ኤች አይ ቪን የመከላከል ሥራ ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን ይገባል

– በዓመት ከ11 ሺህ በላይ ዜጎች በኤች አይ ቪ ቫይረስ ሕይወታቸውን ያጣሉ

አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ የኤች አይ ቪ (ኤድስ) ቫይረስን የመከላከል ሥራ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ በዓመት 11 ሺህ 322 ዜጎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ተጠቁሟል፡፡

የዓለም ኤድስ ቀን «የማኅበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች አይ ቪ መከላከል» በሚል መሪ ሃሳብ ለ35ኛ ጊዜ ትናንት ተከብሯል፡፡ በወቅቱ የጤና ሚኒስትር ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር ፤ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የመከላከል ሥራውን ከፍተኛ አጀንዳ ሊያደርጉት ይገባል፡፡

በሀገሪቱ የቫይረሱን የስርጭት መጠን በቫይረሱ ተጋላጭ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ሊጨምር እንደሚችል ጠቁመው፤ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም፣ የሲቪክ ማኅበራትንና የሌሎች ባለድርሻ አካላትን አቅም በመጠቀም ኤች አይ ቪን የመከላከል ሥራው ላይ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ610 ሺህ 350 በላይ ዜጎች ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ሊያ፤ በቂ የመድኃኒት አቅርቦትና ሕክምና ባለማግኘት በዓመት 11 ሺህ 322 ዜጎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን እንደሚያጡ አስታውቀዋል፡፡

ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ ያለባቸው ዜጎች በቂ ሕክምና እንዲያገኙና እራሳቸውን የማያውቁ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ምርመራ በማድረግ ጤንነታቸውን እንዲጠብቁ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አመልክተዋል።

ኤች አይ ቪ በደማቸው የሚገኝባቸው ዜጎች ሕክምና እንዲያገኙ እንዲሁም ሕክምና ከጀመሩት መካከል ደግሞ የቫይረሱ መጠን ዝቅ እንዲል የማድረግ ሥራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል።

በየደረጃው በሚገኙ አስተዳደሮች ኤች አይ ቪ/ኤድስ መከላከል የሚችል የሥራ አመራር ቦርድ በሚፈለገው ደረጃ አለመቋቋምና ሥራ ላይ አለመሆን፣ የኤችአይቪ ስርጭት ባለባቸው አካባቢዎች የሚሰጠው ምላሽ በቂ አለመሆን እንዲሁም ቫይረሱ በደማቸው ካለ እናቶች ለሚወለዱ ሕፃናት የሚደረገው ክትትል አናሳ መሆን፣ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ተግዳሮት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ጄ ማሲንጋ በበኩላቸው፤ የአሜሪካ ሕዝብና መንግሥት ኤች አይ ቪ/ ኤድስን ለመከላከል በኢትዮጵያ በተለያዩ ዓመታት ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ መደረጉን አውስተው፤ በቀጣይም አሜሪካ የምታደርገው ድጋፍ እንደሚጠናከርና ኅብረተሰቡ የሚያደርገው የመከላከል ሥራ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመድረኩ በጤና ዘርፉ የሚሠሩ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች፣ አምባሳደሮች፣ የተለያዩ የክልልና የከተማ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሄለን ወንድምነው

አዲስ ዘመን ኅዳር 22 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You