‹‹ለብሔራዊ ቡድን የሚሆኑ አጥቂዎች ማግኘት ከባድ ነው››አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ

ለ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አንድ የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎቹን ከሳምንት በፊት አከናውኖ በአንድ ነጥብ መመለሱ ይታወቃል። የመጀመሪያውን ጨዋታ ከሴራሊዮን አድርጎ ካለምንም ግብ የተለያየው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው ማጣሪያ በቡርኪናፋሶ 3ለ0 ተሸንፏል።

የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም ባለመኖሩ ሁለቱንም የሜዳው ላይ ጨዋታዎች በገለልተኛ ሜዳ ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድም ግብ ሳያስቆጥር ቀርቷል። ከማጣሪያ ጨዋታዎቹ ጥቂት ቀናት በፊት የዋልያዎቹ አዲስ አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት ገብረመድህን ኃይሌ በአጭር ጊዜ ዝግጅት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጅማሬያቸው ተስፋ የሚሰጥ አልነበረም። ከሁለቱ ጨዋታዎች መልስ አሠልጣኙ የሚሰጡት ማብራሪያ ሲጠበቅ የነበረ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ መግለጫውን ሰጥተዋል።

አሠልጣኙ በመግለጫቸው ‹‹በሀገራችን ለብሔራዊ ቡድን የሚሆኑ የአጥቂ ተጫዋቾች ለማግኘት ከባድ ነው።›› በማለት ዋልያዎቹ በሁለቱ ጨዋታዎች አንድም ግብ ሳያስቆጥሩ የተመለሱበትን ምክንያት ተናግረዋል። ይህንን በዝርዝር ሲያብራሩም “ብዙዎቻችሁ የምታውቁት ይመስለኛል አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ብዙ 9 ቁጥሮች አሉ ለማለት እኔ ለእራሴ የማያስደፍረኝ ነው። ግን ያሉትን 9 ቁጥሮች ወደፊት ወስደን ማየት ይጠበቅብናል። ሌላ አማራጭ መውሰድ እንደሚጠበቅብኝ አስባለሁ። እዛ ቦታ ላይ ሌላ ሰው ማለማመድ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ያላቸው ቴክኒካል ብቃት ፣ የአጨራረስ አቅማቸው እና የቴክኒክ አረዳዳቸው በየክለቡ ያሉትን 9 ቁጥሮች ስናያቸው ለብሔራዊ ቡድን በጣም አስቸጋሪ ነው። እንደ ሀሳብ የያዝነው እንደ ቡድን ተንቀሳቅሰን ሌላ 9 ቁጥር መፍጠር ካልሆነ እንደዚህ ዓይነት ኳሊቲዎች እየጠፉ ነው ወደፊት የሁላችንም ጥረት ይጠበቃል።” ብለዋል።

‹‹ቡርኪናፋሶ እኛን በ90 ደረጃዎች ይበልጡናል›› ያሉት አሠልጣኝ ገብረመድህን ቢያንስ ቢያንስ ከሁለቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች ቡድናቸው ቢያንስ 4 ነጥብ ማግኘት ይገባው እንደነበር ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ በመልሶ ማጥቃት የተሻለ ነገር ለማድረግ እንደቡድን መክረን እንደነበር በማስታወስ አጨራረስ ላይ ደካማ መሆናቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው አስረድተዋል። “እኛ ለመከላከል አልገባንም፤ ያለውን ደረጃችንን እናውቀዋለን። ዝግጅታችን እነርሱ በግል ብዙ ነገር ቢኖራቸውም እኛ እንደ ቡድን ተንቀሳቅሰን አንድ ነገር መሥራት እንችላለን የሚል ነበር። አቀራረባችንም ለማሸነፍ ነበር። በዛ መንገድ ነበር የሄድነው ነገር ግን በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሦስት ግቦች ተቆጠሩብን። ይህም የሆነው በግል በተፈጠሩ ቀላል ስህተቶች ነው እንጂ እንደ ቡድን ብልጫ ወስደውብን አልነበረም። በግል የሚፈጠሩ ስህተቶችን ደግሞ ለማረም አይቸግርም እንደ ቡድን ተበልጠን ሳንደራጅ ቀርተን ብንሸነፍ ምናልባት ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል። ይሄ ግን በዛ መልኩ አልነበረም።” ብለዋል፡፡

ተጫዋቾቻቸው የስነልቦና ጫና እንደነበረባቸው የገለፁት አሠልጣኝ ገብረመድህን ይህንን ችግር በፍጥነት መቅረፍ ከባድ እንደሚሆን ተናግረዋል።

አሰልጣኙ በመጀመሪያው ጨዋታ በወቅቱ የነበረው አየር ንብረት በጣም ተለዋዋጭ እንደነበር አስታውሰዋል። በዚህም ጨዋታውን ለማቋረጥ ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ጠቁመው ፊፋ ጨዋታው እንዲቋረጥ እንዳልፈለገ አብራርተዋል።

አሰልጣኙ ወደ ፊት ቡድኑን ለማጠናከር ከ23 ዓመት በታች ያሉ ተጫዋቾችን መልምሎ እንደ ‘ሻዶ ቲም’ የማዘጋጀት ሀሳብ እንዳላቸው የጠቆሙ ሲሆን፣ የአሠልጣኝ ቡድን አባላትን ቁጥር የመጨመር ሃሳብ እንዳላቸውም አንስተዋል፡፡

“ጠባብ እንደሆነ እናውቃለን። የጊዜ ማነስ ፣ ችኮላ እና ያልተስተካከሉ ነገሮች ነበሩ። ወደፊት የአሠልጣኝ ቡድን አባላትን ሰፋ ለማድረግ እንሠራለን ጊዜ ስለሚኖረን። አንድ ለውጥ ለማምጣት የግድ ብዙ ነገሮችን ማየት አለብን፣ በተለይ የትውልዱ አንድ ቦታ ላይ የመቆም ነገር ይታያል እና ወጣቶችን የምናመጣበት መንገድም አንድ ነገር ነው። ለፌዴሬሽናችን በፕላን ደረጃ የማቀርበው ነገር ይኖራል። ከ23 ዓመት በታች ያሉ ተጫዋቾችን መልምሎ የተወሰነ እንደ ሻዶ ቲም የማዘጋጀት ሀሳብ አለኝ። የፕሪሚየር ሊጉ ወድድር አንድ ቦታ ላይ ስለሚደረግ እነዚህን በየክለቡ የሚመረጡ ልጆች በሳምንት አንዴ እያገኙ ለማብቃት ሰብስበን በተደጋጋሚ እያሠራን ብሔራዊ ቡድኑን የመተካት ሥራ ያስፈልገናል።” በማለት ገልፀዋል፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 20 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You