አዲስ አበባ:- ኢትዮጵያ ባለፉት 15 ዓመታት በህዋ ሳይንስ ያስመዘገበችውን ስኬት እንዲሁም እያደረገች ላለው ጥረት የዓለም አቀፍ አስትሮኖሚ ህብረት እውቅና በመስጠት አዲስ ለተገኙ አንድ ኮከብና አንድ ፕላኔት ኢትዮጵያ የሯሷን ስያሜ እንድትሰጣቸው ዕድል ተሰጣት።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ትናንት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ መስክ ለምታከናውነው ስኬታማ ተግባር የዓለም አቀፉ አስትሮኖሚ ህብረት 100ኛ ዓመቱን በአከበረበት ወቅት፤ በኢትዮጵያውያን በተሰየመችው አንድሮሜዳ በምትባለው ህብረ ኮከብ አቅጣጫ ውስጥ የሚገኙት በሳይንሳዊ መለያዋ HD161175 / ኮከብና HD16175b ፕላኔት ኢትዮጵያ የራሷን ስም እንድትሰጣቸው ዕድሉን ማግኝቷን ተናግረዋል።
እንደሳቸው ማብራሪያ፤ ኢትዮጵያ የራሷን ስያሜ እንድትሰይም የተሰጧት እኒህ ኮከብና ፕላኔቶች በ196 የብርሃን ዓመት አካባቢ ከፀሐይ እርቀው በኛው ጋላክሲ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ኮከቧ ከፀሐይ በ 1 ነጥብ 34 ጊዜ የምትገዝፍ፣ በስፋቷ በ 1 ነጥብ 66 እጥፍ ከፀሐይ የምትበልጥና ከሶስት እጥፍ በላይ ከፀሐይ የምታበራ ሲሆን፤ ፕላኔቷ ደግሞ በግዙፍነት ጂፒተር ከሚባለው ፕላኔት በ 4 ነጥብ 8 እጥፍ ትበልጣለች።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ቤዛ ተስፋዬ በበኩላቸው፤ የህዋ አካል ሥርዓት ውስጥ ለሚገኙት ለእኒህ ኮከብና ፕላኔት ኢትዮጵያ የምትሰጠው ስያሜ ዝንት ዓለም ለኢትዮጵያውያን መጠሪያ ሆኖ ለትውልድ የሚተላለፍ ታሪክ ሲሆን፤ የዓለም አቀፍ አስትሮኖሚ ህብረት ለነዚህ ኮከብና ፕላኔት ስም እንዲወጣ ቀን ቆርጦ ማስቀመጡን ጠቁመዋል። ሥራ አስኪያጇ ኢትዮጵያ በረሃብና በድርቅ ትታወቅበት ከነበረው ገፅታዋ ወጥታ በዓለም መድረክ በሳይንሱ ዘርፍ በምታደርገው አስተዋጽኦ የምትታወቅበትና ለትውልድ ታሪክ ሆኖ የሚተላለፍ በመሆኑ ትውልዱን ይቻላል በሚል መንፈስ በመቅረጽ ነገ ላይ አገሪቱ የራሷን ተመራማሪዎች በብዛት በማፍራት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችልና መነቃቃትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለኒህ ኮከብና ፕላኔት የሚሰጠው ስያሜ ሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎ ማግኝት ስላለበት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ሌሎች ትምህርት ቤቶች፣ ወጣቶች፣ የእድር ማህበራት፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የሙያ ማህበራት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ተማሪዎች፣ በአጠቃላይ በገጠርና በከተማ የሚኖሩ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲና በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስም ማህበረሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግና ስያሜውን በመስጠት እንዲሳተፍ ሥራ አስኪያጇ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 16/2011
ሰሎሞን በየነ