ናይጄሪያዊቷ በዓለም ረጅሙን በእጅ የተዘጋጀ ዊግ አዘጋጅታ ክብረ ወሰን ያዘች

ሄለን ዊሊያምስ የተባለችው ናይጄሪያዊት በዓለም ረጅሙን በእጅ የተዘጋጀ የፀጉር ዊግ በመሥራት አዲስ የጊነስ የዓለም ክብረ ወሰንን ያዘች።

በተለያዩ ዘርፎች በዓለም ዙሪያ የሚያዙ ክብረ ወሰኖችን የሚመዘግበው ጊነስ ዎርልድ ሪከርድስ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ የሌጎስ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ሄለን ከ350 ሜትር በላይ የሚረዝም ዊግ ሠርታለች።

ለስምንት ዓመታት ዊግ በመሥራት ሙያ ላይ ተሰማርታ የቆየችው ሄለን ዊሊያምስ፣ ረጅሙን ሰው ሠራሽ ዊግ ለመሥራት 11 ቀናት የፈጀባት ሲሆን፣ 2,493 ዶላርም አስወጥቷታል።

ሄለን በዓለም ረጅሙን ዊግ በሠራችበት ጊዜ ጥሩ ልምድ ብታገኝበትም የመሥሪያ ዕቃዎቹን ማግኘትን ጨምሮ ሌሎች ፈታኝ ነገሮች እንደገጠሟት ተናግራለች።

ሄለን ለጊነስ ዎርልድ ሪከርድ እንደተናገረችው እየሠራች ሳለ «በጣም ደክሟት» ሥራውን ለማቆም ደርሳ ነበር።

«ነገር ግን ጓደኞቼ እና ቤተሰቦቼ ስላበረታቱኝ፣ የእነሱን ድጋፍ ችላ ላለማለት ትኩረት አድርጌ መሥራቴን ቀጠልኩ። በውጤቱም በዓለም ረጅሙን በእጅ የተዘጋጀ ዊግ ለመሥራት ቻልኩኝ» ብላለች ሄለን።

ዊጉን ከሠራች በኋላ ዋነኛ ችግር ሆኖባት የነበረው የዊጉን ርዝመት ለማወቅ በቀጥታ መስመር ተዘርግቶ በትክክል የሚለካበት ቦታ ማግኘት ነበር።

በመጨረሻ ግን ረጅሙን ዊግ ዘርግቶ ለመመተር ሌጎስን እና አቢዮኩታ ከተሞችን በሚያገናኘው የፍጥነት መንገድ ላይ ሥራዋ ተለክቶ ከ350 በላይ ሜትር እንደሆነ ተረጋግጧል።

ናይጄሪያውያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መስኮች በጊነስ ዎርልድ ሪከርድ ላይ ያልተመዘገቡ ክብረ ወሰኖችን በመያዝ ለመታወቅ ጥረቶችን እያደረጉ ነው።

ከወራት በፊት ናይጄሪያዊቷ ምግብ አብሳይ ሂልዳ ባቺ ለበርካታ ተከታታይ ሰዓታት ምግብ በማብሰል የዓለም ክብረ ወሰንን ለመያዝ በመቻሏ በናይጄሪያ መነጋገሪያ መሆኗ ይታወሳል።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት የሂልዳ ክብረ ወሰን በሌላ አገር ዜጋ ተሰብሮ ቦታዋን ለቃለች።

አሁን ደግሞ ሄለን ዊሊያምስ ረጅሙን በእጅ የተዘጋጀ ዊግ በመሥራት ክብረ ወሰን በመያዝ በዓለም ቀዳሚ ሆናለች።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን   ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You