አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን መስፈርቱን ለሚያሟሉ ድንበር ተሻጋሪ የሞሪንጋ አምራቾች ፈቃድ እየሰጠ መሆኑን ገለጸ። አምራቾች ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ እና ለተጠቃሚ ድርጅቶች ለማቅረብ ‹‹ምርቱ ለሥራችን አዲስ ነው›› በሚሉ የባለስልጣኑ ባለሙያዎች ፈቃድ ለማግኘት መቸገራቸውን አመለከቱ።
የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የምግብ ተቋማት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ በትረ ጌታሁን ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ባለስልጣኑ መስፈርቱን ለሚያሟሉ ድንበር ተሻጋሪ የሞሪንጋ አምራቾች ፈቃድ እየሰጠ ነው።
ድንበር ተሻጋሪ ምርቶቹ በአንድ ከተማ ወይም ክልል ተመርተው በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች የሚሸጡ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ነገር ግን ሞሪንጋም ይሁን ሌላ የምግብ ዓይነት በተመረተበት ከተማም ሆነ አካባቢ ብቻ ለገበያ የሚቀርብ ከሆነ ፈቃድ የሚሰጠው በባለስልጣኑ ሳይሆን በሚገኝበት የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ቢሮ ነው ብለዋል። ለድንበር ተሻጋሪ ሞሪንጋ ምርት እስከአሁንም በባለስልጣኑ ፈቃድ እየተሰጠበት በመሆኑ ለባለስልጣኑ ባለሙያዎች ጉዳዩ አዲስ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።
እንደ አቶ በትረ ገለጻ፤ የምግብ ማምረቻ ቦታቸው መስፈርቱን ለጠበቁ እና የሞሪንጋላብራቶሪ ምርመራው ጥራት ታይቶ ለአምራቾች ፈቃዱ መስጠቱ ይቀጥላል። ይሁንና ሞሪንጋን በምግብ መልክ ሳይሆን በመድሃኒት መልክ ለተለያዩ በሽታዎች ይፈውሳል የሚል የተሳሳተ ማስታወቂያ የሚለጥፉ አምራቾች አሉ። ነገር ግን ባለስልጣኑ ምርቱን በምግብነት መዝግቦ ከሆነ ፈቃድ የሚሰጠው ትክክለኛው መረጃ መቅረብ አለበት።
በሌላ በኩል በአነስተኛ ማምረቻ እና ሼዶች ውስጥ ምግብ ነክ ነገር የሚያመርቱ ሰዎች በአካል ተኪዶ መስሪያ ቦታቸው ሲፈተሽ ፈቃድ የሚከለከሉበት ጊዜ አለ። በመሆኑም የሞሪንጋ አምራቾቹም በመጀመሪያ ፈቃድ ለማግኘት ከመጠየቃቸው በፊት አስፈላጊ መስፈርቶችን ስለማሟላታቸው ማረጋገጥ እንዳለባቸው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የሞሪንጋ ምርት ምግብነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የላብራቶሪ ፈቃድ ማግኘትአልቻልንም የሚሉት የፀሐይ ሞሪንጋ አምራች የሆኑት ወይዘሮ ፀሐይ ዴአ እንደገለጹት፤ ምርታቸውን ለተለያዩ ድርጅቶች ለማቅረብ እና ወደ ውጭ አገራት በእራሳቸው ስም ለመላክ የባለስልጣኑ የላብራቶሪ ፈቃድ ሰርተፍኬት ያስፈልጋቸዋል። ይሁንና ምርቱ ለሥራችን አዲስ ስለሆነ በምን ፈቃድ እንስጥ በሚል የባለሙያዎች ምክንያት የተነሳ የሞሪንጋ ምርት የላብራቶሪ ፈቃድ አላገኙም።
እንደ ወይዘሮ ፀሐይ ከሆነ፤ ምርታቸውን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ከሚገኘው እርሻቸው ላይ የሚዘጋጅ መጠነ ሰፊ አቅርቦት አለው። ነገር ግን የባለስልጣኑ ሰርተፍኬት ባለመገኘቱ ለግለሰብ ተጠቃሚዎች እንጂ ለትላልቅ የሞሪንጋ ተጠቃሚዎች ምርታቸውን መሸጥ አልቻሉም።
በተለይ የሞሪንጋ ለስላሳ መጠጥ አምራቾች ቀጥታ ግብይት ከእርሳቸው ለመፈጸም ቢፈልጉም የመጀመሪያ ጥያቄያቸው የባለስልጣኑን የምግብ ፈቃድ ሰርተፍኬት በመሆኑ ከገቢ አንጻር ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰባቸው ይገኛል።
የሞሪንጋ አምራች የሆኑት ወይዘሮ ዓለም አሸናፊ በበኩላቸው፤ የሞሪንጋ ምግብነት ፈቃድ ለመስጠት ብዙ ባለሙያዎች ችግር ሲገጥማቸው ማስተዋላቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በርካታ የሞሪንጋ አምራቾች በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች እንደመኖራቸው በአግባቡ የላብራቶሪ ምርመራ አድርጎ ፈቃዱን መስጠት ቢቻል በንግዱ ለተሰማሩ ሰዎች የተሻለ ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚረዳ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
ጌትነት ተስፋማርያም