”አካባቢው አረንጓዴ ነው፤ ለም አፈሩ ከአስፓልት መንገዱ በታች በጉልህ ይታያል። ለጥ ባለው ሜዳ ላይ የተለያዩ ሰብሎች ይመረታሉ። ይሄ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ባለመዋሉ ግን አርሶአደሩ አሁንም ህይወቱ አልተለወጠም። ”ይህን ያሉት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የተሰባሰቡ የአንድ መድረክ ተሳታፊዎች ናቸው። መድረኩ ደግሞ “ዕድገት ለጎጃም ደብረ ማርቆስ” የተሰኘው የኢንቨስትመንት ፎረም እና የፓናል ውይይት ነበር።
የአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ መላኩ አለበል እንዳሉት ከኢትዮጵያ የግብርና ምርት 35 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከጎጃም አካባቢዎች ነው። ከዚህ ውስጥ አብዛኛው ምርት ደግሞ የሚመረተው በምሥራቅ ጎጃም ቢሆንም ምርቱን ግን አቀነባብሮ የመላክ ልምድ አልዳበረም።
አብዛኛው ምርት እሴት ሳይጨመርበት ለገበያ የሚቀርብ በመሆኑ አምራቹ አርሶአደር አሁንም የተሻለ ገቢ ማግኘት አልቻለም። ይህንን ልምድ በመቀየር የተሻለ ልማት ለማምጣት ሁሉም አመራር ዓይኑን በመግለጥ ኢንቨስተሮችን በሰፊው መሳብ ይኖርበታል።
በጎጃም ሁሉም ዓይነት የአየር ንብረቶች እና በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ይገኛሉ። በተለይ ለአግሮ ፕሮሰሲንግ እና ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ የሚሆኑ ግብአቶች እንዲሁም በቱሪዝም ሀብት የበለጸጉ መዳረሻዎች በመኖራቸው ለኢንቨስተሮች በአግባቡ እየተዋወቁ ይገኛል።
ስለዚህ ኢንቨስ ተሮች ምቹ አሠራር በመፍጠር መሳብ እና ሰላምን ማስጠበቅ ያስፈልጋል። ስለልማት ሲታሰብ ሰላም ዋነኛው አስፈላጊ ጉዳይ በመሆኑ እያንዳንዱ ህብረተሰብ ንቁ ተሳትፎ ይጠበቅበታል። በተለይ ልሂቃን አንድ የሆነውን ህዝብ የማይረብሹ ሃሳቦች ላይ ብቻ በማተኮር ለአካባቢው ኢንቨስትመንት ቀጣይነት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሰተዳዳሪ አቶ አብረሃም አለኸኝ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ ጎጃም የታላላቅ ሃሳብ ባለቤቶች የሆኑ በርካታ ምሁራንን ያፈራ አካባቢ ነው። በመሆኑም ዕውቀትን አቀናጅቶ ለኢንቨስትመንት ሥራ የማዋል ሥራ ያስፈልጋል። በሌላ በኩል የአባይ ሸለቆ ውስጥ ያለ አካባቢ በመሆኑ ከመሬት በታች እና በላይ የሚገኙ በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶችን ይዟል።
በመሆኑም በማዕድንና የከበሩ ማዕድናት እንዲሁም በማምረቻ ፋብሪካዎች ግንባታ ሰፊ ሥራ ማከናወን የሚያስችል አቅም አለ። በመሆኑም ለኢንቨስተሮች የሚያመች አሠራር በመከተል የህብረተሰቡን ልማት ለማጎልበት ጠንካራ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል።
የ ደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ካሳሁን እንደሚናገሩት ደግሞ፣ በዘንድሮ ዓመት ብቻ 644 ሚሊዮን ብርየካፒታል መጠን ያላቸው 31 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ አውጥተዋል። ከሰባት ሄክታር መሬት በላይ ወስደውም ለ656 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በከተማው ለኢንቨስተሮች የሚሰጠው ዕድል እየጨመረ በመምጣቱ በርካታ ባለሀብቶች እንደሚመጡ ይጠበቃል። በተለይ የመሬት ካሳ ክፍያን ከሊዝ ክፍያ ላይ ቀንሰው ለአርሶአደር እንዲከፍሉ በማድረግ ባለሀብቶች በፍጥነት መሬት እንዲያገኙ የሚያስችል አሠራር ተጀምሯል።
እንደ ወይዘሮ ዓለምፀሐይ ከሆነ፣ ኢንቨስተሮች ወደ ደብረማርቆስ እና የተለያዩ የጎጃም አካባቢዎች ቢሰማሩ በስፋት የሚገኝ የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ። በተለይ በአካባቢው ያለውን የደን ምርት ተጠቅመው ማር እና ሰም እንዲሁም የወረቀት ፋብሪካዎች ግንባታ ላይ መሳተፍ ይችላሉ።
በደጀን አካባቢ ያለውን የግራናይት እና የተለያዩ ማዕድናት ለማዘጋጀት በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ደብረማርቆስ ከተማ ፋብሪካ ቢከፍቱ ለኤክስፖርት ምርት አመቺ የትራንስፖርት አማራጭ በባህርዳትር ኤርፖርት አለ። በሌላ በኩል በጨርቃጨርቅ እና ምርት ያለውን እምቅ ሀብት በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ መፍጠር የሚያስችል ዕድለ ለኢንቨስተሮች ተመቻችቷል።
ምቹ የተፈጥሮ ሀብት እና የሰው ኃይል ቢኖርም ከብድር ጋር ያለው ችግር በርካታ ባለሀብቶችን በአካባቢው እንዳያለሙ አገዷቸው እንደነበር የሚያስረዱት ወይዘሮ ዓለምፀሐይ አሁን ጉዳዩ በከፍተኛ ባለስልጣናት እጅ በመሆኑ ወደመፍትሔው እየሄደ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይ የልማት ባንክ 30 በመቶ ገንዘብ ይዘው ለሚበደሩ ባለሀብቶች በፍጥነት ብድር ያለመስጠት ችግር ነበረበት።
አሁን የአማራ ክልል ባለስልጣናት እና የፌዴራል መንግሥት በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ችግሩን ለመፍታት ስምምነት በማድረጋቸው የብድር አማራጭ የማግኘት ዕድሉ መስፋቱን ተናግረዋል። በመሆኑም በጎጃም ለማልማት ያለው አማራጭ የተመቻቸ መሆኑን በመረዳት ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ጥሪ ያቀርባሉ።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስተባባሪ አቶ ከፍአለ አድነው እንደሚገልጹት፤ ከነዋሪው ፍጆታ በላይ የሆነ ምርት በዞኑ አለ። ነገር ግን ወደማቀነባበር ሥራው አልተገባም። በተለይ በሥጋ እና ቆዳ ውጤቶች የቁም እንስሳት ለገበያ ይቀርባሉ እንጂ አቀነባብሮ የሚልክ ፋብሪካ አልተስፋፋም።
እንደ አቶ ከፍአለ ከሆነ፣ በአካባቢው ከበረሃማ አየር ንብረት ጀምሮ እስከ ውርጭ እና ወይና ደጋ አየር ንብረቶች ይገኛሉ። በዚህ ምክንያት የተለያዩ የሰብል ዓይነቶችን እና በተለያየ አየር ንብረት ማደግ የሚችሉ እንስሳትን ላይ መሥራት ይቻላል። እስከአሁን 17 ቢሊዮን ሀብት ያላቸው 700 ባለሀብቶች የተሰማሩ ቢሆንም በርካታ ሌሎች ባለሀብቶችን የሚጠብቁ የተፈጥሮ ሀብት ይገኛል። በመሆኑም አብረን እንሥራ የሚል ጥሪ ያቀርባሉ።
አዲስ ዘመን ግንቦት 18/2011
ጌትነት ተስፋማርያም