ኢትዮጵያ ታሪክና ትውስታዋን ጥላ ያላለፈችባቸው አቀበትና ቁልቁለቶች የሉም። እኚህ ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪክና ትውስታዎች የአዲስ ዘመንም ናቸው፡፡ ዛሬ “አዲስ ዘመን ድሮ” እያለ የድሮውን ሀገርና ሕዝባችንን ያስታውሰናል። በመዲናችን አዲስ አበባ የመንግሥት ገንዘብ በነፃ ልስጣችሁ እያለ የመረጠውን ሰው ወደ ሕንፃዎቹ ይዞ የሚገባው ግለሰብ ለ11ኛ ጊዜ ችሎት ቆሟል። ብልጧ ውሻ 4 ኪሎ ሜትሮችን አቋርጣ የጌታዋን በጎች አርደው የበሉትን ሰዎች ባለቤቱን እየመራች ወስዳ እጅ ከፍንጅ አሲዛቸዋለች። ብላቴን ጌታ ወልደ ኅሩይ ሥላሴ ኢትዮጵያ በፋሽስት በተወረረችበት ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት አቤቱታዋን ባለመሰማቱ ተበሳጭተው እራሳቸውን አጠፉ፤የሚል ነገርም አለ፤ እውነት ይሆን? የጳውሎስ ኞኞ ደብዳቤዎች እንደተለመደው ይጠብቁናል።
ገንዘብ ልስጣችሁ እያለ የሚገፋፋው ተያዘ ተባለ
“እኔ የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ። መንግሥት ለድሆች ገንዘብ በነፃ ለሚሰጥበት ክፍል ዋና ጸሀፊ ነኝ” በማለት ከዚህ በፊት አሥር ጊዜ በማታለል ወንጀል ተከሶ የነበረው ዘውዱ አንዱዓለም ለ11ኛ ጊዜ ተይዟል።
ተከሳሹ ከአዲስ አበባ ከተማ በተለይም ከምድር ባቡር፤ ከአውቶቡስ መቆሚያና ከልዩ ልዩ የገጠር ሕዝብ መገኛ ሥፍራ እየተዘዋወረ ባላገሮችን “ገንዘብ በነፃ የሚሰጥበት መሥሪያ ቤት አለ” በማለት ከአንዱ ሕንፃ በራፍ ቆሞ ባላገሮችን የሚያታልል መሆኑ በፖሊስ ተደርሶበታል።
ዘውዱ የገጠር ባላገሮችን የሚያታልለው አለባበሱን አሳምሮ ከአንድ ከፍተኛ ሕንፃ በራፍ በመቆም “ይኸ የእኔ መሥሪያ ቤት ነው” በማለት ፎቅ ቤት ለሰዎቹ አሳይቶ “ገንዘብ ለመውሰድ የሚፈቀድለት ከኪሱ ምንም ገንዘብ የሌለውና ራቁቱን የሆነ ብቻ ነው” በማለት ባላገሮቹን ከኪሳቸው በርብሮ ገንዘብ ወስዶ፤ ልብሳቸውን አስወልቆ አስቀምጥላችኋለሁ፤ በማለት በስተጀርባ በር በኩል የሚጠፋ መሆኑን ባለፈው ክስ ተረጋግጧል።
ተከሳሹ በአሁኑ ለ11ኛ ጊዜ የቀረበበት ክስ፤ ከሐረር ጠቅላይ ግዛት የመጡትን አቶ ተገኔ የተባሉትን ሰው ከባቡር ጣቢያ፤ ከባቡር ሲወርዱ ጠብቆ “ገንዘብ ከመንግሥት አሰጥዎታለሁ” በማለት ከአንድ ከፍተኛ ሕንፃ በራፍ ላይ ወስዶ ቢሮዬ ነው በማለት ልብሳቸውን አስወልቆ ከኪሳቸው 14 ብር ወስዶ በቁምጣ ሱሪ ብቻ ጥሏቸው ሔደ።
….,,,….
(አዲስ ዘመን ጥር 20 ቀን 1965ዓ.ም)
ውሻዋ የጌታዋን በጎች ሰርቀው ያረዱትን ሌቦች አስያዘች
አቶ መኮንን ደሞሴ የተባሉ አዛውንት ያሳደጓት አንዲት ውሻ፤ የጌታዋን ሁለት በጎች በሌሊት ሰርቀው ወስደው ያረዱትን ሌቦች መርታ አሳይታ የበጎቹ ቆዳና ትርፍራፊ ሥጋ ከጭንቅላታቸው ተያዘ።
ብልጧ ውሻ በጎቹ ተሰርቀው ከተወሰዱ በኋላ ከታረዱበት ሥፍራ አጥር ዘልላ ገብታ ለምልክት የበግ አንጀት ይዛ ከባለቤቱ ፊት ቀረበች። ባለቤቱም በጎቹን ፈልገው ሰልችቷቸው ከቤታቸው ተቀምጠው ነበር።
አቶ መኮንን የውሻቸውን ፈለግ በመከተል ከአንድ አጥር ግቢ ደርሰው ለመግባት ስጋት ስላደረባቸው ከአጥር ውጪ ቆሙ። ብልጧ ውሻ ለሁለተኛ ጊዜ በአጥር ሾልካ ገብታ ሌላ የበግ ሳንባ ይዛ መጥታ ለጌታዋ አሳየች። የበጎቹ ባለቤትም 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ሔደው በማመልከት ግቢው ሲፈተሽ ተሰርቀው የታረዱት በጎች ጭንቅላታቸውና ቆዳቸው ተገኝቷል።
…….
በውሻዋ ጠቋሚነት ከተያዙት ሰዎች ቤት ከሌሎች ሰዎች የተሰረቁ 7 ኩንታል ጤፍና ግምቱ 5 መቶ ብር የሆነ ንብረት ተገኝቷል። ውሻዋ መርታ ያሳየችበት ሥፍራ ከጌታዋ መኖሪያ ቤት 4 ኪሎ ሜትር ይርቃል። ቦታውም አዲስ አበባ አማኑኤል ቤተ ክርስቲያን አጠገብ መሆኑ ታውቋል።
(አዲስ ዘመን ህዳር 4 ቀን 1965ዓ.ም)
ጨዋ ተመልካች
“ከበሮ በሰው እጅ ያምር ሲይዙት ያደናግር” የሚል የአበው አነጋገር አለ። ይህን ያልኩት ከሜዳ ገብተው ቢታዩ የኳስ አቋቋም የማይችሉ ሁሉ ብሔራዊ ተጫወቾቻችን ኢንተርናሽናል የእግር ኳስ ግጥሚያ ባደረጉ ቁጥር ጥላ ቢስ ነቀፋቸው የብዙዎቹን ጨዋ ተምልካች ጆሮ ስላሰለቸ ነው።
…..
ተጫዋቾቹን እየጠሩ መዝለፍና እግሌ ይግባ፤እግሌ ይውጣ ማለቱ ከሞራል ውድቀት በቀር የሚያስገኝ ነገር የለም። ማስገባትና ማስወጣቱ ያሰልጣኝ ፈንታ ነው። ዛሬ በሚደረገው ጨዋታ ፌዴሬሽኑ የጠራን ከያለንበት ተጠራርተን እንድንነቅፍ አይደለም። ስለዚህ ሁላችንም ወደ ስታዲየም ስንመጣ ለድጋፍ እንጂ ለተቃውሞ ሰልፍ አለመሆኑን አስቀድመን እንወቅ።
(አዲስ ዘመን መጋቢት 13 ቀን 1968ዓ.ም)
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
አዘጋጅ ጳውሎስ ኞኞ
*የፍቅር በሽታ ይዞኝ መሞቴ ነውና እባክህን ስለወንድ ልጅ አምላክ መድኃኒት ያለው እንደሆን ንገረኝ።
ከበደ አበራ
-መድኃኒት የለውምና ትንሽ ጊዜ ማቅ።
*ሱሪ ተንተርሰው ሲተኙ ሕልም ያሳያል ይባላልና እውነት ነው?
-እኔስ ሞክሬው አላውቅም፤እስቲ አንተው ሞክረው።
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 3 ቀን 1965ዓ.ም)
* የኢትዮጵያ ፓርላማ አሁን የጀመረውን የሴተኛ አዳሪዎች ጉዳይ ወደ መልካም ግብ አድርሶት ያንን የሚናፍቀኝን ትዳር አግኝቼው እረካ ይሆን?
-ምናልባት ይሆን ይሆናል፡፡
(አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 1964ዓ.ም)
*ደካማ ጎኔን ብቻ ፈልጎ የሚጨቀጭቀኝን ወዳጄ ወይንስ ጠላቴ ማን ልበለው?
-ገንቢዬ!
*ብላቴን ጌታ ወልደ ኅሩይ ሥላሴ ኢትዮጵያ በፋሽስት ተወራ በነበረችበት ጊዜ፤ የተባበሩት መንግሥታት ማኅበር አቤቱታዋን ሰምቶ ትክክለኛ ፍርድ ባለመስጠቱ ተበሳጭተው ሕይወታቸውን በገዛ እጃቸው አጠፉ የሚሉት እውነት ነው?
ምህረት ከበደ
– እንዲህ አይነቱን ወሬ ገና ዛሬ መስማቴ ነው። እኔ የማውቀው ታመው ነው የሚባለውን ነው።
*ከመሪ ሁሉ የትኛውን መሪ ታደንቃለህ?
ከበደ(ከበደሌ)
-መኪና ስገዛ እነግርሃለሁ!
(አዲስ ዘመን ታህሳስ 15 ቀን 1966ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2016