ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድምኒስትሬሽን፣ ማስተርሳቸውን በማርኬቲንግ ማኔጅመንትና ኢንተርናሽል ቢዝነስ ነው፡፡ ሦስተኛ ዲግሪያቸው (ዶክትሬታቸው) ደግሞ ሂዩማን ካፒታል ዲቨሎፕመንት ላይ ነው የሠሩት፡፡ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህር ሲሆኑ ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከማቅናታቸው በፊትም በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ከሌክቸረር እስከ ረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ በመምህርነት አገልግለዋል፡፡ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚም ናቸው፡፡ በዛሬው ዕትማችን ሂዩማን ካፒታል፣ ቴክኖሎጂ፣ ፋይናንስ እና ተያያዥ ጉዳዮችን በማንሳት ቆይታ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡-ሂዩማን ካፒታል ምን ማለት ነው?
ገመቹ ዶ/ር፡- በሀገር ሆነ በተቋም ደረጃ ስንወስድ ሃብቶች አሉን። አንድን ተቋም ውጤታማ የሚደርጉት ደግሞ በርካታ ሃብቶች ተደምረው ነው። ለአብነትም የፋይናንስ፤ የቴክኖሎጂ ብሎም የሰው ኃይል አቅም አለ። በአጠቃላይ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ሃብቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሰው ኃይል ነው። አንድ ድርጅት ውጤታማ የሚሆነው በርካታ የሠው ኃይል ስለተቀጠረ አይደለም። ዕውቀት፣ ክህሎትና አስፈላጊውን ባሕሪ ወደ ሥራ ቦታ ይዞ ሲመጣ እና ለተቋም የአጭር እና ረጅም ጊዜ ውጤታማነት ማበርከት ሲችል የዚያ ተቋም ሃብት ይሆናል። የሰው ኃይል ልማት በደንብ ሲሠራበት ካፒታልም ይሆናል ማለት ነው።
የሰው ኃይል ልማት በጣም ወሳኝ ነው። ከጊዜ ጋር አያይዘን ብንመለከት ከዚህ ቀደም ሲል ድርጅቶች ውጤታማ የሚሆኑትና ተሞክሮዎች የሚያሳዩን ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያላቸው በተወዳዳሪነት ንፅፅራዊ እይታ ተጠቃሚ ናቸው። በተለያዩ ወቅቶች የስኬት መለኪያ ፋይናንስ ሆኖ ነበር። በቀመጠል ቴክኖሎጂ መጣ። ስለዚህ ቴክኖሎጂ በፋይናንሱ መግዛት የቻለ ተቋም ተወዳዳሪ መሆን ችሏል። ቴክኖሎጂ ለውጥ አመጣ ማለት ነው። በዚህ ዘመን ፋይናንስ እና ቴክኖሎጂ በቀላሉ ይገኛሉ።
ለአብነት የዛሬ 10 ዓመት ስልክ መግዛት እና ዛሬ ላይ ስልክ መግዛት አንድ ዓይነት አይደለም። በአሁኑ ወቅም ባንኮች ማንኛውንም ቴክኖሎጂ መግዛት ይችላሉ። ነገር ግን ልዩነቱን እያመጣ ያለው ዕውቀት ነው። አሁን በእውቀት የሚመራ ዓለም ውስጥ ነን። የዕውቀት ኢኮኖሚ ላይ ነን። ስለዚህ ስኬትና ተወዳዳሪነት የሚመጣው እውቀት ላይ ተመሥርተን ሥንሰራ ነው። ዕውቀትና ፈጠራ የሚመነጨው ደግሞ ከሰው ኃይል ነው። ስለዚህ ከቴክኖሎጂም እና ዕውቀት በበለጠ የሰው ኃይል በጣም ወሳኝ ነው። ጠንካራ ተወዳዳሪ የመሆንና ያለመሆን ልየታ የሚመጣው ከሰው ኃይል ነው ማለት ነው።
ስለዚህ ይህን ማድረግ የሚችል፣ የተፈጠረን አዳዲስ ነገር ወደ ገበያ የሚያመጣ፣ በተፈለገው ደረጃ ማምረት የሚችል፣ ደንበኛን በሥርዓት የሚያስተናግድ እና ቴክኖሎጂን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችለው የሰው ሃብት ነው። አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ የሰው ኃይል ስንል ስለቁጥር እያወራን አይደለም። በበርካታ ሠራተኞች ውስጥ ቢሆን ለውጥ የሚፈጥሩ፣ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ፣ ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችሉ፣ ደንበኛን በአግባቡ የሚያስተናግዱ፣ የረጅም ጊዜ እቅድና ስትራቴጂ የሚነድፉ እና መሰል ሠራተኞችን እንዴት መፍጠር ይቻላል ለሚለው ሂዩማን ካፒታል ዲቨሎፕመንት ቁልፍ ሆኖ መጥቷል።
ስለዚህ ዛሬ ተወዳዳሪነት ብቁ ሰው ሃብት ያለው እና የሌለው መካከል ነው። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት ባንክ ብንሄድ አገልግሎት የምናገኘው ወይ በሰው ወይ ደግሞ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ነው። ዲጂታል ዓለምን የፈጠረው ሰው ነው፤ ይህን በአግባቡ እንድንጠቀም የሚያግዘንም ሰው ነው። ለዚህ ሁሉ ወሣኙ የሰው ሃብት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከነበረዎት የሥራ ልምድ እና ሂዩማን ካፒታል ዲቨሎፕመንት የትግበራ ሁኔታን ከኢትዮጵያ አኳያ እንዴት ይመለከቱታል?
ገመቹ ዶ/ር፡– አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ከሁኔታዎች ጋር ለማነፃፀር ስንሞክር፤ 120 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ሀገር ናት። ይህ ማለት ግን ከዚህ ሕዝብ ጋር ሙሉ ለሙሉ የሚመጥን ሥራ እንሠራለን ማለት አይደለም። በእርግጥ ሕዝብ ሲበዛ ጥቅም አለው። ከብዛት ውስጥ ጥራት ያለውን ለማግኘት ያግዛል። ይህን የሚወስነውና ያንን ለማፍራት የሚያግዝ ሥራ መሠራት አለበት። ነገር ግን ዋናው ዓላማ ሰዎችን ምርታማ ዜጋ ማድረግ ነው። በአንድ ድርጅት ውስጥ 100 ሠራተኞች መኖራቸው ሳይሆን የተቋሙን ቀጣይነትና ውጤታማነት የሚወስነው ሠራተኞቹን ብቁ ማድረግ ነው። ለአብነት በተመሳሳይ አንድ ቻይናዊ ፋብሪካ ውስጥ በአንድ ሰዓት የሚሠራውና አንድ ኢትዮጵያዊ በሰዓት የሚሠራው ማነፃፀር ብንጀምር ልዩነቶች አሉ።
ፈጠራንም ብንመለከት እዚህ ሀገር ውስጥ ፈጠራ በምን ደረጃ እየተበራከተ ነው የሚለውንም ማየት ተገቢ ነው። ስለዚህ ማነፃፀሪያችን ብዙ ነገር ነው። የተቋማት ወሳኝ መወዳደሪያቸው ሂዩማን ካፒታል ዲቨሎፕመንት ነው ካልን የእኛ ተቋማት ምን ያክል ተወዳዳሪ ናቸው የሚለውን ማወቅ ተገቢ ነው። እኛ አውሮፓ እና ኤዥያ ሳንሄድ ጎረቤት ሀገር ኬኒያ ጋር ካለው ጋር ብናነፃፅር በፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ልዩነቶች አሉ። አንድ ማወቅ ያለብን ግን በደንብ ከተሠራበት ሁኔታዎችን በተሻለ ደረጃ መለወጥ የሚያስችል አቅምም አለ።
የሕዝብ ቁጥር ጠቃሚ ነው፤ ግን ይህን በአግባቡ ለመጠቀም ትምህርት፤ ሥልጠና እና አስፈላጊ ባሕሪያት ሥርዓት የሚዳብሩበትን መንገድ እስከዘረጋን ድረስ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንችላለን። ግን ንፅፅራችን እንደየሁኔታው ይለያያል። በመሆኑም በደምሳሳው ሁሉንም ማነፃፀር ያስቸግራል። አንዱን ኢንዱስትሪ ከሌላው ጋር ለማነፃፀር የመሪነት አቅም፣ የፈጠራ ብቃትና አቅም፣ አምራችነት፣ አመለካከት በተለይም ነገን አሻግሮ የመመልከት ብቃት ምን ይመስላል የሚለውንና ዓለምን የምንረዳበት መንገድ ምን ይመስላል የሚለውን ማነፃፀር ተገቢ ነው። ከዚህ አኳያ በብዙ ሴክተሮች ብንወስድና ሥርዓታቸውን ብንመለከት፣ ሰዎች የሚለሙበትና የምናሳድግበት መንገድ ብንወስድ በርካታ ነገሮችን መገንዘብ እንችላለን።
ሁላችንም የሥርዓት ውጤት ነን። ስለዚህ ፈጠራን የሚያበረታታ ሥነ ምሕዳር አለን ወይ፣ ሌሎች የፈጠሩትንም ቢሆንም በአግባብ የመጠቀም አቅማችን ምንድን ነው የሚለውን በጥልቀት ማየት ይገባል። እንደ ኢትዮጵያ ግን ብዙ የሚቀሩን ነገሮች መኖራቸውን መጠቆም እፈልጋለሁ። መሥራት እየተገባን ብዙ ያልሠራናቸው ነገሮች አሉ። በተለይም ከሰው ሃብት ኃይል ልማት ጋር በተያያዘ ካፒታል ጋር ገና ብዙ መሥራት ይገባል። ይህን ስንል ሌሎችስ ሀገራት እንዴት ማድረግ ቻሉ፣ እኛስ በምን ደረጃ ላይ እንገኛለን ወደሚለው ንፅፅር እንገባለን። ይህ ከሆነ ብዙ አገራት ብዙ ነገር መፍጠር የሚችሉበት ሥነ ምህዳር ላይ መሆናቸውን እንረዳለን። የትምህርት ሥርዓታቸው፣ ሥልጠናቸው እና በድርጅቶች ውስጥ ከገቡ በኋላ ራሳቸው የሚያሳድጉበት መንገድ ሥርዓት ገንብተዋል። ሌሎች ሀገራት ይህን ለማድረግ ብዙ ርቀት ሄደዋል። ይህን ሳወራ ሀገርን ከሀገር ጋር እያነፃፀርኩ ሳይሆን የሰው ሃብት ሀገርን እንደሚገነባ፤ ድርጅቶችን ተወዳዳሪ እንደሚያደርግ ለማንሳት ነው።
አዲስ ዘመን፡- በእኛ ሀገር ይህን መሠረት አድርገው የተሠሩ የጥናት ውጤቶች ምን ያሳያሉ?
ገመቹ ዶ/ር፡– የሰው ሃብት ልማት ሰፊ ነው። በሀገር ደረጃ ማየት እንችላለን። በሀገር ደረጃ የትምህርት ሥርዓታችን፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ ሀገር፣ እንደ ሴክተር ደግሞ ግብርና ፋይናንስ የመሳሰሉት ብለን ልናነሳ እንችላለን። በሀገር ደረጃ በትምህርት ሥርዓት ሰው የሚለማበትን ጉዳይ ልናነሳ እንችላለን። ስለዚህ በርካታ ጥናቶች አሉ። ለአብነት ፋይናንስ ላይ ትኩረት አድርገን ብናይ፤ የኢትዮጵያ እና የሌሎች ሀገራት የፋይናንስ ሴክተር ተወዳዳሪነታቸው፣ አገልግሎት አሰጣጣቸው፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው፣ የሰው ኃይል እና የአመራር ብቃታቸው ብለን ማነፃፀር እንችላለን።
የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሴክተር ከዕውቀት አንፃር ሲታይ የተከፈተ አይደለም፤ የተዘጋ ሴክተር ነው። ይህ ማለት ደግሞ የሰው ኃይሉም የዚያኑ ያክል በሀገር ውስጥ ትምህርት፣ ሥልጠና እና ማዕቀፍ ውስጥ የተያዘ ነው። አልፎ አልፎ የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ ሄዶ ከማየት የዘለለ ዕይታ የለውም። ሌሎች ሀገራት በዚህ ረገድ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ለምሳሌ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው መሠረት የፋይናንስ ሴክተሩ ሁለት ከመቶ የሚሆን በጀታቸውን ለሰው ኃይል ልማት እንዲያውሉት ነው። ይህ በጣም ትልቅ አኃዝ ነው፤ እንደ ሀገርም ትልቅ ውሳኔ ነው። ይህ የፋይናንስ ሴክተር ትልቅ ቀጣሪ ከመሆን በዘለለ ለኢትዮጵያ ዕድገት ትልቅ አበርክቶ አለው። ሌላው ደግሞ ይህ ሴክተር ከሌላው አኳያ ሲታይ በጣም የተማረ የሰው ኃይል ይፈልጋል። ስለዚህ የተማሩ፣ ፈጠራን የሚያበረታቱ እና ጠንካራ አመራሮችን የምንፈልገውና እንዲሁ የምናገኘውም ከፋይናንስ ሴክተር ውስጥ ነው።
እኛ ሁሌም የምንጠይቀው ይህ የፋይናንስ ሴክተሩ ሁለት ከመቶ የሚሆን በጀታቸውን ለሰው ኃይል ልማት እንዲያውሉት የተወሰነው ምን እየሠሩበት ነው፤ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እየዋለ የሚለው ነው። ለምሳሌ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ አለ። ባደጉትና ጠንካራ ባንክ ሴክተር ባላቸው ሀገራት ስንመለከት 70፤ 20፤ 10 የሚባል ጥናት አለ። እኛም ተቋማት እንዲተገብሩት የምንፈልገው ነው። 70፤ 20፤ 10 የሰው ኃይል ልማት አካሄድ ማለት 70 ከመቶ ሥልጠናና ልማት መካሄድ ያለበት በሥራ ቦታ ነው። ሥራው እየሠሩ መማር አለባቸው። ይህ ምርጥ ማሠልጠኛ ቦታ የሚባለው ሰው በሚሠራው ቦታ እየሠራ ስለሆነ ነው። 20 ከመቶ የሰው ኃይል ልማት አካሄድ ደግሞ ሰዎች እርስ በእርሳቸው ባላቸው ግንኙነት ይማራሉ። 10 ከመቶ የሰው ኃይል ልማት አካሄድ ደግሞ ከሥራ ቦታ ውጭ ወጣ በማለት ወርክሾፕ፣ ኮንፈረንስንና የመሳሰሉትን ያካትታል።
ይህ በጥናት የተደገፈ እና ብዙዎች ውጤታማ የሆኑበት ነው። እኛ ይህን መሠረት አድርገንና ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው መሠረት የፋይናንስ ሴክተሩ ሁለት ከመቶ የሚሆን በጀታቸውን ለሰው ኃይል ልማት እንዲያውሉት የሚለው መነሻ በማድረግ ረገድ ምን ደረጃ ላይ እንዳሉ ለማወቅ ጥናት አካሂደን ነበር። በዚህ አሠራር መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ እያንዳንዳቸው ባንኮች ከ50 ሚሊዮን እስከ አንድ ቢሊዮን ብር የሚበጅቱ አሉ። ነገር ይህን ገንዘቡን እንዴት እያወጡት ነው? 70፤ 20፤ 10 ሥርዓትን ይከተላሉ ወይ? ብሎ ለማየት ተሞክሯል። አሁን ባለው አሠራር 90 ከመቶ በላይ የእያንዳንዱ ተቋም ኢንዱስትሪን ጨምሮ የሚውለው 10 ከመቶ መዋል የነበረበት ወይንም እነዚህ ተቋማት 90 ከመቶ የሚሆነውን ሥልጠና የሚሰጡት በወርክ ሾፕ፣ ኮንፈረንስና በመሳሰሉት ነው።
ይህ ጥናቶች ከሚመክሩት በተቃራኒ ሆኗል። ይህ ማለት 90 ከመቶ የሚሆነው የሕዝብ ሃብት 10 ከመቶ አበርክቶ ባለው ጉዳይ ላይ እየዋለ ነው ማለት ነው። ይህ ክፍተት በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ሳይሆን በበርካታ ሀገራት የሚስተዋል ነው። በእርግጥ መሰል ችግሮችን በአንድ ጊዜ ማቃለል አይቻልም። ሆኖም ብሔራዊ ባንክ በዚህ ላይ በትኩረት መሥራት ይጠበቅበታል። 70፤ 20፤ 10 ወይንም አዲሱ የሰው ሃብት ልማት አሠራር ነው። ይህ በፋይናንስ ሴክተር ብቻ ሳይሆን በኢንዱስትሪ፣ በሲቪል ሰርቪስ እና በሌሎች ሴክተሮችም ይሠራል። ስለዚህ ይህ እንደሃገር መተግበር አለበት።
ሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ውስጥ መተግበር አለበት፤ ፋይናንስ ሴክተር ውስጥ የትኛውም ቦታ የሚሠራ አሠራር ነው። ይህን ስናደርግ ወደ ፋይናንስ ሴክተሩ ስንመጣ ሁለት ክፍተቶች ነው የምናየው። አንደኛ የሥራ ላይ ሥልጠናው በእንደዚህ ዓይነት እየተካሄደ አይደለም። በዘልማድ የሚካሄደው ያለበጀት እንዲሁ ‹‹ስታራክቸርድ›› ያልሆነ ዝም ብሎ እንትና ጋ ቁጭ በልና ልምድ ውሰድ ዓይነት አሠራር፤ እንትና ጋ ቁጭ በልና እሱ የሚሠራውን እይ ተብሎ የሚሠራ ሥራ ውጤታማ አይደለም።
“ስትራክቸርድ ኦን ዘ ጆፕ ትሬንግ” የሚባል አሠራር አለ። የሥራ ላይ አሠራር ሥርዓት ራሱ ስትራክቸርድ ይደረጋል። ፕሮሰስ አለው። ሞጁል አለው፤ አሠልጣኞች አሉት። እነኝህ አሠልጣኞች ማን ናቸው? እዚያው ያሉ ሠራተኞች እንዴት ማሠልጠን እንዳለባቸው የሠለጠኑ ልምድ ያላቸው መሆን አለበት። የራስህን ሰው ነው የምትጠቀመው። ይህ ሲደረግ ሲስተም ነው የሚዘረጋው። በየጊዜው ሰዎች እየሠለጠኑ ይወጣሉ።
ሁለተኛው የሥራ ቦታ ሥልጠና በጀት የለውም። በጀት ያለው የቱ ነው? ሆቴል ሂደህ ውጭ ሄደህ የሚሠለጠን ሥልጠና ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ የሰው ኃይል በተለይ ፋይናንስ ሴክተር ላይ እንዲቀየር ከተፈለገ የሠው ኃይል እንዴት ይለማል የሚለውን አመለካከታችን መቀየር አለበት። ስለዚህ ቅድም እንዳልኩህ 90 በመቶ ለትምህርት የሚበጀት በጀት ወይ ብክነት ነው። ወደ 20 ፐርሰንቱ ልምጣልህ፤ 20 ፐርሰንቱ ስትመጣ በልምድ (ኢንፎርማል) ነው የሚመራው።
በባንኮች ከሄድን ጥሩ የጀመሩት ሥራ አለ። ወደሌሎች ሀገራት ይሄዳሉ። ከሌሎች ሃገራት ጋር በመገናኘት ልምድ ይቀስማሉ። ምክንያቱም ልምድ መቅሰም ሌላ ሃገር መሄድ ያለባቸው እዚህ ሀገር ሆቴል ሄደው የሚሠለጥኑትን ሥልጠና መሆን የለበትም። ጃፓን እንደዚህ አደገች እያልክ ሦስት ቀን ክፍል ውስጥ አስቀምጠህ ብትነገረው ዋው! ሊልህ ይችላል። ኢንተርናላይዝ ግን አያደርገውም። ጃፓን ሂዶ ጃፓኖች እንዴት እንደሠሩት ፤የሠሩትን ማሽን ሲያይ፤ እርስ በርስ ያላቸውን ግንኙነት ሲያይ የሆነ ነገር ይማራል። ግን እዚህ የሦስት ቀን ክላስ የሚያስፈልጋቸውን የግድ ውጭ መሄድ ላያስፈልጋቸው ይችላል።
አዲስ ዘመን፡- የሰው ሃብት በዋናነት ከትምህርት ሥርዓት ጋር የሚያያዝ ነው። በዚህ ረገድስ ያለው ምን ይመስላል?
ገመቹ ዶ/ር፡– የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት መንገዱን የሳተ ነው። ከኢንዱስትሪው ጠቀሜታ አንፃር ከመዘነው ትልቅ ክፍተት አለበት። አሁን የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓት ኢንዱስትሪው ቀድሞታል። በማስተርስም፣ በመጀመሪያ ዲግሪም በለው ኢንዱስትሪው በብዙ እርቀት ነው ያሉት። ቴክኖሎጂን ከወሰድክ ዩኒቨርሲቲዎች የሌላቸውን ቴክኖሎጂ ዘመናዊ የሆነውን ቴክኖሎጂ ኢንዱስትሪው አለው። በልምድም ከወሰድን ኢንዱስትሪዎች ዛሬ የሚሠሩት ዓለም ዛሬ የደረሰችበትን አሠራር ስለሆነ ኢንዱስትሪዎች ይበልጣሉ። በሊደር ሺፕ አቅምም ኢንዱስትሪዎች ይበልጣሉ። አሁን ላይ ያለው የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ኢንዱስትሪን ማብቃት ሳይሆን ከኢንዱስትሪው መማር ነው ያለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ አልተናበበም ማለት ነው?
ገመቹ ዶ/ር፡- የሰው ሃብት ገበያ የሚመራው በፍላጎት እና አቅርቦት ነው። አቅራቢው ማን ነው? የትምህርት እና የሥልጠና ተቋማት ናቸው። የትምህርት ተቋማት ማምረት ያለባቸው ገበያው የሚፈልገውን ነው። ገበያው የሚፈልገውን ታመርታለህ እንጂ አምርተህ ቢገዛኝም ባይገዛኝም ብለህ ወደ ገበያ ዝም ብለህ አትለቅም። የእኛ የትምህርት ሥርዓት እንደዚያ ነው። የሚገዛ ኖረም አልኖረም እያመረተ ገበያ ውስጥ ነው የሚያራግፈው።
ኢንዱስትሪው በሰው እጦት ይሰቃያል እዚህ ጋ ለአንድ ሥራ 10ሺ፤ 30ሺ ሰው ለሥራ ቅጥር እያመለከተ ብቁ ባለሙያ ፈልጌ አጣሁ ይላል። ኢንዱስትሪው የምቀጥረው አጣሁ፤ የሚሆነኝ ሰው አጣሁ ይላል። ይህ በየጊዜው የምንሰማው ነገር ነው። ሳፋሪኮም በቅርቡ ሥራ ቅጥር አውጥቶ የተመዘገበው ሰው ብዛት የጉድ ነው። ባንኮችም ሰው ይፈልጋሉ። እኛም በአቅማችን እንፈልጋለን። ነገር ግን ገበያው የሚፈልገው ብቁ ሰው አይገኝም። ብዙ ድርጅቶች ውስጥ ብንሄድ ቦክስ ፈጥረው ቦክሶቹ ባዶአቸውን የሚቀጥር ሰው አጥተው ተቀምጠዋል። ይህ ማለት ምን ማለት ነው? የኢንዱስትሪውን ፍላጎት መሠረት ያደረገ የሰው ሐብት ልማት አካሄድ የለንም ማለት ነው።
የኢትዮጵያ የሰው ልማት አካሄድ ስንመለከት አቅርቦት ላይ የተመሠረተ እንጂ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ አይደለም። እነዚህን የሚሠሩ ተቋማትን ከተመለከትክ በራሳቸው ደሴት ላይ ያሉ ነው የሚመስላቸው። ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች በራሳቸው ደሴት ላይ ቁጭ ብለው፤ የቲቪቲ ተቋማትንም ብትጨምር ኦኮፔሽናል ስታንዳርድ ብለው የሚፈጥሩት ቁጭ ብለው እራሳቸው ናቸው። ኢንዱስትሪው አይደለም እየፈጠረ ያለው። ይህ ማለት ኢንዱስትሪው የሰው ሃብት የተራበ ኢንዱስትሪ ነው። የሰው ሃብት ይህን ካልቀየረ እና በፍላጎት የሚመራ ካላደረግነው የኢትዮጵያ የሰው ሃብት ልማት ለሚቀጥሉት አስርተ ዓመታት እንደተራበ ይቆያል። የሆነ ጊዜ ላይ ከውጭ ለማምጣት የሚጠበቅበት ጊዜ ላይ እንደርሳለን። ወይም ኢንዱስትሪዎቻችን በሰው ማጣት የሚሰቃዩበት ጊዜ ላይ እንደርሳለን።
አሁን ላይ በሲሚንቶ ፋብሪካዎች በባንኮች እና መሰል መሥሪያ ቤቶች ሠራተኞችን መቀማማት አለ። ስንት ሥራ ፈላጊ ባለበት ሀገር ሠራተኛ መቀማማት አለ ቢባል የሚገርም ነው። ይህ ብክነት ነው። ምክንያቱም ሃገር ኢንቨስት አድርጋባቸዋለች። እንደገና ኢንዱስትሪው ደግሞ ኢንቨስት ያደርግባቸዋል። ይህን ለማስተካከል በሀገር ደረጃ ትልቅ የሆነ የተደራጀ ፖለሲ ያስፈልጋል። በሴክተር ደረጃም ትልቅ ሥራ ያስፈልጋል።
ከፊታችን አንድ እውነታ አለ። ከዩኒቨርሰቲ የሚወጡ ሰዎች ዲግሪ ይዘው በሚወጡበት ጊዜ ጊዜውን የዋጀ ዕውቀት ይዘው መሆን አለበት። መምህራንም ብንመለከት ኢንዱስትሪ ምን እንደሆነ የማያውቁ እና ኢንዱስትሪ ውስጥ ገብተው ሠርተው የማያውቁ መምህራን አሉ። ቢዝነስ ምን እንደሆነ የማያውቁ፤ ስለቢዝነስ ሲያስተምሩ፣ ስትራቴጂ ምን እንደሆነ የማያውቅ መምህር ስትራቴጂ ሲያስተምር ታገኛለህ። በመሆኑም ትልቅ የአቅም መበላለጥ አለ።
አዲስ ዘመን፡- ይህን ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት?
ገመቹ ዶ/ር፡- ይህ እንዳለ ሆኖ በባሕሪው እውቀት በቴክኖሎጂ ምክንያት ቀደም ሲል የነበረ ዕውቀት ዋጋ ቢስ እየሆነ እየመጣ ነው። የትምህርት ሥርዓታችን ዲግሪ መያዝ እና አለመያዝ ልዩነት የሌለበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። አንድ ልጅ ዲግሪ ተምራ ሊስትሮ ስትሠራ የሚያሳይ አርቲክል አነበብኩ። ይህች ልጅ እንዲሁ ነው አራት ዓመት ያባከነችው። እዚህ ላይ በሚቀያየር ዓለም ውስጥ ዜጎች እንደዜጋ አስፈላጊ የምንሆነው ምን ብናደርግ ነው የሚለውን መገንዘብ ያስፈልጋል። ምክንያቱም ትናንት የነበረኝ ዕውቀት ዛሬ አያስፈልገኝም። ስለዚህ ‹‹ሪስኪሊንግ፣ አፕስኪሊንግ›› ተጀምሯል። እንደ ሀገርም ‹‹ሪስኪሊንግ፣ አፕስኪሊንግ›› ወደሚባሉ ነገሮች ላይ መሄድ አለብን።
የቴክኖሎጂ እና የፋይናንስ ሴክተር ለዚህ የተጋለጠ ነው። አሠራሩ ሁሉ እውቀትን መሠረት ያደረገ ነው። ክህሎትን መሠረት ያደረገ ነው። ቴክኖሎጂን መጠቀም አለብን። ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ የምንላቸው ዲጂታል ሶሉዩሽን የምንላቸው በየቀኑ ሲፈበረኩ ነው የሚውሉት። ይህንን ተጠቅሜ ደንበኛን የማላረካ ከሆነ ራሴ ብቁ አይደለሁም ማለት ነው። ቴክኖሎጂን እገዛለሁ እንጂ መጠቀም እየቻልኩ አይደለም። ትልቅ ገንዘብ አውጥቼ ቴክኖሎጂ እየተለማመድኩ እያለ አዲስ ቴክኖሎጂ ይመጣል። ሌላውን እንተወውና የደንበኞች ፍላጎትም በኢትዮጵያ በጣም በፍጥነት እየተቀያየረ ነው። የደንበኛ ፍላጎትን ማርካት አልተቻለም። ይህን ለማደርግ ሥርዓት ካለበጀንለት፤ የትምህርት ሥርዓታችንን ካልቀየርን፣ ኢንዱስትሪው የሰው ኃይል ልማቱን ካልመራው፣ኢንዱስትሪው የሚመራበት ፖለሲ ፍሬም ወርክ ካልተፈጠረ መቀየር አይቻልም የሚል ሐሳብ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- የዝግጅት ክፍላችን እንግዳ ሆነው ሙያዊ ማብራሪያ ስለሰጡን አመሰግናለሁ።
ገመቹ ዶ/ር፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2016