ብልጥ ከሌሎች ይማራል ሞኝ ከራሱም አይማር

በሰላም ሥራውን እየሰራ የሚገኝ ዶክተር በሚሰራበት ሐኪም ቤት ለሕክምና እርዳታ የመጣችው ሴት ልጁ ከአትንኩኝ ውጭ ብዙም አትጠይቅም፡፡ ሚስቱ የራሷን ጉዳት ረስታ “ልጄ የሱፍን አግኘው” ስትል ወንድ ልጁም የራሱም ሕመም ዋጥ አድርጎ “ወንድሜን አግኝልኝ” የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ ይሄን ሊመልስ በሆስፒታል ከሚገኙ ሕሙማን መሀል ያለመታከት ልጁን የፈለገው ዶክተር ልጁን ማግኘት አልቻለም፡፡

የማይቀር ግዴታ ሆኖቦት ልጁን ከሬሳ ማቆያ ክፍል ቢፈልገው የስድስት ዓመት ሕጻን ልጁ እንደሌሎቹ ልጆቹ አባቱን ላይጠይቅ በዛ ክፍል ተኝቷል፡፡ ይህ ጽሁፍ ልብወለድ ድርሰት ቢመስልም በጋዛ በአንድ ፍልስጤማውያን ቤተሰብ የደረሰ እውነታ ነው፡፡ የእዚህ እውነታ ምክንያትን እስራኤል ብትጠየቅ ሽብርተኛ ብላ የፈረጀችው ሀማስ ያመጣው ጣጣ ነው፡፡ ፍልስጤማውያን ቢጠየቁ እስራኤል ያደረሰችባቸው ጥቃት ነው፡፡

ይህ የእስራኤልና የሀማስ ጦርነት ውጤት ሳይሆን አጠቃላይ የጦርነት ውጤት ነው፡፡ ጦርነት የትም ቢደረግ አንደኛው ወገን ቢያይል ሟቾቹና ተጎጅዎቹ ቁጥራቸው ይለያይ ይሆናል እንጂ ሟች የማይኖርበት ወገን የለም፡፡ በሀገራችንም የሰሜኑ ጦርነት የሆነው ይሄ ነው፡፡ በርካቶች የተጎዳው ወገኔን ላገልግል ብለው ደፋ ቀና በሚሉበት ቦታ የተጎዳ ወገናቸውን አግኝተዋል፡፡

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሀገራችን ጨለማ ቀን ቢባል ማገነን አይደለም፡፡ ሳይታሰብ በሰሜን ዕዝ ላይ በሕወሓት ቡድን በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት በርካታ የመከላከያ አባላት ላይመለሱ አሸልበዋል። ክስተቱን ተከትሎ በቀጠለው ግጭት በርካቶች ውድ ሕይወታቸውን እና አካላቸውን አጥተዋል፡፡

በትግራይ ከሁለት ዓመታት በፊት የተፈጠረው ሁኔታ ወደ ጦርነት ከማምራቱ በፊት መንግሥት የሰላም አማራጮችን ሁሉ ሞክሯል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች ሞክረዋል። እናቶች እያለቀሱ ለምነዋል፡፡ መንግሥት ለውይይትና ለፖለቲካዊ ንግግር ቅድሚያ በመስጠት ከልክ በላይ ትችቶችን አስተናግዷል፡፡

ሁለት ዓመት በቆየው ጦርነት “የሞተው ወንድምሽ የገደለው ባልሽ ሐዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ” የሚለው ሀገራዊ እንጉርጉሮ በተግባር ታይቷል፡፡ የአንድ ቤተሰብ አባላት ጎራ ለይተው እርስ በእርስ ተገዳድለዋል፡፡ ገደልኩ ብሎ ለመፎከር የማይመች፤ ጠላት ተብሎ የማይጨከንበት ሁኔታ ውስጥ እንደ ሀገር ለሁለት ዓመት ተዘፍቀን ቆይተናል፡፡

በዚህም በርካቶች ደረሰልኝ ያሉት ልጃቸውን አጥተው በሀዘንም በደጋፊ ማጣትም ተጎድተዋል። በርካቶች የቤተሰባቸው እጣ ፋንታ ባለማወቅ አንዴ ይመጣ/ትመጣ ይሆን? በሚል ተስፋ ሲያደርጉ፤ ሌላ ጊዜ ሞቶ/ሞታ ይሆን በሚል ተስፋ መቁረጥ ሲዋልሉ ሰንብተዋል፡፡

መንግስት ጦርነቱ በሰላም ስምምነት ቢቋጭ ሀገርን አትራፊ የሚያደርግ መሆኑን ስለአመነበት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እንዲፈረም አድርጓል፡፡ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በኢትዮጵያ መንግስትና በሕወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት እነሆ አንድ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ በዚህ ስምምነት የጠፋውን መመለስ ባይቻልም እንኳ የጦር መሳሪያ ድምጽ የማይሰማበት አካባቢ መፍጠር መቻሉ ትልቅ ስኬት ነው፡፡

ባለፈው አንድ ዓመት የፌዴራል መንግሥት የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተመለከተ ከሚጠ በቅበት በላይ በሆደ ሰፊነትና ቁስሉ እንዲሽር ካለው ፍላጎት ለሰላም ያለውን ጽኑ አቋም ደጋግሞ አሳይቷል፡፡ በትግራይ ክልል የተለያዩ የመሰረተልማት ዝርጋታዎችን የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የባንክና የአውሮፕላን አገልግሎቶች በፍጥነት እንዲጀምሩ፣ ዩኒቨርሲቲዎችንና ትምህርት ቤቶችን ወደ አገልግሎት ለመመለስ የተለያዩ ተግባራትን ፈፅሟል፡፡ ከፌዴራል መንግሥቱም አልፎ ክልሎች ከአነስተኛ በጀታቸውና ገቢያቸው በመቀነስ የትግራይ ክልልን ደግፈዋል፡፡

የስምምነቱን አንድ ዓመት ተከትሎ ከሰሞኑ የመንግስት ባወጣው መግለጫም፣ መንግስት ለሰላም ባለው ፅኑ ፍላጎት ብዙ ርቀትን ቢጋዝም በዚያኛው ወገን እግር የመጎተት አዝማሚያ ይታያል፡፡ ይህም ሆኖ ግን የፌደራል መንግስቱ ለክልሉ የሚደረገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አላቋረጠም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም ፍላጎት ፅኑ ነው፡፡ መንግስትም በአፈ ሙዝ የሚደረግ ትግል ያልተገባ ዋጋ ከማስከፈል የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ጠንቅቆ ይረዳል፡፡ የሰላም አማራጭ ማስቀደምና ወደ ጠረጴዛ የማምጣት ፍላቱን በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሚያጠራጥር አይደለም፡፡

መንግሥት ከሁሉም በላይ በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍንና የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ ከማድረግ አኳያ ካለበት ኃላፊነት አንጻር ችግሮችን በሆደ ሰፊነት በድርድር ለመፍታት የሚሄድበት መንገድም ሊደነቅ፤ እውቅና ሊሰጠው የሚገባ ነው። የጠረጴዛ ዙሪያ የሰላም ውይይት የሰላምን ዋጋ ለሚረዳ፣ እርስ በእርስ መገዳደል ለሰለቸው፣ የዜጎች ሰቀቀን ለሚሰማው ሁሉ ልብን በደስታ የሚሞላ፣ ‘ጮቤ’ የሚያስረግጥ ነው።

የሰላም ውይይት ንፁሃን ዜጎች እየከፈሉት ያለውን ያልተገባ ዋጋ ስቃይ፣ ጥፋት በፍጥነት ለማስቆም አቅሙ ግዙፍ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ካለበት አለመረጋጋት ወጥቶ እፎይ እንዲል ትልቅ አቅም ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ወገን መትጋት አለበት፡፡ ማንኛውም ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ምላሽን በጠመንጃ ለማግኘት ከመሽቀዳደም ይልቅ የሰላምን አማራጭ ስለመኖሩ ጠንቅቆ መረዳት ይኖርበታል፡፡

በሌላ በኩል በአንድ ክልል ሰላም አለመስፈን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሁሉንም ክልሎች ሰላም ያናጋል። ስለዚህ ኅብረተሰቡ የጦርነቶች ዋነኛ ገፈት ቀማሽ እራሱ መሆኑን ከትናንት የጦርነት ታሪኮች በመማር የጦርነት ነጋሪት ጎሳሚዎችን በቃችሁ ሊል፤ ለሰላም ዘብ መቆምና ጦርነትን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ማውገዝ ይጠበቅበታል።

ከሌሎች መማሩ ቢቀርብን ከራሳችን እንማር፤ ግጭቶችን ለመፍታት ትልቅ ጦርነት እስኪሆኑ፤ በርካቶች እስኪሞቱ በርካታ ንጹሃን ቀያቸውን ለቀው እስኪሰደዱ አንጠብቅ፡፡ የአንድ ሰው ሕይወት ዋጋ አላትና በተቻለ አቅም ችግሮችን ከሥር ለመፍታት እንጣር፡፡ በትላንት ትርክቶች ዛሬ ግጭቶች እንደሚፈጠሩት፤ ዛሬ በኛ ትውልድ በሚፈጠር አምባጓሮ ለነገ ትውልድ ግጭት መንስኤ ላለመሆን ግጭቶቻችንን በጊዜው መፍታት እንጀምር፡፡

ከጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን   ኅዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You