በአዲስ አበባ ከተማ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ ዋስትናቸው እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ምግብ ዋስትናና ልማት ሴፍቲኔት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ወጋየሁ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት በከተማ ደረጃ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የተጀመረው በ2009 ዓ.ም ሲሆን ከዚያን በፊት ግን በገጠር የሀገሪቱ ክፍል እየተተገበረ ነበር፤ ይሁን እንጂ የከተሞች የድህነት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ መንግስት ከአለም ባንክ ጋር በመተባበር ፕሮግራሙ ተጀምሯል፡፡
በአለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት ድጋፍ የተጀመረው የከተሞች ምግብ ዋስትና ፕሮግራም 450 ሚሊዮን ዶላር የተመደበለት ሲሆን 300 ሚሊዮን ዶላሩ ከአለም ባንክ በተገኘ ብድር እንዲሁም ቀሪው 150 ሚሊዮን ዶላር በኢትዮጵያ መንግስት የተሸፈነ ነው፡፡
ፕሮግራሙ በ11 ከተሞች እየተተገበረ ያለ ሲሆን 70 በመቶ የሚሆነው በጀት የተመደበው ለአዲስ አበባ ከተማ መሆኑን ለዚህም በከተማዋ ያለው የድህነት ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑ በምክንያትነት እንደሚጠቀስ አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ዘላለም ፕሮግራሙ በአዲስ አበባ በሰኔ 2009 ዓ.ም መጀመሪያው ዙር ተጠቃሚዎች የተጀመረ ሲሆን በ35 ወረዳዎች በድህነት መጠናቸው የተለዩ 123 ሺህ 918 ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ ዜጎቹ በቀጥታ ድጋፍ እና በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ የተካተቱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 84 በመቶ የሚሆኑት በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ቀሪዎቹ 16 በመቶ ደግሞ ቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡
አቅመ ደካሞች፣ ህፃናት፣ መስራት የማይችሉ እና መሰል ችግር ያለባቸው የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ አካባቢቸውን እያለሙና የስራ ባህላቸውን በሚያዳብር መልኩ የማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች መሆናቸውን አቶ ዘላለም አስረድተዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር ፕሮግራም በ55 ወረዳዎች 200 ሺህ ያህል ዜጎች ተጠቃሚ የተደረጉ ሲሆን እንደመጀመሪያው ዙር 84 በመቶ የሚሆኑት በማህበረሰብ አቀፍ ድጋፍ ቀሪዎቹ 16 በመቶ ደግሞ የቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ አግኝተዋል፡፡
ፕሮግራሙ እስከአሁን በአዲስ አበባ 90 ወረዳዎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በዚህም 392 ሺህ 918 የሚሆኑ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሙ በአምስት ዘርፎች ማለትም በአረንጓዴ ልማት፣ ውበትና መናፈሻ፣ ደረቅ ቆሻሻ የማንሳት ስራ፣ የመሰረተ ልማት አገልግሎት የመስጠት ስራ እና ለከተማ ግብርና ምቹ ሁኔታን የመፍጠር ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ነው፡፡
በቀጥታ ድጋፍም ይሁን በማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሙ አንድ ቤተሰብ እስከ አራት የቤተሰብ አባላት ድረስ ተጠቃሚ መሆን የሚቻል ሲሆን በቀጥታ ድጋፉ በመጀመሪያው ዙር በግለሰብ 170 ብር በየወሩ ድጋፍ ይደረግ የነበረ ሲሆን ከኑሮ ውድነት መጨመር ጋር በተያያዘ ክፍያው ወደ 215 ብር ከፍ እንዲል መደረጉን ዳይሬክተሩ የተናገሩ ሲሆን በዚህ ስሌት መሰረትም አራት ቤተሰብ ያለው አንድ የፕሮግራሙ ተጠቃሚ በወር 860 ብር በአካውንቱ በየወሩ ይገባለታል፤ ይህ ድጋፍም እስከ ህይወት ፍፃሜ የሚቀጥል ነው ብለዋል፡፡
በማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሙ የታቀፉት ደግሞ ፕሮግራሙ አብሯቸው የሚቆየው ለሶስት አመታት ብቻ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር በቀን 60 ብር ይከፈላቸው ነበር ያሉት አቶ ዘላለም ካለው ነባራዊ የኑሮ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ክፍያቸው ወደ 75 ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል ብለዋል፡፡
እንደ ቀጥታ ድጋፉ ሁሉ አንድ ግለሰብ እስከ አራት የቤተሰብ አባላቱን ማስጠቀም የሚችል ሲሆን በወር ውስጥ እንደቤተሰቡ ብዛት ከአምስት እስከ 20 ቀን በመስራት ገቢ ያገኛል፤ ለአብነትም አራት ቤተሰብ ያለው በወር ውስጥ 20 ቀናትን በመስራት 1 ሺህ 500 ብር ገቢ የሚያገኝ ሲሆን ከጠዋት 12፡00 ሰዐት እስከ ረፋድ 04፡00 ሰዐት ድረስ ይሰራሉ፤ ከሚያገኙት ገቢም 20 በመቶውን በፈቃደኝነት እንደሚቆጥቡ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በማህበረሰብ አቀፍ ስርዐቱ ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች ሶስት አመት ሲሞላቸው የሚመረቁ ሲሆን ወደ ዘላቂ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮግራም እንዲገቡ በማድረግ ከቆጠቡት ገንዘብ በተጨማሪ ፕሮግራሙ ከ13-15 ሺህ ብር ድጋፍ በማድረግና ልዩ ልዩ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ በግል፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ወይም በማህበር ተደራጅተው እንዲሰሩ ሁኔታዎች ይመቻችላቸዋል፡፡
ወ/ሮ ዘውዴ ሙሉ የየካ ክ/ከተማ ወረዳ ስምንት ነዋሪ ናት፤ በከተማ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም የማህበረሰብ አቀፍ ተጠቃሚ ከሆነች ሰባት ወራት ማስቆጠ ሯን ትናገራለች፡፡ አራት ቤተሰብ ያላት ወ/ሮ ዘውዴ በየወሩ በምታገኘው 1 ሺህ 500 ብር ገቢ እራሷንና ቤተሰቦቿን ከማስተዳደር ባለፈ ኑሮዋ መቀየሩን ነግራናለች፡፡
በሰው ቤት ልብስ በማጠብ በወር እስከ 500 ብር አገኝ ነበር ያለችው ወ/ሮ ዘውዴ አሁን ላይ ግን ገቢዋ በመሻሻሉ በህይወቷ ለውጥ መታየቱን ተናግራለች፤ ወ/ሮ ዘውዴና የስራ ባልደረቦቿ የወደፊት እቅዳቸውን በመንደፍ ፕሮግራሙ ከተጠናቀቀ በኋላ በጓሮ አትክልት ልማት በመደራጀት ዘላቂ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸትም አስበዋል፡፡
በሁለቱ ዙሮች ተጠቃሚ ያልሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችን በሶስተኛው ዙር በማካተት ለመስራት ወደፕሮግራሙ ባልገቡ 26 ወረዳዎች 92 ሺህ 05 የሚሆኑ ጠጠቃሚዎች መለየታቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ዘላለም ገለፃ ተጠቃሚዎችን የማጥራትና የኑሮ ደረጃ ምዘና የመስራት ስራ ከተሰራ በኋላ በያዝነው አመት ወደ ፕሮግራሙ የሚቀላቀሉ ሲሆን በሁለቱ ዘርፎች ማለትም በቀጥታ ድጋፍና በማህበረሰብ አቀፍ እንደ ቅደም ተከተሉ 16 በመቶ እና 84 በመቶ ተጠቃሚ የሚሆኑ ይሆናል፡፡
በድልነሳ ምንውየለት