ዲጂታል ኢኮኖሚን የመተግበር ጉዞ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ የዲጂታል አማራጮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ፤ በዓመትም እስከ አራት ትሪሊዮን የሚደርስ ብር በዲጂታል የክፍያ አማራጮች እየተዘዋወረ መሆኑንና ከ170 በላይ የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ውስጥ መግባታቸውን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል::

የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ አካታች የሆነ ዲጂታል ኢኮኖሚን ማልማት እንደሆነ፣ ስትራቴጂውም የተቀረፀው፣ አሁን ላይ ያለው ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታና ተሞክሮ ላይ ተመስርቶ መሆኑን መረጃዎቹ ያሳያሉ:: ኢትዮጵያ ከነበረችበት ሁኔታ ተነስታ በ2025 ዲጂታል ኢኮኖሚ እንዲኖራት እየሰራች መሆኑም በተለያየ ጊዜ በተሰጡ መረጃዎች ተገልጿል::

በዚህ መልኩ ኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እያደረገችው ያለው ጉዞ ምንን ያሳያል? በዘርፉ ያሉ ጥንካሬዎችና ውስንነቶች ምን ይመስላሉ የሚሉ ሃሳቦችን አንስተን የባለሙያ ማብራርያ ጠይቀናል::

የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር ዳዊት ሐዬሶ እንዳብራሩት፤ ቴክኖሎጂ በየጊዜው እያደገ ነው:: በዚያው ልክ የሰው ልጅ የእውቀት ሁኔታና ኢኮኖሚውም እያደገ ነው:: ከእድገቱ ጋር ተያይዞ የሰዎች ማሕበራዊ ግንኙነት ጨምሯል:: በመሆኑም እየጨመሩ ያሉ ፍላጎቶችን በቀደመው አሰራር ማሟላት ስለማይቻል የተቀላጠፈ አገልግሎት መሥጠት ይጠበቃል::

አገልግሎትን በማሻሻልና የተጠቃሚውን ፍላጎት ለመመለስ፤ ዘመናዊና የተሻሻሉ አሰራሮችን መተግበርና ተወዳዳሪ ሆኖ መገኘትም ያስፈልጋል:: ተወዳዳሪ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ ተፎካካሪም የሀገር ውስጥንም የዓለምንም ሀብት መጠቀም፣ እንዲሁም የዓለምን ሀብት መሳብ የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት በቴክኖሎጂ መታገዝ ግዴታ ሆኗል::

በአሁኑ ጊዜ ተወዳዳሪ ለመሆን፤ የምርትና አገልግሎት ግብይት ወጭን (ትራንዛክሽን ኮስት) መቀነስ ያስፈልጋል:: ትራንዛክሽን ኮስትን መቀነስ የሚቻለው ዲጂታል ቴክሎጂ በመጠቀም ነው:: ትራንዛክሽን ኮስት ቀነሰ ማለት የሚመረተው ምርትና አግልግሎቶች በዓለም ደረጃ ተፈላጊና ተፎካካሪ እንዲሆን ከማስቻሉ በተጨማሪ በዋጋም ቅናሽ ይሆናል:: ይህ ማለት አንድ ሰው የትራንስፖርትና የተለያዩ ወጭ ሳያወጣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም የሚፈልገውን እቃም ሆነ መረጃ ባለበት ቦታ ሆኖ ማግኘት ሲችል ወጭና ድካም ይቀንስለታል::

የምርትና አገልግሎት ወጭም በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲቀርብና ተወዳዳሪ እንዲሆን በማድረግም ያግዛል:: አምራችና አገልግሎት ሰጭዎችም የራሳቸውን የትራንዛክሽን ኮስት በሚቀንሱበት ወቅት፣ እንዲሁም የሚፈልጉት ምርትና አገልግሎት በቴክኖሎጂ አማካኝነት ለብዙሃን ማስተዋወቅ ሲችሉ የሚያመርቱትን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ አቅም ይኖራቸዋል:: በተመጣጣኝ ዋጋ አቀረቡ ማለት ደግሞ በገበያ ላይ ተወዳዳሪነታቸው ይጨምራል:: ይህ ደግሞ ምርታማነት በኢኮኖሚው ውስጥ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ይኖረዋል::

ከተለያየ ዓለም ጋር መገበያየትና መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ዲጂታል ኢኮኖሚ እየተፈጠረ መሆኑንና በዚህ ውስጥ ማለፍና አብሮ መራመድ ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ዳዊት፤ ቴክኖሎጂ አንዱ ፍጥነት መሆኑና በፍጥነት መሸጥና መረጃንም መለዋወጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል::

ከዚህ አንጻር ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት አስፈላጊ እንደሆነ የጠቀሱት ዶክተር ዳዊት፤ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ስላለው ምቹ ሁኔታና ተግዳሮቶችም እንዳሉት አብራርተዋል::

ዶክተር ዳዊት እንደሚሉት ያደጉ ሀገራት በዲጂታል ቴክሎጂ ላይ ብዙ ኢንቨስት አድርገው የፈጠራ ሥራ ሰርተዋል:: እነዚህ ታዳጊ ሀገራት ዘግይተው ወደ ትግበራ መግባታቸውም ለጥናትና ምርምር የሚወጣውን ወጪ ቀንሶላቸዋል:: የሌሎችን ተሞክሮና ልምድ በመቀመር ከሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዋሀድ ቀጥታ ወደ ፈጠራ ሥራ መግባት ነው የሚጠበቅባቸው::

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ከአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ጋር የተላመዱ በርካታ የሰለጠኑ ወጣቶች ባለሙያዎች በመኖራቸው ለነዚህ ባለሙያዎች መለስተኛ ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ከሌሎች ሀገሮች ልምድ በመቀመር በቀላሉ ቴክኖሎጂውን መተግበር የሚቻልበት ምቹ ሁኔታ አለ::

በሌላ በኩልም እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመፍጠር ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል:: ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ መኖርም ለዘርፉ ወሳኝ ከሚባሉት ውስጥ ይጠቀሳል:: የሕዝብ ቁጥሩ ሲጨምር ገበያውም ይሰፋል:: በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ከ120 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ መኖሩ የግብይቱን እድል ያሰፋዋል:: ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር ሊሄድ የሚችል የመሠረተልማት ግንባታም በተለይም በከተሞች አካባቢ በበቂ ሁኔታ መኖሩም ከዝግጅት አንጻር በቂ ተደርጎ ይወሰዳል::

የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች እንዲጨምሩና እንዲሻሻሉ፤ ልምድ ያላቸው የውጭ ኩባንያዎችን እንደ ሳፋሪ ኮም ያለ ድርጅትን ወደ ሀገር በማስገባት የመሠረተልማት አማራጮችን ለማስፋት የተደረገው ጥረት ለዲጂታል ኢኮኖሚ የተሰጠውን ትኩረት ያሳያል::

ዶክተር ዳዊት እንደተግዳሮት ብለው ባነሱት ላይም እንዳስረዱት፤ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ሲውል የሉዓላዊነት ጉዳይም አብሮ ይነሳል:: አንድ ሀገር ዳርድንበሯን በሰራዊት እንደምታስጠብቀው ሁሉ ከዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የኢኮኖሚ ጥቃትን ለመከላከል የቴክኖሎጂ ሰራዊት ያስፈልጋል::

በትልቅ ደረጃ የተገነባ የባንክ አሰራር (ሲስተም)፣ በድረገጽ የሚከናወን ገበያ (ኦንላይን ሺፒንግ) ድርጅቶች በቀላሉ በመስበር (ሀክ) በማድረግ በምርትና አግልግሎት ላይ በቀላሉ ጉዳት በማድረስ፣ ገንዘብ ከአንዱ ወደሌላ በማዘዋወር፣በምርት ጥራት ላይ እንዲሁ ንጥረነገሩን (ኢንግሪዲየንት) በመቀየር ሕዝብ ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ ማድረግ ከተጽእኖዎቹ ጥቂቶቹ ናቸው::

እውነተኛና ታማኝ የሆነ ዜጋ ከመገንባት አንጻርም ሥራዎች እንደሚያስፈልጉ የጠቀሱት ዶክተር ዳዊት፤ ቴክኖሎጂን በመጠቀም በሚደረግ ግንኙነት፤ የአንድን ድርጅት ወይንም የሀገርን ሚስጥር በቀላሉ ለሌላ ወገን አሳልፎ ለመስጠት እድሉ ሰፊ ነው:: በመሆኑም የመረጃ ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ ለድርጅቶችም ሆነ ለሀገር ታማኝ የሆነ አገልጋይ ዜጋ መፍጠር ያስፈልጋል:: ጎን ለጎን ሕግና ሥርዓት መኖር አለበት:: ተግዳሮቶችን መቋቋም ከተቻለ ዲጂታል ኢኮኖሚን መግንባትና መተግበር ይቻላል::

ተግዳሮቶች ቢኖሩም ዕድሎቹ ላይ ማተኮሩ የተሻለ እንደሆነ የሚገልጹት ዶክተር ዳዊት፤ ኢትዮጵያ ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ መግባቷ ከዚህ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ያልነበራቸው ባለሃብቶች ፍላጎት እንዲኖራቸው እንደሚያስችልና በአጠቃላይ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ አስረድተዋል::

ዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት ማህበረሰቡ ለቴክኖሎጂ ያለው ቅርበት ወሳኝ ነው:: በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂው ያለው ቅርበት እንደተግዳሮት የሚነሳ አይደለም:: ለአብነትም በግል እንደራይድ ያሉ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ፤ ቀድመው ቴክኖሎጂውን መተግበራቸው ማህበረሰቡ ቶሎ ቴክኖሎጂውን እንዲቀላቀል መንገድ ተከፍቷል:: ይህም እያደገና እየጨመረ የሚሄድ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል::

ኢትዮጵያ ዘግይታም ቢሆን ዲጂታል ኢኮኖሚን መተግበር መጀመሯ በመልካም ጎን ይወሰዳል ያሉት ዶክተር ዳዊት፤ በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ የዲጂታል አማራጮች በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋ፤ በዓመትም እስከ አራት ትሪሊዮን የሚደርስ ብር በዲጂታል የክፍያ አማራጮች እየተዘዋወረ መሆኑንና ከ170 በላይ የመንግሥት ተቋማት የዲጂታል ግብይት ሥርዓት ውስጥ መግባታቸው ከፍተኛ እመርታ መሆኑን አስረድተዋል::

ዲጂታል ኢኮኖሚ በሆነ ዓለም ውስጥ በር ዝግ ማድረግ ማለት ለውጭው ዓለም በር እንደመዝጋት ይቆጠራል የሚሉት ዶክተር ዳዊት በርን ሊጂታል ኢኮኖሚ ዝግ ማድረግ በውጭ ያለውን ሀብት በበቂ ሁኔታ መቀራመት እንዳትችል ያደርጋል::

እስከ ዛሬ በነበረው ሂደትም ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚው ጀርባዋን ሰጥታ ኖራለች:: ይህ ደግሞ በውጭ ሀገር የሚፈጠሩ ሀብቶችን ተሻምቶ ወደ ራስ ሀገር ለማስገባት እንዳትችል አድርጓታል::

ኢትዮጵያ ንግድንም ሆነ ፋይናንስ፣ እንዲሁም ኢንቨስትመንት ከዓለም ተሻምታ ወደ ሀገር አለማስገባቷ በኢኮኖሚ እድገቷ ላይ አሉታዊ (ኔጌቲቭ) ተጽእኖ ፈጥሯል:: በዚህ ምክንያትም ማደግ በሚገባት ልክ አላደገችም ማለት ነው::

ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በረኸተስፋ በበኩላቸው፤ ዓለም ወደ ዲጂታል መግባት ብቻ ሳይሆን፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ብዙ ስራዎችም እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል::በአሁኑ ጊዜም ሰዎች ሥራ ሊያጡ ይችላል የሚል ስጋትም እየተፈጠረ ነው ይላሉ:: እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ማብራሪያ፤ ብዙ ሀገራት ወደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እየሄዱ ነው:: ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ (ፊንቴክ) የሚባለው ዲጂታል ቴክኖሎጂን እንደሚያራምድ ታምኖበት በሴኔጋል፣ ናይጄሪያ፣ ኬኒያ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እስከ አንድ ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ያላቸው ወጣቶች መፍጠር ተችሏል:: እነዚህ ወጣቶች እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የቻሉት፤ የድረገጽ (ኢንተርኔት) አቅርቦት በስፋት በመኖሩ ነው::

ኢትዮጵያም በዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ማለፏ ግድ ነው:: ከመሠረተ ልማት አንጻር የኢንተርኔት አገልግሎቱ ወደ 5G ቢያድግም አገልግሎቱ ፈጣን ባለመሆኑ አሰራር ላይ ተግዳሮት እየተስተዋለ ነው:: ዲጂታል ኢኮኖሚ መሠረቱ ድረገጽ (ኢንተርኔት) በመሆኑ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ይገባል:: ተጨማሪ ኩባንያዎች መምጣታቸው አገልግሎቱ የተሻለ እንዲሆን ስለሚያግዝ ይበረታታል::

ሥራዎች በአዲስ አበባ በክፍለ ከተሞች ደረጃ በስፋት እንደሚከናወን የጠቀሱት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ አገልግሎቱ ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን ኃላፊዎችም ሆኑ ሰራተኞች ብቃት ሊኖራቸው እንደሚገባ አመልክተዋል::

በዘርፉ የሰለጠኑ ወጣቶችን ማፍራት፣ ወጣቶቹ ፍላጎትም ሊኖራቸው እንደሚገባ ገልጸዋል:: በቅርቡ ይፋ የሆነው የ12ኛ ክፍል ውጤት ደግሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ እንዳይሆን በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል::

ትምህርት ቤቶችም በቴክኖሎጂ የተደራጁ፣ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ግንዛቤ ላይ በመሥራት ወጣቶችን እያበቁ ስለመሆናቸውም መፈተሽ አስፈላጊ እንደሆነ የተናገሩት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ብዙ ሀገራት መንግሥታዊ የሆኑ አሰራሮችን ዲጃታል ማድረጋቸውን አመልክተዋል:: ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ ጅምር እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን በመጥቀስ፤ እንደ ፓስፖርት ባሉ አሰራሮች ላይ ሰዎች መሥሪያቤቱ ድረስ መሄድ ሳያስፈልጋቸው በኢንተርኔት ተጠቅመው አገልግሎቱን ማግኘት መጀመራቸው ይበረታታል ብለዋል::

እንደ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ኢኮኖሚ ለማጠናከር ቀድመው ዲጂታል ኢኮኖሚን ከተገበሩት ትምህርት መውሰድ ያስፈልጋል:: ጉዳዩ ከባንክ ጋር የሚያያዝ ባይሆንም በአንድ ወቅት ናይጄሪያ ሀገር ውስጥ በማጭበርበር ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ መንግሥትም አገልግሎቱን እስከ መዝጋት የደረሰበት የኤሌክትሮኒክስ ገንዘብ አሰራር ይጠቀሳል:: በዚህ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥም ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር አንደ አንድ ትምህርት ሊወሰድ ይችላል:: ከዚህ ተሞክሮ የቁጥጥር ሥርዓት ማበጀት ያስፈልጋል::

የቁጥጥር ሥርዓት ሌላውም ላይ ያስፈልጋል የሚሉት ዶክተር ቆስጠንጢኖስ፤ ለአብነትም ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ባንኮች እንዲሰሩ ፍላጎት አለ፤ እንቅስቃሴዎችም ተጀምረዋል:: ባንኮቹን ለማስተዳደር ሳፋሪ ኮም ሀገር ውስጥ እንዲሰራ ልክ ኢትዮቴሌኮም ላይ እንደተተገበረው ሁሉ የውጭ ባንኮችም ሲገቡ በተመሳሳይ መፈጸም ይኖርበታል:: በዚህ አካባቢ የሚሰሩ ባለሙያዎች እውቀቱ፣ፍላጎቱና ራዕይ ያላቸው፤ የተሻለ ተከፋይም መሆን ይኖርባቸዋል::

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ እንዳሉት፤ ለአንድ ሀገር ምጣኔ ሀብት እድገት ዲጂታል ኢኮኖሚ በእጅጉ ያስፈልጋል:: ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማሳለጥ የመሠረተልማት ግንባታው ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት::

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የጀመረችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞ ተስፋ ሰጪ ነው:: ሆኖም አገልግሎቱን የበለጠ ተደራሽና የኢኮኖሚውም አንቀሳቃሽ እንዲሆን የተቀላጠፈ የኢንተርኔት አግልግሎት ሊኖር ይገባል:: በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልም እንዲበራከት መስራት ያስፈልጋል::

ለምለም መንግሥቱ

አዲስ ዘመን   ኅዳር 4 ቀን 2016 ዓ.ም

Recommended For You