አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለሚደርጉ የቻይና ባለሀብቶች ጊዜና ወጪን ለመቆጠብ የሚያስችል የኦን ላይን ምዝገባ ሊደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ለኦን ላይን ኢንቨስትመንት ምዝገባ አገልግሎት የሚውለውን ድረ ገፅ ከትናንት ጀምሮ ክፍት አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ እንደገለጹት፤ ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር የኢንቨስትመንት ፈቃድ የሚሰጠው የተለያዩ ሰነዶችን ለኮሚሽኑ በአካል በማቅረብ ነበር፡፡
ይህን አሠራር ዘመናዊ ለማድረግ ሲባል የኦን ላይን አገልግሎት እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ ይህም ባለሀብቶች መምጣት ሳያስፈልጋቸው ባሉበት መሟላት ያለባቸውን ነገሮች ሞልተው እንዲልኩ በማድረግ የባለሀብቶቹ ጊዜና ገንዘብ ሳያባክኑ ባሉበት ሆነው ከኢትዮጵያ ጋር ለማገናኘት ያስችላቸዋል፡፡
በተጨማሪም አሁን በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ሥራዎችን እየሠሩ ያሉ ባለሀብቶች በአገሪቱ የተፈቀዱ ህጎችንና ማበረታቻዎችን መጠየቅ ሲፈልጉ ወደ ኮሚሽኑ በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን ኤሌክትሮኒክስ በሆነ መንገድ ማቅረብ የሚያስችላቸውአሠራር መዘርጋቱን አመልክተዋል፡፡ አሠራሩም ጊዜና ወጪን እንደሚቆጥብ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አበበ ማብራሪያ፤ ድረ ገፁን ለማዘጋጀት ሰባት ወር የፈጀ ሲሆን በቀጣይ ሙሉ በሙሉ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል፡፡ የተዘጋጀው ድረ ገፅ ለባለሀብቶቹ መረጃዎችን በዝርዝር የሚያስረዳ ሲሆን በተለይም እንዴት መመዝገብ እንደሚችሉ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የኢንቨስትመንት ሁኔታዎችን፣ ኢንቨስት የሚያደርጉባቸውን ዘርፎችና የሚደረግላቸውን ማበረታቻና ሌሎችንም አስፈላጊ መረጃዎች ይሰጣል፡፡
ይህም የሚሆነው በመንደሪን እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች መሆኑ ደግሞ ለባለሀብቶቹ የበለጠ ተደራሽ ለመሆን ያስችላል፡፡
በዓለም አቀፍ የገንዘብ ትብብር የምሥራቅ አፍሪካ የግል ዘርፍ ስፔሺያሊስት ሄንዝ ዊልሄም እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንት ፍሰት እያደገ ነው፡፡
ይህም የአገሪቱ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ያመጣው ውጤት ሲሆን በኢንቨስትመንት እ.ኤ.አ 2017 3ነጥብ6 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ አሁን ላይ ያለውን አሃዝ አዲስ መረጃ ባይገኝም በ2017 የነበረው ከፍተኛ መሆኑን ያሳያል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን የሚያሳይ ሲሆን አሁን የድረ ገፁ አሠራር መጀመሩ ደግሞ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የበለጠ ምቹ ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ዋለልኝ አየለ