በኢትዮጵያ ዋንጫ ሶስተኛውን ዙር የተቀላቀሉ ክለቦች ተለይተዋል

ከሶስት ዓመታት መቋረጥ በኋላ ሂደቱን በመቀየር ወደ ውድድር የተመለሰው የኢትዮጵያ ዋንጫ ወደ ሶስተኛው ዙር ያለፉ ክለቦች ተለይተው ታውቀዋል፡፡ በሁለተኛው ዙር 32 ክለቦችን እርስ በእርስ በማፋለም ቀጣዩን ዙር የተቀላቀሉ 16 ቡድኖችን በመለየት የቀጣይ መረሃ ግብሮች ይፋ ተደርገዋል፡፡

በታሪካዊው የኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች ላለፉት ሶስት ቀናት ማለትም ቅዳሜ፣ እሁድ እና ሰኞ የተካሄዱ ሲሆን፤ በዚህም ወደ ሶስተኛ ዙር ያለፉ ክለቦች ተለይተዋል፡፡ ጨዋታዎቹ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ፣ በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳና በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም በማካሄድ ቀጣዩን ዙር የተቀላቀሉት ክለቦች ታውቀዋል፡፡ ዘንድሮ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕሪምየር ሊጉን ክለቦችና የታችኛውን እርከን ክለቦች በአንድ በማፋለም ላይ የሚገኘው ውድድሩ ጠንካራና ያልተጠበቁ ውጤቶችንም በማስመልከት ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካካል ለረጅም ዓመታት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲወዳደር የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ተሸንፎ ከውድድር መውጣቱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተጨማሪም እርስ በርስ የተገናኙት የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ከወዲሁ ከውድድሩ አንዲወጡ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡

በዚህም በመጀመሪያ ቀን በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያ መድን፣ ኮልፌ ቀራኒዮ እና ደብረ ብርሃን ከተማ ሶስተኛውን ዙር የተቀላቀሉ ክለቦች ሆነዋል፡፡ ኢትዮጵያ መድን ድሬደዋ ከተማን በመግጠም በጠባብ ውጤት አሸንፎ ቀጣዩን ዙር የተቀላቀለ ሲሆን፤ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ኢትዮ ኤሌክትሪክን አስተናግዶ 1ለ0 በማሸነፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል፡፡ ደብረብርሃን ከተማ ከጋሞ ጨንቻ ያደረጉት ጨዋታ መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ግብ ተጠናቆ በመለያ ምት ደብረብርሃን ከተማን 5ለ4 አሸንፎ እሱም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀል ችሏል፡፡

በተመሳሳይ ቀን በተካሄዱ ሌሎች ጨዋታዎች ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉ ክለቦች የተለዩ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ወደ ቀጣይ ዙር ገብተዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አዳጊውን ሀምበሪቾ ዱራሜን ገጥሞ 2ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ አጼዎቹ በበኩላቸው ነቀምቴ ከተማን አስተናግደው 3ለ0 በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር ሲቀላቀሉ፣ ወላይታ ድቻ ደሴ ከተማን 3ለ1 በሆነ ውጤት በመርታት ማለፉን አረጋግጧል፡፡

እሁድ ዕለት ሌሎች ቀጣዩን ዙር የተቀላቀሉ ክለቦች የተለዩባቸው ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን በነዚህም የተለያዩ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ሁለቱን የሊጉን ክለቦች ያፋለመው የመቻል እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ በመቻል 2 ለምንም አሸናፊነት

 ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡ ኦሮሚያ ፖሊስን ከ አርባ ምንጭ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ ደግሞ በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1ለ1 ተጠናቆ በመለያ ምቶች አዞዎቹ 10 ለ9 አሸንፈው ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል፡፡ ሻሸመኔ ከተማ ከከፋ ቡና ያደረጉት ጨዋታ በመለያ ምት በሻሸመኔ ከተማ 5ለ4 አሸናፊነት ተጠናቆ ሻሸመኔ ቀጣዩን ዙር ተቀላቅሏል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ወልዲያ ከተማን 4ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ቀጣዩን ዙር የተቀላቀለ ሌላኛው ክለብ ሲሆን ባህርዳር ከተማ እንደ አዲስ የተመሰረተውን ሸገር ከተማን ገጥሞ 1ለ0 በማሸነፍ ወደ ቀጣይ ዙር አልፏል፡፡ አዳማ ከተማ ሲዳማ ቡናን ገጥሞ በአስገራሚ ሁኔታ 4ለ0 በሆነ ውጤት ረቶ ማለፍ ችሏል፡፡ ከትላንት በስቲያ በተካሄዱ የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ነገሌ አርሲ ስልጤ ወራቤን፣ ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን፣ ሀዋሳ ከተማ ቤንች ማጂ ቡናን እና ቢሾፍቱ ከተማ ሀላባ ከተማን በማሸነፍ ቀጣዩን ዙር የተቀላቀሉ ክለቦች መሆን ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሶስተኛው ዙር የሚገናኙትን ክለቦች ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ጨዋታዎቹ ከታህሳስ 12-14 ባለው ጊዜ ወደ ፊት በሚገለጽ ቦታ፣ ቀንና ሰዓት እንደሚካሄዱ ገልጿል፡፡ በዚህም መሰረት 16 ክለቦች ሩብ ፍጻሜውን ለመቀላቀል ጠንከር ያለ ፉክክርን እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል፡፡ ይፋ በሆነው መረሃ ግብር መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሻሸመኔ ከተማ፣ ሀዲያ ሆሳዕና ከወላይታ ድቻ፣ ቢሾፍቱ ከተማ ከአዳማ ከተማ፣ ነገሌ አርሲ ከኢትዮጵያ መድን፣ ባህርዳር ከተማ ከአርባ ምንጭ ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ ከ መቻል፣ ደብረብርሃን ከተማ ከፋሲል ከነማ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ይጫወታሉ፡፡

አለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን   ኅዳር 19 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You