ረመዳን በእስልምና ሐይማኖት የዘመን አቆጣጠር በዘጠነኛው ወር ላይ የሚደረግ የፆም ስነ- ስርዓት ሲሆን፤ ረመዳን ወር የእዝነት፣ የርህራሄ፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የመፈቃቀር፣ የተቸገሩትን የሚረዳበት፣ ያለውን አካፍሎ የሚበላበት የሚጠጣበት፣ የአንድነት ወር ነው። በመሆኑም በዚህ ወር ሙስሊሙ ማህበረሰብ ከመጥፎ ንግግር አፉን የሚቆጥብበት፤ እጁን የሚሰበስብበት እንዲሁም እጅጉን የፈጣሪን ቸርነት በጾም በጸሎት የሚማጸንበትም ነው። በተጨማሪም ሙስሊሙ ማህበረሰብ በዚህ ወቅት ለህዝብ አንድነትና ለአገር ሰላም አብዝቶ ጸሎት በማድረግና በመስገድ የሚያሳልፍበት ወር ነው።
አብሮ መብላት፣ መጠጣት፣ መገባበዝ፣ ስጦታ መሰጣጠት፣ ያለውን ማካፈል፣ በጋራ መጸለይ፣ በጋራ መመገብ፣ ወ.ዘ.ተ….. የረመዳን መገለጫ መሆኑ ጋር ተያይዞ፤ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለበዓሉ የሚያስፈልገውን ዕቃ በአንድ ቦታ እንዲያገኝ፤ ለእህት ወንደሙ የተለያየ የስጣታ ዕቃ በመግዛት ማበርከት እንዲችል እና ከሌሎች እምነት ተከታይ እህት ወንድሙ ጋር ተገናኝቶ በጋራ እንዲሸምት ታሳቢ በማድረግ በመዲናዋ ከግንቦት 15 እስከ 27 ድረስየዒድ ኤክስፖ እተካሄደ ይገኛል።
ኤክስፖው የሙስሊሙን ማህበረሰቡ እምነትና ባህሉን ያከበረ ሲሆን፤ ገና ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከል ስንዘልቅ የሰማነው መንዙማ ልዩ ድባብ የሚፈጥር ነው። ሙስሊሙ ማህበረሰብ ሶላት ሲያደርስ የሌላው እምነት ተከታይ የወንድሙን ዕቃ በመሸጥና በመጠበቅ ይተባበራል። የማፍጠሪያ ስዓት ሲደርስ ሙስሊሙ፣ ክርስቲያኑ እንዲሁም የውጭ ዜጋው በአንድ ላይ እየተጎራረሰ ሲበላ ሲታይ ኤክስፖው በትንሿ ኢትዮጵያን ይመሰላል።
እኛም ወደ ውስጥ ዘልቀን በመግባት በየዓመቱ የዒድ ኤክስፖን የሚያዘጋጀውን የሐላል ፕሮሞሽን ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አክረም ኢብራሂምን ስለዒድ ኤክስፖ አነጋግረናቸዋል። አቶ አክረም እንዳብራሩት፤ ኤክስፖው ለረመዳን በዓል ዋዜማ ተብሎ የተዘጋጀ ቢሆንም ከእምነቱ ተከታይ ማህበረሰብ ባሻገር ለመላው ህዝብ የተለያየ ፋይዳ አለው ብለዋል።
ኤክስፖው በአንድ ማዕከል የተለያዩ ግብአቶችን አሰባስቦ የያዘ በመሆኑ፤ ሸማቹ ሳይወጣናሳይወርድ፤ ለተለያዩ ወጪ ሳይጋለጥ ጊዜውን ቆጥቦ የሚፈልገውን ዕቃ እንዲያገኝ ያደርገዋል። አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ በዓልን ተመርኩዞ በሁሉም ምርቶች ላይ የተወሰነ የዋጋ ቅናሽ በማድረግ ብዙ ከመሸጥ ትርፍ የሚያገኝበት ነው ብለዋል።
አብዛኛውን ምርት በማቅረብ ከፍተኛውን ቦታ የያዙት የሁሉም እምነት ተከታይ የሆኑ የአገር ውስጥ ነጋዴዎች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አክረም፤ በተጨማሪም ከህንድ፣ ከቱርክ፣ ከፊሊፒንስ፣ ከቻይና፣ ከሶሪያ እና ከግብጽ የመጡ ነጋዴዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። ነጋዴዎቹም የተለያዩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና ተሻሽለው የቀረቡ ምርቶችን ይዘው እንደቀረቡ ጠቁመዋል። እንዲሁም የባህል ትስስርን የሚፈጥሩ የተለያዩ አገሮች የባህል አልባሳት እና ለሙስሊሙ ማህበረሰብ በዓሉን በድምቀት ለማክበር የሚያግዙ የተለያዩ ምርቶችን ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
በ8ኛው የዒድ ኤክስፖ ላይ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ከህንድ አገር ባቀረቡ ባለሀብት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላት የተለያዩ የቴክኖሎጂ ምርቶችን ስትሸጥ ያገኘናት ወይዘሪት ውዴ ገመቹ በበኩሏ፤ ለአስራአምስት ቀን በቀን ሁለት መቶ ብር እየተከፈላት እንደምትሥራ ጠቁማ፤ በየዓመቱ ይህ ፕሮግራም የሚካሄድ በመሆኑ በየዓመቱ የሥራ ዕድል ፈጥሮልኛል ብላለች። ከህንድ አገር የመጡት ባለሀብቶች በኤክስፖው ላይ በየዓመቱ የተለያዩ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑ ዕቃዎችን ይዘው እንደሚቀርቡ ገልጻ፤ አሁን ኃይልና ጉልበት ቆጣቢ የቤት ውስጥ መገልገያ ማሽኖችን ማቅረባቸውን ገልጻለች።
ወይዘሮ ሳምራዊት ፈንታው የክርስትና እምነት ተከታይ ቢሆኑም ከእስልምና እምነት ተከታይ ጎረቤቶቻቸው ጋር በመሆን የተለያዩ ዕቃዎችን ለመግዛት በኤክስፖው ተገኝተዋል። እርሳቸውም እንደገለጹት በሌላ ገበያ ላይ በውድ ዋጋ የሚጠራን ዕቃ በአነስተኛ ዋጋ ገዝተዋል።
”የተለያዩ የልጆች አልባሳትን ለገበያ አቅርቢያለሁ” የሚሉት ወይዘሮ ብርሃን ገብረእግዚአብሔር፤ በዓላትን አስመልከቶ በኤግዚቢሽን ማዕከሉ በሚዘጋጁ ባዛሮች ላይ ሁሌም እንደሚሳተፉ ገልጸዋል። በእንደዚህ ዓይነት ኤግዚቢሽን ላይ መሳተፍ ለህብረተሰቡ ምርትን ለማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።
በስምንተኛው ዒድ ኤክስፖ ላይ የተለያዩ የቤት ማስዋቢያ ቁሳቁሶችን ለማህበረሰቡ በማቅረብ ያገኝናቸው ሙሀመድ መኪን በበኩላቸው፤ የተለያዩ የቤት ማስዋቢያ አበባዎችን፣ ምንጣፎችን፣ ጨሌዎችን እየሸጡ እንደሆን ጠቁመው፤ በብዛት በመሸጥ ትርፍ ማግኝታቸውን ገልጸዋል። እንዲሁም ሸማቹ በአስተያየት ዋጋ ምርቶቹን ከመግዛቱ ባሻገር የተለያየ የእምነት ተከታይ በአንድነት በአንድ ማዕከል ተገናኝቶ ምርቱን ሲሸጥና ሲገዛ አንድ ነቱን የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
ሶሎሞን በየነ