በተገልጋዮች የተወደሰው የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ

በመዲናዋ የሚነሱ የመሬት ይዞታ ጉዳይ ክርክሮች ለዘመናት የመልካም አስተዳደር ጥያቄ መነሻ እንደነበሩ የሚታወስ ነው።

በተለያዩ ወቅቶች በመሬት ይዞታቸው ላይ ለሚነሱ ክርክሮች መፍትሔ ለማግኘት ወራትን አለፍ ሲልም ዓመታትን የሚጠብቁ ዜጎች አገልግሎቱን በሚሰጠው ተቋም አማካኝነት ምሬት ውስጥ ገብተው እንደነበር በተደጋጋሚ ጊዜያት ሲገለጽ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በመሬት ይዞታ ጉዳይ የሚነሱ ችግሮችን መፍትሔ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት መሻሻሉንና አሠራሩ ቀልጣፋ መሆኑን የተለያዩ ተገልጋዮች ይገልጻሉ።

በመሬት ይዞታቸው ላይ ቅሬታ ይዘው ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ያቀኑት አቶ ውብሸት ጀምበር፤ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ጥያቄያቸውን በፍጥነት ምላሽ አግኝቶ ለተጨማሪ አገልግሎት ወደ ክፍለ ከተማቸው መመለሳቸውን አስረድተዋል። በወቅቱ በመልካም ሥነምግባርና ፈጣን አገልግሎት የተቀበሏቸው የኤጀንሲው ሠራተኞች መሆናቸው አስታውሰዋል፡፡

የአገልግሎት አሰጣጡ ምቹና ቀልጣፋ በመሆኑ የመልካም አስተዳደር ችግር አያስነሳም ያሉት አቶ ውብሸት፤ ፈጣን አገልግሎት አሰጣጡ በተለያዩ ተቋማትም ሊስፋፋ ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። ወደ ኤጀንሲው ከመምጣታቸው በፊት የሚፈልጉትን አገልግሎት በፍጥነት አላገኝም የሚል ስጋት በውስጣቸው እንደነበር የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪዋ ወይዘሮ እሙዬ መላኩ ናቸው።

የመሬት ይዞታ ክሊራንስ ለመቀበል ወደ ኤጀንሲው ያቀኑት ወይዘሮ እሙዬ፤ አገልግሎቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማግኘቴ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል ብለዋል። ወደ ማዕከሉ ከመጡ በኋላ ስጋታቸው ተቀርፎ ሳይጉላሉ አገልግሎቱን ማግኘት በመቻሌ፤ ቀሪውን ጊዜዬን ለምፈልገው ሥራ ማዋል የምችልበት ዕድል አግኝቻለሁ ያሉት ተገልጋይዋ፤ ለተሰጠኝ አገልግሎት ምስጋና አቅርቤ ወጥቻለሁ፤ ይህ ሊለመድ የሚገባው ቀልጣፋ አሠራር ነው ሲሉ አስተያየታቸው ሰጥተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ በበኩሉ፤ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመቅረፍ ረገድ ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ይገልጻል። ከኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ጀምሮ ታችኛው እርከን ድረስ የሚገኙ ሠራተኞች መመሪያን ተከትለው የሚሠሩ መሆናቸውንና የቀድሞ ብልሹ አሠራሮችን በማደስ የተሻለ ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኝ በአካል ተግኝቼ ተረድቻለሁ ይላሉ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግፋወሰን ደሲሳ፤ በመሬት ይዞታ ላይ የሚነሱ ክርክሮች በአብዛኛው በኤጀንሲው አሠራር ሂደት የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንደሚሆኑ ለኢፕድ አስረድተዋል። በ2016 በጀት ሩብ ዓመቱ ወደኤጀንሲው ለመጡ 15 ሺህ የመሬት ይዞታ ክርክር መዝገቦች መፍትሔ በመስጠት የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲቀንሱ መደረጉን ነው ያስታወቁት።

በተጨማሪ 25 ሺህ የተለያየ ይዞታ ያላቸው የመሬት ባለቤትነት ጥያቄዎች ላይ መፍትሔ ለመስጠት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመላክታሉ። እንደ አቶ ግፋወሰን ከሆነ፤ ዜጎች በካርታው ላይ ከተመዘገበላቸው የተለየ የመሬት ይዞታ ካላቸው ጉዳዩ ተጨማሪ ምርመራን ይጠይቃል፤ በመሆኑም በክርክር መዝገብ ተይዞ መፍትሔ እንዲገኝለት ይደረጋል።

ወደኤጀንሲው የሚመጡ የመሬት ይዞታ ክርክሮች ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ ለመሬት ባለቤቶቹ የይዞታ ማረጋገጫ ሰርተፍኬት እንደሚሰጥ አስገንዝበዋል። ተቋሙ በመሬት ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዳይከሰቱ የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን ዘርግቶ እየሠራ ሲሆን፤ የሪል እስቴት ካዳስተር ሥርዓት አንዱ የመፍትሔ አሠራር ሆኖ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ይላሉ።

የሪል እስቴት ካዳስተር ሥርዓት የመሬት መረጃን በካርታ ላይ ሰብስቦ ወደዘመናዊ ሥርዓት የሚገባበትና ስለይዞታው ባለቤቱ መብት፣ የሕግ ክልከላና ኃላፊነት የሚያስረዳ የተደራጀ የቁጥጥር ሥርዓት መሆኑን ነው የሚገልጹት። ወደተቋሙ የሚመጡ የመሬት ጉዳይ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መፍትሔ እንዲያገኙ ከአዲስ አበባ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ይጠቁማሉ። ኤጀንሲው 24 አይነቶችን የአገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የአዲስ መሬት ይዞታ ምዝገባ፣ የካዳስተር አገልግሎት፣ የወሰን ክርክር መፍታት፣ የንብረት ዝውውር፣ የወሰን ይዞታ ቅያሪና ሌሎችም አገልግሎቶች በቀልጣፋ መንገድ እየሰጡ መሆኑን ነው ያመላከቱት።

ቃልኪዳን አሳዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 13/2016

Recommended For You