የፋሽን ኢንዱስትሪውን የሚያነቃቁት የንግድ ትርኢቶች

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ የፋሽን ኢንዱስትሪው ዘርፍ መነቃቃት እያሳየ መጥቷል፡፡ ለዚህም በቅርብ በኢትዮጵያ የተካሄደውን ዘጠነኛውን የአፍሪካ ሶርሲንግና ፋሽን ዓለም አቀፍ (ASFW) የንግድ ትርዒት በማሳያነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በዚህ ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት ላይ በተለያዩ ዲዛይኖች የተሰሩ ቦርሳዎች፣ ጫማዎች፣ ጌጣጌጦች፣ የሀበሻ ልብሶች ፣ ዘመናዊ የፋሽን አልባሳት፣ ወዘተ በስፋት ቀርበዋል፡፡

አውደ ርዕዩ በርካታ የፋሽን ስሪቶች ለዕይታ የቀረቡበት ነው፡፡ በመድረኩ የቆዳ፣ የጨርቃጨርቅ፣ የአልባሳት እና የፋሽን ኢንዱስትሪ ውጤቶች በሽበሽ ሆነው በአንድነት ቀርበው መታየታቸው የፋሽን ኢንዱስትሪው ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርገውታል ማለት ያስችላል፡፡በአውደ ርዕዩ የቀረቡት ምርቶች በጥራታቸው፣ በውበታቸውና በማራኪነታቸው የተመልካችንም ሆነ የሸማቹን ቀልብ ሰቅዘው የሚይዙ ከመሆናቸውም በላይ የፋሽን ኢንዱስትሪው ያለበትን ደረጃ ፍንትው አድርገው ሊያሳዩ የሚችሉ ናቸው፡፡ በንግድ ትርዓቱ የተሳተፉ አካላትም መድረኩ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል፡፡

የካቨና ዲዛይን ኃላፊነቱ የተወሰነ ማህበር/ፒኤልሲ/ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወጣት ስመሃል ጎሹ ድርጅቷ የካቨና ዲዛይን ብራንድ የቆዳ ውጤቶችን ይዛ በንግድ ትርኢቱ መቅረቡን ትናገራለች፡፡ ስመሃል እንደምትለው፤ ድርጅቱ የቆዳ ቦርሳዎችን እና ጫማዎችን በማምረት ምርቶቹን ለውጭ ገበያ በተለይ ለአሜሪካ እና ለአውሮፓ ሀገራት ያቀርባል፡፡ ወደ ውጭ የሚላካቸው የቆዳ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ጥሩ ተቀባይነት እንዳላቸውም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ትገልጻለች፡፡

ድርጅቱ የቆዳ ውጤቶች ማምረት ከጀመረ ሰባት ዓመታት ማስቆጠሩን ጠቅሳ፣ የቆዳ ምርቶች ገበያ ከኮቪድ በኋላ ያለው የገበያ ሁኔታ መነቃቃት እያሳየ መምጣቱን ትናገራለች፡፡ ቆዳን በማምረት ሂደት ዋንኛ ችግሮች የግብዓት ችግሮች መሆናቸውን ገልጻ፣ የቆዳ ውጤቶችን ለመስራት የሚያገለግሉት ዚፖችና ሌሎች የአክሰሰሪ እቃዎች በገበያ ላይ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑንም ጠቁማለች፡፡

የቆዳ ምርቶችን ለማምረት ቆዳ፣ ጨርቅ እና የመሳሰሉት የተለያዩ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ የምትለው ስመሃል፤ እነዚህ ብቻቸውን ግን ቦርሳ ሊሆኑ አይችሉም ነው የምትለው፤ አስፈላጊዎቹን ግብዓቶች ከውጭ ለማምጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንደሚጠይቅ ጠቅሳ፣ በመንግሥት በኩል ከቀረጸ ነጻ የሚገቡበት ሁኔታ ቢመቻች መልካም እንደሆነም አመልክታለች፡፡ ይህ ሲሆን የቆዳ ምርቶች ጥራት ይጨምራል፤ ከውጭ የሚገቡት ምርቶችን የሚተኩ ምርቶች ማምረት ይቻላል፤ ብቁ የሆነ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ይበልጥ እንዲበረታቱ ያስችላል ስትል ታብራራለች።

የኢትዮጵያ ቆዳ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ በጣም ተወዳዳሪና ተቀባይነት ያላቸው ናቸው የምትለው ስመሃል፤ የግብዓት ችግሮች ከተፈቱ በቆዳው ዘርፍ የበለጠ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ትናገራለች፡፡ እንደዚህ አይነት ኤግዚቢሽኖች ከዓለም አቀፍ ሀገራት የመጡ የዘርፉ አካላት የሚሳተፉባቸው መሆናቸውን ጠቅሳ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ከማስቻላቸው በላይም የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት የሚቻሉበት ሁኔታም እንዳለ ነው ያመለከተችው፡፡

እሷ እንዳለችው፤ አሁን ላይ የቆዳ ቦርሳዎች ዋጋ እንደቦርሳው አይነትና እንደዲዛይኑ ይለያያል፡፡ ዋጋውም ተመጣጣኝ የሚባል ነው። ድርጅቱም እነዚህን ምርቶቹን እያመረተ ለገበያ እያቀረበ ይገኛል። በስሩም 60 ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ ከእነዚህ በተጨማሪም 130 ለሚሆኑ ሰዎች (ቋሚና ጊዜያዊ) የሥራ እድል የፈጠረ ነው፡፡

ሌላኛው የአውደ ትርኢቱ ተሳታፊ አሌክስ አቬን ፓሪስ የተሰኘው ድርጅት ነው፤ ድርጅቱ የውበት መጠበቂያ ሜካፖችን ይዞ ቀርቧል፡፡ የድርጅቱ ስቶር ማናጀር ኤልሳቤት አልማው እንደምትለው፤ ድርጀቱ የውበት መጠበቂያ ሜካፖችን ከውጭ በዋናነት ከፓሪስ እና ከተለያዩ የአውሮፖ ሀገራት ያስመጣል፡፡ ወደዚህ ሥራ ከገባም አንድ ዓመት ያህል ያስቆጠረ ሲሆን፤ የሜካፕ እቃዎች (ፋውንዴሽን፣ ሊፕስቲክ፣ አይላሽ፣ የመሳሳሉትን) ያስመጣል፡፡

ኤልሳቤት እንዳለችው፤ ሰዎች ለሠርግና ለተለያዩ ፕሮግራሞች እንዲሁም ለሁልጊዜ አምሮና ተውቦ ለመታየት የሚያስችሉ የሜካፖ አይነቶችን ያስመጣል፤ በቅርቡም የጥፍር ምርቶች እንደ ጥፍር ቀለም፣ ሺላክ፣ ጄል እና የመሳሳሉትን ማስመጣት ጀምሯል፡፡ ደንበኞቻቸው በአብዛኛው የውበት ሳሎን ያላቸው፣ የሜካፕ አገልግሎት ና የጥፍር አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦች፣ ማሰልጠኛዎችና ድርጅቶች ናቸው፡፡

ሜካፕ ሲባል ለፊት ውበት መጠበቂያነት የሚያገለግለው እንደሆነ የምትናገረው ኤልሳቤት፤ እነዚህ ሜካፖች ከውጭ እንደሚመጡ ነው የተናገረችው፡፡ የውበት መጠበቂያዎቹን ሰዎች ወደዋቸውና አይተዋቸው እንዲገዙ ለማድረግም በቅድሚያ የፊት ቆዳዎች በሚመስሉ የተለያዩ ነገሮች ላይ እንደሚሞክሩ ገልጻለች፡፡

እንደዚህ አይነት ዓለም አቀፍ ኤግዚቪሽኖች ላይ መሳተፍ ደግሞ ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠር ደንበኛ ለማፍራት እንደሚጠቅም አልሳቤት አስታውቃለች፤ አሌክስ አቬን ፓሪስ የሚያስመጣቸው እቃዎች ጥራታቸው የጠበቁ መሆናቸውን ጠቅሳ፣ ሁሉም ሰው ቢሞክራቸው ይወዳቸዋል ብላለች፡፡ አልሳቤት እንደምትለው፤ ሜካፖቹ በዋጋቸውም ቢሆን ተመጣጣኝ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ፋውንዴሽን 2ሺ500 ብር ይሸጣል፡፡ ይህም ዋጋ አሁን በገበያ ላይ ካሉት ከሌሎች ዋጋዎች አንጻር ሲታይ ተመጣጣኝ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙ አገልግሎት በሚሰጡ ግለሰቦችም ሆነ ድርጅቶች ይመረጣሉ፡፡

ድርጅቱ የራሱ የሜካፕ አገልግሎት መስጫ ቦታ እንዳለውም ጠቅሳ፣ በዚህም ምርቶቹን ሰዎች እንዲያውቃቸው እያደረገ እንደሆነ ገልጸለች፡፡ በሰዎች ፍላጎት መሠረትም የሜካፕ አይነቶች እንደሚሰሩም ትናገራለች፡፡ ‹‹እኛ ብዙ ሜካፕ አርቲስቶች ስላሉን ለተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ለሠርግ መሠራት የሚፈልጉ፣ ሰዎች መጥተው መርጠው መሠራት ይችላሉ›› ብላለች፡፡

የጥበብ ደርጅት በአውደ ርዕዩ የተገኘ ሌላው ድርጅት ነው፤ የድርጅቱ መስራች ወጣት ቤዛዊት ጥበቡ ድርጅቱ በዘመናዊ መልኩ የተሰሩ የሀበሻ ልብሶች ይዛ መቅረቡን ትናገራለች፡፡ ቤዛዊት እንደምትለው፤ ወደ ሥራው ከገባች 10 ዓመታት ተቆጥረዋል። የሀበሻ ልብሶችን (ቀሚሶች፣ቶፕ፣ለወንዶች የሚሆኑ ልብሶች እና የመሳሳሉት በተለያዩ መልኩ ዲዛይን ታቀርባለች፡፡

የሀበሻ ልብስ ዘወትር እንዲለበስ አድርጎ በመስራት ማንኛውም ሰው በሚመቸው ቦታ ላይ ሆኖ እንዲለብስ ማስቻል አላማዋ አድርጎ ተነስታለች፤ እነዚህን ልብሶች እያመረተች በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ገበያ ታቀርባለች፤ ከደንበኞቿ በሚቀርብላት ትዕዛዝ መሰረት ደግሞ ወደ ተለያዩ ውጪ ሀገራት እንደምትልክ ተናግራለች፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት የሀበሻ ልብሶች የሚለበሱት በተለያዩ ፕሮግራሞችና ሰርግ ሲኖር ብቻ ነበር የምትለው ቤዛዊት፤ አሁን ላይ ሁሌም እንዲለበሱ ተደርገው ቀለል ባለመልኩ የሚሰሩ የባሕል አልባሳት እንዳሉም ተናግራለች፡፡ አልባሳቱ ተመራጭ እየሆኑ መምጣታቸውንም ገልጻለች፡፡

የምትሰራቸው ልብሶች ጥራታቸውን የጠበቁ እንደመሆናቸው መጠን ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለውጭም ገበያ ሊላኩ የሚችሉ መሆናቸውንም ጠቅሳ፤ ለውጭ ገበያ በመላክ ሂደት ላይ መሆኗንም ጠቁማለች፡፡ በዚህ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ላይ መሳተፍ ከብዙ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ እና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችልም ነው ያስታወቀችው፡፡ የሀገራችንን የሀበሻ አልባሳት ብዙ ያልተሰራባቸውና ያልተነኩ ናቸው የምትለው ቤዛዊት፤‹‹እኛ ለብሰን በሀገራችን ምርት እየኮራን ለሌሎች ማስተዋወቅ አለብን ብላለች፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ህዳር 3/2016

Recommended For You