«በቀን የድብደባና የዝርፊያ ወንጀል ተፈጽሞብኝ ነበር። በአካባቢው ባለው የማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ፅሕፈት ቤት ለመጠቆምና ወንጀለኛውን ተጠያቂ ለማድረግ ሙከራ ባደርግም ዝግ በመሆኑ ወንጀለኛው እንዲያመልጥ ሆኗል» ሲል በከተማዋ የማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሥራ በተደራጀ መልኩ እየሠራበት አለመሆኑን የገለጸልን አራት ኪሎ አካባቢ ያገኘነው አቶ ፈጠሳ አብዲሳ ነው።
እንደ ፈጠሳ ገለጻ፤የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ የተቋቋሙት የቅድመ መከላከል ሥራ ለመሥራት ቢሆንም ሥራቸው ግን ለየቅል ነው። በተለይ በዚህ ወቅት ወንጀል እንዲበራከት ዕድል የከፈቱት የሚገባቸውን እየሠሩ ባለመሆኑ ነው። ስለሆነም የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችም ከምንጊዜውም በላይ ከህዝብ ጋር በመሆን መሥራት ይኖርባቸዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ ላምበረት አካባቢ ነዋሪ የሆነው ወጣት ኤፍሬም አርኪሳ በበኩሉ፤ ማዕከላት መቋቋማቸው ጥሩ ሆኖ እያለ ጠንካራ አለመሆናቸው ግን የበለጠ ለአደጋ ያጋልጣል ይላል። ክፍተቶች በስፋት እንዲስተዋሉም በር የከፈተው ይኸው ችግራቸው መሆኑን ያነሳል። ሕብረተሰቡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወንጀል እየተፈፀመበት ነው፡፡
በመሆኑም የማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ሥራ ከመንግሥት አካል ውጪ በሆነ አልያም በተለየ ሁኔታ በክፍለ ከተማና በከተማው አስተዳደር ክትትል ሊደረግባቸው እንደሚገባ ይናገራል። ሕብረተሰቡም ወንጀልን መከላከል ለፖሊስ ብቻ ሳይተው የእርሱም ድርሻ እንዳለበት በማመን ከማሕበረሰብ አቀፍ ፖሊሶች ጋር መሥራት ይገባል ብሏል።
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ 9 ነዋሪ የሆነው ወጣት ሄኖክ ግርማ፤ የማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች ብዙ ጊዜ ዝግ ናቸው፡፡ ባለሙያዎቹም ቢሆኑ ወደ ሕብረተሰቡ ወርደው የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ መሥራት አልቻሉም ይላል፡፡
በማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ላይ የሚሠሩ ፖሊሶች ወንጀለኛን ተከታትሎ ለመያዝ ተነሳሽነት እንደሌላቸው የሚገልጸው ሄኖክ፤ ከሕብረተሰቡ ጋር ጥብቅ የሆነ ትስስር ስለሌላቸው በቁጥጥር ስር መዋል የሚችሉ ወንጀሎች በሰውና በንብረት ላይ ብዙ ጉዳት እያደረሱ መሆናቸውንም ያስረዳል። ይህ ችግር በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ወንጀሎች በከተማችን ከምንጊዜውም በላይ ይበራከታሉ ሲል ስጋቱን አጋርቷል፡፡
በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት ዳይሬክተር ኮማንደር ሰለሞን ፈንታሁን እንደሚናገሩት፤ ማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ በቅድመ መከላከል ሥራ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ወንጀል ከመፈጠሩ በፊት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ የሚሠራ እንጂ እንደ መደበኛ ፖሊስ ወንጀልን ተከታትሎ
የሚይዝ አይደለም፡፡ ችግር አፈታት ላይና አካባቢን መሰረት ያደረገ ሥራ በመሥራትና በአጠቃላይ ወንጀሎች እንዳይሠሩ ቅድመ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በከተማዋ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ቀጠናዎች ላይ ማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት የሚሰጡ ማዕከላት እንዳሉ የሚያነሱት ኮማንደር ሰለሞን፤ ከለውጡ በኋላ ወንጀሎች መበራከታቸውን ተከትሎና አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ኩነቶች በመበራከታቸው ምክንያት የሰው ኃይሉ ወደ እነዚያ ተግባራት ላይ በመግባታቸው ማዕከላቱ በሰው ኃይልእጥረት ምክንያት እንዲቀዛቀዙ ሆነዋል።
እንደ ኮማንደር ሰለሞን ገለጻ፤ ለአገልግሎቱ መቀዛቀዝ መንስኤው የሰው ኃይል በመሆኑ በቀጣይ ጠንካራ ሥራ የሚሠራ ይሆናል። አሁን የተቀዛቀዘውን ለማነቃቃት ከአስተዳደሩ ጋር የጋራ መዋቅር ዘርግተን በአስሩም ክፍለ ከተማ የንቅናቄ ሥራ በመሥራት ላይ እንገኛለን። ከህዝብ የሚደርሱ አስተያየቶችን እንደመነሻ በመውሰድ በአዲስ መልክ ለማደራጀት ቅድመ ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው፡፡ ስለዚህም በቀጣይ በየቦታው የሚፈጠሩ ወንጀሎችን ለመከላከል ከምንጊዜውም በላይ ህዝብን ያሳተፈ ሥራ ይሠራል፡፡
በ መዲናችን ወንጀልን ለመከላከልና ማሕበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎቶችን ለመስጠት ታስበው በሁሉም ክፍለ ከተሞች ላይ ጥቁርና ቢጫ ቀለም የተቀቡ የቆርቆሮ ቤቶችን መመልከት የተለመደ ነው። ይሁንና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አንዳንዶች ተዘግተው፤ የተቀሩት ደግሞ ሰዓታቸውን ጠብቀው አለመከፈታቸውን ለመታዘብ ችለናል። ይህ ደግሞ የሥራ መቀዛቀዙን የሚያሳይ ሲሆን፤ በየቀኑ በየቦታው የሚፈጠሩ ወንጀሎችም ለዚህ ማሳያ ናቸው።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
ሞገስ ፀጋዬ