አዳማ፡- ግብርና ዋነኛ የኢኮኖሚ ማነቆዎችን የሚፈታ የህልውና መሰረት በመሆኑ ማዘመኑ ላይ ወቅታዊ አጀንዳ አድርጎ መሥራት እንደሚያስፈልግ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታወቁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ትናንት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የግብርናው ዘርፍ የውይይት መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ ግብርናው ባለፉት ዓመታት እየመጣ ባለው ዕድገት ትልቅ ሚና የነበረውና አገር ሲያሳድግ የቆየ ነው። ይሁንና በዕድገት ላይ ዕድገት ከማምጣት አንጻር ከፍተኛ ማነቆዎች እንዳሉበት ገልጸዋል።
የግብርናው መዘመን አንገብጋቢ ነው ሲባል ወቅታዊ ትኩረትን ይሻል ማለት እንደሆነ የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአመራርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሂደትን ማሳለጥ ያስፈልጋል። ለግብርናው መዘመን ከከፍተኛው እስከ ታችኛው አመራር ድረስ የተግባቦት ሥራ ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።
“ግብርናው የሚሰጠን እኛ በሰጠነው ልክ ነው።” ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ የመስኖ ልማት፤ የቴክኖሎጂ ልህቀትን ማሳደግ ላይ ጠንክሮ መሥራት ካልተቻለ ግብርናው ምንም ዓይነት ውጤታማ መሆን አይችልም። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያልተቻለበት ሁኔታ የተፈጠረውም ከዚህ አኳያ ነው። ሚሊዮኖችን ከችግር ማላቀቅም አዳጋች ሆኗል። ስለሆነም ግብርናውን ማዘመን ላይ ጠንካራ ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል።
አሁን በግብርናው ዘርፍ ሁለት ነገር ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የመጀመሪያው የመኸር ወቅት ውጤታማ እንዲሆን መሥራት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የግብርና ልማት ሥራው የቀጣይ የሪፎርም ግብ መሰረት እንዲሆን ማድረግ ላይ ያነጣጠረ ሥራ ማከናወን መሆኑን ገልጸዋል። የአርሶአደሩን የመሥራት አቅም ማጎልበትም እንደሚገባ ተናግረዋል።
ወጣቱም የነገ አገር ተረካቢ በመሆኑ የግብርና ሜካናይዜሽን አቀንቃኝ እንዲሆን ማድረግ ላይመሥራት ለነገ የማይባል መሆኑን አስገንዝበዋል። የጂቲፒ ሁለት ሥራዎች ወደቀጣይ እንዳይተላለፉም ማድረግ ላይ መሠራት እንዳለበት አሳስበዋል
የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን በበኩላቸው የግብርና ዘርፉን ከዝናብ ባለማላቀቅ 18 ሚሊዬን ዜጎች የሴፍትኔት መርሐ ግብር ጥገኛ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ስለዚህም የግብርናው መዘመን ውዴታ ብቻ ሳይሆን ግዴታና አንገብጋቢ መሆኑን ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፋቸው አመላክተዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ግብርናው ብዙ የሰው ኃይል የሚያሳትፍ፣ የሥራ ዕድል መፍጠሪያና የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ እንዲሁም የኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃ ግብዓት የሚሆን ነው። የምግብ ዋስትናን ማረጋገጫም ነው። ይሁንና ዕድገቱ ላይ ቀጣይነት ባለው መንገድ ባለመሠራቱ ብዙ ችግሮች አጋጥሟል።
“ምርትና ምርታማነትን ከመጨመር አንጻር አገሪቱ ብዙ እየሠራች አይደለም“ ያሉት አቶ ኡመር፤ በሞዴል አርሶ አደሮችና በአማካይ የአገራዊ ምርት መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ እንኳን ቢቻል በዓመት 100 ሚሊዬን ኩንታል ተጨማሪ ምርት ይገኝ ነበር። ሆኖም በዚያ ልክ መሥራት ባለመቻሉ በገጠር አካባቢ በቂ ምግብ የማያገኙ 25 ሚሊዬን ዜጎች ተፈጥረዋል። በዕለት ደራሽና ዕርዳታ፣ በልማታዊ ሴፍትኔት የታቀፉት ስምንት ሚሊዬን ህዝቦች እንዲኖሩም በር ከፍቷል።
የልማታዊ አክቲቪዝም የግብርናው ትራንስፎ ርሜሽን ቋንቋ መሆን እንዳለበት የገለጹት አቶ ኡመር፤ የወጪና ገቢ ምርቶችን ማመጣጠን፣ የኩታ ገጠም ግብርናን ማስፋፋት፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት መሥራት፣ ውሃን መሰረት ያደረገ ሥራ ማከናወን፣ ገበያ መር ኤክስቴንሽን ማስፋት ለግብርናው መዘመን መፍትሔ ይሆናሉ ብለዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
ወንደሰን ሽመልስ