ሰላም ልጆች እንዴት ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? በሚገባ እያጠናችሁ እንደሆን ተስፋ አደርጋለሁ። ልጆችዬ እንኳን አደረሳችሁ? መቼም የምን በዓል ኖሮ ነው እንኳን አደረሳችሁ የተባልነው? ልትሉ ትችላላችሁ። ለምን መሰላችሁ? የሕፃናት ቀን ባሳለፍነው ሳምንት መከበሩን ምክንያት በማድረግ ነው። ‹‹እንኳን አብሮ አደረሰን።›› የሚል ምላሽ እንደምትሰጡኝ ምንም ጥርጥር የለኝም።
ልጆች የሕፃናት ቀን እንዴት መከበር እንደተጀመረ ጥቂት እናስታውሳችሁ አይደል? እኤአ በ1959 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የሕፃናት መብቶች መግለጫ ያፀደቀበት ቀን ኅዳር 20 ነበር። በተጨማሪም በ1989 የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ያፀደቀበት ቀን እንደሆነ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት የሕፃናት መብቶች ኮንቬንሽን ከፀደቀበት ቀን እና የሕፃናት መብቶች መግለጫ የፀደቀበትን ቀን ለማስታወስ እ.ኤ.አ. ከ1990 ጀምሮ የዓለም የሕፃናት ቀን ኅዳር 11 ይከብራል ማለት ነው።
ታዲያ ልጆችዬ ይህንን ምክንያት በማድረግ በየዓመቱ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው የሕፃናትን መብት፣ ደህንነትን እና ክብካቤን እንዲጎለብት የሚያላክቱ መልዕክቶችን እንዲሁም የተለያዩ ዝግጅቶችን በመቅረጽ መንግሥታዊ በመሆኑ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ይከበራል። ዘንድሮም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ተኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ ለ18ኛ ጊዜ ተከብሯል።
ስለዚህም የሕፃናትን ቀን በማስመልከት ከተደረጉት ዝግጅቶች መካከል ቅዳሜ ኅዳር 08 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ‹‹በልጅ ዓይን ሁሉም ንጹህ ነው›› በሚል መሪ ሃሳብ በድምቀት የተከበረው ፌስቲቫል አንዱ ነው። በዚህ ፌስቲቫል ላይ የሕፃናት መጽሐፍት ኤግዚቢሽን፣ የሕፃናት ማርሽ ባንድ፣ የሰርከስ ትርኢት፣ ግጥም፣ ሙዚቃ እና ሌሎች ዝግጅቶችም ቀርበዋል።
በሰም እና ወርቅ ሚዲያ እና ኢንተርቴመንት በተዘጋጀው በዚህ ፌስቲቫል ላይ መስማት ለተሳናቸው ታዳሚዎችም በምልክት ቋንቋ መልዕክቶች ሲተላለፉ ነበር። እንዲሁም የሜሪ ጆይ የልማት አቀፍ ሕፃናት ማኅበር አባላት መዝሙሮችን ያቀረቡ ሲሆን፡-
ይብቃ ይብቃ የጎዳና ሕይወት፤ ይበቃ ይቁም የሕፃናት ጥቃት።
የሚል የሕፃናት መዝሙር በማቅረብ የጎዳና ሕይወት አስከፊ መሆኑን ፤ ትኩረት ጎዳና ላይ ላሉ ልጆች ማድረግ እንደሚገባም በመልዕክታቸው አስተላልፈዋል። በተጨማሪም ልጆች ሀገራቸውን እንዴት እንደሚወዱ እና ሀገራቸውን በሚገባ በግጥም መልክ አቅርበዋል።
የፌስቲቫሉ አዘጋጅ ጌታቸው ዓለሙ ስለፌስቲቫሉ ዓላማ ሲናገር በምርምር፣ በሀገር በቀል ሥራዎች፣ በቴክኖሎጂ፣ ሥነ ፈለክ እንዲሁም በትምህርት ጎበዝ የሆኑ ተማሪዎችን በመሸለም እና በማበረታታት ከዚህ ከፍ ሲልም ተስፋ ሊሰጥ የሚችል ትውልድ ለመቅረጽ እና ሌሎችንም ለማነቃቃት ትኩረት ያደረገ ነው።
በፌስቲቫሉ ላይ የግጥም ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት መካከል ቃለአብ ሸዋፈራሁ አንዱ ሲሆን፤ የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነው። በዓሉን ለማክበር ስለተደረገው ዝግጅት እንዲሁም ግጥሙን ለታዳሚዎች ለማቅረብ ዕድሉን በማግኘቱ ምስጋናውን አቅርቧል። ሌላው በፌስቲቫሉ ላይ ከታደሙት ሕፃናት መካከል እህትማማቾቹ ኤፍራታ ዓለሙ እና ዮስቲና ዓለሙ ናቸው። እነርሱ እንደሚሉት የሕፃናት ቀን በዚህ መልኩ በመከበሩ ደስታቸውን ገልጸዋል። በዕለቱ ሽልማት እንደተሰጣቸው ልጆች ለመሸለምም በርትተው እንደሚያጠኑ ተናግረዋል።
በዚህ ፌስቲቫል ወላጆችም ተገኝተዋል። የፌስቲቫሉ ታዳሚ ወይዘሮ ቅድስት መኮንን እንዳሉት ፌስቲቫሉ ለልጆች በጣም ደስ የሚል እንደሆነ ነው የገለጹት። እንዲህ ዓይነቱ ፌስቲቫል ልጆችን ከማጫወት ባሻገር ከወላጆቻቸው ጋር በጋራ እንዲያሳልፉ ዕድል የሚሰጥ መሆን ገልጸዋል። በተጨማሪም ለሽልማት የበቁትን እንዲሁም የተለያዩ ሥራዎችን ሲያቀርቡ የነበሩ ልጆችን በመመልከት ልጆች የራሳቸውን ፍላጎት እንዲያጤኑ የሚያደርግ መሆኑን አስታውቀዋል።
ልጆችዬ በዚህ ፌስቲቫል ላይ ከተገኙት መካከል ዶክተር አሉላ ፓንክረስት፣ የሙዚቃ ባለሙያ የክብር ዶክተር ዳዊት ይፍሩ፣ ሰዓሊ ጋሽ አክሊሉ መንግሥቱ እና የሜሪጆይ ኢትዮጵያ በጎ አድራጎት ማኅበር መሥራች ሲስተር ዘቢደር ዘውዴ የተገኙ ሲሆን፤ ልጆች በጥሩ መንገድ መቀረጽ እንዳለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የኢትዮጵያን ታሪክ በማጥናት እና የሳይበር ደህንነት ላይ ለተመራመሩ ልጆች ሽልማት አበርክተው አበረታተዋቸዋል።
ልጆችዬ በአጠቃላይ በመድረኩ ለልጆች በጎ መሆን የመምህራን ሚና፣ የኪነጥበብ ሰዎች እና የወላጆች ሚና ድርሻ ከፍተኛ እንደሆነ ተነስቷል። ልጆችዬ እናንተስ ቀኑን እንዴት አሳለፋችሁ? እናንተም ጥሩ ሥራ ሠርታችሁ ለሽልማት እና ሀገራችሁን ለመጥቀም እንደምትበቁ ምንም ጥርጥር የለኝም። ልጆችዬ ለዛሬው በዚህ እናብቃ። ሳምንት በሌላ ርዕሰ ጉዳይ ለመገናኘት ያብቃን።
እየሩስ ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 16/2016