‹‹የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የንግድ ሥርዓቱን በደንብ መፈተሽ ያስፈልጋል›› የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርና ማዘመንና የገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል አስተባባሪ ታደሰ ኩማ (ዶ/ር)

የቀድሞ የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት የአሁኑ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት መሥራች ተመራማሪ ናቸው፡፡ በእርሳቸው መሪነት በኢትዮጵያ ግብርና ዙሪያ 30 የሚደርሱ ምርምሮች ተካሂደዋል። ከምርምሩ ጎን ለጎን የሁለተኛ ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልም ነበሩ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪቸውን በኢትዮጵያ በኢኮኖሚክስ፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በኮሪያ በዴቨሎፕመንት ኢኮኖሚክስ፣ ሶስተኛ ዲግሪያቸውን በደቡብ አፍሪካ በግብርና ኢኮኖሚክስ ላይ አተኩረው ተምረዋል፡፡

የዛሬው የዘመን እንግዳችን እስከ ሶስተኛ ዲግሪ ተምረው ጥሩ ደረጃ ላይ ቢደርሱም፤ ውልደታቸው ከአርሶ አደር ካልተማረ ቤተሰብ ሲሆን፤ ትምህርት ለመማር ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ወላይታ ዞን በሶዶ ዙሪያ ወረዳ በ1957 ዓ.ም የተወለዱት የዛሬው የዘመን እንግዳችን ታደሰ ኩማ (ዶ/ር)፤ የልጅነት ሕይወታቸውን ያሳለፉት አረካ ከተማ አካባቢ ወይቦ በተሰኘ መንደር በአያታቸው ቤት ነበር፡፡

በእርሳቸው የልጅነት ዘመን በአካባቢው ልጅ የሚወለደው በትምህርት ራሱን ከፍ ያለ ደረጃ እንዲያደርስ አልነበረም፡፡ ይልቁኑ በእርሻ ወይም ከብት በመጠበቅ ቤተሰቡን እንዲያግዝ ይፈለግ ነበር፡፡ የታደሰ (ዶ/ር) ቤተሰብ ግን፤ ከአካባቢው ማህበረሰብ የነቁ በመሆናቸው ትምህርት ቤት ላኳቸው፡፡

ትምህርት እንዲጀምሩ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ደግሞ አክስታቸው ነበሩ፡፡ የአክስታቸው ሴት ልጅ እና እርሳቸው ቃለሕይወት የተባለ ትምህርት ቤት ፊደል ቆጥረው፤ አረካ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርት እንዲቀስሙ ተላኩ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን መማር ግን ቀላል አልነበረም። ከአያታቸው ቤት ተነስተው ትምህርት ቤት እስከሚደርሱ በልጅነት ጉልበታቸው በትንሹ ለአንድ ሰዓት ተኩል በእግር የመሔድ ግዴታ ነበረባቸው፡፡ ሲመለሱም በተመሳሳይ መልኩ ለአንድ ሰዓት ተኩል ተጉዘው አምሽተው ቤታቸው ይደርሱ ነበር።

አካባቢው ጫካ እና ወንዝ ያለበት በመሆኑ መንገድ ላይ ከሚያጋጥማቸው አውሬ ጋር እየፈሩ ይተላለፉ ነበር፡፡ መጋቢት እና ሚያዚያ ላይ ደግሞ እንደአሁኑ ድልድይ ባለመኖሩ ከትምህርት ቤት ሲመለሱ የሞላ ወንዝ እስኪጎድል በወንዝ ጫፍ ተቀምጠው እየጠበቁ፤ ተለቅ ያለ አቅም ያለው ጠንካራ፤ ሊያሻግራቸው የሚችል ሰው ሲገኝ እየለመኑ እየተሻገሩ፤ ወንዙ አልጎድል ሲላቸው ደግሞ እየመሸባቸው ለምነው ሰው ቤት እያደሩ ከበድ ያሉ ፈተናዎችን አሳለፉ፡፡

ልጅ ስለነበሩ እየሮጡም እየተራመዱም፤ በቀን ለሶስት ሰዓት በእግር በመጓዝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ከ1964 እስከ 1968 ዓ.ም ተከታተሉ፡፡ ችግሩ ግን መንገዱ ብቻ አልነበረም። በአካባቢው ስንቅ አስቋጥሮ ትምህርት ቤት የሚልክ ቤተሰብ አልነበረም፡፡ ቤት ያፈራውን፤ በእጅ በተሰፋ የአቡጀዴ ጨርቅ ቂጣም ሆነ ጥሬ ያገኙትን ይዘው ወደ ትምህርት ቤት ይሔዳሉ። አንዳንዴ ቤተሰብ ምንም ላያዘጋጅ ይችላል። በዛ ጊዜ ገንዘብ ውድ በመሆኑ፤ ገዝቶ መብላት የሚታሰብ አይደለም። በእርግጥ የተራበ ሰው አንኳኩቶ ማንንም ቢጠይቅ ወተት የሚሰጥ አይጠፋም። ነገር ግን ሁልጊዜ ሰውን ማስቸገር ከባድ ነው፡፡ እንዲህ እያሉ የእግር መንገዱንም፣ ከአውሬ ጋር መተላለፉንም፣ ረሃቡንም ሆነ ደራሽ ውሃውን አሳልፈው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀቁ፡፡

ድቦ እመቤታችን መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ሲማሩ፤ ቀደም ሲል የነበረው መከራ ተቃለለ፡፡ መንገዱ ሜዳ ከመሆኑም ባሻገር፤ ወንዝ ስላልነበረ ብዙ አልተቸገሩም፡፡ ወደ ዘጠነኛ ክፍል ሲሸጋገሩ እና ሶዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲገቡ ግን፤ ሌላ ፈተና ገጠማቸው፡፡ ወይቦ አካባቢ ካለው የአያታቸው ቤት ተነስተው ሶዶ ከተማ ለመድረስ በትንሹ 35 ኪሎ ሜትር አካባቢ መጓዝ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ በእግር ይሔን ያህል መጓዝ ከባድ ነበር፡፡

እሁድ ለሰኞ አጥቢያ ለሊት ዘጠኝ ሰዓት ተነስተው በእግራቸው ተጉዘው ትምህርት ቤት ይደርሱ ነበር። እስከ አርብ አጎታቸው ቤት እያደሩ ትምህርታቸውን ተከታትለው፤ አርብ ማታ ተጉዘው ቤተሰባቸው ጋር ይመለሱ ነበር፡፡ በአብዛኛው ከጓደኞቻቸው ጋር በቡድን የሚሄዱ ሲሆን፤ አንዳንዴ ደከም ብሎ ከቡድኑ የመነጠል አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ በዚህ ጊዜ ለብቻ ቀበሮ፣ ድብ፣ ጅብ ያጋጥማል፡፡ ይህንን ሁሉ አልፈው ብዙ ውጣ ውረዶችን ተቋቁመው አሁኑ የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የግብርና ማዘመንና የገጠር ልማት ፖሊሲ ጥናት ማዕከል አስተባባሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ታደሰ ኩማ (ዶ/ር) አጠቃላይ የህይወት ውጣ ውረዶቻቸውን፣ ያጠኗቸውን ጥናቶች እና የምርምር ግኝቶቻቸውን በተመለከተ ቆይታ አድርገን እንዲህ አቅርበንላችኋል፡፡ መልካም ንባብ፡-

አዲስ ዘመን፡- ገጠር ተወልዶ ለከፍተኛ ደረጃ መድረስ ምን ያህል ፈታኝ ነው? እስኪ የልጅነት አጋጣሚዎን ይንገሩን?

ዶ/ር ታደሰ፡- በጣም ከባድ ነው፡፡ አንድ ጊዜ 10ኛ ክፍል ሆኜ ሰኞ ፈተና ነበረኝ፡፡ ሌሎቹ ጓደኞቼ አስቀድመው እሁድ ማታ ወደ ሶዶ ከተማ ሲሔዱ፤ እኔ ግን በለሊት ወጥቼ በመኪና እደርሳለሁ ብዬ ቀረሁ፡፡ከአያቴ ቤት ገንዘብ ለምኜ 35 ኪሎ ሜትር በመኪና ትምህርት ቤት ለመሔድ አስቤ ነበር፡፡ ነገር ግን ልቤ አላረፈም፡፡ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ሆኗል ብዬ በጨለማ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ብዙ ብሔድም አልነጋም፡፡ ድብ አንገቱን አቀርቅሮ ጉድጓድ ሲቆፍር ግማሽ አካሉ ጉድጓድ ውስጥ በመሆኑ ድብ መሆኑን ሳላውቅ እላዩ ላይ ወጣሁ፡፡ በጣም ደነገጥኩ፤ ድቡም ደነገጠ፡፡ በድንጋጤ ተንደርድሬ ዛፍ ላይ ወጣሁ፡፡

ድቡ ደንግጦ ስለነበር አላጠቃኝም ትቶኝ ሔደ፤ ዛፍ ላይ እንዳለሁ መንጋት ሲጀምር፤ ከሰዎች ጋር ተቀላቅዬ ሔድኩ፡፡ በአጋጣሚ መኪና አግኝቼ ለፈተና ደረስኩ፡፡ ወደ ትምህርት ቤት መሔድ ብቻ ሳይሆን አምሽቶ ወደ ቤት መመለስም እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ከአውሬ ጋር መጋፈጥ ብቻ ሳይሆን፤ ድካም እና ረሃቡ ቀላል አልነበረም፡፡ በዛ ላይ ለደብተር መግዣ እና በበጋ ለሚወጣ ወጪ ክረምት ላይ እነግድ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ የትምህርት ውጤትዎ እንዴት ነበር? ንግዱ መቼ ቆመ?

ዶ/ር ታደሰ፡- በጣም ምጡቅ ተማሪ ነኝ ብዬ ባላጋንንም፤ ጥሩ የሥራ እና ትምህርት የመማር ባህል አለኝ፡፡ ከክፍል ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ እወጣለሁ፡፡ በባህሪዬ ጭምት ነኝ፡፡ ሥራ እወዳለሁ፡፡ በ1964 ዓ.ም አንድ ቀድሞ ተምሮ አስመራ ይሠራ የነበረ የእኔ አጎት በድምፅ መቅረጫ ቀድቶኝ ነበር፡፡ ‹‹ ሥራ ሥሩ፤ ሥራ ሥሩ አገር የሚለማው በሥራ ነው፡፡›› ብዬ አዜም ነበር፡፡ ለሥራ ያለኝ ጉጉት ከዛ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

በእርግጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስማር አይኔን በመታመሜ ለአንድ ዓመት ትምህርቴን አቋርጬ ነበር፡፡ በተጨማሪ በ1975 ዓ.ም አባት እና እናቴ ተለያይተው፤ እናቴ እና አያቴ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ማጠቃለያ ፈተና ሲደርስ ፤ እሁድ ለስንቅ ቤት ሔጄ እናቴ በድንገት ታመመች፡፡ ሰኞ እና ማክሰኞ እናቴን ሃኪም ቤት ወስጄ አሳክሜ፤ እኔ ታመምኩኝ፡፡ ፈተናውን ታምሜ በመፈተኔ ውጤቴ ዝቅ አለ። በጣም አዝኜ ነበር፡፡ ነገር ግን በኋላ የመምህርነት መግቢያ ፈተና ተፈተንኩኝ፤ ከብዙ ሰዎች መካከል ሁለተኛ ሆኜ የሐዋሳ መምህራን ማሠልጠኛ ገባሁ፡፡

የመምህርነት ሥልጠናውን እንዳጠናቀቅኩ በመንግሥት ትምህርት ቤት ማገልገል ጀመርኩ፡፡ በሲዳሞ አካባቢ ሀገረ ሠላም ወረዳ ከስድስት ሰዓት የእግር ጉዞ በኋላ ወደ ሚገኘው ቀጭኑ ሳምኣሎ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመደብኩ፡፡ በዛ ጊዜ ሲዳማ ከፍተኛ ጫካ ነበር፡፡ መሃል ላይ ወንዝም አለ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤቱ ሰዎች ወሰዱኝ፤ ትምህርት ቤቱ የተሠራው መሃል ሜዳ ላይ ነው፡፡ ለእኔ ማደሪያ ቤት አልነበረም፡፡ እንደምንም አርሶ አደሩን በማስተባበር ቤት አሰርቼ መኖር ጀመርኩ፡፡ ለሶስት ዓመት እዛው በመምህርነት ሠራሁ፡፡

መንገዱ የማይመች በመሆኑ ወደ ከተማ በወር አንድ ጊዜ ደሞዝ ለመውሰድ እንኳን ችግር ነበር፡፡ ነገር ግን ከአውሬ ውጪ አካባቢው ሰላም ነበር፡፡ ሕዝቡም መምህር በመንገድ ላይ ሲገኝ ያከበር ነበር፡፡ በኋላ በዝውውር ወላይታ ገባሁ፡፡ ለስድስት ዓመታት ወላይታ ሆኜ ሳስተምር ጎን ለጎን እነግድ ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ሁሉ በኋላ ትምህርቶትን የቀጠሉት እንዴት ነው?

ዶ/ር ታደሰ፡- መጀመሪያ ግልገል ጊቤ ሶስት ያለበት ኪንዶ ኮይሻ በሚባል አካባቢ ተመደብኩ፡፡ ቦታው በረሃ ነው፡፡ ከባድ ነው፡፡ እባብ ብዙ ጊዜ ይተናኮለን ነበር። ደጋግሜ ወደ ቤተሰቦቼ እሔዳለሁ፤ እነግዳለሁ፡፡ ቤተሰቦቼ ገፋፍተውኝ በ1984 ዓ.ም ጋብቻ መሠረትኩ፡፡ ባለቤቴ ከእኔም በላይ በጣም ልጅ ነበረች። በተከታታይ ሶስት ልጆች ወለድን፡፡ ሶስቱም አሁን ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የመጀመሪያዋ ሃኪም ናት፡፡ አሁን ስፔሻሊስት ለመሆን እያጠናች ነው፡፡ ሁለተኛ ልጄ ወንዱም ኢንጂነር ሆኖ የዩኒቨርስቲ መምህር ነው፡፡ ትዳር መስርቷል፡፡ ሶስተኛዋ ፋርማሲስት ነች፡፡

ልጆች እያሳደግኩ ርቄ ሔጄ ትምህርት ለመማር አልቻልኩም፡፡ አለመማሬ ይቆረቁረኝ ነበር፡፡ የልጆቼ ነገር ያሳስበኛል፤ ባለቤቴ ደግሞ ልጅ ነበረች፡፡ ከአካባቢው ሰው ጋር መልካም ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ማስተማር፣ መነገድ እና ልጆች ማሳደግ ቤተሰቦቼን በእርሻ ሥራ ማገዝ እነዚህን ተደራራቢ ሃላፊነቶች መወጣቴን ቀጠልኩ፡፡

በ1986 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ግን አዲስ ዕድል ተገኘ። የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ማስተማር ሊጀምር ነበር፡፡ አዲስ አበባ ሔጄ የምፈተንበት ገንዘብ አልነበረኝም፡፡ የፓርላማ አባል ለነበሩ አጎቴ ሳማክራቸው ፈተናውን ተፈተነህ ትምህርት ካልተማርክ ፊቴን እንዳታይ አሉኝ፡፡ ‹‹ገንዘብ ከሌለህ እኔ እሰጥሃለሁ፤ አሁኑኑ ሔደህ ተፈተን›› ብለው ገንዘብ ሰጡኝ፡፡ ፈተናውን ተፈትኜ አልፌ፤ኢኮኖሚክስ ተማርኩ። ስጨርስ ደቡብ ኦሞ ፕላን እና ልማት መምሪያ የሚባል ድርጅት ተመደብኩ። ስድስት ወር ሰርቼ በአጋጣሚ ኮሪያን ዴቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት ለጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የትምህርት ዕድል መስጠቱን ሰማሁ፡፡ ውጤቴ ጥሩ ስለነበር፤ ፍላጎት ካለህ መፈተን ትችላለህ ተብሎ ተነገረኝ፡፡

ለሁለተኛ ዲግሪ የመግቢያ ፈተና ወሰድኩ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ኮሪያ ሔድኩኝ፡፡ ከኮሪያ ዴቨሎፕመንት ኢንስቲትዩት በኢኮኖሚ ልማት ሁለተኛ ዲግሪዬን አገኘሁ። ኢንስቲትዩቱ በዛ ጊዜ የራሳቸውን የእድገት ተሞክሮ ለብዙ አገሮች ለማስተላለፍ ያቋቋሙት ሲሆን፤ አሁን ዩኒቨርስቲ ሆኗል፡፡ በዛ ጊዜ የተላክነው ኮሪያዎች እንዴት እንዳደጉ የልማት ተሞክሯቸውን አምጡ በሚል ነበር፡፡ የእነርሱ ዕድገት አንደኛው ጥሩ የተማሩ ሰዎች ተሳትፎ ማድረጋቸው እና የአሜሪካን ዕገዛም ታክሎበት ነበር፡፡ ብዙ መፅሃፍ አምጥቼ ለመንግሥት ሠጥቻለሁ፡፡

እንደመጣሁ የሄድኩት አርባ ምንጭ ሳይሆን፤ ‹‹ኮሪያ ተምሮ ስለመጣ ይጠቅመናል እዚሁ ይሁን›› ተብሎ ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ገባሁ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የኢኮኖሚ አማካሪ ቡድን ሥር ሆኜ እሠራ ጀመረ፡፡ ነገር ግን እኔ እና ሌሎች አብረውኝ ተምረው የመጡ ሁለት ልጆች ነበሩ፡፡ አንዱ ወደ ንግድ ሚኒስቴር ሲገባ እኛ ሁለታችን ጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ቀረን፡፡

በጊዜው የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት (ኢ ዲ አር አይ) መንግሥት ለመመስረት ውስጥ ለውስጥ ሲሠራ ቆይቶ ነበር፡፡ ወዲያው የኢትዮጵያ ልማት ኢንስቲትዩት ተቋቋመ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ውስጥ ሆነን ከ1992 ጀምሮ እንደ መሥራች ተቆጠርን፡፡ ከ1992 ዓ.ም ጀምሮ የሁለተኛ ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነህ ተመረጥ ተባልኩ። ብዙም የፖለቲካ ፍላጎት ባይኖረኝም እምቢ ማለት አልቻልኩም። ምንም እንኳ የምክር ቤት አባል ብሆንም፤ አብዛኛው ሥራዬ እና ዝንባሌዬ የምርምር ሥራ ላይ ነበር፡፡ ለቀረበልኝ ጥያቄ አልፈልግም ማለት ስለማልችል፤ የምክር ቤት አባል ሆንኩኝ። ለአራት ዓመት በኢትዮጵያ ልማት ምርምር ኢንስቲትዩት ተመራማሪ እና የህዝብ ተወካዮች አባል ሆኜ ቆየሁ፡፡

ሁለቱን ሥራ አብሮ ማስኬድ ከባድ ነበር፡፡ በተለይ የምክር ቤት አባል መሆኔ ፈተና ሆኖብኝ ነበር፡፡ ገጠር በመኖሬ ጥሬ ሃቅ ላይ አተኩራለሁ፡፡ የፖለቲካ ነገር እንደማይሆንልኝ አሰብኩኝ፤ ችግሮች ሲያጋጥሙ ከመውደቅ ይልቅ በብልሃት ማለፍ ይሻላል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ለመማር ፈለግኩ፡፡ ነገር ግን ማንም አይፈቅድልኝም ብዬ ፍራቻ አደረብኝ፡፡ ምክንያቱም የምክር ቤት አባልነትን ማቋረጥ አይቻልም፡፡ የትምህርት ዕድል ማፈላለግ ጀመርኩ፤ በአጋጣሚ በአራተኛው አመት የምክር ቤት ዘመን በክረምት ወደ ተመረጡበት አካባቢ የሚኬድበት ጊዜ ላይ መጀመሪያ ስውዲን የትምህርት ዕድል መጣልኝ፤ እርሱን ለመማር ገንዘብ ያስፈልግ ነበር፡፡ ያንን መክፈል አልቻልኩም፡፡

 በሁለተኛነት ብዙ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ሰዎች የተማሩበት በደቡብ አፍሪካ የእርሻ ኢኮኖሚክስ ማዕከል የትምህርት ዕድል አገኘሁ፡፡ ነገር ግን ከምክር ቤት አባልነት መውጣት ከባድ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ብልሃት ያስፈልጋል። በቅድሚያ የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ነዋይ ገብረአብን ጠየቅኩ፡፡ ምክር ቤቱ ከለቀቀህ እኔ አስተምርሃለሁ አሉኝ፡፡ ፓርላማ ሄጄ ‹‹ተቋሜ ሊያስተምረኝ ነው፤ ሄጄ ልማር›› ብዬ ስጠይቅ፤ ከተቋምህ ደብዳቤ አምጣ ተባልኩ፡፡ እኔ ተምሬ አገር እንዳገለግል የአንድ ዓመት የምክር ቤት ዘመን ይፈቀድልኝ ስል አመለከትኩ፤ ተቋሙ መማር እንዲችል ፈቅደንለታል የሚል ደብዳቤ ሰጠኝ፡፡ ለሶስተኛ ዲግሪ ወደ ደቡብ አፍሪካ ሔድኩ፡፡ ለአራት ዓመት ተምሬ በጥሩ ውጤት ተመረቅኩ፡፡

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ትዳር ከመሰረትኩ በኋላ የባለቤቴ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ አራተኛ ልጅ ወልደን፤ አነስተኛ ንግድ እየሠራች፤ ልጆቼን የማሳደግ ሙሉ ሃላፊነት ወስዳ ልጆቼን ለቁም ነገር አድርሳለች፡፡ እኔም ኮሪያም፣ ደቡብ አፍሪካም ስማር ቤተሰቦቼ ከእኔ የሚያገኙት የመንግሥት ሰራተኛ ግማሽ ደሞዝ ነበር፡ ትምህርት ጨርሶ ልጅ ወልዶ ማሳደግ እና እየተማሩ ልጅ ማሳደግ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ የባለቤቴ ድጋፍ ባይታከል እዚህ አልደርስም ነበር፡፡

አዲስ ዘመን፡- ገጠር ተወልዶ፤ ከቲ ቲ አይ ተነስቶ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ለመማሬ ቁልፉ ምክንያት ምንድን ነው ይላሉ?

ዶ/ር ታደሰ፡- የሰው ልጅ ጠንክሮ ከሠራ እና ባለበት ደረጃ ካልረካ በየጊዜው ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገር ይችላል። እኔ አንድም ጥረት አደርጋለሁ። ከፊደል ቆጠራ ጀምሬ የጥናት ጊዜዬን አስተጓጉዬ አላውቅም፡፡ መማርና ማጥናት ከሚገባኝ በላይ አነብ ነበር፡፡ ሕይወቴን ለማሻሻል በተለያየ መልኩ እጥር ነበር፡፡ ትእግስትና ጥረት ጥሩ ነው፡፡

በቤተሰብም በሥራ ባልደረባም በሌሎችም በተለያዩ ሁኔታዎች ፈተናዎች ያጋጥሙኝ ነበር፡፡ ትዕግስት ባይኖረኝ እና በብልሃት ባልንቀሳቀስ ብዙ መጓዝ አልችልም ነበር። ሌላው ስለትምህርት ማሰብ ጥሩ ነው፡፡ ከወረዳ ወጥቼ በዓለም ላይ በትንሹ ከ18 ያላነሱ አገራትን አይቻለሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ስለተማርኩ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡-የምርምር ሥራ እንዴት ነው? ምን ያህል ምርምር አድርገዋል? በኢትዮጵያ የምርምር ተቀባይነት በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶ/ር ታደሰ፡- ምርምር በጣም አስደሳች ሥራ ነው። ምርምር ድብቅ የሆኑ ነገሮችን በሳይንስ ላይ ተደግፎ ተንትኖ ግኝቶችን ማቅረብ ነው፡፡ ሂደቱ ከባድ እና የብዙ ሰው ተሳትፎን የሚጠይቅ ነው፡፡ ከትምህርት ቤት ወጥቼ ግብርና እና ገጠር ልማት ላይ ጥናት የማካሔድ ሥራ ስሰራ ነበር። በዚህ በምርምር ሥራ 30 የሚደርሱ የምርምር ሥራዎችን ለህትመት አብቅቻለሁ። አብዛኛዎቹ ግብርና ላይ ሲሆኑ፤ የግብርና ቴክኖሎጂ፣ የግብርና ምርታማነት፣ ግብይት፣ የምግብ ዋስትና እና ሌሎችም ከግብርና ጋር የተያያዙ ናቸው።

ቀድሞም ቢሆን የመጀመሪያ ዲግሪዬንም ስማር የመሬት መጠን እና የምግብ ዋስትና ላይ ያተኮረ ነበር። የሁለተኛ ዲግሪዬንም የሰው ሃይል ብዛት እና ልማት ለይ የሚያተኩር ነበር። ኮሪያዎች አንድም አገራቸውን ያሻገሩት በትምህርታቸውም ጭምር ነው፡፡ የሶስተኛ ዲግሪዬን የግብርና ምርት ግብይት ላይ ያተኮረ ነበር። በዋናነት ቡና ላይ ያተኮርኩ ሲሆን፤ የመንግሥት ቁጥጥርን እና የገበያ ሁኔታው ላይ ተመርኩዤ ነበር፡፡

በእነዚህ ጥናቶች ውስጥ ተቀባይነት ያገኙ እና በመንግስት ፖሊሲ ውስጥ የተካተቱ ነበሩ፡፡ በተለይ ገና ምርምር እንደጀመርኩ ከዓለም ባንክ እና በወቅቱ ከኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር የሠራነው ቀደም ሲል በጀቱ ለክልል ሲሰጥ ክልል የራሱን ቀንሶ ለዞን፣ ዞንም የራሱን ቦጭቆ ለወረዳ፣ እታች ሲደርስ ሥራ ላይ የሚውለው ትንሽ ነበር፡፡ በጥናት ግኝቱ በመመርኮዝ ሁሉም እንደየደረጃው እንዲሰጠው ሲደረግ ወረዳ የተሻለ ሥራ ላይ የሚውል ገንዘብ ማግኘት ጀመረ፡፡

ሌላው የታክስ መጠንን መቀነስ እና የሰፋፊ እርሻዎች ውጤታማነት ላይ በእኔ መሪነት ጥናት ተጠንቶ በመንግስትም ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። በተጨማሪ የዓየር ንብረት ለውጥ እና የቤተሰብ የመቋቋም አቅም ላይ ጥናት አካሒደናል። አየሩ እየተለወጠ፤ የማይታወቁ በሽታዎች እየተስፋፉ በመሆኑ እነዚህን ችግሮች እንዴት መቋቋም ይቻላል? የሚል ጥናት በእኔ መሪነት እያጠናን ነው፡፡ አራት አመት ሆኖናል። ሌላው አሁን ማንም እንደሚያውቀው የዋጋ ግሽበት አለ፡፡ የዋጋ ግሽት መንስኤው ምንድን ነው? ምን መሠራት አለበት በሚለው ላይም ጥናት አጥንተን ለመንግሥት አቅርበናል። ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ የፖለቲካ ለውጡ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ያስከተለው ጫና ላይ በማተኮር ሠርተን መሠራት ያለበትን ለመንግሥት አቅርበናል፡፡

አዲስ ዘመን፡- በምርምር ሥራ ውስጥ ያለው ፈተና ምንድን ነው?

ዶ/ር ታደሰ፡- በዚህ ሁሉ ውስጥ ያለው ፈተና ጥናት ወዲያውኑ ተቀባይነት ይኖረዋል ብሎ መናገር ከባድ ነው። ዓለም አሁን ላለችበት ደረጃ የደረሰችው ዕውቀት ተይዛ ነው። ዕውቀትን ማዕከል አድርጎ መሔድ ለሀገር እና ለሕዝብ ይጠቅማል፡፡ ምርምር ብዙ ፈተና አለው፤ ተቀባይነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ነው፡፡

ሰዎች መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው አንደኛው ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ላይ የግብርና ዕድገት ፕሮግራም ላይ የሚካሔድ ጥናት አለ፡፡ በዓለም ባንክ እና በግብርና ሚኒስቴር የሚሠራ ሲሆን፤ በየዓመቱ ምን ውጤት መጣ በሚል ሥራው ይሠራል፡፡ ነገር ግን መረጃ ለመሰብሰብ ስንሔድ አርሶ አደሩ እና ተጠቃሚው ፈቃደኛ ሆኖ መረጃ ካልሠጠ በጣም አስቸጋሪ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ሕዝብ ጥናት ለማካሔድ የሚረዳ መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለም። መንግሥት ደግሞ ጥናትን በመቀበል በኩል ውስንነት አለበት ማለት ነው? ስለዚህ ከላይም ከታችም ችግር ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ታደሰ፡- በጥናት ላይ በርከት ያለ ችግር አለ። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች መኖራቸውን መካድ አይቻልም፡፡ በመንግስት በኩል በዚህ ላይ ጥናት አካሒዱ፤ ይህንን አድርገናል ምን ውጤት መጣ? አጥኑልን የሚሉ ጥያቄዎች ይቀርባሉ። ከየመንግስት መስሪያቤቶችም ጥናት አጥኑልን ይባላል፡፡ አሁን ያለው ፍላጎት እና ትኩረት ከአስር ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ይለያያል፡፡ ነገር ግን አሁንም ትልቁ ፈተና ምርምር ብዙ መረጃዎች መሰብሰብን ይፈልጋል፤ መረጃ ማግኘት በጣም ችግር ነው፡፡

አንዳንድ ተቋማት መረጃ አይሰጡም፡፡ ጤና ጥበቃ ወይም ግብርና ሚኒስቴር የሰበሰበው መረጃ ቢኖር ለሌሎች አካላት የሰበሰበውን መረጃ አያጋራም። ይሄ ትልቅ ችግር ነው። ብዙዎች ተመራማሪዎችን በጣም ያመላልሳሉ፡፡ ለምሳሌ ግጭቱ እና ያስከተለው ጉዳትን በተመለከተ ጥናት ስናካሔድ በተቋም ደብዳቤ ፅፈን ብንመላለስም የመንግስት ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋማት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ይሔ የመረጃ ውስንነት ይፈጥራል፡፡ ሲያያዝ አንዳንድ ጊዜ ጥናቱ ላይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡

ሌላው ጥናት ለመስራት ሁሉንም ኮርነሮችን ማየትን ይጠይቃል፡፡ አንድ ሰው ጥናቱ እስከሚያስፈልግበት ጫፍ ድረስ መሔድን ይጠይቃል፡፡ ለእዚህ ምቹ የፀጥታ ሁኔታ የለም። ይህ በጥናታችን ላይ ከፍተኛ እንቅፋት ፈጥሯል። ደህንነት በማይጠበቅበት ሁኔታ መረጃ ሰብሳቢ ባለሙያ መላክ ከባድ ነው፡፡

አዲስ ዘመን፡- የሚካሔዱ ጥናቶች ላለመተግበራቸው አንደኛው ምክንያት የጥናት ጥራት ችግር መሆኑ ይነገራል፡፡ አንዳንድ ምርምሮች ለመመረቅ ብቻ ወይም ሥራ ተብሎ እንጀራ ስለሚበላባቸው ብቻ እንደሚካሔዱ ይታሰባል፡፡ በእርግጥ በእርሶ እምነት በኢትዮጵያ ምርምር በትክክል ችግር ለመፍታት ወይም አዲስ ነገር ለማግኘት እየተካሔደ ነው?

ዶ/ር ታደሰ፡- በእርግጥ የጥናት ጥራት በጣም ወሳኝ ነው። አንድ ሰው ያጋጠመውን በሽታ ለማወቅ በተደጋጋሚ ምርመራ ሳይካሔድ እና በሽታው ሳይለይ በግምት ሕክምና ከተጀመረ ውጤቱ በሽተኛውን ከማዳን ይልቅ መግደል ይሆናል፡፡ ጥናትም ተመሳሳይ ነው። በግምት በሽታ ማዳን አይቻልም፡፡ በቂ መረጃ እና ዕውቀት ሳይኖር በተካሔደ ምርምር ምክረ ሃሳብ መስጠት በሽተኛውን አድናለሁ ብሎ እንደመግደል ነው።

ምርምር ዓይነት ብዙ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች የሚሠሯቸው ብዙ ምርምሮች አሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ጥናት የዕውቀት ፍላጎትን ለማሟላት ነው፡፡ ይህኛው ግን የፖሊሲ ምርምር ነው፡፡ ይህኛው ምርምር ሁልጊዜ የሚመነጨው ከፍላጎት ነው፡፤ ስለዚህ ሁልጊዜም ጥናት ከማድረጋችን በፊት የመንግሥት ተቋማትንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን እንጠይቃለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከመንግሥት ከራሱም አጥኑልን የሚል ጥያቄ ይቀርባል፡፡ ለምሳሌ የነዋሪዎች የኢኮኖሚ ለውጥ ምን ይመስላል ዳሰሳ አድርጉልን የሚል ጥያቄ ይቀርባል። ሌላው በተመራማሪዎች በኩልም ሃሳብ ይነሳል፡፡ ነገር ግን በዋናነት እንደተጠቀሰው ከሁሉም በፊት ጥራት ይቀድማል፡፡

መጀመሪያ የተሰበሰበው መረጃ ቢቂ ነው ወይ? ሽፋኑ ትክክል ነው ወይ? ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች ምን ያህል ተሳትፈዋል? የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ይፈልጋሉ። ይህ ተቋም ፌዴራል ነው፡፡ የሚሰበስበው መረጃም ፌዴራልን የሚወክል መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ስለግብርና ሲጠና የአንድ ክልልን ብቻ ወስዶ በሀገር ደረጃ እንደተሰራ መታሰብ የለበትም፡፡ ከሀገር አንፃር ከታየ ጥልቅ መሆን አለበት፡፡

በሌላ በኩል የጥራት ጉዳይ ሲነሳ የወጪ ጉዳይም መታሰብ አለበት፡፡ በጥራት ለመስራት ሽፋንን ማስፋት ያስፈልጋል። በጉዳዩ ላይ ብዙ የሚመለከታቸውን ሰዎች መጋበዝ እና ማሳተፍ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ ወጪ አለው። ስለዚህ ብዙ ጊዜ የምናካሂዳቸው ጥናቶች ናሙናን በመውሰድ ነው፡፡ ናሙናው ወካይ መሆን መቻሉ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሚፈለገው ሕዝብ ውስጥ ወካይ የሆነ ሰው መምረጥ የግድ ነው፡፡ ለአምስት ሺህ ሰው አንድ ሰው እንጠይቃለን፡፡ አምስት ሺውንም ሰው ብንጠይቅ ተመሳሳይ ሃሳብ እናገኛለን ብለን የምንሠራቸው ጥናቶች አሉ፡፡

እዚህ ተቋም ላይ ከጥናት ጋር በተያያዘ መጀመሪያ ከእኛ በፊት የተጠኑ ጥናቶችን በደንብ እንዳስሳለን፡፡ ሁለተኛ የጥናቱ አስፈላጊነት እና የሚጠናበት መንገድ ምን ያህል ያስኬዳል የሚለው በቅድሚያ በባለሞያዎች ታይቶ ይተቻል፡፡ መስክም ተሔዶ ይታያል፡፡ በዚህ ዓይነት ተገምግሞ ወደ ውጪ ይሔዳል። ስለዚህ ጥራቱን በደንብ እናየዋለን፡፡

አዲስ ዘመን፡- የዋጋ ግሽበት ላይ ጥናት አካሂዳችኋል። በትክክል ተጨባጭ መንስኤው ምንድን ነው? መፍትሔ ብላችሁ ያስቀመጣችሁትስ ምንድን ነው?

ዶ/ር ታደሰ፡- የዋጋ ግሽበት መኖሩን መካድ አይቻልም። የዋጋ ግሽበት ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ብለን ከተነሳን በሁለት መልኩ መታየት አለበት፡፡ አንደኛው መሠረታዊ ምክንያት ሲሆን፤ ሌሎች አባባሽ ምክንያቶችም አሉ፡፡ መሠረታዊው ጉዳይ በዚህች ሀገር የፍላጎት መጠን ከአቅርቦት መጠን ፈጥኖ አድጓል። ፀጥታ እና ሠላም ቢኖርም የምርት ፍላጎት እና አቅርቦት ካልተመጣጠነ የዋጋ ግሽበት መከሰቱ የማይቀር ነው፡፡

ከተሞች እጅግ በጣም ተስፋፍተዋል፡፤ በስፋት ፋብሪካዎች አሉ፡፡ ምርት ቢመረትም በሚፈለገው መጠን አላደገም፡፡ ስለዚህ የዋጋ ግሽበት ቁልፉ ከጀርባው ካሉት አባባሾች በፊት መሠረታዊው የምርት አቅርቦት ተመጣጣኝ አለመሆን ሲሆን የእዚህ ምክንያት ደግሞ የግብርና ዘርፍ አለማደግ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ግብርና ላይ ነባር ከሆኑ ዋጋዎች በተጨማሪ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ፣ ፀረ ተባይ እና ምርጥ ዘር ይገዛል፡፡ የሚያርሰው ሰው ጉልበት ዋጋ አለ፡፡ ይህ ሁሉ ሲደማመር የማምረቻ ወጪ ጨምሯል፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያው ምክንያት ግብርና በሚፈለገው መጠን ባለማደጉ ፍላጎት እና አቅርቦት ሊጣጣሙ አልቻሉም፡፡

አባባሽ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከአባባሽ ምክንያቶች መካከል መሬት ላይ ያለው ምርት መጠን አነስተኛ ስለሆነ የገበያ ሥርዓታችን ተበላሽቷል፡፡ ገበያው ባለቤት የለውም። የገበያ ሥርዓት አደረጃጀት ደካማ ከመባልም በላይ ቦታው ላይ የለም ማለት ይሻላል፡፡ በየመጋዘኑ ጣራ የነካ ክምችት እያለ፤ ገበያ ላይ ምግብ የለም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ ምክንያቱ በአገር ደረጃ የገበያ ሥርዓታችን ለተፈጠረው የዋጋ ግሽበት አንደኛው ምክንያት ነው፡፡ ሰዎች ያገኙትን ሁሉ መደበቅ ባህል አድርገውታል፡፡ አገራዊ እና ማህበራዊ ሃላፊነት የማይሰማቸው ነጋዴዎች ምርት መደበቃቸው፤ አሁን ላለው የዋጋ ግሽበት ሌላኞቹ ምክንያት ነው፡፡ ምርቱ በበቂ መጠን ሳይኖር፤ ከእርሱም ላይ መደበቁ ግሽት አስከትሏል፡፡

የገንዘብ የመግዛት አቅም እየወረደ መምጣትም ሌላኛው ምክንያት ነው፡፡ ሰው ገንዘብ ከሚያስቀምጥ ሁለት ኩንታል ጤፍ ቢገዛ ይመርጣል፡፡ ምክንያቱም ዋጋው በየቀኑ ስለሚያድግ ዕህል መያዙ ገንዘብ ከመያዝ ይሻላል ብሎ ያስባል፡፡ ይሔም በራሱ አንድ አባባሽ ምክንያት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በየትም ዓለም የሌለ ተጨባጭ ምክንያት የሌለው የዋጋ ጭማሪ ይደረጋል። ለምሳሌ ግማሽ ሊትር ወተት ከ10 ብር በአንድ ጊዜ ወደ 50 ብር አድጓል። ይሔ እውነት በጥሬ ዕቃ ችግር ነው? ይሔ ያጠያይቃል። መንግሥት የገበያ ሥርዓቱን በደንብ መፈተሽ አለበት፡፡

ሌላኛው የፀጥታ መናጋት ጉዳይ ነው፡፡ ይህ በብዙ መልኩ የሚታይ ነው፡፡ አንዳንዱ ማምረት የሚችል እና ሀገር የሚመግቡ አርሶ አደሮች ማምረት አቁመዋል፡፡ ተመፅዋች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል ምርት ቢመረትም በፀጥታው ችግር ምክንያት ወደሚፈለግበት አካባቢ ማጓጓዝ አይቻልም፡፡ ይህኛው ደግሞ ሌላኛው ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ወለጋ አካባቢ በቆሎ ሲመረት ነበር፡፡ ወላጋ ላይ አንድ ኩንታል አንድ ሺህ ሰባት መቶ ብር እየተሸጠ አዲስ አበባ ሶስት ሺህ ስምንት መቶ ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ምክንያቱም ትራንስፖርት ላይ ችግር አለ፡፡

የገንዘብ አስተዳደር ጉዳይ ደግሞ ሌላኛው አባባሽ ምክንያት ነው፡፡ ከሚመረተው በላይ ገበያ ላይ ገንዘብ ከተረጨ የዋጋ ግሽበት ያጋጥማል፡፡ በእርግጥ አሁን ገንዘቡ ያዝ እየተደረገ የተወሰኑ ለውጦች እየታዩ ናቸው፡፡ ጠቅለል ሲደረግ ግን በዋናነት ከምርት አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ብዙ ነገር አለ፡፡ የወተት ላም እንክብካቤ ስታገኝ የምትሰጠው ወተት ይጨምራል፡፡ ግብርናም ተመሳሳይ ነው፡፡ በወሬ ብቻ የሚገኝ ነገር የለም፡፡ ዋናው ነገር ግብርና ላይ በስፋት ኢንቨስት ማድረግ እና መሥራት ነው፡፡ ለግብርና የሚሠጠው ትኩረት ከፍ ካላለ ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፡፡ ከላይ ከላይ በንግግር ደረጃ ሳይሆን መሬት ላይ የሚወርድ ነገር መሠራት አለበት፡፡

የተገነቡ የመስኖ ሥራዎች ምን ያህል ውጤታማ ሆነዋል? ምን ያህሎቹ ተሠራባቸው የሚለው መታየት አለበት፡፡ የግብርናን ስፋት እና አስፈላጊነትን ያህል ለግብርና ትኩረት መሠጠት አለበት፡፡ የሚሰጠው ትኩረት በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ኩታ ገጠም ላይ መንግሥት ዘር ያቀርባል ማዳበሪያም ይሠጣል፤ ሰፊ ቦታዎች ላይ ትራክተርም ሠጥቷል፡፡ እነርሱ የተሻለ ውጤታማ ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ የውጤታማነታቸው ምንጭ የተሠጣቸው ትኩረት ውጤት ነው፡፡ ስለዚህ ሌላው አባባሽ ጉዳይ ለግብርና የተሠጠው ትኩረት አናሳነት ነው ማለት ይቻላል፡፡

በደንብ መታወቅ ያለበት፤ የምግብ ዋጋ ግሽበት የድሃ ድሃውን ይገድለዋል፡፡ ምንም ዓይነት ቋሚ ገቢ የሌላቸው ጡረተኞች በረሃብ እንዳይሞቱ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ግጭት ባለባቸው ቦታዎች ያለው የዋጋ ግሽበት በጣም ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን በሌሎች ከተሞች ያለው የዋጋ ግሽትም ቀላል አይደለም፡፡ በጣም ከባድ ሁኔታ በመኖሩ የድሃ ድሃዎችን በቅርበት ማየት ይገባል፡፡ ሰው የሚበላውን ዳቦ መግዛት ሲያቅተው ሁኔታው በጣም አስፈሪ ይሆናል፡፡ እኔ የምለው የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የግድ የንግድ ሥርዓቱን በደንብ መፈተሽ እና በስፋት ግብርና ላይ ኢንቨስት ማድረግ ለይደር መቆየት የሌለባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡

አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም እጅግ አመሰግናለሁ፡፡

ዶ/ር ታደሰ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ምሕረት ሞገስ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You