አቶ ኢያሱ ወሰን የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ

 የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ወሰን የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል። የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ዛሬ ሲካሄድ አቶ ኢያሱ በሙሉ ድምፅ መመረጣቸው ታውቋል።

አቶ ኢያሱ ፕሬዚዳንት ሆነው በተመረጡበት ውድድር የካሜሮኑ ዕጩ በርትራንድ ሜንዱጋ እንዲሁም የሞሮኮ ሞሐመድ ቦድር ተወዳዳሪ ነበሩ። ይህም አቶ ኢያሱ የአፍሪካን ስፖርት በበላይነት በመምራት ከቀድሞ የካፍ ፕሬዚዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በመቀጠል ሁለተኛ ኢትዮጵያዊ አድርጓቸዋል።

አቶ ኢያሱ ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ለመላው ኢትዮጵያውያን የእንኳን ደስ አለን መልእክት አስተላልፈዋል።

አምባሳደሩ ባሰፈሩት መልእክት “የኢትዮጵያን ቦክስ ፌደሬሽን በመምራት የተሻለ ልምድ እና እውቀታቸውን በመስጠት የሚታወቁት አቶ እያሱ ወሰን ለዚህ የበቁት በፌዴሬሽኑ፣ በመንግሥትና በስፖርት ቤተሰብ የተቀናጀና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራና ሀገራችን ልዩ ጉባዔውን በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ በመቻሏ ነው።” ብለዋል።

ከታላቁ የስፖርት አመራር ከክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በኋላ ኢትዮጵያ የአፍሪካን ስፖርት ለመመራት ያገኘችው ታላቅ ውጤትና እድል ተደርጎ እንደሚወሰድም አምባሳደሩ አክለዋል። “ከጥላቻና ከመገፋፋት ወጥተን በጋራ ለሀገራችን ስንቆም የተሻለ ውጤትና እድል ሀገራችን ማግኘት እንደምትችል ያስመሰከረ ምርጫ ነው።” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ከዚህ በተጨማሪ የአቶ ኢያሱ መመረጥ በኢትዮጵያ የሚወደደውን የቦክስ ስፖርት የሚያነቃቃ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፕሮፌሽናል ውድድሮች በሀገራችን እንዲዘጋጅ እድል የሚፈጥር ፣ ገቢያችንን የሚጨምር፣ የሀገራችንን በጎ ገፅታ ለመገንባት የተሻለ እድል የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ በስፖርት ማዘውተሪያ በተለይም በቦከስ ስፖርት ያለብንን የማዘውተሪያ ችግር ለመፍታት መልካም አጋጣሚን እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

“የመረጡንን አፍሪካውያን ወንድሞች እናመሰግናለን፣ ድሉ የጋራችን የተሰጠንን ሃላፊነትም በጋራ የምንወጣው ቀጣዩ የቤት ሥራችን ይሆናል” ሲሉም መልእክታቸውን ቋጭተዋል። አቶ ኢያሱ የአፍሪካን ቦክስ ስፖርት በመምራት ከግዙፍ የስፖርት ትጥቅ አምራቾች ጋር ባላቸው ቁርኝነት አማካይነት የስፖንሰርሺፕ ስምምነቶችን ወደ ቦክስ ፌዴሬሽኖች በማምጣት በፋይናንስ እጥረት እየተፈተነ ያለውን ስፖርት ለማሳደግ ዕቅድ እንዳላቸው ተጠቁሟል፡፡

ከዚህም በላይ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ፌዴሬሽኖች የቦክስ ስፖርትን እንዲያዘምኑና ፕሮፌሽናል መንገድ እንዲከተሉ ለማስቻል የተለያዩ ሥልጠናዎችንና የትምህርት ዕድሎችን ለማመቻቸት ዕቅድ አላቸው። ፕሬዚዳንቱ የኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽንን መምራት ከጀመሩበት ወቅት አንስቶ ፌዴሬሽኑ የነበረበትን የፋይናንስ እጥረት ለመቅረፍ በግል ድርጅታቸው አማካይነት ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ይነገራል።በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኑ በተለያዩ አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ ማስቻላቸው ተገልጿል።በቅርቡም ለፓሪስ ኦሊምፒክ ማጣሪያ በሴኔጋል በተደረገ ውድድር ኢትዮጵያ እስከ ፍፃሜ መድረስ የቻለችበት ውድድር እንደ ምሳሌነት ይነሳል፡፡

አቶ ኢያሱ አህጉር አቀፍ ውድድሮች እንዲበራከቱ ማድረግና ስፖርቱ ከትምህርት ቤት ጀምሮ እንዲዘወተር ማድረግ ዋና ተግባራቸው መሆኑን ከምርጫው አስቀድሞ በሰጡት መግለጫ ጠቅሰዋል።ከዚህም ባሻገር የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ከዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚያጠናክሩና አፍሪካ በኦሊምፒክ ላይ ያላት ተሳትፎ እንዲሰፋ የማድረግ ዕቅድ እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን መቀመጫው አዲስ አበባ እንደሚሆን ጥረት ከማድረግ ጀምሮ፣ ከዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር ጋር በመነጋገር ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ በአዲስ አበባ ለማስገንባት ውጥን እንዳላቸውም ጠቅሰዋል።ግንባታውን ለማከናወን ከዓለም አቀፉ ቦክስ ማኅበር እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር እንደሚመደብላቸው የጠቀሱት አቶ ኢያሱ፣ በተለምዶ ትንሿ ስታዲየም የምትባለው ቦታ ላይ ግንባታውን ለማድረግ ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ጋር መወያየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽንን የሚመሩ አመራሮች ከከፍተኛ የገንዘብ ማጭበርበርና ሙስና ጋር ስማቸው ይነሳል።ይህም አመራሮቹ ስፖርቱን ለማሳደግ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን የሚለቀቁ ገንዘቦችን ለአባል ፌዴሬሽኖች እንደማይለቁና አመራሮቹ ለግል ጥቅም እንደሚያውሉት በተደጋጋሚ ይገለጻል፡፡

የአፍሪካ ቦክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ማክሰኞ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. በዱባይ እንደሚደረግ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም፣ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ የቦታ ለውጥ ለማድረግ ተገዷል። መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው ‹‹በአፍሪካ እንጂ በሌላ አህጉር መሆን አይገባውም›› የሚል መከራከሪያ በመቅረቡ የአፍሪካ ቦክስ ኮንፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባዔውን እንዳራዘመና የቦታ ለውጥ እንዳደረገ ታውቋል።

 ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ህዳር 9/2016

Recommended For You