አዲስ አበባ፡- ዳኞች በአዲስ መልክ ከተሾሙና የአሠራር ለውጡ ከተደረገ በኋላ በግብር አከፋፈል ቅሬታ የቀረበባቸው ከ700 በላይ ውዝፍ መዝገቦች ውሣኔ እንዲያገኙ መደረጉን የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የፌዴራል ታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ትናንት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የኮሚሽኑን መመሪያና ተግባር በተመለከተ ምክክር ባደረገበት ወቅት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አያሌው እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ በአግባቡ ከመቋቋሙ በፊት ውሣኔ ያልተሰጣቸውና የንግዱን ማኅበረሰብ ሲያንጋላቱ የቆዩ አሠራሮች ተወግደው፤ በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ በመቋቋሙ ከሐምሌ ወር 2010 ዓ.ም እስከ ሚያዝያ ወር 2011 ዓ.ም ድረስ ከ700 በላይ ውዝፍ መዝገቦች ውሣኔ አግኝተዋል፡፡
በ2008 ዓ.ም የተቋቋመው ኮሚሽኑ ወደ ሥራ ባለመግባቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ እንደገና እንዲቋቋም ተደርጎ የአሠራር መመሪያዎችን ማውጣቱንና በግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችና በግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የማይታወቁ መመሪያዎችን እንዲታወቁ መድረጉን አቶ ሙሉጌታ ጠቁመው፤ መዛግብትን የመለየት ሥራውም በተቀላጠፈ መልኩ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩት የአሠራር መመሪያዎች ግልፅ አለመሆናቸውን እንደ ችግር ያነሱት አቶ ሙሉጌታ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ኮሚሽኑ በችሎት አማካኝነት የዳኝነት ሥራን የሚሠራ ቢሆንም፤ ይግባኝ ባዩ አቤቱታውን አቅርቦ ሳይገኝ እንደሚቀርና ባለጉዳዩ ምን ያህል ጊዜ ሲቀር ነው በህግ የሚወሰነው የሚለው ስላልተደነገገ ለአሠራር እንቅፋት ሆኖ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ አዲሱ መመሪያ ይህንና መሰል ችግሮችን እንደሚቀርፍ፣ በተለያዩ ጊዜ የሚወጡትን ህጎች የንግድ ማህበረሰቡ ባለማወቁ ችግሮች እየተከሰቱ መሆኑንና ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት እንደማይድን ጠቁመው፤ መመሪያዎችን ለንግዱ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የህግ ማስፈፀም ዘርፍ ምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ አቶ ገለታ ስዩም በበኩላቸው፤ መንግሥት የታክስ አሰባሰብ ሥርዓቱን ለማጠናከርና የህብረተሰቡን ታክስ የመክፈል ግዴታ ለመወጣት የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት እየዘረጋና በየጊዜው ማሻሻያዎችን እያደረገ በመሥራት ላይ መሆኑን በመጥቀስ፤ ኮሚሽኑ የታክስ ከፋዩ ኅብረተሰብ የታክስ ባለስልጣኑ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታቸውን አቅርበው የሚያሰሙበትና ፍትህ የሚያገኙበት ሥርዓት መኖር አስፈላጊ መሆኑን በማመን ነፃና ገለልተኛ ሆኖ መቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡
አቶ ገለታ፤ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ ፍትህ የማግኘት መብት ወሳኝ የማኅበራዊ ፍትህ መርኅ አካል ሆኖ ሁሉም ሰው በህግ ፊት እኩል መታየት አለበት የሚለውን መርኅ ተግባራዊ ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ እንደሚሆን ጠቅሰው፤ የኮሚሽኑ አገራዊ ተልዕኮው የግብር ይግባኝ ቅሬታዎችን ተቀብሎ በመመርመር በህግና አሠራር መሠረት ውሳኔ በመስጠት የቅሬታ አፈታት ሂደቱን በማሳለጥ የማኅበረሰቡን እርካታ ማሳደግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አቶ ገለታ ለአሠራሩ ስኬታማነት የተቋሙ ውስጣዊና ውጫዊ አደረጃጀት አሁን ካለው በበለጠ ሊጠናከር እንደሚገባና የታክስ ይግባኝ ሥርዓቱ የተሟላ እንዲሆን ለማድረግ ደንቦችና መመሪያዎች ግልፅና ተደራሽ ሆነው ሊቀርቡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011
አዲሱ ገረመው