስለ ሀገር ፍቅር ያስተማሩኝ በመሆኑ ነው።

ያ በልጅነቴ የተሠራብኝ ከውስጤ ሊወጣ አልቻለም። ነገር ግን የመጣው በተለያየ ሁኔታ ነው። ድሮ ወጣት ሳለሁ በአብዮታዊነት ስሜት መጥቷል። አሁን ደግሞ ብዙ ጓደኞቼን አጥቼ ስበስል ለውጥ የሚመጣው በሰላማዊ መንገድ ነው ብያለሁ። ምክንያቱም የጦርነት ለውጥ ለማንም አልበጀም። በቀዳማይ ኃይለስላሴ ጊዜም የተገደሉት ሚኒስትሮች እና በደርግ ጊዜም ያጣናቸው ብዙ ወጣቶች ሀገር መጥቀም የሚችሉ ነበሩ። ነገር ግን በጦርነት ሰው በመግደል ለውጥ እናመጣለን ብለን አጣናቸው።

ብዙ የተማሩ ሰዎች፤ በጊዜው ሀገር ጠል አድርገን ያሰብናቸው እነአክሊሉ ሀብተወልድ አሁን ስናውቃቸው፤ ለሀገራቸው የከፈሉትን ዋጋ ስንረዳ ባለፈው ድርጊታችን እንቆጫለን። ስለዚህ አሁንም ከመቸኮል ይልቅ ረጋ ብለን መንቀሳቀስ አለብን። በእርግጥ አውቄያለሁ ብሎ መምከር ይከብዳል። ነገር ግን አንድ በችግር ያደገ ሰውን ለምን እንደዚህ አላደረግክም ወይም ለምን እንደዚህ አታደርግም ማለት ይቸግራል። እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳልቸገር ኖሬያለሁ። ለሀገሬ የሆነ ነገር መስራት አለብኝ። ብዬ በምችለው አቅም እየሠራሁ ነው።

ነገር ግን ሰው ጦርነት ውስጥ እንዲገባ አልፈልግም። በእርግጥ አሁን እኔ አርጅቻለሁ፤ ጦር ይዤ ጫካ መግባት አልችልም። ስለዚህም ሕፃናት ሲያድጉ ስለጦርነት እንዳያስቡ የማያልቅ የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸው የአቅሜን አደርጋለሁ። አሁንም እናት እና አባቴ እኔ ላይ የሠሩትን እየሠራሁ ነው። በኋላ እየኮተኮትኳቸው ያሉ ልጆች እያደጉ ሲመጡ ሁሉንም ማመዛዘን ሲጀምሩ ስለሀገራቸው በጥልቀት ያስባሉ።

አዲስ ዘመን፡- ልጆች የሀገር ፍቅር እንዲኖራቸው ወላጆች በምን መልኩ መሥራት አለባቸው?

ወ/ሮ አዜብ፡- እኔ ስለአባቴ ብናገር አባቴ ለሁለት ዓመት የድሬዳዋ ገዢ ነበር። የድሬ ሰዎች በስሙ ድልድይ ሰይመውለታል። አልፍሬድ ሻፊ የተሰኘ ድልድይ በድሬዳዋ አለ። አባቴ ድሬዳዋ ሔዶ ሀገር ያቀናው ሀገሩን ስለሚወድ ነው። ቤተሰቦቼ በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባርም የሀገር ፍቅር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሲያሳዩን ነበር። እናቴም ሀገሯን የምትወደው ከልቧ ነበር። ምንም እንኳ ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ያ የተገነባው ፍቅር መልሶ መምጣቱ አይቀርም።

አባቴ ድሬዳዋ የሔደው የደቡብ ተወላጅ ጉራጌ ሆኖ ነው። ድሬዳዋ በነበረበት ጊዜ ለድሬዳዋ ሕዝብ ሙሉ ፍቅር ሰጥቷል። እኔም ከእዛ ብዙ ተምሬያለሁ። የሀገር ፍቅር ግን አንዳንዴ የሚወረስ ይመስለኛል። አሜሪካን ሀገር ሰባት እህት እና ወንድሞች አሉኝ። ሁኔታዎች ከኢትዮጵያ በእጅጉ የተለዩ ናቸው። እዛ ኑሪ ብባል አይመቸኝም። ምክንያቱም የሀገር ፍቅር ጉዳይ ከልጅነቴ ሰርፆብኛል።

የተማሪ ንቅናቄ ውስጥ መግባቴም ደግሞ ሀገሬን የበለጠ እንዳውቃት አድርጎኛል። ከዛ በኋላ ሁልጊዜ ሀገሬ የመግባት ፍላጎት ነበረኝ። ኢትዮጵያ ከገባሁ አሁን አሥራ አምስት ዓመት ሆነኝ። ኢትዮጵያ ይመቻል ማለት አይደለም። በተለይ አሜሪካ ሀገር ለኖረ ሰው ኢትዮጵያ ላትመቸው ትችላለች። እኔ ግን የትም ሀገር ብኖር እንደዚህ ሀገር አያስደስተኝም።

አዲስ ዘመን፡- በውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?

ወ/ሮ አዜብ፡- እንዲህ ያድርጉ ለማለት ይከብዳል። ነገር ግን ሁሉም ራሱን ይፈትሽ። ሀገር መውደድ እና ሀገርን ማገዝ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ ብቻ አይደለም። የትም ሆኖ ኢትዮጵያን አለመርሳት ይቻላል። ለምሳሌ እህት እና ወንድሞቼ እነርሱም ባሉበት እንዳልረሷት እርግጠኛ ነኝ። አሁን ልጆች ላይ እየሠራሁ ያለሁት እናት እና አባቴ ባቆዩልኝ ቤት ውስጥ ነው። ቤቱን እና ቦታውን ሀገሬን ለማገልገል እንድጠቀምበት ወንድም እና እህቶቼ መፍቀዳቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው። እህት እና ወንድሞች ሀገር ወዳድ ስለሆኑ ይህንን ፈቅደውልኛል።

አሜሪካን ሀገር ብዙ ቤተሰብ አለኝ። ሁሉም ኢትዮጵያ ገብተው መኖር እና ለኢትዮጵያ መሥራት ይፈልጋሉ። ነገር ግን የተሻለች ኢትዮጵያን እየጠበቁ ነው። እኔ ግን ኢትዮጵያን የተሻለች የምናደርጋት ራሳችን ነን ብዬ ሀገሬ ገብቼ እየሠራሁ ነው። አሁን በእኔ ይቀናሉ። በእርግጥ መብራት ይጠፋል፤ ውሃ ይቋረጣል፤ ሌባ ቤት ቢሰብር ፖሊስ የሚደርሰው ቆይቶ ነው። ነገር ግን ያም ቢሆን ሀገር ሀገር ናት።

አዲስ ዘመን፡- ስለሕፃናት ማቆያው የተወሰነ ነገር ይበሉን?

ወ/ሮ አዜብ፡- የሕፃናት ማቆያ ነው። አሁን 53 ልጆች አሉ። ሲጀመር በስምንት ልጆች ነበር። ከተቋቋመ 10 ዓመቱ ነው። በየዓመቱ እየተመረቁ ወደ ትምህርት ቤት ይገባሉ። እዚህ በመሆኔ ደስተኛ ነኝ። እየሰራሁ ያለሁት ትርፍ ገንዘብ ለማግኘት አይደለም። የምሰራው ለሀገሬ ሥጦታ ለማበርከት ነው።

አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ስለተጀመረው ሀገራዊ ምክክር ምን ይላሉ?

ወ/ሮ አዜብ፡– ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሌላ አማራጭ ከመግባት ይልቅ ምክክሩን መሞከር አለበት። ብዙ ሌሎች ነገሮችን ሞክረናል፤ ነገር ግን አልተሳካልንም። ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ መድረስ ያለባት ደረጃ ላይ መድረስ ነበረባት። እዛ ላይ መድረስ ያልቻለችው እኛ የሞከርናቸው መንገዶች ትክክለኛ ባለመሆናቸው ነው።

ዋነኛው ጉዳይ ኢትዮጵያ እንዳታድግ የሚፈልጉ የራሳቸው ዓላማ ያላቸው እንዳሉ እርግጠኛ ነኝ። አሜሪካም ቢሆን ኢትዮጵያን የምትፈልገው ከራሷ ጥቅም አንፃር ብቻ ነው። የምትፈልጋት ለእርሷ ጠቃሚ እስከሆነች ብቻ ነው። አሁን አለም ላይ ከባድ ችግር አለ። ምክክሩ ምናልባት ሀገራችን ላይ ብቻ ሳይሆን ዓለም ላይ ያለውንም ችግር እንድናውቀው ያስችለናል። ኢትዮጵያ እንዳታድግ ፣ እንድትከፋፈል የሚሠሩ ኃይሎችን ለይተን እንድናውቀው ያስችለናል።

አንዳንዴ የገዛ የሀገራችን ሰዎች በገንዘብ ተገዝተው መከፋፈል ላይ እንደሚሠሩ ማወቅ አለብን። ይህንን ስንል ኢትዮጵያን የመከፋፈል አጀንዳን ይዘው የሚንቀሳቀሱ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የሌሎች ሀገር ዜጎች መነሻቸው ኢትዮጵያውያንን ጠልተው ሳይሆን፤ የእነርሱ ሀብት በእኛ መውደቅ ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው። እኔ መጠቀም አለብኝ በሚል ነው።

እኛም እርስ በእርስ መጣላታችንን እስካላቆምን ድረስ፣ እርስ በእርስ እስካልተረዳዳን እስካልተደማመጥን ድረስ በሀገራችን ያለው ችግር መፍትሔ ያገኛል ብዬ አላምንም። እስከ አሁንም ያለነው በፈጣሪ እርዳታ ነው። ሃይማኖተኛ አይደለሁም። ነገር ግን እንደጠላቶቻችን ብዛት፣ እንደተሠራብን ሥራ እንፈርስ ነበር። በፈጣሪ እርዳታ እስከ አሁን ቆይተናል። ከዚህ በኋላ አብረን እንደ ሀገር አብረን ለመዝለቅ ሀገራዊ ምክክሩ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሀገራት ኢትዮጵያን ለምን በጠላትነት ማየት አስፈለጋቸው ?

ወ/ሮ አዜብ፡– ኢትዮጵያ በብዙ መልኩ ታሰጋቸዋለች። ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ጥሩ ምሳሌ በመሆኗ ቅኝ ገዢዎች በጠላትነት ያዩዋታል። ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ምሳሌ የምትሆንበት ሁኔታ በመኖሩ፤ ጥሩ ምሳሌ እንዳትሆን መፍረስ ይኖርባታል የሚል ፍላጎት አላቸው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ካደገች ልክ ቅኝ ገዢነታቸው እንደተመናመነው ሁሉ፤ አፍሪካን እንደፈለጉ የሚዘርፉበት ዕድልም ይመናመናል። ሀገሪቱ ማደግ ያልቻለችው በዚህ ምክንያት ነው። ምንም እንኳ በየዘመኑ መንግሥታትን ብንቃወምም፤ መንግሥታቱም የሚችሉትን ሲሞክሩ ነበር።

የኢትዮጵያ ማደግ ሌሎችንም ስለሚያነቃ እና እንዲያድጉ ስለሚያደርግ እንድታድግ አልተፈለገም። ያንን የውጪ ጠላቶችን ሴራ እስከምንረዳ እና እርስ በእርስ መጣላታችንን እስካላቆምን ድረስ ሀገራችን ማደግ አትችልም። ኢትዮጵያ እንዳታድግ ይልቁኑም እንድትፈርስ በውጪ ጠላቶች ስትራቴጂ ተነድፎ በየጊዜው ይሠራባታል። ይህንን ማወቅ አለብን። ትልቁ የውድቀታችን መንስኤ የውጪ ጠላት የሚሠረው ሥራ ነው። ይህንን በቅጡ እስካልተረዳን ድረስ ሀገራችንን አንድ አድርጎ ማስቀጠል እና ማሳደግ አንችልም።

ልብ ብለን ከተመለከትን ኢትዮጵያን የሚል ኃይል በውጪ ጠላት ሴራ እንዲከፋፈል ይደረጋል። እኔ የተማሪ ንቅናቄ ውስጥ ሆኜ ሲጀመር ንቅናቄው አንድ ቢሆንም፤ በኋላ ግን ለሁለት ተከፍሏል። በየቦታው ኢትዮጵያውያንን እየከፋፈሉ አንድ እንዳንሆን የሚሠሩበት ሁኔታ አለ። ይህንን ካልተረዳን የውጪ ጠላት እየተጫወተብን ይኖራል። ለምሳሌ በትግራይ ጦርነት የነበረ ጊዜ የጠላቶቻችን መገናኛ ብዙኃኖች በምን መልኩ እንደሚዘግቡ ስንታዘብ ነበር። ቢቢሲ፣ ሲ ኤን ኤን እና አልጀዚራ እንዴት ሲዘግቡ እንደነበር አይተናል። ኢትዮጵያ እንድትበተን እንዳትጠነክር ፍላጎት ስለነበራቸው የሚዘግቡት በዛው መልኩ ነበር። አሁንም ቢሆን ውስጥ ውስጡን እየቦረቦሩን መሆኑን ማወቅ አለብን። ነገር ግን ተስፋ እንደማደርገው ያቋስሉን ይሆናል እንጂ አያፈርሱንም።

አዲስ ዘመን፡- የሀገራዊ ምክክርን በተመለከተ ምን ይላሉ?

ወ/ሮ አዜብ፡- መዳን ያለባቸው ብዙ ቁስሎች መኖራቸውን አውቀን፤ እነዚህ በእኛ ብቻ ሳይሆን በውጪ ጠላቶች የተተከሉት ቁስሎች እንዲነቀሉ ሁሉንም ሀገራዊ ምክክር ላይ ለማሳተፍ ጥረት መድረግ አለበት። ለዘመናት እንድንለያይ ሲሰራብን ኖረናል። እኔ ቀዳማይ ኃይለስላሴ ይውረዱ ብዬ ሰልፍ መውጣቴ ትክክል ይመስለኝ ነበር። የኢትዮጵያ የውጪ ጠላቶች እየሠሩ መሆኑን በሰዓቱ አልገባኝም ነበር። ሀገሬን ወደ ኋላ ያስቀረው የራሴ መንግሥት ነው ብዬ ተቃወምኩ። አሁን ግን ካረጀሁ በኋላ ተረዳሁት።

እነርሱ የተፈጥሮ ሀብታቸውን ጨርሰውታል። አልበቃ ብሏቸው ጨረቃ ላይ እየወጡ ያሉት ሀብት ፍለጋ ነው። አፍሪካን መቦርቦር የእነርሱ የመኖር ዋስትና ነው። ይህንን መረዳት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከ60 ዓመታት በላይ የሰሩትም አፍሪካን የመዝረፍ ጉዟቸው እንዳይደናቀፍ ነው። ያጣሉን፣ አሁንም እያጣሉን ያሉ እና ወደ ፊትም ለማጣላት ጥረት የሚያደርጉ መኖራቸውን እስካልተገነዘብን ድረስ ሀገር ማደግ አትችልም። ሀገራዊ ምክክሩ እስከአሁን ሲያጣሉን የቆዩ እና አሁንም እያጣሉን ያሉ መኖራቸውን እንድንረዳ ያግዘናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

በሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ጥቅም በማግኘታቸው ሀገራቸውን ለጠላት አሳልፈው የሚሰጡ አሉ። ምክክሩ እነዚህ ምን እየሠሩ መሆኑን ለማወቅ ያግዘናል የሚል እምነት አለኝ። አሁን በዓለም ላይ ያለው የሀብት ሽሚያ ከፍተኛ ነው። ሀብታም ሀገሮች ከምን ጊዜውም በላይ የእኛ ሀብት ያስፈልጋቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- ሀገራዊ ምክክር ላይ በሚካሔዱ ስብሰባዎች ተሳትፈው ነበር። ጅምሩን እንዴት አዩት ?

ወ/ሮ አዜብ፡- ቀዳማይ ኃይለስላሴ ‹‹መጀመር እናውቃለን፤ ችግራችን መጨረስ ነው። ›› ብለው ነበር። ጅምሩ በጣም ጥሩ ነው። በጣም ተደስቻለሁ። ነገር ግን አንድ የውጪ ጠላት ገብቶ ከበጣጠሰን እንወድቃለን። ስጋቴ ይሔ ነው። ሌላው ግን ምክክሩ ላይ የሚሳተፉ ሰዎች ፍላጎት ያላቸው ቢሆኑ መልካም ነው። ቀስ ብሎ መሠረቱ የጠነከረ ነገር ወደ ላይ ሲወጣ ያድጋል እንጂ አይፈርስም።

ሀገራዊ ምክክሩ ላይ መሠራት ያለበት ሥር መሠረቱን በማጥበቅ ነው። ይሔ ውስጣዊ ስሜትን ይጠይቃል። ምን አገኛለሁ ብሎ የሚመጣ እና ምን ላድርግ ብሎ የሚመጣ ይለያያል። ዋናው ጉዳይ ፈጣሪ የኢትዮጵያ ዘመን ያድርግልን።

አዲስ ዘመን፡- አሜን፤ ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ።

ወ/ሮ አዜብ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘም ህዳር 22/2016

Recommended For You