የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመመኘት ብቻ ያልቀረው ወጣት

ሺሀብ ሱሌማን ይባላል ገና የ22 አመት ወጣት ነው። እስከ አሁን የደረሰበትና የሰራው ግን ብዙ ነው። ውልደቱ አሊባሌ በምትባል ከተማ ውስጥ ሲሆን ያደገው ደግሞ በዶዶላ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም እስከሚያጠናቅቅ ድረስ የተማረው በዚህች ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ከልጅነቱ ጀምሮ ቴክኖሊጂ ነክ የሆኑ የህፃናት መጫወቻዎችን ያዘወትራል አብዝቶም ይወዳቸው ነበር፡፡ በቤት ውስጥ የሚገኙ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችም ሲበላሹ የሚያስተካክለው ሺሀብ ነበር፡፡ ይህም በቴክኖሎጂ ላይ ያለውን እውቀት ከልጅነቱ ጀምሮ እንዲያዳብር አድርጎታል፡፡

ሺሀብ በልጅነቱ የሰራቸው አስደናቂ የፈጠራ ስራዎች አሉት ፡፡ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ በነበረበት ወቅት በሚሰጣቸው የተግባር የቤት ስራዎች አማካኝነት የተለያዩ ቁሳቁሶችን ተጠቅሞ ስቶቭ ፣ የዳቦ መጋገሪያና የኩኪስ መጋገሪያዎችን ሰራ፡፡ በዚህ ስራውም በአስተማሪዎቹ ፣ በቤተሰቦቹ ፣ በአካባቢው ማህበረሰብ ማበረታቻን አገኘ ሌሎች ስራዎችን እንዲሰራ እድል ፈጠረለት ፡፡

ሺሀብ ከልጅነቱ ጀምሮ የሚመለከታቸው የተለያዩ እቃዎች ለቤት ውስጥ አገልግሎት የሚውሉም ሆኑ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥቅም ላይ የሚውሉ በሌላ ሀገር የተመረቱ ናቸው ፡፡ በርሱ አገላለጽ ‹‹ ራሴን ካወቅኩ ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ የተመረተ የሚል አንድም እቃ ገጥሞኝ አያውቅም እናም ለምን ሁልጊዜ ገዢ ብቻ እንሆናለን ራሳችን አምርተን አንጠቀምም ከኛ አልፎ ለሌሎች ሀገራት ለምን አንልክም የሚል ጥያቄ ነበረኝ፡፡ ›› የሚለው ሺሀብ ይህንን ጥያቄውን ብቻ ይዞ አልተቀመጠም፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶ የተለያዩ እቃዎችን በመጠቀም የፈጠራ ስራዎቹን መስራት ጀመረ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከእንጨት ላይ ሬዲዮ ሰርቶ በቤት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውል አደረገ። በሪሞት ኮንትሮል የሚከፈትና የሚዘጋ በር በጊዜው ከሰራቸው ስራዎች ውስጥ ናቸው፡፡

ሺሀብ በሚሰራቸው የተለያዩ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ስራዎች አማካኝነት የኢትዮጵያ ኢኖቬሽንና ቴክኖሊጂ ሚኒስቴር ባዘጋጀው ውድድር እ.አ.አ በ2017 ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ እንዲሁም በ2019 ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሽልማት ተቀብሏል፡፡

ሺሀብ የ12ተኛ ክፍል ትምህርቱን ሲጨርስ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርት ክፍልን በማታ መርሀ ግብር ተቀላቀለ። በቀን ጊዜው ደግሞ የተለያዩ የትርፍ ሰዓት ስራዎችን እና ተማሪ በነበረበት ወቅት ይሰራቸው የነበሩ የፈጠራ ስራዎቹን ወደገበያው የማምጣትና የሀሳቡ እና የእጁ ሥራ ውጤት የሆኑ ስራዎቹ ላይ ማተኮር ጀመረ፡፡ ሺሀብ አስቀድሞ ይሰራቸው የነበሩ የፈጠራ ሥራዎቹ በገበያው ላይ እየተወደደለት እየታወቀለት ነበር ፡፡ በመሆኑም ቢዝነሱ ተጠቃሚዎችን ማምጣት ሲጀምር የቢዝነሱ አለም በይበልጥ ሺሀብን ይፈልገው ጀመር ስለዚህም የሁለተኛ አመት የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርቱን አቆይቶ ሙሉ ለሙሉ ወደ ሥራው ተመለሰ ፡፡

በዚያን ወቅትም የፈጠራ ስራዎቹ በገበያው ላይ ተፈላጊ እና ታዋቂ ሆነው ሌሎች የፈጠራ ስራዎቹም ወደ ገበያው ማቅረብ ሲጀምር በአለም አቀፍ ደረጃ የኮቪድ ወረርሽኝ መግባቱ ይፋ ተደረገ፡፡ በዚያን ወቅትም በአካል የሚደረጉ አብዛኛው የሥራ እንቅስቃሴዎች ተከልክለው ነበር፡፡ በመሆኑም የዘመኑን ቴክኖሎጂ ተመራጭ የሚያደርጉ ሲስተም ሶፍትዌሮች አስፈላጊ ሆኑ ፡፡ ሺሀብም እነዚህን ችግሮች የሚያቀሉ ለትምህርት ቤቶች የበይነመረብ የመማሪያ ሶፍትዌር ፣ የተለያዩ የሥራ ተቋማት የሚያስፈልጋቸውን ሲስተሞች ሶፍትዌሮች ሰርቶ ማቅረብ ቻለ፡፡

ሺሀብ በአሁን ሰዓት አይ ስታር የተሰኘ ኩባንያ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሆኖ እየሰራ ይገኛል፡፡ ኩባንያው የተመሰረተው እ.አ.አ በ2021 ከአንድ ጓደኛው ጋር በጋራ ሲሆን ከ35 በላይ ሰራተኞችን በውስጡ ይዞ እየሰራ ይገኛል ፡፡ ኩባንያው አራት ኢንዱስትሪዎች ላይ መሰረቱን አድርጎ የተቋቋመ ሲሆን በሀገራችን ክፍተት የታየባቸው ብዙ መሰራት የሚገባቸው የኢንተርኔትና ሶፍትዌር ኢንዱስትሪ ፣ የኤሌክትሮኒክስ ፣ አውቶሞቲቭና የሮቦቲክስ ኢንዱስትሪን በኢትዮጵያ የተሻለ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

ኩባንያው በተጨማሪም በሀገራችን የሚታየውን ከፍተኛ የስራአጥ ቁጥር፣ በአዲስ አበባ የሚገኘውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት፣ የሚታየው የኑሮ ውድነት ችግር የአቅርቦት እጥረት ነው በማለት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎችን ይሰራል፡፡ በይበልጥ ደግሞ ሺሀብ ከልጅነቱ ጀምሮ ህልሙ የሆነውን ሀገራችን ከውጪ የምታስገባቸውን ምርቶች በመቀነስ በኢትዮጵያ የተመረተ የሚሉ ምርቶችን ማበራከትና እቃዎችን ከውጪ ለማስገባት የምናወጣውን የውጪ ምንዛሬ ለመቀነስ ይሰራል ፡፡

ሺሀብ በኩባንያው ከሰራቸው የፈጠራ ስራዎች ውስጥ እ.አ.አ በ2021 ታይተን የሚባል መኪናን አስተዋውቆ ነበር። የዚህን መኪና ፕሮቶታይፕ ሰርቶ በሚለከታቸው ባለሙያዎች አስገምግሟል ፡፡ ከዚያም ወጣቶችን ከባንክ ጋር በተያያዘ ብድር ገዝተው የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ገቢ እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው፡፡ በአሁን ሰዓትም ምርቱ ተቀባይነት አግኝቶ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ በብዛት እየተመረተ ይገኛል፡፡ ሺሀብ በቅርቡም ኡርጂን የተሰኘ በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሞተር ሳይክል ሰርቷል፡ ይህ ሞተር ሳይክል ለየት የሚያደርገው በኤሌክትሪክ የሚሰራ ሲሆን ነዳጅ ሳያስፈልገው አገልግሎት ይሰጣል፡፡

የሞተር ሳይክል ሲሰራ ሺሀብ አላማው የነበረው በአሁን ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች የተለያዩ እቃዎች ፣ ምግብ እና ሰነዶችን ከቦታ ቦታ በሞተረኛ የማድረስ ለሚመለከተው ሰው የማቀበል ስራ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ይህንን ስራ የሚሰሩት ወጣቶች ሲሆኑ ለዚህ ስራ ሳይክልንም ይጠቀማሉ፡፡

በመሆኑም በከተማው ውስጥ ያለውን የሞተር ሳይክል ፍላጎት ስራው ያለውን ስፋት የተገነዘበው ሺሀብ ኩባንያም አቅርቦቱን ለሟሟላት እና ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች ከአከባቢው ተፈጥሮ ጋር የተስማሙ መሆን አለባቸው፡፡ በመሆኑም ኡርጂን ሞተር ሳይክል በኤሌክትሪክ የሚሰራ በመሆኑ የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል የራሱ አስተዋፅኦ አለው ፡፡

ሺሀብ የሚያመርታቸው የኡርጂን ሞተር ሳይክል 70 በመቶ የሚሆነው ግብአት ከውጭ ሀገር 30 በመቶ የሚሆነውን ከሀገር ውስጥ አድርጎ ይሰራል። ምርቱ ከአንድ ወር በፊት ለገበያ የቀረበ ሲሆን ምርቱን ተጠቃሚዎች ጋር ለማድረስ ከተለያዩ አጋሮች ጋር አብሮ በመስራት ከ100 በላይ የሚሆኑ ምርቶቹን ለገበያ አቅርቧል። ሺሀብ ከተማሪነት ጊዜው አንስቶ የሚሰራቸው የፈጠራ ስራዎቹን እያሳደገ እዚህ ላይ ደርሷል ፡፡

ነገር ግን አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ለመድረስ ብዙ መንገዶችን አልፏል፡፡ የፈጠራ ስራዎቹን ለመስራት በቅድሚያ ሀሳብ መጥቶለት ለመስራት ሲነሳ በሀሳቡ ውስጥ ያለውና ወደመሬት የሚወርደው አለመገናኘት አጋጥሞት እንደሚያውቅ ይናገራል ፡፡ ነገር ግን ሀሳቡን በማስተካከል እና እንደገና በመሞከር አዲስና የተሻለ ነገር ለመፍጠር ይሞክራል፡፡ ከዚህም ባሻገር የፈጠራ ስራውን ሰርቶ ለማጠናቀቅም ይሁን ወደ ገበያለማቅረብ ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ነበሩት ፡፡

ከፈጠራ ስራዎች ጋር በተያያዘ በሀገራችን ለተመረቱ ምርቶች እና ለአዳዲስ የስራ ፈጠራዎች ይሰጥ የነበረው አመለካከት የስራ ፈጣሪዎች ተቀባይነት ለማግኘት ይቸገሩ ነበር የሚለው ሺሀብ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ አመለካከት እየተቀየረ እና ሰዎች ለሀገራቸው ምርት ያላቸው ቦታ እየተሻሻለ መምጣቱን ይናገራል ፡፡ ነገር ግን የስራ ፈጣሪዎች የሚሰሯቸውን አዳዲስ ፈጠራዎች ከሀሳብ በበለጠ ወደ ገበያው እንዲያስገቡ የሚደረገው ድጋፍ አሁንም በቂ እንዳልሆነ እና በተለይም በመንግስት በኩል ድጋፍ ቢደረግላቸው ከዚህ በላይ መስራት እና ሀገርን መቀየር ይቻላል ብሎ ያምናል ፡፡

ዘመኑ ሰዎች የሰሯቸውን ስራዎች ወደገበያ አቅርበው ውጤታማ እንዲሆኑ የተለያዩ የመገበያያ አማራጮችን ያቀረበ ቢሆንም ውድድሩም የዛን ያክል ከፍ ያለ ነው ። በመሆኑም ሺሀብ በአይ ስታር ኩባንያው ለሚሰራቸው ስራዎች የራሱን ድረገፅ በመመስረት ፣ የተለያዩ ማህበራዊ ገፆች ላይ በማስተዋወቅና የማህበራዊ አንቂዎችን በመጠቀም ምርቶቹን ያስተዋውቃል ፡፡

እንደ ሺሀብ አመለካከት ወጣት አንድ ሀገር ያላት ትልቅ ሀብት ነው ብሎ ያምናል ፡፡ እናም ይህ ሀብት ደግሞ ኢትዮጵያ አላት ፡፡ እነዚህም ወጣቶች ሀገራችን ላይ ያሉ ችግሮችን የመፍታት አቅም አላቸው ፡፡ ስለሆነም የተለያዩ የፈጠራ ስራዎች ላይ ፍላጎት ያላቸው በሌሎች ዘርፎች ላይም የሚሰሩ ወጣቶች በሀገራችን በብዙ መንገድ መፍትሄ የሚፈልጉ ችግሮች ያሉ ሲሆን በአካባቢያቸው ያሉ ችግሮችን በማስተዋል እና መፍትሄ የሚሆኑ ስራዎችን ፈጠራዎችን ለማምጣት ቢሰሩ ውጤታማ ይሆናሉ የሚል ጥቆማም ሰጥቷል ፡፡

ሺሀብ ሁሉም ነገር ከሀሳብ እንደሚጀምር ያምናል። በመሆኑም የፈጠራ ሥራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ወደ ሥራ ለመግባት ሲያስቡ የራሳቸውን ተቋም ማቋቋም ቢፈልጉ የብዙ ባለሙያዎች የሙያ የገንዘብ ስብጥር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ብቻቸውን ከመሆን ይልቅ በአቅራቢያቸው ካሉ ሌሎች ወጣቶች ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ ህልማቸውን እውን ማድረግ ይችላሉ ሲል የመተባበርን ሀያልነት ይገልጻል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ጠንካራና ማደግ የሚችሉ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች እየተፈጠሩ ሲሆን መንግሥት እንዲሁም የተለያዩ ባለሀብቶች ድጋፍ ቢያደርጉላቸው ከዚህ የተሻለ ሊሰሩ ይችላሉ የሚል እምነት አለው ፡፡

ሺሀብ እስካሁን ድረስ ባለው የስራ ህይወት ወደቀደመ ትምህርቱ መመለስ ባይችልም ጊዜው ሲፈቅድ ተመልሶ እንደሚጨርሰው ይናገራል፡፡ ነገር ሺሀብ በሚሰራቸው ስራዎች ላይ ቢዝነሱን ለማሳደግ የሚጓዛቸው ሒደቶች በራሳቸው እውቀቱን ለማሳደግ በብዙ ጠቅመውታል የተለያዩ ኦንላይን ትምህርቶችንም ይማራል፡፡

ሺሀብ ለስራው ትኩረት ሰጥቶ መስራቱ ብዙ አዳዲስ ስራዎች ኃላፊነቶች እየተቀበለ ሲሆን፤ በአይ ስታር ኩባንያ አማካኝነት ወደፊት በኢትዮጵያ የተመረቱ ምርቶችን ለማሳደግ በሚሰራው ስራ ወደፊት በኢትዮጵያ የተመረቱ የኤሌክትሪክ መኪናዎች እና ሞባይሎችን የማምረት እቅድ አለው፡፡

ሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን  ህዳር 14/2016

Recommended For You