እንደ ዓባይ ዥረት ፈሶ፤ እንደ ጣና ሐይቅም ተንጣሎ፤ ትናንትናን ከዛሬ አጋምዶ አዲስ ዘመን በትውስታዎቹ ያመላልሰናል። አንዴ ወደ ትናንት ደግሞም ወደዛሬ እየመለሰ የሕይወት ዘመን መስታየታችን ነው። ዓባይ አልነጠፈም፤ ጣናም አልደረቀም። የአዲስ ዘመን የትውስታ ገጸ በረከቶችም ተመዘው አያልቁም። ወጣ ብለን ከባሕር ማዶ አሻግረን እያስታወስን፤ በዓለማችን ዙሪያ ከተከወኑ አስገራሚ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን መራርጠን ልናካፍላችሁ ወደናል። ዝነኛው፤ የጡጫው ጌታ መሐመድ ዓሊ ቂሙን ለመበቀል ሲል መቶ ዛፎችን ቆራርጦ ፈልጧል… ከዛሬ አርባ ዓመታት በፊት አዛውንቱ በርከት ያሉ የእግር ኳስ ጨዋታ ውጤቶችን፤ ከጨዋታው በፊት በትክክል በመገመት 3 ሚሊዮን ብራቸውን ዝቀዋል… ነገሩ እንደዛሬው የቤቲንግ አጀብ ይሆን? ከወደ ጃካርታዋ ሲሊበስ ደግሞ በአይጦች ላይ የጦርነት ዘመቻ በመክፈት እያንዳንዱ ሰው 8 አይጦችን እንዲገድል ትዕዛዝ ተላልፏል:: በአንድ ጀንበርም 2 ሚሊዮን ያህል አይጦችን ገድለዋል። ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ…ደብዳቤዎቹ ከነምላሾቻቸው ይጠብቁናል።
ዓሊ ቂሙን ለመበቀል መቶ ዛፎች ፈልጧል
ባለፈው መጋቢት ወር አገጩ ወልቆ ሆስፒታል እስኪገባ ለብዙ ዓመት የያዘውን ክብር በኬን ኖርተን የተነጠቀው መሐመድ ዓሊ በድጋሚ ግጥሚያ በማሸነፍ ቂሙን ሊበቀል ችሏል።
…….
ዓሊ ይህ ውድድር የሕይወቱ ብርሃን መዳፈኛ መሆኑ ስለገባው መሞት ወይም መዳን የሚለውን ዓላማ ተከትሎ የተጋጠመ ስለሆነ በጨዋታው ላይ ያደረገው እንቅስቃሴ ሁሉ በጣም ጥንቃቄ የተሞላበት እንደነበር ተገልጧል።
የ36 ዓመት ዕድሜ ያለው ዝነኛው ዓሊ ባለፈው መጋቢት ወር ሊሸነፍ የቻለው በመንደላቀቁና አለሁ አለሁ በማለቱ መሆኑ ስለገባው በአሁኑ ጊዜ የቀረበው ቂሙን ለመወጣት አፍ ሳያበዛ በምስጢር ጥንቃቄ የተሞላበት ልምምድ በማድረግ ነው::
ዓሊ የአሁኑ ልምምዱ ከ92 ኪሎ ወደ 86 ዝቅ ያደረገውን፤ ለክብደት ቅነሳና ጥንካሬ እንዲረዳው ከመቶ በላይ ዛፎችን የፈለጠና የቆረጠ መሆኑ ታውቋል።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 1965ዓ.ም )
በሲሊበስ 2 ሚሊዮን አይጦች ተገደሉ
ጃካርታ-በኢንዶኔሺያ ውስጥ በሲሊበስ ደቡባዊ ክፍል ተባዮችን ለማጥፋት በተደረገ ዘመቻ ሁለት ሚሊዮን አይጦች የተገደሉ መሆናቸውን የክፍሉ ባለሥልጣኖች ገለጡ::
እያንዳንዱ የሲድራፕ ቀበሌ ነዋሪ ቢያንስ ስምንት አይጦችን እንዲገድል በተሠጠው ትዕዛዝ መሠረት፤ ሕዝቡ ዘምቶ የተጠቀሱትን አይጦች ለማጥፋት ችሏል። አይጦቹ የተገደሉበት ምክንያት 24 ቶን ያህል የሩዝ ምርት በማውደማቸው ነው።
(አዲስ ዘመን መስከረም 13 ቀን 1966ዓ.ም)
አይጦችን ከቤት ለማባረር የሚመገቡትን ማሳጣት ነው
አይጦች ቤት ውስጥ እየገቡ በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለማድረግ አንዱ የመከላከያ ዘዴ፤ ምግብ እንዳያገኙ ማድረግ መሆኑን ፕሮፌሰር ሰር ዊሊያም ጃክሰን ገለጡ:: አይጦች ወደ ሰዎች መኖሪያ ቤት የሚገቡት ለምግብ ፍለጋ ስለሆነ፤ ሰዎች ዕቃቸውን በሚገባ ከድነውና አይጦች እንዳይደርሱበት ካደረጉ አይጦቹ ሲራቡ ቤቱን ለቀው በመውጣት በውጪ ምግብ ፍለጋ ይሄዳሉ ብለዋል::
…….
ፕሮፌሰር ዊሊያም ጃክሰን ከኢትዮጵያ የእርሻ ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር አይጦች በሰብል ላይ የሚያደርሱትን ጉዳት ለአንድ ወር ያህል በየጠቅላይ ግዛቱ ተዘዋውረው አጥንተዋል::
(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 5 ቀን 1965ዓ.ም)
አዛውንቱ በስፖርት ትንቢት 3 ሚሊዮን ብር አገኙ
ሚስተር ዴቪድ ግሪፊት የተባሉ የ80 ዓመት አዛውንት በስፖርት ትንቢት 3 ሚሊዮን 525 ሺህ ብር ያገኙ መሆኑን ሬውተር ከለንደን አስተላለፈ::
ለቅድማያትነት የበቁት ሚስተር ግሪፊት ከውድድሩ በፊት የስምንት የእንግሊዝ ሻምፒዮን ያለፈውን ቅዳሜ ውጤት በቅድሚያ በትክክል ስለተነበዩ ይኸው ገንዘብ ወዲያው በቼክ እንዲከፈላቸው ተደርጓል።
አዛውንቱም ገንዘባቸውን እጃቸው ካደረጉ በኋላ፤ ይህን ሁሉ ገንዘብ እንድበላ የሚያደርገኝን ዕድሜ ፈጣሪ እንደሚሰጠኝ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል::
(አዲስ ዘመን ጥር 9 ቀን 1965ዓ.ም)
ይድረስ ለጳውሎስ ኞኞ
*ወይዘሮ ንጋትዋ ከበደ ስለ ወንደ ላጤዎች የቤት ንጽሕና ጉድለት የጻፈቸውን አንብቤያለሁ:: ለመሆኑ ወይዘሮዋ ለምን ወንደላጤዎች ቤት ሔደች?
አብርሃም አሉማ
-ሌላውጋማ በሩ ዝግ ነው::
(አዲስ ዘመን ታኅሣሥ 14 ቀን 1965ዓ.ም)
*አፖሎ 15 ጨረቃ ላይ ባረፈችበት ሌሊት አንድ ልጅ ተወለደልኝ:: አሁን ደግሞ አፖሎ 17 በመጠቀችበት ሌሊት ሌላ አንድ ልጅ አግኝቻለሁ:: ያቺኛዋን ስምዋን ጨረቃ ብያታለሁ:: ለዚህችኛዋ የሚስማማትን ስም አንተ አውጣልኝ?
መሐመድ ይማም
ከጅማ
-ይሄ የአየሩ ጉዳይ ተስማምቶሃል ማለት ነው:: ጸሐይ ብትላትስ? ያለዚያም ኮከቤ በላት:: ግን በአላህ ይዤሃለሁ አፖሎ እንዳትላት።
(አዲስ ዘመን ኅዳር 10 ቀን 1965ዓ.ም)
*እስከዛሬ ድረስ እኔ የማጠናው ማታ ማታ ጫት እየቃምኩ ነው:: ግን ከዚህ የተሻለ የአጠናን ዘዴ እንዳለህ ንገረኝ ምክንያቱም ዘንድሮ የአሥራ ሁለተኛን ክፍል መልቀቂያ ፈታና ስለምወስድ ነው::
-ኋላ ሱስ ሆኖብህ እንዳትቸገር ተጠንቀቅ:: ለጥናቱ ማታ ጥሩ ነው:: ቀን ሙቀቱ አያስጠናህም::
(አዲስ ዘመን ኅዳር 23 ቀን 1965ዓ.ም)
*ከዚህ በፊት የጡት ማሳደጊያ አለ ብለህ ነበር:: እኔ ደግሞ ጡቴን ለመቀነስ ስለምፈልግ እባክህ መቀነሻ ያለበትን ንገረኝ?
በዛብሽ በቀለ
— መቀነሻው የት እንደሚገኝ አላውቅም:: እንደኔ እንደኔ ባትቀንሽው መልካም ይመስለኛል:: ከሴት ልጅ መልክ አንዱ ጡት ነው:: የሌላቸው ተቸግረው በጡት መያዣ አሳድገውት ሲሔዱ አንቺ ልቀንስ ማለቱን ትተሸ «ደህና ጡት የሰጠከኝ አምላክ ተመስገን» እያልሽ ኑሪ::
(አዲስ ዘመን ሰኔ 10 ቀን 1965ዓ.ም)
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2016