አዲስ ዘመን ድሮ

ማታ ሊሰርቀን ከቤታችን የገባውን ሌባ፤ ጠዋት ሀገር ሰላም ብለን ማልደን ስንነሳ ከሳሎናችን ተኝቶ ብንመለከተው ምን ይሆን የሚሰማን? ይዞ የሚሄደውን ዕቃ እየተመለከተ ሲያሰላስል ድንገት በጠጅ የተሞላውን በርሜል ቢያገኝ ጊዜ፤ መጠጡ አስጎመዠውና ለቅምሻ ብሎ ጀምሮ በስካር ወድቋል… በድሮው አዲስ ዘመን እንዲህ ያሉ ጉዶችም ታትመው ለንባብ በቅተዋል:: በመዲናችን አዲስ አበባ ያለሰፈሯ ስትዞር የነበረችው ግለሰብም ተይዛ በእስር ተቀጥታለች። የዱኩላ ሥጋ በቤተሰቡ መሃል ጉድ አፈላ…የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ ወደ ፓርላማው ዘልቆ፤በመላ ፓርላማው አነጋጋሪው ጉዳይ ሆኗል:: በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ በብዛት ወንጀል ነክ ዜና የያዙትን እነዚህን ጉዳዮችን ጨምሮ ሌሎችም ትውስታዎች ተካተውበታል።

የመጠጥ ቤቶች ጉዳይ ለፓርላማ ቀረበ

የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ስለ ሴተኛ አዳሪዎችና መጠጥ ቤቶች መስፋፋት ላይ ከተነጋገረ በኋላ፤ ጉዳዩን አግባብ ያለው የመወሰኛው ምክር ቤት ኮሚቴ ከሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ልዩ ኮሚቴ ጋር እንዲያጠና ትናንት ባደረገው ስብሰባ ወሰነ::

በኢትዮጵያ የሴተኛ አዳሪዎችና እንዲሁም የመጠጥ ቤቶች መስፋፋት የሚያስከትለውን ፕሮብሌም ገልጸው፤ ምክር ቤቱ በጉዳዩ መክሮበት አንድ መፍትሔ እንዲገኝለት በማለት ለምክር ቤቱ

 ሐሳብ ያቀረቡት የተከበሩ አቶ አመዴ ለማ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ናቸው።

ይኸው ጉዳይ በቀደምትነት የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት ሚኒስቴር ከውጭ አገር ባስመጣቸው ኤክስፐርቶች በመጠናት ላይ መሆኑም ተገልጿል።

ከኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ

(አዲስ ዘመን ኅዳር 28 ቀን 1958 ዓ.ም)

ሊሰርቅ የሄደው ሌባ ጠጅ አስክሮት ተያዘ

መስከረም 30 ቀን 1959 ዓ.ም አባዲ ተስፋዬ ከሌሊቱ አምስት ሰዓት ላይ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ የአቶ ካህሳይን ቤት ለመስረቅ ሄዶ ከዚያም ሲደርሱ በሩ ስለተዘጋባቸው በዕድሜና በሰውነት ያነሰው አባዲ በአጥር ተንጠልጥሎ ገባ።

አባዲ የቤቱን በር ከፍቶ እንደገባ እያማረጠ ለመስረቅ ጥሩ ጊዜ ሆነለት። በዚህ ሁኔታ የተሰረቀውን ዕቃ እያማረጠ እያጋዘ በማመላለስ እውጭ ካስቀመጠ በኋላ ጠጅ ጠጅ ሸተተው። ወደኋላው መለስ ቢል ጠጅ የሞላው በርሜል አየ። ጎንበስ ቢል የውሃ መቅጃ ቆርቆሮ አገኘ። ከዚህ በኋላ ምን ይጠየቃል ራሱን በራሱ ጋባዥ ሆነ። ከዚያ በኋላ ስካር ተጫጭኖት ስለተሸነፈ አባዲ ከወደቀበት ሥፍራ ሳይነሳ በዚያው ተኝቶ አደረ:: በማግስቱ ጠዋት ባለቤቶቹ ከእንቅልፋቸው ተነስተው ቤት ሊጠርጉ ሲሉ አባዲ ተጋድሞ አገኙት። ወዲያው በፖሊስ አስያዙት። ከዚያም ወደ ማረፊያ ቤት ተወስዶ በወታደር ደስታ በቃኸኝ አማካኝነት ቃሉን ሲሰጥ «ለመስረቅ ሔጄ ጠጅ አስክሮኝ በዚያው ተኛሁ» ሲል አረጋግጧል ብለው ሻለቃ ጌራ ወርቅ

 ገልጠዋል።

በትግራይ ግዛት የኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ (አዲስ ዘመን ጥቅምት 10 ቀን 1959ዓ.ም)

የእስረኞች ሱቅ የሰረቀው በእስራት ተቀጣ

ጥቅምት 10 ቀን 1972 ዓ.ም የጊቢ አውራጃ ወህኒ ቤት ባልደረባ የነበረው ተሾመ አያና የወህኒቤቱ የሕግ እስረኞች ዕቃ የሚሸጡበት ሱቅውስጥ ሌሊት ገብቶ ከሁለት ሺ 232 ብር በላይ መስረቁ ስለተረጋገጠበት በሰባት ዓመት ጽኑእስራት እንዲቀጣ የአውራጃው ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ውስጥ በዋለው ችሎት በይኖበታል። በተያያዘም በገሙ ጎፋ ክፍለ ሀገር የጎፋ አውራጃ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆነው አሰግድ አስፋው በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋ ለተጎዱ ወገኖች ዘላቂ መፍትሔ ማካሄጃ እንዲውል በኃላፊነት ከተሰጠው ገንዘብ ውስጥ ሦስት ሺ 147 ብር ከ45 ሳንቲም አጉድሎ ለግል ጥቅሙ አውሏል በመባል ተከሶ አድራጎቱ በማስረጃ ስለተረጋገጠበት ሰሞኑን በአምስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ የጎፋ አውራጃ ፍርድ ቤት ወስኖበታል።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 1972ዓ.ም)

በሌሊት ያለሰፈሯ ስትዞር የነበረችው ግለሰብ ተይዛ ታሰረች

ወይዘሮ ፋንቱ ወልደማርያም የተባለች በንፋስ ስልክ አካባቢ የምትኖር ሴት ያለሰፈሯ ከሌሊቱ 10

ሙሉጌታ ብርሃኑ

 ሰዓት በየካቲት 12 አደባባይ ስትዞር በመገኘቷ ተይዛ፤ የሦስተኛ ወረዳ ፍርድ ቤት የአንድ ወር እሥራት የቀጣት መሆኑን አስታውቋል። ስትዘዋወር መገኘቷንና ተላላፊ መኪናዎችንም አድርሱኝ በማለት ማስቸገሯን ፖሊሶች መመስከራቸውን አስታውቋል።

ተከሳሿም ፍርድ ቤት ቀርባ በተጠየቀች ጊዜ በአድራጎቷ ጥፋተኛ መሆኗን ስላመነች ፍርዱ ተሻሽሎ በ30 ብር መቀጮ ወይም በአንድ ወር እሥራት እንድትቀጣ ተደርጎ መቀጮውን መክፈል ስላልቻለች አንድ ወር እንድትታሰር ወደ ወህኒ ወርዳለች ሲል ከአንደኛ ፖሊስ ጣቢያ የተገኘ ዜና ያስረዳል።

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 1963ዓ.ም)

የድኩላ ሥጋ ሰው ገደለ

–አሥሩ በጠና ታመዋል

ነቀምቴ፤(ኢ-ዜ-አ-) በወጥመድ ተይዞ የተገደለ የድኩላ ሥጋ በተመገቡ የአንድ ቤተሰብ አባል በሆኑ አሥራ አንድ ሰዎች ላይ የሞትና ጤና ጉዳት መድረሱ ተገለጠ:: ቡልቻ ቶኬ የተባለ ሰው መስከረም 22 ቀን 62 ዓ.ም አንድ ድኩላ በወጥመድ ይዞ ከገደለ በኋላ ወደ ቤት ወስዶ አሥራ አንዱም ቤተሰቦች ሥጋውን መመገብ ጀመሩ:: በዚሁ ጊዜ ከመካከላቸው ቡርሜሳ ወዳጆ ይባል የነበረው ወዲያውኑ ታሞ ሲሞት፤ የቀሩት አስሩ ሰዎች በጠና ታምመው በሕክምና ላይ ይገኛሉ::

የድኩላውን ሥጋ በመመገብ የሞትና በጤና ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በወለጋ ጠቅላይ ግዛት በቄለም አውራጃ የአንሲሎ ወረዳ ኗሪ መሆናቸው ታውቋል::

(አዲስ ዘመን ጥቅምት 6 ቀን 1962ዓ.ም)

አዲስ ዘመን   ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You