የሀገራችን የባሕር በር ጥያቄ እና አንድምታው

የምንኖርባት ፕላኔት ሦስት አራተኛዋ በውሃ የተሸፈነ እንደሆነ ይነገራል፡፡ መቶ በመቶ በገጸ- ምድሯ ላይ የፍጡራንን አስትንፋስ የሚያስቀጥል አየር ይናኝባታል፡፡ ብርሃንና ጨለማ ጊዜያቸውን ጠብቀው ይፈራረቁባታል፡፡ ፍጡራን ከመሬት፣ ከውሃ፣ ከአየር፣ ከፀሐይ ብርሃን በሚያገኙት የተፈጥሮ ፀጋ ሕይወት ይቀጥልባታል፡፡

እነዚህ የተፈጥሮ ፀጋዎች ለፍጡራን ያለከልካይ የተሰጡ በረከቶች ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ፍጡር በምድር ላይ መኖር የቻለው ምድር ለሕይወት መቀጠል የሚያስፈልጉ ነገሮችን አሟልታ በመያዟ ነው፡፡ ከነዚህ ፀጋዎች አንዱ እንኳን ቢጓደል ሕይወት አይቀጥልም፤ ይህ ደግሞ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡

ሰው ቁጥሩ ጨምሮ በከለር፣ በብሔር፣ በቋንቋ በጎሳ እየተከፋፈለ ወሰን አካሎ ይሄ የኔ፣ ይሄ ያንተ፣ ማለት ከመጀመሩ በፊት መሬትም ብትሆን ፍጡራን ያለምንም ከልካይ የሚጠቀሙባት የተፈጥሮ ስጦታ ስለመሆኗ ማንም አይከራከርም፡፡

ዛሬ የሰው ልጅ በመሬት ሀብት ላይ እንዳስፈለገው የሚያዝበት ጊዜ አብቅቷል፡፡ ዓለም በአህጉር፣ በሀገር፣ በክፍለሀገር፣ በወረዳ፣ በቀበሌ መሸንሸኗን ተከትሎ እንደ ጥንቱ ወይም እንደ ዘመነ ፍጥረት በዘፈቀደ ከአንድ አህጉር ወደሌላ አህጉር፣ ከአንድ ሀገር ወደሌላ ሀገር ሄዶ የሚኖርበት ሁኔታ የለም፡፡ የመሬት ነገር ሥርዓት ተበጅቶለታል፡፡

እርግጥነው በአንድ አካባቢ የሚኖር ማኅበረሰብ የአኗኗር ሥርዓቱ፣ ቋንቋው፣ ባህሉ፣ ወጉና እምነቱ በብዙ ምክንያቶች ከሌላው ሊለይ ይችላል፡፡ እያን ዳንዱ ማኅበረሰብ በሚኖርበት አካባቢ ጤናማ መስተጋብር እንዲኖር የራሱን መተዳደሪያ ሕግና ሥርዓት አበጅቶ መኖር ግድ ይለዋል፡፡

ዓለምን በአህጉርና በሀገር የሸነሸናት አንዱ ምክንያት የሰዎች ማኅበራዊ መስተጋብርና የአኗኗር ሥርዓት ነው፤ (ለተለያዩ አገሮች መፈጠር ቅኝ ገዢዎች ያሳደሩት ተፅዕኖ ሳይረሳ ማለት ነው፡፡) እነዚህ ሁኔታዎች ሀገራት የራሳቸውን ድንበር እንዲያካልሉ፣ የራሳቸውን መተዳደሪያ ሕግ እንዲያወጡ፣ የራሳቸውን ባንዲራ እንዲያውለበልቡ አድርገዋል፡፡

እንግዲህ መሬት በዚህ መልክ ባለቤት ኖሯታል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዓለማችንን ተቆጣጥሮ ‹‹Man­age›› አድርጎ ለመኖር ጠቀመን እንጂ አልጎዳንም። እንደውም በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በልማትና እድገት የፉክክርና የትብብር መንፈስ ይዘን ዓለምን እንድንለውጣት ረድቶናል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ሐይቆች እንደምንተ ነፍሰው አየር እና እንደፀሐይ ብርሃን የዓለም ሕዝብ በጋራ የሚጠቀማቸው ተፈጥሯዊ ሀብቶች እንጂ እንደ መሬት የጥቂት ሀገር ንብረት የመሆን ባሕሪ የላቸውም። የዓለም ሀገራት የሰማይ ግዛታቸውን ለአውሮፕላን ትራንስፖርት ክፍት በማድረጋቸው እና በትብብር በመሥራታቸው ተጠቃሚ የሆነው የዓለም ሕዝብ ነው፡፡

ልክ እንደዚህ ሁሉ ሐይቆችና ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን በጋራ የመጠቀሙ ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ተጠቃሚ የሚያደርገው ሁሉንም ነው፡፡ ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በር ፍላጎት ማሳየቱ ያልተመቻቸው፣ ያስኮረፋቸውና ያስገረማቸው አካላት ተፈጥረዋል፡፡

ውቅያኖስ ግዙፍ ነው፤ የዓለም ሀገራትንም ያስተሳስራል፤ እና ይህ ዓለምን የሚያካልል የተፈጥሮ ፀጋ ሰው በሆነ አጋጣሚ ድንበር አካሎ ለፈጠራቸው አንድና ሁለት ሀገራት ብቻ መጠቀሚያ እንዲሆን ተብሎ የተፈጠረ አለመሆኑን እንኳንስ ሀገርን የሚመሩ ታዋቂ ሰዎች ይቅርና ሕጻን ልጅም ሊረዳው የሚችል እውነት ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአቅራቢያዋ በሚገኝ ባሕር /ቀይ ባሕር/ የመጠቀም መብቷ ተፈጥሯዊ ነው፤ (ታሪካዊ እውነታዎች ሳይረሱ ማለት ነው፡፡) በባሕሩ መጠቀም የሚችሉት እጅግ በጣም በቅርበት ያሉና በእጃቸው መንካት የሚችሉት ብቻ ሳይሆኑ የሰው ልጆች ሁሉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር በ60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ተቀምጣ እንደ ነጠላ ጥለት በውሃው ዳር ቀጭን መስመር ሠርተው የተቀመጡ ሀገራት ብቻ ብቸኛ ተጠቃሚ እንሁን ቢሉ ዓለም ከሚከተለው የትብብርና የዲፕሎማሲ መንገድ አንጻር የሚያዋጣቸው አይሆንም፡፡

ከዚህ አንጻር የዓለምን ተሞክሮ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳይ ዲፓርትመንት እንደ እ.ኤ.አ ከ2005 እስከ 2015 International Decade for Action ‹‹ WATER FOR LIFE›› በሚል ርዕስ ባጠናው ጥናት በዓለማችን የውሃ ጥራት እየተጓደለ በአንጻሩ የውሃ ተጠቃሚነትና ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ይጠቅሳል፡፡ በውሃ የተነሳ በሀገራት መካከል አለመግባባት እየተፈጠረ እንዳለና ውሃ ፖለቲካዊ ጉዳይ እስከመሆን እንደደረሰም ያትታል፡፡

ይሁንና አንዳንድ ሀገራት በማይገመት ሁኔታ ምንም አይነት ግጭት ውስጥ ሳይገቡ በትብብርና በመግባባት የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ሲያረጋግጡ ይታያል ይላል፡፡ በውሃ ይገባኛል ምክንያት የሚፈጠሩ ግጭቶችን እና አለመግባባቶችን ለመቆጣጠር ብቸኛው መንገድም ዲፕሎማሲ እንደሆነ ጥናቱ ዓለማቀፍ ተሞክሮዎችን ዋቢ አድርጎ ይገልጻል፡፡

ጥናቱ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አስቀድሞ ባሉት 50 ዓመታት ውስጥ በውሃ ምክንያት ስምምነት ካደረጉና ለናሙና ከተወሰዱ 150 አገሮች ውስጥ ሠላሳ ሰባቱ ብቻ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ተመላክቷል። አብዛኛዎቹ ግን ስምምነታቸውን ጠብቀው ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸው ሳይሻክር እየኖሩ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የምግብና የእርሻ ድርጅት መረጃ ደግሞ ከክርስቶስ ልደት ወዲህ ከ805 ዓመት ጀምሮ ከውሃ ጋር በተያያዘ ከ3 ሺህ 600 በላይ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተደርገዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ አብዛኛዎቹ ስምምነቶች ከመርከቦች መጓጓዣ ጋር ተያይዞ በሐይቆች ይገባናል ወሰን ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡

ባለንበት ክፍለ ዘመን ግን ውሃ የሕልውና ጉዳይ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ በውሃ ሀብት በመልማት፣ የውሃ ሀብትን በጋራ በመጠቀምና በመጠበቅ ላይ ያነጣጠሩ ስምምነቶች እየበዙ መምጣታቸው ተመላክቷል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሀገራቱ በሌላ ጉዳይ ግጭት ውስጥ ቢገቡ እንኳ በውሃ ጉዳይ ያደረጉትን ስምምነት የሚያስከብር ውል ይፈራረማሉ ይላል፡፡

በሰነዱ ላይ እንደተመላከተው፤ ካምቦዲያ፣ ላሆስ፣ ታይላንድ እና ቬትናም በማኮንግ ወንዝ ላይ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ስምምነት እ.ኤ.አ በ1957 ተፈራርመዋል፡፡ እ.ኤ.አ በ1955 እስራኤል እና ጆርዳን የጆርዳን (ዮርዳኖስ) ወንዝን በጋራ መጠቀም የሚያስችላቸውን ስምምነት አድርገዋል፡፡

የናይል ወንዝም ድህነትን ለመዋጋትና ኢኮኖሚን ለማሳደግ በቀጣናው የሚጫወተውን ሚና ታሳቢ ባደረገ መልኩ አስር የተፋሰሱ አባል አገራት እ.ኤ.አ ፌብረዋሪ 1999 በጋራ ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል ይላል፡፡ በተመሳሳይ ዘጠኙ የኒጀር ወንዝ ተፋስስ አባል አገራትም በጋራ የመጠቀም ስምምነት ማድረጋቸውን ሰነዱ ይጠቅሳል፡፡

እንደ ጥናቱ ማብራሪያ እነዚህ ስምምነቶች ዓለም አቀፍ የውሃ ሃብት ትብብርን አስመልክቶ ሁለት ወሳኝ ጉዳዮችን አሳክተዋል፡፡ የመጀመሪያው የሁሉንም ሀገራት ተሳትፎና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚችል ተቋም እንዲፈጠር ማድረጋቸው ሲሆን ሁለተኛው ለጋራ እድገትና ብልጽግና ምቹ የሆነ አመኔታ የሚጣልበትና ድጋፍ የሚደረግለት የትብብር ተቋም እንዲፈጠር ማስቻላቸው እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡

ኢትዮጵያም የባሕር በር ጥያቄ ማቅረቧ የወጪ ገቢ ንግዷን ከማሳለጥና ከጎረቤት አገራት ጋር በትብብር ሠርቶ እድገትና ብልጽግናን ከማረጋጋጥ ያለፈ ፍላጎት የላትም፡፡ ስለዚህ ጥያቄዋ የመጪውን ዘመን ፍላጎት የዋጀና በቀጣናው ሀገራት መካከል የትብብር መንፈስ ተፈጥሮ ሕዝቦችን ከድህነትና ከጉስቁልና ሕይወት ለማላቀቅ ያለመ ነው፡፡

ሜላት ኢያሱ

አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016

Recommended For You