አፍንጫቸውን በነጠላቸው ሸፍነዋል፤ ፊታቸውን ጨፍገግ አድርገው ከአካባቢው በፍጥነት ለማለፍ ጠደፍ ጠደፍ እያሉ ይራመዳሉ። ጠራራ በሆነው የቀትር ፀሐይ ታግዞ አካባቢውን በመጥፎ ጠረን ያጀበው ስፍራ እኔም ቆም ብዬ ሰዎችን እንዳነጋግር ዕድል አልሰጠኝም። ሽታው አፍንጫን ከሚሰነፍጥበት የራስ መኮንን ድልድይ ትንሽ ራቅ ብዬ በነፋስ ሽውታ የሚደርሰኝን መጥፎ ጠረን በእጄ እያባረርኩ በጥድፊያ የሚራመዱትን ወይዘሮ ላነጋግራቸው ወደድኩ።
ወይዘሮ ፀሐይ ለማ ይባላሉ። በየአካባቢው በእግራቸው ሲዘዋወሩ የሚያጋጥማቸው መጥፎ ሽታ የአስም በሽታቸውን እየቀሰቀሰባቸው መቸገራቸውን ይናገራሉ። ከወንዝ ደርቻ፣ ከቱቦዎች ውስጥ የሚወጣው ሽታ እንዲሁም በየመንገዱ ግንብ ስር ያለው መጥፎ ሽታ ለሕፃናት ልጆች ጭምር የጉንፋን በሽታ መንስኤ መሆኑን ነው ያጫወቱኝ። ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲወስዱና ሲመልሱም አፍንጫቸውን ሸፍነው ለመጓዝ መገደዳቸውን ነግረውኛል።
” እኛ ባልተመቸ ሁኔታ በተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች እየተያዝን ኖረናል፤ መጪው ትውልድ ግን ጽዱ የሆነች ከተማ ሊኖረው ይገባል“ ሲሉ የተናገሩት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰዴ አሻግሬ ናቸው፡፡
አቶ ሰዴ እንደሚሉት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ወደ ተግባር ተገብቶ ልማቱ በሚሠራበት ጊዜ፣ በሚገባበት ጊዜ ተጠቃሚ የሚሆነው የአዲስ አበባ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን መላው የአገሪቱ ህዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡
ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ የሆኑት አቶ አብርሃም ምንተስኖት እንደሚሉት የወንዝ ዳርቻዎች ጸድተው ለመናፈሻ፣ ለመዝናኛ እንዲሁም ለተለያዩ ማህበራዊ ተግባራት ለማዋል ታቅዶ መሠራቱ መልካም ነው፡፡ “አዲስ አበባ የታሰበውን መሆን የነበራባት አሁን አልነበረም ፤ አሁን መታሰቡ ጥሩ ነው። ከተማዋ ለነዋሪዎቿ በጣም ምቹና ሳቢ እንዲሁም የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን መሥራት ያስፈልጋል፤ በወንዝ ዳርቻ ያሉ ነዋሪዎችንም በጎርፍ እንዳይጠቁ መሥራት ተገቢ ነው” ብለዋል፡፡
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ መምህር ኢሳያስ ውብሸት በበኩላቸው የወንዝ ዳርቻዎችን የማልማት ፕሮጀክቱ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ዕቅድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ተግባራዊ እስኪሆንም በጉጉት እየጠበቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መምህር ኢሳያስ እንዳሉት ፕሮጀክቱ በከተማዋ የሚኖሩ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መስህቦችን እንዲሁም የዕረፍት ጊዜ ማሳለፊያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የውጭና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ለመሳብ ያስችላል። ፕሮጀክቱ የብስክሌት መስመር፣ የንጹሕ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የመናፈሻ አገልግሎትን የያዘ ሲሆን፤ በዋናነት ከፀሐይ ለሚመነጭ ታዳሽ ኃይል እንደሚጠቅም መስማታቸውን ያስታወሳሉ። ይህ ደግሞ አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ የሚያደርጋት፣ለነዋሪዎቿም ምቹ እንድትሆን ያስችላል የሚል እምነት አላቸው።
“አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ብሎም የአፍሪካ መዲና መሆን አትችልም“ ከሚያስብሏት ግንባር ቀደም ምክንያቶች አንዱ ፅዱ አለመሆኗ ነው፡፡ ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ አበባ ላይ በድምሩ 79 ቢሊየን ብር የሚያወጡ የመዝናኛ እና የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን ይፋ ያደረጉት። አንዱ 50 ቢሊየን ብር ወጪ የሚደረግበት ለገሃር የተቀናጀ የመኖሪያ አገልግሎት መስጫና የመዝናኛ ስፍራ ልማት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ 29 ቢሊየን ብር ዋጋ ያለው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻዎች ማልማት ፕሮጀክት ነው።
በፕሮጀክቱ የቤተ መንግሥት አካባቢ የከተማ መናፈሻ ፕሮጀክት፣ ከእንጦጦ ተራራ የሚነሱ ሁለት ዋና ዋና ወንዞችን አንደኛው 23 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ሌላው 27 ነጥብ 5 ኪሎሜትር በከተማዋ ውስጥ በመጓዝ በቀበና፣ ግንፍሌ፣ቡልቡላ በሚል እየተጠሩ ወደ አቃቂ ወንዝ ይቀላቀላሉ፡፡ በከተማዋ ብዙ ገባር ወንዞች የሚገኙ ሲሆኑ የወንዞቹ ውሃ ለብክለትና ለብክነት በከፍተኛ ሁኔታ የተጋለጠ ነው፡፡ በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ ከባቢ አየር ለመንከባከብ የተወጠነ ሲሆን የከተማ ቱሪዝም ለማስፋፋት ታቅዷል፡፡
በዚህ ፕሮጀክት ከቤተመንግሥት ጋራዥ፣ፒያሳ፣ ውጭ ጉዳይ እያለ አቃቂ የሚደርሰው የአዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በይፋም ተጀምሯል፡ ፡ ከወንዞቹ አጠገብ የህዝብ መናፈሻ ፓርኮች፣ የእግረኛ መንገዶችና የቢስክሌት መንገዶች ተገንብተው፣ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የከተማዋን ገፅታ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚቀይር ይታመናል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
አብርሃም ተወልደ