‹‹ከሀገራችን አልፈን ለአፍሪካ ኮንስትራክሽን መሠረት የሚጥል ተቋም መገንባት እንፈልጋለን›› -የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው

የአንድ ሀገር የእድገት ደረጃ ከሚታይባቸው የልማት እንቅስቃሴዎች መካከል የኮንስትራክሽን ዘርፉ ቀዳሚና ተጠቃሽ ነው፡፡ኮንስትራክሽን ባሕልን የሥልጣኔ ደረጃን እንዲሁም የወደፊት ሕልምን ለማሳየት የሚያግዝ ከመሆኑ ጋር በተያያዘም ሀገራት እድገታቸው በዛ ሊለካ ይችላል፡፡

ኢትዮጵያም ረዘም ያለ የኮንስትራክሽን ጥበብ ባለቤት እንደመሆኗ ባሕሏን ወጓን የሥልጣኔና የእድገት ደረጃዋን ለማሳየት የሚያስችሉ በርካታ የኮንስትራክሽን ግንባታዎች ባለቤት ናት፡፡የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በዘርፉ አንጋፋና ብዙ የሥራ ልምዶች ያሉት በሀገር ደረጃም አንቱ ያስባሉትን ሥራዎች ያከናወነ ነበር። ነበር ያልንበት ዋናው ምክንያት ደግሞ በሥራ ሂደቱ ላይ ተፈጥረውበት በነበሩ ችግሮች ከዘርፉ ባይወጣም የሚጠበቅበትን ያህል ሚና እንዳይወጣ እንቅፋት ሆነውት ስለቆየ ነው፡፡

ተቋሙ ዛሬ በሚያስደንቅ ቁመና ላይ ያለ ከመሆኑም በላይ ወደፊት ከራሱ አልፎ ለሀገር ተስፋን የሚያጭሩ ሥራዎችን እየሠራ በአስደናቂ ብቃት ላይ የሚገኝ ሆኗል፡፡እኛም ይህንን የተቋሙን እድገትና የወደፊት ራዕዩን አስመልክተን ከተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው ጋር ቆይታን አድርገናል፡፡መልካም ንባብ፡፡

አዲስ ዘመን፦ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የለውጥ እሳቤዎቹ እንዲሁም ሀገራዊ ተልዕኮዎቹ ምንድን ናቸው?

ኢንጂነር ዮናስ፦ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን መድረስ ያለበት ቦታ ለመድረስ የሚያስችሉትን በርካታ የለውጥ ሥራዎች ሠርቷል። ነገር ግን ሁሉም ጅምር ናቸው ብሎ መውሰዱ ጥሩ ነው፡፡ በሌላ በኩልም ለለውጡ መነሻ የሆኑት ነገሮች በጠቅላላ በሀገራችን ያለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ችግር ነው፡፡

በሀገራችን ላይ ያለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ መነሻ ተደርጎ እንዲሁም ደግሞ እንደዚህ ዓይነት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ያሉባቸውን ችግሮች ፈተን ለሀገር የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለውጥ መሠረት መጣል የሚያስችል ተቋም መገንባትን መሠረት ያደረገ ሥራ ነው፡፡በመሆኑም የእኛ የሪፎርም ሥራ ግንባታዎችን መገንባት አልያም ከኮንስትራክሽን ጋር የተገናኙ ሥራዎችን መሥራት ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ከሀገራችን አልፈን ለአፍሪካ ኮንስትራክሽን መሠረት የሚጥል ተቋም መገንባት የሚል ነው፡፡

እዛ ለመድረስም የተለያዩ ጎዳናዎችን መጓዝ ነበረብን ከዚህ መካከል ቀዳሚው ተቋም እንደየትኛውም የመንግሥት የልማት ድርጅት ከለውጡ በፊት በጣም ብዙ ችግሮች የነበሩበት ነበር፤ በተለይም የአቅም ማነስ፤ ብክነት፤ የንብረት አያያዝና አጠቃቀም ቴክኖሎጂን ከመጠቀም አንጻር ብዙ ችግሮች ነበሩ፡፡በሌላ በኩልም ባለሙያዎችና አመራሮች የሚሠሩትና እቅዶቻቸውን የሚተገብሩበት መንገድ የዘልማዳዊ አይነት ነበር። ፕሮጀክት የሚመራ ተቋም ይሁን እንጂ ፕሮጀክት ለመምራት የሚያበቃ ሥርዓትን ተከትሎ አልነበረም የሚመራው፤ ሠራተኛውና አመራሩ መካከል የነበሩ ልዩነቶች ችግሮች በጣም ከፍተኛ ነበሩ፡፡

አመራሩ ሠራተኛውን አያገኘውም በዚህ መካከል ደግሞ በሠራተኞች ከፍ ያለ ቅሬታ ነበራቸው፡፡ይህ ሁኔታ ደግሞ በሠራተኛ ማኅበር በመገናኛ ብዙኃን ሁሉ ይቀርብ ነበር፡፡እነዚህ የተቋሙ ውስጣዊ ችግሮች ሲሆኑ ከውጭ ደግሞ ዓለም አቀፍ መነሻዎችን መሠረት ያደረጉ ሥራዎችን መሥራት አለመቻሉ ነው። እነዚህን ችግሮች በሚቀለብስ መልኩ እንደ አዲስ ተቋሙን ሪፎርም የማድረግ ሥራዎች አከናውነናል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ለዚህ የሪፎርም ሥራችን መነሻ የሆነን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መሥራት መቻላችን ነው፡፡

እንደ አጋጣሚ ሆኖ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ፕሮጀክቶች እሳቸው እየመሩ ሠርተናል፤ ይህ ደግሞ በተለይም እሳቸው የሚመሩበትን የአካሄድ ሥርዓት ወደራሳችን ለመውሰድ ቻልን፡፡በሌላ በኩልም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች በሚመሩበት አግባብ ሌሎቹንም መምራትና ማስተዳደር የሚቻል ከሆነ ትልቅ ስኬትን ለማምጣት እንደሚቻል ማሳያ ሆኑን። በመሆኑም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የሠራናቸውን አንድ ሁለት ፕሮጀክቶች ተሞክሮ አድርገንም ለለውጥ መነሻ አደረግነው፡፡

ሪፎርሙ ከመጀመሩ በፊት በምሥራቅ አፍሪካ ካሉ መሰል ተቋማት አንዱ መሆን የሚል ራዕይ ተቀምጦ ነበር ፡፡እውነት ለመናገር ግን ተቋሙ በነበረው ቁመና እንኳን ከምሥራቅ አፍሪካ ከሀገር ውስጥም ተወዳዳሪነቱ ምን ያህል ነው የሚለውን ማየት ያስፈልግ ነበር ፤ ምክንያቱም እዚህ እደርሳለሁ ተብሎ ሲታቀድ የቱ ጋር ነኝ? ምን ሠርቼ ነው የምደርሰው? የሚለውም መታየት ያለበት ወሳኝ ጉዳይ ነውና፡፡የእኛ ቪዝን የተቀመጠው ይህ በውል ሳይታወቅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ተቋሙ ላለፉት በርካታ ዓመታት በሥራው ላይ የነበረ ብዙ ልምዶች ያሉት በርካታ አንቱታን ያተረፈባቸውን የግንባታ ሥራዎች በጥሩ ሁኔታ ያከናወነ ቢሆንም መካከል ላይ በተፈጠሩበት ችግሮች ከጨዋታ ውጪ የሆነ ተቋም ነበር፤ እንዴት አድርጎ ነው የምሥራቅ አፍሪካ ተወዳዳሪ የሚሆነው የሚለውን በደንብ ያልታየና ያልታሰበበት ነበር፡፡

በመሆኑም ይህንን ማጥራት ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነበር፤ ነገር ግን እኛ ወደተቋሙ ከመጣን በኋላ በችግሮቹ ዙሪያ ቁጭ ብለን ውይይት በማድረግና እንደ አጠቃላይም የአመራር ለውጥ አድርገን በለውጥ አስተሳሰብ መሥራት የሚችሉ አመራሮችን ተክተን ሥራዎችን ለመሥራት ሞክረናል፡፡አመራሩን ለመቀየራችን ዋናው ምክንያት ደግሞ ተቋምን ሪፎርም ማድረግ ጥሩ ሆኖ ሳለ በውስጡ አላሠራ በማለት ሲጎትቱ የነበሩ አካላትን ይዞ መቀጠል ተገቢ ስላልሆነ በመጀመሪያ የተሄደበት ተቋማዊ ሪፎርም መሥራት ላይ ነው፡፡

ተቋሙ ሪፎርም መሆን እንዳለበት አምነናል፤ ተስማምተናል፡፡ነገር ግን አሠራሩ በሠራተኞች ላይ ያለው አስተሳሰብ የተጠያቂነት ደረጃና ዓይነት በጠቅላላው በተቋሙ ላይ ያሉ ችግሮች ሳይፈቱ ወደሪፎርም መሄድ ማለት ተቋሙ ሊለውጠው ሳይሆን ሊያጠፋው የሚችል ስለነበር በቀጥታ ትኩረታችንን ያደረግነው ችግሮችን መፍታት ላይ ነበር፡፡

በውስጥ የነበሩብንን ችግሮች ደረጃ በደረጃ ከፈታን በኋላ በቀጥታ ያመራነው ተቋሙን ሪፎርም ወደማድረጉ ነበር፤ በዚህም ለሠራተኛው ምቹ የሆነ የሥራ አካባቢን መፍጠር፡፡ሠራተኛውና አመራሩ መካከል ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ማድረግ፡፡ሠራተኛው የተሰጡትን ተልዕኮዎች ፈጽሞ ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችሉ ማትጊያዎችን ማድረግ፡፡ከገንዘብ ጋር ያሉበትን ጥያቄዎች በደመወዝና በጥቅማ ጥቅም መመለስ፡፡የተቋሙ ሀብት ሳይባክን ጥቅም ላይ የሚውልበትን አሠራር መቀየስ፡፡ተቋሙ ተጨማሪ ገቢን የሚያገኝባቸውን ሥራዎች መሥራት። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተቋሙ ጋር የሥራ ውል አስረው ለማሠራት እምነት አጥተው የነበሩ አገልግሎት ፈላጊዎች እምነታቸው እንዲመለስ የማድረግ ሥራዎችን በመሥራት ዛሬ ላይ ተቋሙ መቶ በመቶ ስኬታማ ሥራን እየሠራ ስለመሆኑ መናገር የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ተወዳዳሪ ተቋም መገንባት ችላችኋል ማለት ይቻላል ? አሁን ያለበትን ሁኔታስ ከቀድሞ አንጻር ሲታይ እንዴት ይገልጹታል?

ኢንጂነር ዮናስ፦ አዎ፤ አሁን ላይ በተቻለ መጠን ተወዳዳሪና ብቃት ያለው ተቋም እየተገነባ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ በተለይም ከፕሮጀክቶች መምራት ጋር ያሉብንን ችግሮች መቅረፍ ችለናል፡፡ፕሮጀክት የመምራት እውቀት ሲባል እንግዲህ አንድ ፕሮጀክት ሲመጣ እንደሚጠናቀቅ ማሰብ መቻልን ይጠይቃል፤ ከዚህ ቀደም አንድ ፕሮጀክት ከ 7 እስከ 10 ዓመት እጃችን ላይ የሚዘገይበት ሁኔታ ነበር፤ ይህንን ለማስቀረት ዓላማው ያደረገውን ሪፎረም ወደተግባር ስናስገባ ግን አሁን ላይ ተቋሙ ቀጣይነት ባለው ሪፎርም እንዲመራ የማድረግ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነን፡፡

በዚህም በተለይም ተቋሙ የነበረበትን የሪፎርም ማኔጅመንት ችግር ከ 80 በመቶ በላይ መሻገር የቻልንበትና ስኬት የሚባለው ደረጃ ላይ እየደረስን ያለንበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ፕሮጀክቶችንም በተያዘው ዕቅድ መሠረት የማስረከብ ብቃት ላይ ደርሰናል፡፡

አዲስ ዘመን፦ የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ያወጣቸውን የፕሮጀክት አስተዳደር መመሪያዎች ከራሳችሁ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስታርቃችሁ የመጠቀም ሁኔታውን እንዴት ይገልጹታል?

ኢንጂነር ዮናስ፦ አዎ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ከሆኑ ሌሎች ኢንስቲትዩቶች የሚመጡትንም የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓቶች ከራሳችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ የመሥራት አካሄድን እየተከተልን ነው፡፡በሌላም በኩል የራሳችን የሆኑ 16 የፕሮጀክት አስተዳደር መመሪያዎችን በማበልጸግ እየተጠቀምን ነው፡፡በመሆኑም ከላይ እንደጠቀስኩት ፕሮጀክት አስተዳደር ሪፎረም ብለን የራሱ የሆነ መለያ (ሎጎ) አስቀምጠን ተግባራዊ አድርገናል፡፡

የፕሮጀክት አስተዳደር እውቀት ማለት እንግዲህ አንድ ፕሮጀክት ለተቋሙ ሲሰጠው እንደሚያልቅ ማሰብ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው አስተሳሰብ ፕሮጀክት ሲመጣ ገንዘብ ይዞ ይመጣል የሚል ብቻ ነበር፤ ይህ ደግሞ በአብዛኛው ሠራተኛ አዕምሮ ውስጥ ለዘመናት የተቀመጠ ነው፡፡በዚህም ምክንያት ፕሮጀክቶች እስከ አስር ዓመት የሚጓተቱበት ሁኔታ ነበር፡፡

ነገር ግን የሀገራችንንም የሌሎች ዓለማትንም ተሞክሮ በመቀመር በሠራነው የሪፎርም ሥራ አሁን ላይ በርካታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መጠናቀቅ እየቻሉ ነው፡፡በዚህ ሂደት ውስጥ ደግሞ ሥርዓት ከመፍጠርም ባሻገር ተጠያቂነትም እንዲኖር በማስቻል አሁን ላይ ተቋሙ በማያቋርጥ የሪፎርም አስተሳሰብ ውስጥ እንዲቀጥል ለማድረግ ተችሏል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ለኮንስትራክሽን ሥራዎች ትልቁ ተግዳሮት የግብዓት ችግር እንደሆነ ተደጋግሞ ይነሳል እናንተም በሪፎርም ላይ ሆናችሁ ብዙ ሥራዎችን በመቀበል ላይ ከመሆናችሁ አንጻር ይህንን ችግር እንዴት እያለፋችሁት ነው?

ኢንጂነር ዮናስ ፦ እስከ አሁን በያዝነው ለውጥ በፕሮጀክት አፈጻጸም ደረጃችን 80 በመቶ ላይ ነን ካልን ለምንድን ነው 20 በመቶውን ማሳካት ያልቻልነው? ወደሚለው ነው በቀጥታ የገባነው፤ ለዚህ እንደ ምክንያት ያገኘነው ደግሞ የአቅርቦትና የምርት ችግር ነው፤ ይህ በምን ይፈታል ስንል ደግሞ ኢንዱስትሪያላይዜሽን የግድ መሆኑን ተረዳን፤ በተለይም በያዝነው ፍጥነት ተጉዘው በመላው ሀገሪቱ እንዲሁም በአፍሪካ ፕሮጀክቶችን የምንዘረጋ ከሆነ እንዴት ባለው መልኩ ነው ልንከታተል የምንችለው በማለት ዲጂታላይዜሽን እና ኢንዱስትሪያላይዜሽን ሪፎርም ወደማድረጉ ገባን፡፡

በነገራችን ላይ ለምሳሌ እንደ አገር በቁጥር በዛ ያሉ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቢኖሩንም ለእኛ ተቋም በምንፈልገው ልክ እያቀረቡልን አይደለም፡፡ለምሳሌ ተቋማችን በዓመት በጣም ብዙ ሚሊዮን ኩንታል ነው የሚያስፈልገን ነገር ግን አሁን ላይ እየቀረበልን ያለው አንድ አራተኛ እንኳን አይሆንም፤ ይህ ደግሞ በተቋሙ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ ችግር እየፈጠረ ነው፡፡

ሌላው የሚመጡ ሴራሚኮችና የማጠናቀቂያ (ፊኒሺንግ) ዕቃዎች ከውጭ አገር መግባታቸው ሌላው ችግር ነው፡፡በመሆኑም እነዚህን ነገሮች ከውጭ የሚመጡትንም በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እጥረት ያለባቸውንም ነገሮች በቂ አቅርቦት እንዲኖራቸው የኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዟችንን ከምን እንጀምር ብለን ተነሳን፤ በዚህም እስኪ እጃችን ላይ ባለው የተገጣጣሚ ፕሮጀክት መምሪያ ማሽኖቻችን ከወዳደቁበት አንስተን በማስተካከል ወደ ሥራ እናስገባ ብለን አስገባናቸው። በተጨማሪም ከውጭ የሚገባውን የአልሙኒየም ብረት እየቆራረጥን በመገጣጠም ትርፋማና ውጤታማ ለመሆን ቻልን፡፡

በተመሳሳይ ከውጭ የሚመጣውንም ጂፕሰም በሀገር ውስጥ በማምረት ውጤታማ ለመሆን ቻልን። በጠቅላላው በኢንዱስትሪያላይዜሽን ጉዟችን የእንጨት በር፡፡አልሙኒየም ጂፕሰም እና ሌሎችንም በማምረት እየሠራን ሲሆን በቀጣይም እንደ ማርብልና ሌሎችንም ለማምረት የሚያስችሉ ሂደቶች ላይ እንገኛለን፡፡

አዲስ ዘመን፦ እንደ ሀገር ያለውን የፕሮጀክት አስተዳደር እውቀታችንን እንዴት ይገልጹታል?

ኢንጂነር ዮናስ፦ በጣም ትልቅ ክፍተት አለበት። በጣም ውስን ባለሙያዎች ሳይት ላይ ፕሮጀክት እንዴት እንደሚመራ እውቀትና ልምድ አላቸው ፤ ነገር ግን ፕሮጀክት መርተው የማያውቁ ምን እንደሆነ እንዴት እንደሚመራ በራሱ ምንም እውቀት የሌላቸው ሰዎች ሕግና ሥርዓቱ ስለሚፈቅድላቸው ብቻ ፕሮጀክት ማኔጀር ይሆናሉ፡፡

በዚህ ደግሞ ፕሮጀክት ማለት ሠራተኛ ግብዓትና ማሽን በቦታው ላይ አስገብቶ ሥራ ማስጀመር የሚመስለው በጣም ብዙ ባለሙያ እየተፈጠረ ነው። በመሆኑም መምራቱ በእውቀት የተመራ መሆን ይኖርበታል፡፡አሁን ላይ ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ሥልጠናዎችን መስጠት ጀምሯል፡፡ይህ ብቻውን በቂ ስላልሆነ እኛም እንደ ተቋም የራሳችን የሥልጠና ማዕከል ያስፈልገናል በማለት ከትምህርት ቤት የወጡ መሐንዲሶችን በደንብ ኮትኩተን መሪ መሆን የሚያስችል እውቀት ልናስጨብጣቸው የሥልጠና ማዕከል አቋቁመናል፡፡የመጀመሪያዎቹ ተማሪዎችም በቅርቡ ትምህርታቸው ይጀምራሉ፡፡

ይህ የተቋሙ የሥልጠና ማዕከል ሰዎች ሥራቸውን እየሠሩ የሚሠለጥኑበት ሲሆን የፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እንዲሁም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የሥልጠና ማዕከሉን ከጎበኙ በኋላ በመደነቅ ይህ ከእናንተ አልፎ የእኛንም ባለሙያዎች የምናሠለጥንበት እንዲሆን ማስፋት አለባችሁ የሚል ሀሳብ ነው የሰጡን።

አዲስ ዘመን፦ በአሁኑ ወቅት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ያለውን እድል እንዴት ይገልጹታል?

ኢንጂነር ዮናስ፦ ኢትዮጵያ እንደአዲስ እየተገነባች ያለች ሀገር ነች፡፡ስለዚህም በዚህ ሙያ ውስጥ ያለን በሙሉ ሰፊ ዕድል አለን፡፡ዕድለኞች ነን፤ ዕድለኞች ብቻም ሳንሆን በሙያችን ልንኮራ የሚገባን ነው። ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች ከጥንት እስከ ዛሬ ድረስ ሀገራቸውን ገንብተዋል፤ ይህ አይነቱ ዕድል ግን በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት የለም፤ ለምን መሰላችሁ አፍሪካን የገነቧት በተለያዩ ምክንያቶች የመጡ የውጭ አገር ዜጎች በመሆናቸው ነው፡፡

በመሆኑም ይህንን ዕድል እኛ እንደ ተቋም በቀላሉ የምናየው አይደለም፡፡መልካም ዕድሎችን ሁሉ ተጠቅመን አስቻይ ሁኔታዎችን በሙሉ አይተን ሀገራችንን በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ የምትጠቀስና የምትጠራ ብሎም በራሷ አምርታ የምትገነባ ለማድረግ እየሠራን ነው፡፡

በነገራችን ላይ አሁን ከለውጡ ወዲህ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ የማጠናቀቁ ሂደት በመሻሻል ላይ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምረውታል ከተማ አስተዳደሩም በዛው መንገድ እየሄደ ነው፤ ነገር ግን አሁንም በቀደመው የፕሮጀክት አስተዳደር ውስጥ እየዳከሩ ያሉ ተቋማት እንዳሉም ይታያል፡፡

በመሆኑም ተቋማት ፕሮጀክቶችን የሚያዩበትን መነጽር መቀየር አለባቸው፡፡አሁን ጊዜው ተለውጧል። በአንድ ቀን መፈታት የሚችሉ ችግሮች ዓመታት እየተሻገሩ መንግሥትን ላልተገባ ወጪ እየዳረጉ ኅብረተሰብንም እያማረሩ ነው፡፡በመሆኑም አሁን ላይ ፕሮጀክት ስንጀምር ከምንም በላይ የተጠያቂነት ሥርዓትን አበጅተን ሊሆን ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን፦ ተቋማችሁን ዓለም አቀፍ ደረጃ ያሟላ እንዲሆን እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ካሉ ቢያብራሩልን ?

ኢንጂነር ዮናስ፦ አዎ አምና 2015 ዓ.ም ላይ ኢንተርናሽላይዜሽን የሚል ነገር ጀመርን፡፡በዚህም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነቶችን ማድረግ ነበረብን፤ የተለያዩ አምራቾች ፋብሪካዎች ተቋማትም አብረውን ይሠሩ ዘንድ የስምምነት ፊርማዎችን ተፈራረምን፤ በሌላ በኩልም ከሕንድ ቻይናና ዱባይ ካምፓኒዎች ጋር የጋራ ካምፓኒ ስምምነት በመፈራረምና 30 በመቶ እነሱ 70 በመቶውን እኛ በማድረግ ፋብሪካውን በዚህ ዓመት ሥራ እናስጀምራለን ብለናል።

ከሀገር ውስጥ ካምፓኒ ጋርም ሴራሚክ ለማምረት የመጀመሪያውን ስምምነት ጨርሰን ወደቀጣይ ምዕራፍ የመሄዱን ነገርም ጀምረነዋል፡፡ ከሁሉም በላይ ይህ ተቋም ሁልጊዜ ከብሔራዊ ባንክ ዶላር እየለመነ ብቻ መሥራት የለበትም፤ ወደውጭ ሀገር ሄዶ በመሥራት ራሱም የዶላር ምንጭ መሆን አለበት በማለት አሁን ለጊዜው ጅቡቲ ላይ የግንባታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነን። በዚህም ያለፉትን ሁለትና ከዚያ በላይ ዓመታት ከመንግሥት ምንም ዓይነት ዶላር አልወሰድንም። ወደፊትም በጅቡቲ የጀመርነውን ኬንያ፡፡ደቡብ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ እንቀጥላለን። በነገራችን ላይ ሌሎችም ሀገሮች ቅርንጫፍ ክፈቱ እንጂ እያሉ እየጠየቁን እኛም እየሠራንበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡

ሌላው ዓለም አቀፍና አፍሪካዊ የሆኑ ስብሰባዎችን በመካፈል በኩልም ለመጀመሪያ ጊዜ በኮንስትራክሽን ሙያ ላይ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ለውይይት የሚቀርብበት ፎረም አዘጋጅተን ነበር፡፡እኛም እንደ ተቋም (ቢግ 5) የሚባል በዱባይ ዓለም የሚገኝበት መድረክ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሳተፍና ተቋማችንን እንዲሁም ሀገራችንን በማስተዋወቅ ተመልሰናል፡፡በቀጣይም እነሱም ወደ ሀገራችን መጥተው እየተሠሩ ያሉትን ሥራዎች ተመልክተው ጥሩ ግንኙነት ፈጥረን የተመለስንበት ነው፡፡ ይህም ቢሆን ግን እኛ ከእነሱ ጋር ስንነጻጻር የቱጋር ነን? የሚለውን እንመልከት በማለት ፌዴሬሸን ኦቭ አፍሪካ ኢንጂነሪንግ ኦርጋናይዜሽን እንዲያወዳድረን በማመልከት ተወዳደርን በዛው ወርቅ አግኝተናል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ተቋሙ አሁን ላይ በግብርናው ዘርፍም እየተሰማራ ነውና ፤ እስኪ ስለእሱ ትንሽ ይንገሩን?

ኢንጂነር ዮናስ፦ እንግዲህ እኛም በተለይ ለሥራችን አጋዥ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የግድ የተለያዩ የገቢ ምንጮችን ማየት ይጠይቃልና እኛም በኩራዝ እያለማን ያለነውን የመስኖ ሥራ ወደ ግብርናውም ብናሰፋው ጥሩ ነው በሚል 6 መቶ ሄክታር የእርሻ መሬት በመረከብና ትራክተሮችን በመግዛት ባለሙያዎችን በመቅጠር ወደሩዝ ምርት ገብተናል፡፡

ይህንንም ምርት በአንድ ጊዜ ወደ ውጭ እንልከውም፤ ነገር ግን በቀጣይ የምናመርተው ምርት ወደውጪ የሚላክ እንዲሆን እናስባለን። በዚህም በጊዜ ሂደት ከውጭ አልሚዎች ጋር በጋራ ሠርተን ወደውጭ በመላክ ዶላር ማምጣት የምንችልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ነገን ዛሬ እንደሚገነባ ተቋም ግን ለእርስዎ የስኬቶቹ ምንጭ ምንድናቸው ይላሉ?

ኢንጂነር ዮናስ፦ ዋናው የአመራርና የሠራተኛው ትጋት ነው፡፡ በነገራችን ላይ እዚህ ተቋም ውስጥ ቁጭት ያለበት ብዙ ሠራተኛ አለ፡፡የሚያሠራን አመራር እስካለ ድረስ ብዙ መሥራት እንችላለን የሚሉ ባለሙያዎች በርካታ ናቸው፡፡የመንግሥት በቅንነት የመደገፍ ሁኔታዎችም ለስኬቱ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

መንግሥት እንደእኛ ያሉ የልማት ድርጅቶች ነፃ ሆነው ሠርተው አትራፊ እንዲሆኑ ከሀገራቸው አልፈው አፍሪካ ላይ እንዲሠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ አሁን እኛ የምንለው ተሳክቶልናል ሳይሆን የስኬት መስመር ውስጥ ገብተናል ነው፡፡ተሳካልን ልንል የምንችለው ዓለም አቀፍ ተቋም ሆነን ለሀገራችንና ለሕዝባችን ማድረግ የምንችለውን ሁሉ ስናደርግ፤ ዓለም ላይም ተወዳዳሪ ሆነን ስንመረጥ ነውና እሱ ላይ ለመድረስ እንሠራለን፡፡

አዲስ ዘመን ፦ ተቋማችሁ በጥሩ አቋም ላይ የሚገኝ ነውና ወደፊትስ የት መድረስ ነው ሕልሙ?

ኢንጂነር ዮናስ፦ አዎ የእኛ ራዕይ ቀደም ብለን ስንነሳ በምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ካሉት ተመሳሳይ ተቋማት ከአንድ እስከ አምስት መሆን ነበር። አሁን ይህ ተቀይሯል፤ አሁን የወርቅ ደረጃ ላይ ነን፡፡ይህ ደግሞ መሪ አድርጎናል በመሆኑም አፍሪካዊ ተቋም ወደማድረጉ ነው የምንሄደው፡፡ አፍሪካውያን እንዲያውቁ ከእነሱ ጋር ጥሩ ግንኙነት በመፍጠር ዓለማቀፋዊነት ሥራችንን መሠረት እናስይዛለን፡፡ የእኛ ቀዳሚ ሆኖ መውጣት ብቻውን ሚዛን ስለማይደፋ በአፍሪካ አገራት ያሉ አምባሳደሮች ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑና እኛንም እንዲያግዙን ጥሪ እናቀርባለን፡፡

አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ፡፡

ኢንጂነር ዮናስ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡

 እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን ህዳር 1/2016

Recommended For You