አዳማ፡- የኦሮሞና የአፋር ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀው አብሮነታቸውና ሰፊ ትስስራቸው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡ የሁለቱ ህዝቦች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መድረክ ትናንት በአዳማ ከተማ አባ ገዳ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ እንደገለጹት፣ ሁለቱ ህዝቦች ለዘመናት የዘለቀው አብሮነታቸውና ሰፊ ትስስራቸው ከነበረውም በላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ለሁለቱም ህዝቦች ስኬት በጋራ ይሠራል፡
እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ ፣ አንዳንድ የሚታዩ ግጭቶች በግለሰብ ቆስቋሽነት የሚነሱ ህዝብን የማይወክሉ እንዲሁም ከህዝቡ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ናቸው፡፡ አልፎ አልፎ የሚከሰቱትን ችግሮች ለመፍታትም መንግሥት፣ የሃገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች በጋራ እየሠሩ ነው፡፡
የሁለቱን ክልሎች አንድነት ለመሽርሸር በሚሠሩ አካላት ላይ ህጋዊ ዕርምጃ ይወሰዳል ነው ያሉት አቶ ሽመልስ፣ አርብቶ አደሩን በልማት ተጠቃሚ የማድረግና የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
ክልሉ ወደፊትም የሚሠራቸው የልማት ሥራዎች የኦሮሚያ ክልልን ብቻ ሳይሆን የአፋርና ሌሎች ክልሎችንም ተጠቃሚ የሚያደረጉ ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የአፋር ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሃጂ አወል አርባ በበኩላቸው፣ በምሥራቁ የኢትዮጵያ ክፍል ከሚገኙት ከሀረሪ፣ ከሱማሌ እና ከሌሎች ህዝቦች ጋር ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
በክልሉ ያሉትን አርብቶ አደሮች ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት ለመቀየር በልማቱ ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎችም ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡
ወደፊት የኦሮሚያንና የአፋርን ህዝቦች በልማት ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውንም ፕሬዚዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡
በቅርቡ ተመሳሳይ መድረኮች በአፋር ክልል እንደሚዘጋጅ የገለጹት ሃጅ አወል፣ ይህን መድረክ ላዘጋጀው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ታላቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ምሁር የኦሮሞና የአፋር ህዝብ የአንድ ዝርያ ልጆች፣ ታሪካቸውም አንድ ዓይነት፣ ባህላቸውና የህዝብ አደረጃጀታቸውም የገዳ ሥርዓትን በተመለከተ ተመሳሳይነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
“ከአንድ ግንድ የወጣን ሲሆን ዕምነታችንና የአኗኗር ዘይቤያችን በአብዛኛው ተመሳሳይ፣ ኢኮኖሚያችንም በአንድ ላይ የተመሰረተ የትናንቱ ታሪካችንም ሳይሆን የነገውም ዕጣ ፈንታችን አንድ ነው” ብለዋል፡፡
ከሁለቱ ክልሎች የተውጣጡ የሕዝብ ለህዝብ መድረኩ ተሳታፊዎች ግጭቶችን በሚቀሰቅሱ ሰዎች ላይ ለምን ህጋዊ ዕርምጃ አልተወሰደም? ኮንትሮባንዲስቶችን ለማስቆም ምን እየተሠራ ነው? ግጭቶችን አስቀድሞ ማስቆም ለምን አልተቻልም? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች አንስተዋል፡፡ የሁለቱም ክልል ፕሬዚዳንቶች ለቀረቡት ጥያቄዎች ሰፊ መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሁለቱም ክልል ህዝቦች ችግር አንድ መሆኑንና አብሮ ለሰላም፣ለዕድገትና ለትብብር ጠንክሮ በመሥራት ችግሮቹን መፍታት እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 17/2011
በወንደወሰን መኮንን