የመንገድ ደህንነት ለልጆች

ሠላም ልጆች፣ እንዴት ናችሁ? ትምህርት እንዴት ነው? በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች ፈተና እየተሰጠ እንደሆነ ይታወቃል። ለፈተና በሚገባ ተዘጋጅታችኋል አይደል? ጎበዞች። ልጆችዬ ታዲያ ለፈተና ብቻ አይደለም መማር እና ማጥናት ያለባችሁ። በመማራችሁ ስለ አካባቢያችሁ፣ ስለ ሀገራችሁ እና ስለዓለማችሁ ልዩ ልዩ ነገሮችን እንድታውቁ ያግዛችኋል። ጤናችሁስ እንዴት ነው? እንደምታስታውሱት የዛሬ ሳምንት ቆሻሻ እንዴት መወገድ እንዳለበት ነበር ያቀረብንላችሁ። የዛሬው ርዕሰ ጉዳያችን ደግሞ የመንገድ ደህንነትን በተመለከተ፤ ወይም መንገድ ስታቋርጡ በጥንቃቄ መሆን እንዳለበት የሚያመላክት ነው።

ልጆችዬ፣ ሰዎች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመጓጓዝ የተለያዩ የትራንስፖርት ወይም የመጓጓዣ አይነቶችን ይጠቀማሉ። ከሦስት እግር (ባጃጅ) አንስቶ፣ የቤት መኪና፣ የድርጅት መኪና፣ ታክሲ፣ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት (ባስ)፣ ብስክሌት እና የመሳሰሉት ከመጓጓዣ አይነቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። ታዲያ እነዚህ ተሽከርካሪዎች በሚንቀሳቀሱበት ቦታ አደጋ እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው።

ልጆችዬ ‹‹ጎበዙ ተማሪ›› የሚለውን መዝሙር ታውቁታላችሁ? መዝሙሩ እንዲህ ይላል፤

ጎበዙ ተማሪ በጣም ጠንቃቃ ነው፤

ሲሄድ በመንገድ ላይ እያስተዋለ ነው።

መኪና ሲመጣ ቀጥታ እንዲታየው፤

የመንገዱን ግራ ይዞ ነው የሚሄደው።

ይላል መዝሙሩ።

ስለዚህ ልጆችዬ ከዚህ መዝሙር ምን ተማራችሁ? ‹‹እንደ ጎበዙ ተማሪ ጠንቃቃ መሆን፣ በመንገድ ላይ ስንሄድ ማስተዋል እንዳለብን፣ መኪና ከፊት ለፊታችን ሲመጣ ለመመልከት የግራ መስመራችንን ይዘን መጓዝ እንዳለብን ተምረናል።›› እንደምትሉ ምንም ጥርጥር የለኝም። ስለዚህም ልጆችዬ፣ ዘወትር በእግረኛ መንገድ ላይ አስተውላችሁ መሻገራችሁን መዘንጋት የለባችሁም። አስፋልት ስትሻገሩ ግራ እና ቀኝ ከማየታችሁ በተጨማሪ ለእግረኛ በተዘጋጀው መስመር (ዜብራ) ላይ ማቋረጥ ይኖርባችኋል። ይህንን በፍፁም እንዳትረሱ፣ እሺ ልጆች።

ልጆችዬ በመኪና አደጋ ምክንያት የብዙ ሰዎች ሕይወት እንደሚጠፋ እና በአደጋው ምክንያት አካል ጉዳተኛ እንደሚሆኑ ታውቃላችሁ አይደል? እናም ራሳችሁን ከእንዲህ አይነት አደጋ ለመከላከል አስፋልት ላይ ወይም መኪና በሚበዛባቸው አካባቢዎች መሯሯጥ የለባችሁም እሺ። ከድልድይ ላይ መሻገር (መዝለል)፤ ከፍታ ካላቸው ድልድዮች ላይ መንጠላጠል፤ እንዲሁም ወደ ታች ማየት በፍፁም የለባችሁም።

ሌላው ደግሞ ልጆች በመኪና ላይ ተንጠልጥሎ መሄድ ለአደጋ እንደሚያጋልጥ መረዳት ይኖርባችኋል። ይህን መጥፎ ድርጊት እናንተ እንኳን ባታደርጉት እንዲህ የሚያደርግ የምታውቁት ተማሪ ካለ አደጋ ሊደርስበት እንደሚችል ማስተ ማር ይኖርባችኋል። እናንተ ነግራችሁት የማይተው ከሆነ ደግሞ ለወላጆቹ (አሳዳጊዎቹ) ወይም ለመምህራኖቹ በመንገር እንዲማሩ ማድረግ አለባችሁ።

ልጆችዬ መቼም ‹‹አስፋልት ሲሻገሩ›› የሚለውን የልጆች መዝሙር ታውቁታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። በዚህ መዝሙር ላይ ልጆች በጥንቃቄ መሻገር እንዳለባቸው እንዲህ ተዘምሯል፤

አስፋት ሲሻገሩ ያልተጠነቀቁ፤

ግራ ቀኝ ያላዩ ሕግን ያልጠበቁ፤

በመኪና አደጋ ይታያል ሲጠቁ፤

ራስን ለማዳን ልጆች ተጠንቀቁ።

ትምህርት ቤት ስሄድ ግራ መንገድ ይዤ፤

ነጩን መስመር ሳገኝ ተጉዤ ተጉዤ፤

ግራ ቀኝ ግራ ቀኝ ሁሉንም አያለሁ፤

ተሽከርካሪ ሲቆም እኔ እሻገራለሁ።

በራ አረንጓዴው በራ፤

የተሽከርካሪ ነው የእኔ ሳይሆን ተራ።

በራ ቀዩ መብራት በራ፤

ግራ ቀኝ ሁሉንም አያለሁ

ተሽከርካሪ ሲቆም እኔ እሻገራለሁ።

ልጆች፣ በጣም ደስ የሚል መዝሙር ነው አይደል? ቀይ የትራፊክ መብራት ሲበራ ግራ ቀኝ ተመልክቶ መሻገር እንዳለብን፤ አረንጓዴ ሲበራ ደግሞ መኪና ብቻ እንዲያልፍ የተፈቀደ ስለሆነ መሻገር የተከለከለ ነው ማለት ነው። ቢጫው ደግሞ ምን መሰላችሁ፣ “ተዘጋጁ” ማለት ነው። ስለዚህም ልጆችዬ ይሄንን በሚገባ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል አይደል? የትራፊክ መብራት በሌሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ ሁሌም ከመሻገራችሁ በፊት አሽከርካሪዎች እናንተን ለማሻገር መቆማቸውን ማረጋገጥ አለባችሁ። በትምህርት ቤት አካባቢ ትራፊክ ባለበት ቦታ ትራፊኩ ተሻገሩ የሚል ምልክት እስከሚሰጣችሁ ድረስ መቆማችሁንም አትርሱ።

ልጆችዬ፣ ከወላጆቻችሁ ጋር የምትሻገሩ ከሆነም የወላጆቻችሁን እጅ መያዝ እና እነርሱ እንድትሻገሩ ሲፈቅዱ ብቻ ነው መሻገር ያለባችሁ። ወላጆችም ልጆቻችሁ በእግረኛ መንገድ ላይ ማቋረጥ እንዲለማመዱ፣ ድልድዮችን እንዳይዘሉ እናንተ ይህንን ባለማድረግ ለልጆችቻሁ አርአያ መሆን ይጠበቅባችኋል።

በተጨማሪም፣ የተለያዩ በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪዎች የሚሉትን በመስማት “ተሻገሩ”ሲሉ መሻገር፤ “ቁሙ” ሲሉ በመቆም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ልጆችዬ፣ ሌላው ማስተዋል ያለባችሁ ነገር ምን መሰላችሁ? በየመንደሩ በፍጥነት የሚያሽከረክሩ ሰዎች አይጠፉምና ራሳችሁን ከአደጋ ለመከላከል ሁል ጊዜም ንቁ መሆን ይኖርባችኋል።

ለልጆች ይህንን አልን እንጂ አሽከርካሪዎች በእርጋት እንዲሁም በጥንቃቄ ማሽከርከር እንዳለባቸው ይታወቃል። ወላጆችም የልጆች የመንገድ ደህንነት አጠቃቀማቸው ምን እንደሚመስል በማጤን፣ ማስተካከል ያለባቸውን እንዲያስተካክሉ በመምከር ልታግዟቸው ይገባል። ልጆችዬ፣ ሁሌም ጥንቃቄ አይለያችሁ እሺ።

እየሩስ ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 9/2016

Recommended For You