የኢትዮጵያዊያን እንግዳና ስደተኛን በክብር የመቀበል ባህል ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። ጉቦ መቀበል ነውር መሆኑንም በተግባር ያሳዩ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ይህ የሆነው የነብዩ መሃመድ ተከታዮች ከመካ ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ እምነታቸው የተለየ ነው ተብለው አልተገፉም።
በወቅቱ ለነበረው ንጉሥ እጅ መንሻ ተሰጥቶት አሳልፎ እንዲሰጥ ሲጠየቅም ጉቦ ሐጥያት ነው፤ ስደተኞቹም እንግዶቻችን ናቸው አሳልፌ አልሰጥም በማለት የኢትዮጵያዊያንን እንግዳ ተቀባይነትና ተንከባካቢነት አሳይቷል። ይህ በዓለም መድረክ አፋችንን ሞልተን ከምንናገርባቸው ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን አንዱ ነው።
ኢትዮጵያዊያን የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የማንነት ልዩነቶች ሳገይድቧቸው ዘመናትን አብረው ተሻግረዋል። በጎና ክፉ ጊዜን በመደጋጋፍ። ይህ የሆነው ግን ጨቋኝ ስርዓቶች በነበሩበት፣ አድሎአዊ መሪዎች በህዝብ ስም እየነገዱ አንዱ ህዝብና ሃይማኖት የበላይ እያሉ ስርዓታቸውን ለማስቀጠል ጥረት በሚያደርጉበት ወቅትም ጭምር አንድነታቸው አልላላም፣ በጠላትነት አልተያዩም። ከዚህ ይልቅ ኢትዮጵያዊያን የጋራ የሆኑትን እሴቶቻቸውን ይዘው በጋራ ዘልቀዋል። አሁንም እንደዚያው አሉ።
በአንድ ሃገር የሚኖሩ ህዝቦች ምንም እንኳ ልዩነት ቢኖራቸውም ለዘመናት አብረው ሲኖሩና ክፉና ደጉን አብረው ሲያሳልፉ የጋራ እሴቶችን ይገነባሉ። ኢትዮጵያዊያንም በረጅም ዘመናት የአብሮነት ጉዟቸው የገነቧቸው የጋራ እሴቶች አሏቸው። አብሮነት፣ መቻቻል፣ የጋራ ጠላትን በጋራ መመከት፣ በክፉ ጊዜ መደጋጋፍ፣ በመልካም ጊዜም በትብብርና በደስታ ማሳለፍን የመሳሰሉ።
እነዚህ አሴቶች ህዝቦችን የሚያስተሳስሩ ድርና ማግ ከመሆናቸውም በላይ በቀላሉ ሊጠፉ የማይችሉ ሀብቶችም ናቸው። እነዚህ ሀብቶቻንን ለጋራ መግባባትና ለሃገራዊ አንድነት መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ሁሉም ማወቅ አለበት። ማወቅ ብቻ ሳይሆን በተለይም በአሁኑ ጊዜ ጥቅም ላይ ማዋል አለባቸው። ለዚህ ደግሞ እነዚህን እሴቶች ለአሁኑ ትውልድ ማሳወቅ ላይ መሠራት አለበት።
የማንኛውም ሃገር መሰረታዊ ጥንካሬ ምንጩ ሀገረ መንግሥቱ የተመሰረተበት የዜጎች የጋራ እሴት ነው። ምክንያቱ የጋራ እሴቶች የአንድ ሃገር ህዝቦች ማስተሳሰሪያ ገመዶች ናቸውና። እኛ ኢትዮጵያዊያንም በቋንቋችን፣ በባህላችን፣ በወጋችን ከአካባቢ አካባቢ፣ ከብሄር ብሄር ልዩነቶች ቢኖሩንም በርካታ የሚያስተሳስሩን የጋራ እሴቶች አሉን። እነዚህ የጋራ እሴቶቻችን ለኢትዮጵያ አንድነት አስተዋጽኦ አድርገዋል። አሁንም እያደረጉ ነው። ወደፊትም እንዲያደርጉ ጠንክረን መሥራት አለብን።
ኢትዮጵያዊን በታሪክ አጋጣሚ በውጭ ወራሪ ኃይሎች በተፈተኑበት ወቅት እንኳ ለመለያየትና ለመበታተን አልፈቀዱም። በጣሊያን ወረራ ወቅት ሃገር ያለ መሪ ለአምስት ዓመታት ስትቆይ በአንድነት ሆነው ሃገራቸውን ነፃ በማውጣት መሪና ሉዓላዊ አገር እንዲኖራቸው ያደረጉት ለዘመናት በአካበቱት የጋራ እሴቶቻቸው በመጠቀም እንጂ ልዩነታቸውን አጉልተው አይደለም።
ልዩነታቸውንአጉልተው ቢከፋፈሉማ አሁን ያለችው ኢትዮጵያ ይህ ትውልድ የሚያውቃት በታሪክ ብቻ በሆነ ነበር። ስለዚህ ሃገር እንዲኖረን ያደረጉ እሴቶች ዛሬም ይጠቅሙናል። ለሚያጋጥመን ፈታና መውጫ መንገዶችም ናቸው። ስለሆንም እንወቃቸው፣ ጥቅም ላይ እናውላቸው።
ከሃገራችን ምስረታ ጀምሮ ያለፍንባቸው ጊዜያት አልጋ በአልጋ አልነበሩም። ነገር ግን ህዝባችን በአካበተው የጋራ እሴት አብሮነቱን ጠብቆ ዘልቋል። ይህ ሃገር እስከአሁን ዘመን ያደረሰው የአንድነት የጋራ እሴት ለዚህ ትውልድ ትልቅ ትምህርት ነው። ስለሆነም መልካም እሴቶችን በማጎልበት በቀጣይ ጠንካራ ሃገር ለመመስረት ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል።
በአሁኑ ወቅት በሃገራችን በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች ኢትዮጵውያንን የማይወክሉ፣ተቀባይነት የሌላቸውና ከኢትዮጵያዊነት ባህልና እሴት ያፈነገጡ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል። ‹‹አንተ የዚህ ክልል አይደለህም…ከክልሌ ውጣ…›› የሚሉ አስተሳሰቦችና ተግባራት ከኢትዮጵያዊያን የቀደመ ታሪክ ጋር የሚጋጩና ‹‹ባልሰለጠነው›› ዘመን እንኳ ከሳውዲዓረቢያ በእምነታቸው ምክንያት ተሰደው የመጡ ወገኖች ተቀብሎ፣ ደህንነታቸውን ጠብቆ በሰላም እንዲኖሩ ላስቻለ ህዝብ የማይመጥኑ ናቸው።
ስለሆነም ይህ ወቅታዊ ችግር በኢትዮጵያዊ እሴቶቻችን፣ ለዘመናት በገነባነው አብሮነታችን ዘላቂ መፍትሔ ልሰጠው ይገባል። አንድነትን እንጂ ልዩነት ማጉላት ለእኛ አይመጥነንም። ታሪካችንም የሚያሳየን የጋራ እሴቶቻችንን ተጠቅመን አንድነታችንን ማጠናከር ነውና!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቢት 17/2011