የአባቷ ልጅ

ያደገችው ብዙ የቤተሰብ አባል የሚንጋጋበት ውስጥ ነው። ከስልሳ በላይ ሰዎች በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩበት ነው። እናትዋ የእንግሊዝ ሀገር ዜጋ ቢሆኑም ነጭ መሆናቸው እስኪረሳ ድረስ በሀበሻዊት ሴት ወግና ማዕረግ ቤታቸውን ያስተዳድሩ ነበር።

እናትነት፤ ሚስትነት ልዩ ስጦታቸው እስከሚመስል ድረስ ልጆቻቸውን ባሰማሩት መስመር ልክ ሲመሩና ለስኬት ሲያበቁ የኖሩ እናት ናቸው። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ሆነውም በርካቶችን ለቁም ነገር አብቀተዋል። እኚህ እናት ወልደው ያሳደጓቸው ልጆች ምን ዓይነት ይሆኑ?

አባትየው ደግሞ ዶክተር ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ይባላሉ። ዶክተሩ በትግራይ ክልል በዓድዋ ከተማ አቅራቢያ ባለችው “አዲ-እስላም” የተሰኘች የገጠር መንደር ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1955 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተቀበሉ በኋላ የማስትሬትና ዶክትሬት ዲግሬያቸውን ከዌልስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ ዶክተር ተወልደ በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ፋኩልቲ ዲን ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከ1975 እስከ 1983 በነበረው ዘመን ደግሞ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው ሰርተዋል፡፡

አስመራ በሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ) እጅ ስትገባ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጥተው የባህል ሚኒስቴር ምክትል ሚኒስትር ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በኋላም ለብዙ ዓመታት በሚታወቁበት የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተርነት አገልግለዋል፡፡

ዶክተር ተወልደ ከእንግሊዛዊት ባለቤታቸው ሱ ኤድዋርድስ ጋር አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚያስተምሩበት ጊዜ ነበር የተገናኙት። ፍቅር የማያስተሳስረው የሰው ፍጥረት የለምና ዘር ቀለምን ሳይቆጥሩ ሰው መሆናቸውን ብቻ አስበልጠው ለወግ ማዕረግ በቁ። እነ ዶክተር ተወልደ ከአብራካቸው ከወጡት ሶስት ሴት ልጆች መካከል የመጀመሪያ ልጅ ሮማን ተወልደ ብርሃን ገብረ እግዚአብሔርን ለዛሬ የሴቶች አምድ እንግዳችን አድርገን ጋበዘናታል።

የመልካም ዘር ፍሬ ሲታይ ይለያልና ብዙ ሰዎችን የምታግዝ ለወጣቶች ተስፋ የሆነች ሴት እንደሆነች ይመሰክሩላታል። ያሰበቻትን ዳር ካላደረሰች አትቆምም የሚባልላት ይህች ሴት «በሕይወቴ ተምሳሌቴ እናቴ ናት፤ ቤት ውስጥ ሚስትም እናትም ናት። ውጭ ደግሞ ጐበዝና ጠንካራ መምህርት» ትለናለች። የሮማን እናት ሱ ኤድዋረድስ ለረዥም ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩ መምህርት ናቸው።

ከመምህርነት ሥራ በኋላም በበጎ አድራጎት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። በጎ አድራጎት መስጫው ለገበሬዎች የተፈጥሮ ማዳበሪያ አሰራር በማሰልጠን ምርታማ ሆነው ኑሯቸው እንዲለወጥ የሚያደርግ ገብረሰናይ ተቋም ነበር። ከሥራ በተጨማሪ ቤታቸው ውስጥ የሚያደጉ ብዙ ልጆች በተለይ በክረምት ፒያኖ፤ ሥዕል፤ እጅ ሥራን በማሰልጠን ልጆቹ የተለያዩ ክህሎቶች እንዲኖራቸው በማድረግ እንዳሳደጓቸው ታስታውሳለች።

«ልጅ ሆነን ቤት ውስጥ ግማሽ ቀን ትምህርት ቤት ከሄድን በግማሹ ጊዜ የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት ግዴታ ነበር።» የምትለው ሮማን «እናቴ የምታሳድጋቸውም ሆኑ የወለደችን ሶስት ልጆች በመካከላችን ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይፈጠርብን በአንድነት በፍቅር እንድናድግ ብዙ ስርታለች» ብላለች።

ወይዘሮ ሱ ኤድዋረድስ ትውልድ ሀገራቸውን እንግሊዝን ረስተው ፍፁም ኢትዮጵያዊት የምትመሰል እናት፤ የባሏን ቤተሰቦች ተቀብለው በሀበሻ ወግ በመስተንግዶ የምታስደስት ሴት እንደነበሩ ታስታውሳለች። «ሁልጊዜ በእናቴ ሚዛን ስለካ ልክ እሆን ይሆን እያልኩ እራሴን እመዝናለሁ» የምትለው ሮማን በምንም ነገር አለመሰልቸትን ግን ሙሉ ለሙሉ ከእናቷ መውረሷን ታስረዳለች።

ወይዘሮ ሱ ኤድዋረድስ እግሊዛዊነታቸውን ፍጹም ትተው ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ኖረውና ኢትዮጵያዊ ሆነው ነው የኖሩት፡፡ ከዚህ ዓለም ሲለዩም ‹‹ሀገሬ ኢትዮጵያ ነች፤ እዚሁ ቅበሩኝ›› ብለው በኑዛዜያቸው መሠረት እዚሁ ኢትዮጵያ ነው የተቀበሩት፡፡

ሮማን ቤተሰባቸው ውስጥ ወደ ስልሳ የሚጠጉ ልጆች አብረው ማደጋቸውን ታስታውሳለች። በዝምድናም ይሆን በሌላ በአጋጣሚ ወደ ቤተሰባቸው የመጣ ሰው ሁሉ ከልጆቻቸው እኩል በማሳደግ ለወግ ማዕረግ ማብቃታቸውን ትናገራለች። «ልጅ ሆነን አታ የሚባሉ ሞግዚት ነበሩን፤ እስካሁንም አሉ። ወደ እኛ ቤት ሲመጡ ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ነበር የመጡት። አታ እንደ ሁለተኛ እናት ቤቱን ያስተዳድሩ የነበረ ሲሆን ልጆቻቸውም ከእኛ እኩል ተምረው አሁን ትልቅ ደረጃ ደርሰዋል» ትላለች ሮማን በትዝታ ወደ ልጅነት ቤታቸው ተጉዛ።

የዛሬ ሃምሳ ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ የተወለደችው ሮማን እስከ አስራ አንደኛ ዓመቷ ድረስ አዲስ አበባ ሕዝባዊ ሠራዊትና ምስካየ ኅዙናን የተባሉ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተምራለች። በአስራ አንድ ዓመቷ አባቷ ዶክተር ተወልደ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ሆነው በመሾማቸው የተነሳ ወደ አስመራ ከተማ ከቤተሰቦቿ ጋር በመሄድ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል አስመራ ተማረች። ከዛ በአስመራ በነበረው ሰላም መደፍረስ የተነሳ ኢህአዴግ ከመግባቱ ከአንደ ዓመት በፊት አዲስ አበባ በመምጣት የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተናን ወሰደች።

«ከሁለት የተማሩ ወላጆች መወለዴ ትምህርቴ ላይ ትኩረት እንድሰጥ አድርጎኛል» የምትለው ሮማን ማትሪክን በጥሩ ውጤት በማለፍ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያዋን ያዘች። ከዛም ብዙም ሳትቆይ ወደ እናቷ የትውልድ ሀገር እንግሊዝ ሀገር ሄደች።

ሮማን በተማረ ቤተሰብ ውስጥ ማደጓ በትምህርት ውጤታማ እንድትሆን ከማድረጉ ባሻገር ለመጻሕፍት ልዩ ትኩረት እንድትሰጥ፤ ከብዙ ሰዎች ጋር መሆንና ማህበራዊ ሕይወት የሚያስደስታት፤ እና ምንም ዓይነት ነገር ቢሆን ጫፍ ሳታደርስ እንዳታቆም እንዳደረጋት ትናገራለች።

በእንግሊዝ ሀገር ቆይታዋ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ማስተርስ ያዘች። ከዛ በኋላ ለምትወደው የመጽሐፍ ድርሰትና ሕትመት ሥራ እንዲያግዛት አርትኦት ተማረች። በመቀጠል ሴክሬታሪያል ሳይንስ፤ የኮምፒውተር ኮርሶች የተለያዩ ትምህርቶችን በመማር ካላት የሕይወት ልምድ ጋር ሁሉን ሞካሪ በሁሉም ዘርፍ የበቃች ባለሙያ እንድትሆን አድርጓታል።

ከትምህርት በኋላ በእንግሊዝ ሀገር በፀሐፊነት፤ በጉዳይ አስፈፃሚነትና በተለያዩ የአስተዳደር ሥራዎች ላይ ተሰማርታ በሀገረ እንግሊዝ መቆየቷን ታስታውሳለች።

ወደ ኢትዮጵያ ጠቅልላ ከገባች አስር ዓመታት ሆኗታል። ወደ ትውልድ ሀገሯ ለመኖር ወስና ከመጣች በኋላ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ በመሆን፤ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ የበላይ ኃላፊ በመሆን ኮቪድ ወረርሽኝ በዓለማችን ላይ እስኪከሰት ድረስ አገልግላለች።

«በኮቪድ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ሥራ በመተው የተወሰኑ የግጥም መጻሕፍቶችን፤ የሕፃናት መጻሕፍትን መጻፍ፤ ግጥሞች በእንግሊዝኛ ቋንቋ በመጻፍ አሳተሜአለሁ» የምትለው ሮማን ለሶስት ዓመታት ያህል ከራሷ መጻሕፍቶች በተጨማሪ የሌሎች ደራሲያንን መጻሕፍት የማሳተምና የማከፋፈል ሥራዎችን ሰርታለች።

የነፍሷ ጥሪ የሆነውን የመጻሕፍት ጉዳይ ከግብ ለማድረስ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጋ ትታ ሙሉ ለሙሉ መጻሕፍትን ወደ ማሳተም፤ ወጣት ደራሲዎች የጻፏቸውን ጥሩ ይዘት ያላቸውን መጻሕፍቶች ማሳተምና ማከፋፈል ሥራን መሥራት ላይ ሙሉ ትኩረቷን አደረገች።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን የሴቶች ደህንነትና ሰላም ኢንስቲቱዩት የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ እየሰራች ትገኛለች። «ድርጅቱ ጡረታ በወጡ አምባሳደሮች የተቋቋመ ሲሆን ሴቶች ሰላምና ደህንነት የሚጠበቅበትን አማራጮች ለማሳየትና ለማስጠበቅ የሚሰራ ድርጅት ነው» የምትለው «ሮማን በሙያዬ ሀገሬ የምትፈልገኝ ቦታ ሁሉ ተገኝቼ ብሰራ ደስታዬ ነው» ትለናለች።

«የሕይወት ፍልስፍናዬ አልሸነፍም ባይነት ነው የምትለው ሮማን ይህ ማለት በምንም ሁኔታ ውስጥ ስኬት ላይ እስከሚደረስ ድረስ መታገል የሕይወቴ አካል ነው» ብላለች። «ለእኔ ስኬት የሚደረስበት ሳይሆን የሚኬድበት መንገድ ነው» የምትለው ሮማን መንገዱ ላይ የሚገጥሙ እንቅፋቶችን እየተሻገሩ ማለፍ፤ መሰናክሎችን መዝለል፤ አለመቆም ሁሉ ስኬት ብላ እንደምትጠራው ታብራራለች። «እኔ ለኢትዮጵያ ሴቶች የምመክረው እናቶች ልጆቻቸውን ቁጭ ብለው ማሳደግ ታላቅ ሥራ ቢሆንም የተለያየ ሥራዎችን መሥራት እንደሚኖርባቸው ነው» ትላለች። ሴቶች ብዙ ክህሎት እያላቸው እጅና እግራቸውን አጣጥፈው መቀመጣቸው ሰብዓዊ መብቶቻቸውን ለማሰነጠቅ እንደፈቀዱ ያስቆጥራቸዋል ትላለች።

የገንዘብ አቅማቸውን ማሳደግ፤ በዕውቀት ራስን ማዳበር፤ የራስ መተማመናቸውን መጨመር ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን ለልጆቻቸው፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ማህበረሰቡ ጠቀሜታው የላቀ ነው።

«ኢትዮጵያዊት ሴት ነኝ። የእናቴ ሀገር እንግሊዝ ሲሄድ እንኳን እንደ አንድ ስደተኛ ከመኖር ያለፈ የሀገር ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም ነበር» የምትለው ሮማን » ኢትዮጵያዊነት ሱስ እስከሚመስለኝ ድረስ እንግሊዛዊት ለመሆን ሞክሬ አላውቅም ነበር» ትለናለች። በእናቷ ትውልድ ሀገር ውስጥ ሆና ፍፁም በባይተዋርነት ስሜት ትሰቃይ እንደነበር ስታስታውስ።

ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያለው የበዛ ወግ አጥባቂነት እንደሚገርማት የምትናገርው ሮማን ማህበራዊ ግንኙነት ጥሩ ቢሆኑም በተለይ የኢትዮጵያ ባህል ሴቶች ላይ በጣም የጠበቀ መሆኑ የወንዶች የበላይነት የጎላ መሆኑ ትንሽ ከበድ እንደሚል ታስረዳለች።

እንግሊዞች ግን ወግ አጥባቂ ቢሆኑም ሴት ወንድ ተብሎ የሚለያየው ነገር የለም። ማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ልጅ አድጎ ሥራ ሰርቶ አግብቶ ወልዶ መኖርን ቢጠበቅም ያ አልሆነም ብሎ ግን ሀሜት ዓይነት ባህሪ አለመኖሩ ልዩነት አለው።

እዚህ ማህበረሰብ ውስጥ ሴት ልጆች በልጅነታቸው ቢያረግዙ አይደገፍም ስህተታቸውንም ለማስተካከል የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት አለመኖሩን ታነሳለች። አእምሮ ህሙማንን የሚሰበስብ የለም። ቤተሰባዊ ትስስር ቢኖርም አደባባይ ለሚወጡ ሰዎች ግን ከመጠቋቆም ባለፈ የመፍትሔ አካል ሲሆኑ አይታየም። ይህ ደግሞ እንደ ማህበረሰብ የሚያስተች በመሆኑ ቢስተካከል የሚል ሃሳብ ታነሳለች።

ሌላው ሴት በተፈጥሮዋ ከወንድ የምትበልጥበት፤ ከወንድ እኩል የማትሆንበት፤ እኩልም የምትሆንበት ሁኔታ አለ። ሴት ወንድ እኩል እንሁን በማለት ከመፎካከር ይልቅ ሁሉም የተለያየ ተፈጥሮ ባለቤት መሆኑን በመረዳት ለስኬት አብሮ መሥራት የተሻለ አማራጭ መሆን አለበት ትላለች።

«በሀገራችንም ማህበረሰብ ውስጥ የሚገርመኝ ወንዶች ኩሽና አይገቡም ማለት ሴት መኪና አትነዳም ከማለት አይተናነስም።» የምትለው ሮማን ሰው ሰው በመሆኑ እኩል ነው በሚለው ሃሳብ በመግባባት ክርክርን መራቅ እንደሚገባ ትናገራለች።

ቀሪ ዘመኗንም ለራሷንም ሆነ የሌሎችን ስኬት በሚያቀላጥፉ ተግባራት ላይ በመሰማራት ለማሳለፍ እንደምታስብ ነግራን የሞቀ ጨዋታችንን አብቅተናል። ቸር ይግጠመን።

አስመረት ብስራት

አዲስ ዘመን ኅዳር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You