አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያውያን ሴቶች ለእርቅና ለሰላም የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ለአገር አንድነት እንደሚሠሩ ተገለጸ፡፡
«እናት ለእርቅና ለሰላም» በሚል መርህ ትላንት በኢሊሊ ሆቴል በተካሄደው መርሐግብር ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው እንደገለጹት፤ ሴቶች ለእርቅና ለሰላም እያደረጉ ያሉት አስተዋጽኦ ለሀገር አንድነት ያለው ሚና ከፍተኛ ነው። እናቶች ስለሀገር አንድነት ሰላምና ፍቅር የተለየ ስሜት ያላቸው በመሆኑ ይህ እውነታ እውን ይሆን ዘንድ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ተሳትፏቸውን በተግባር ያሳያሉ፡፡
«እናቶች ከልብ በሚያሳዩት ርህራሄና ፍቅርም የሰላም ምልክትና ተምሳሌት በመሆን በነጭ እርግብ አምሳያ የሚመሰሉ ናቸው» ያሉት ሚኒስትሯ፤ ይሁንና በማንኛውም ክፉ አጋጣሚ ሁሉ ቀዳሚ የሚባሉት ሰለባዎች ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ግጭቶች ሲፈጠሩ ልጆቻቸውንና ባሎቻቸውን የሚያጡ፣ ተገደው የሚደፈሩና ሞትና የአካል ጉዳት የሚደርሰባቸው በመሆኑ ርህሩህ ልቦናቸው በኀዘንና ስቃይ የሚሰበርና የእነሱ መከራ ለሌሎች እንዳይተርፍ እናቶች መካሪና አስታሪቂ በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እንግዳዬ እሸቴ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎች የጥላቻና የብጥብጥ ምልክቶች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ይህም ዜጎች በነፃነት እንዳይዘዋወሩና ሠርተው እንዳያድሩ እያደረገ ነው። ይህን መሰሉን ችግር በእርቅና ሰላም ለመፍታም የሁሉም መሰረት የሆኑት እናቶች ያላቸው ተሰሚነት የላቀ በመሆኑ የእርቅና ሰላሙን ሂደት ከራስ በመጀመር በመላው ሀገሪቱ ሊያዳርሱ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዕለቱ በክብር እንግድነት የተገኙት ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እንዳሉት፤በአሁኑ ጊዜ በመላው ሀገራችን እየታየ ያለውን የሰላም እጦት መፍትሔ ለማስገኘት የእናቶች የሰላምና የእርቅ ልማድ ሊዳብር ይገባል። ሴቶች የእናት ሀገር ተምሳሌት በመሆናቸው አንድነትን አስከብሮ በፍቅር ተሳስቦ ለማደር የሚኖራቸው ሚና ላቅ ያለ ይሆናል፡፡
በወቅቱ የሰላም አምባሳደር እናቶችና የነጋዴ ሴቶች ተወካዮች ተንበርክከው በማልቀስ ስለ ሀገር ሰላምና አንድነትና ሰላም የተማጸኑ ሲሆን ዕለቱን የሚመለከቱ የኪነጥበብና የስነጽሑፍ ሥራዎችም ለታዳሚያን ቀርበዋል።
«እናት ለእርቅና ለሰላም» በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው መርሐግብር በሰላም ሚኒስቴር፣ በሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ነጋዴ ሴቶች ማህበር እና በርኖስ በተሰኘ የማስታወቂያ ድርጅት ትብብር ነው።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
መልካምሥራ አፈወርቅ