አዲስ አበባ፡- ፌዴራል ፖሊስ መጥሪያ ላልደረሳቸው ተከሳሾች በግንቦት 08 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያደርስ ቀድሞ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት ለተጠርጣሪዎቹ መጥሪያው እንዲያደርስ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ለሦስተኛ ጊዜ አዘዘ፡፡
በእነ አቶ ጌታቸው አሰፋ መዝገብ በከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸው ተጠርጣሪዎች ትናንት ችሎት ቀርበዋል፡፡ ችሎቱ መዝገቡን ትናንት ቀጥሮ ከነበረበት ጉዳይ መካከል በችሎት ያልቀረቡ አራት ተጠርጣሪዎችን አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ አቶ አጽበሃ ግደይ፣ አቶ አሰፋ በላይ እና አቶ ሹሻይ ልዑል መጥሪያ ደርሷቸው መቅረባቸውን ለማጣራት ነበር፡፡
ፌዴራል ፖሊስ መጥሪያውን ከፍርድ ቤት ያወጣው ግንቦት 14 ቀን 2011 ዓ.ም መሆኑን ጠቅሷል፡፡ መጥሪያውን የሚያደርሰው ትግራይ ክልል ስለሆነ እና ቦታው ርቀት እንዳለውም ጠቁሟል፡፡ መጥሪያው ከደረሰው ወቅት አንጻር ጊዜው አጭር በመሆኑ በተባለው ጊዜ ሊያደርስ አለመቻሉንም ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ፌዴራል ፖሊስ መጥሪያ ላልደረሳቸው ተከሳሾች በግንቦት 08 ቀን 2011 ዓ.ም ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሷል፡፡ ቀድሞ ሰጥቶት በነበረው ትዕዛዝ መሰረትም ወጪ የሆነው ደብዳቤ እንዲደርሳቸው አዝዟል፡፡
ሌላው የተመለከተው ጉዳይ ዐቃቤ ህግ ለእያንዳንዳቸው በማስረጃነት ያቀረባቸው 17 የተለያዩ ሲዲዎች ኮፒያቸው ለተከሳሾቹ በችሎት ደርሷቸዋል፡፡ ቢሆንም አንድ ሲዲ መጉደሉንም ችሎቱ አረጋግጧል፡፡ ተራ ቁጥር አራት ላይ የተቀመጠው የሲዲ ኮፒ መጉደሉን በመጠቆም ዐቃቤ ህግ አባዝቶ በቀጣይ ቀጠሮ እንዲያቀርብ ችሎቱ አዝዟል፡፡
ተከሳሾች ደመወዝ በመቋረጡ ቤተሰቦቻችን ተቸግረዋልና እንዲከፈለን በሚል ያቀረቡት አቤቱታንም በቅንንት የችሎት ውሎው የተመለከተው ጉዳይ ሲሆን፤ በወንጀል ችሎት የሚታይ ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ ጉዳዩን የመመልከትም የህግ መሰረት እንደሌለው ጠቅሷል፡፡
በሲቪል ሰርቪስ በኩል የሚቀርብ ጉዳይ መሆኑን በመጠቆምም፤ ተከሸሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው ለሚመለከተው አካል ማቅረብ እንደሚችሉም አስረድቷል፡፡
ችሎቱ አቶ ሰይፈ በላይ በጽሑፍ ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያና ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የሰጠውን ምላሽ እንዲሁም በምስክሮችና የወንጀል ጠቋሚዎች አዋጅ 699/2003 መሰረት ምስክሮች ማንነታቸው እንዳይገለጽ እና ማንነታቸውም ሳይታወቅ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እንዲመሰክሩ ዐቃቤ ህግ የጠየቀውን እና ተካሳሾች የሰጡትን ምላሽ ተመልክቶ ብይን ለመስጠት ሰኔ 3 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
በዘላለም ግዛው